Thursday, June 13, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ችላ የተባሉት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች  ሕገወጥ ተግባራት ከጥቅም ትስስር እስከ አምባገነንነት

በባይከዳኝ ምንተስኖት

መንግሥታዊ ያልሁኑ ድርጅቶችን በተመለከተ ከዚህ በፊት በዚሁ ጋዜጣ ላይ መጻፌ ይታወሳል፡፡ ይሁንና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማኅበራት ኤጀንሲን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት በተነሱት ነጥቦች ላይ ምንም ዓይነት ተገቢ የሆነ ክትትልና ቁጥጥር እያደረጉ እንዳልሆነ እየታዩ ያሉ ችግሮች ቀላል ማሳያዎች ናቸው፡፡ ይህንንም ጽሑፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ በቅርቡ አንድ በሕፃናት ጉዳይ ላይ የሚሠራ ድርጅት ዓመታዊ የጠቅላላ ጉባዔውን እያካሄደ በነረበት ጊዜ፣ በድርጅቱ ውስጥ ሕገወጥ አሠራሮች አሉ ብለው ለማጋለጥ የሞከሩ ሁለት ሠራተኞች የመናገር መብታቸው ታፎኖ በፀጥታ ሠራተኞች ተጎትተው ሲወጡ በዓይኔ የተመለትኩት ክስተት ነው፡፡ ክስተቱ እውን የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ  ምን እየሠራ ነው? የሚል ጥያቄ እንዲጭርብኝ አድርጓል፡፡ ከጉባዔው ተጎትተው የተባረሩት ሠራተኞች እንደገለጹልኝና በማስረጃም አስደግፈው እንዳሳዩኝ ከሆነ፣ በድርጅቱ ውስጥ በርካታ የሕግ ጥሰቶችና የግል ጥቅም ማሳደድ ሥራዎችን በመታዘባቸው ይህንንም በማስረጃ በተደገፈ መልኩ ለድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ  ለማጋለጥ ነበር በወቅቱ በግዮን ሆቴል ጉባዔ ላይ ተገኝተው የነበሩት፡፡ ሆኖም የድርጅቱ ዳይሬክተር ከአንዳንድ የቦርድ አባላት ጋር በመመሳጠር ሠራተኞቹ አቤቱታቸውን እንዳያሰሙና እንዲታፈኑ ብሎም እንዲባረሩ አድርገዋል፡፡ በጣም የሚያስገርመው የዚሁ ድርጅት ዳይሬክተር ይህ ድርጊት በተፈጸመ በጥቂት ቀናት ውስጥ በዚሁ በሪፖርተር ጋዜጣ በምን እየሠሩ ነው በሚለው ዓምድ ላይ ቀርበው ድርጅቱ ሕግን ተክተሎ የሚሠራ ነው ብለው መወትወታቸውና በድርጅቱ ውስጥ ምንም ዓይነት ችግር እንዳልተፈጠረ ለማስመሰል መጣራቸው ነው፡፡ ‹‹ጅብ የማያውቁት አገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ›› ይላል ይሉት ይህ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ለፕሮግራም ማሟያ ሲባል ብቻ አስተማሪና አርዓያ ሊሆኑ የማይችሉ እንደዚህ ዓይነት የድርጅት ኃላፊዎችን የጋዜጣው አዘጋጆች ከማቅረብ መቆጠብ ይኖርባቸዋል ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ የጋዜጣው አዘጋጅ በዚህ ዙሪያ ላይ ዝርዝር መረጃዎችን የሚፈልግ ከሆነ የችግሩ ሰለባዎች የሆኑትን ግለሰቦች ከማስረጃዎቻቸው ጋር ለማገናኘት ዝግጁ መሆኔን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡

በመሆኑም የዛሬ ጽሑፌ ዓላማ በወሰዱት የመንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ፈቃድ ሕግን ባልተከተለ መንገድ እንደዚህ ዓይነት የአፈና ተግባር እየፈጸሙ ባሉት ላይ ኤጀንሲው በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት እስከምን ድረስ የተጠናከረ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል? ምንስ ዓይነት ዕርምጃ ይወስዳል? የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮዎችን  ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው ተፈራራሚ አካላቶችም ቢሆኑ የፕሮጅክቶችን አፈጻጸም ከወረቀት በዘለለ በአካል በመገኘት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጡ ነውን? የሚሉትን አንገብጋቢ ጉዳዮች በማንሳት ኤጀንሲውም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ራሳቸውን አንዲፈትሹ ማድረግ ነው፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በግልጽ ተጠያቂነት ባለውና ሕጉን በጠበቀ መንገድ እየተንቃሰቀሱ መሆኑን መካታተልና መቆጣጠር ለበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ በአዋጁ ክፍል ሁለት ቀጥር አምስት ላይ በግልጽ የተቀመጡ ዓላማዎች ናቸው፡፡ ይሁንንና በአሁኑ ጊዜ ኤጀንሲው ከተቋቋመበት ዓላማ እንፃር የሚጠቀበቅበትን ኃላፊነት በተገቢው ሁኔታ እየተወጣ ነው? የሚለው ጥያቄ በየደረጃው መፈተሸ የሚገባውና ጥናትን መሠረት ባደረገ መንገድ ግልጽ ምላሾችን የሚሻ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ውስጥ ጥቂት በማይባሉ የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ወስጥ እየተፈጸሙ ያሉት ሕገወጥ አሠራሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ አየተወሳሰቡና እየተባባሱ መምጣታቸው በድርጅቶቹ ተቀጥረው በሚሠሩ ሠራተኞች፣ በድርጅቶቹ ተጠቃሚዎች እንዲሁም የድርጅቶቹን አሠራር በቅርብ በሚያውቁና በሚከታተሉ ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ ለዚህም ዓይነተኛ ሚና እየተጫወተ የሚገኘው በየድርጅቶቹ ውስጥ  በሚገኙት የጠቅላላ ጉባዔ አባላት፤ የቦርድ አመራሮችና የየደርጅቶቹ ዳሬክተሮች መካካል ተዘርግቶ የሚገኘው  የጥቅም መተሳሰር ነው፡፡

 ከዚህ አንፃር ኤጀንሲው በየደረጃው የሚደርሱትን ጥቆማዎች መሠረት ባደረገ መንገድ ተገቢውን ክትትልና ምርመራ ማድረግ እንዲሁም የየድርጅቶቹን ልዩ ልዩ አመራር አካላት፣ በአዋጁ መሠረት ተግባራቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን ለመከታተልና ለመቆጣጠር፣ እንዲሁም ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችለውን አቅምና የተቀናጀ አሠራር መፍጠር የግድ ይለዋል እላለሁ፡፡ ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን ኤጀንሲው ራሱና ሠራተኞቹ ከላይ አስከታች በየድርጅቶቹ ውስጥ በጥቅም በተሳሰሩ ግለሰቦች መዳፍ ሥር፣ እንዲሁም እነርሱ ባደራጁት የኪራይ ሰብሳቢነት ትስስር ውስጥ  ሊወድቁ የማይችሉበት ምንም ማስተማማኛ ሊኖር አይችልም፡፡ ሁላችንም እንደምንስማማው በተጎዱትና በተተቸገሩት ወገኖቻቸን ስም እየተለመነ የሚመጣው ገንዘብ በምንም ዓይነት ሁኔታ የጥቂቶች ሕገወጦች መንፈላሰሺያና የግል ጥቅም ማስከበሪያ ሊሆን ስለማይገባው፣ ኤጀንሲው በአዋጅ የተጣለበትን ከፍተኛ ኃላፊነት በተገቢው መንገድ መወጣት ይኖርበታል ባይ ነኝ፡፡ በዚህ ጽሑፌ ላይ ከላይ የገለጽኩትን ገጠመኜን መነሻ በማድረግ በተለያዩ አጋጣሚዎች ያስተዋልኳቸውንና ኤጀንሲውም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላቶች ትኩረት ሰጥተው ሊንቀሳቀሱባቸው ይገባል የምላቸውን፣ በመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እየተፈጸሙ የሚገኙ ሕገወጥ ጉዳዮችን ከብዙ በጥቂቱ እንደሚከተለው አቀርባለሁ

መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዓመታዊ የክንውን፣ የኦዲት ሪፖርቶችና ጎልተው የሚስተዋሉ ሕፀፆቻቸው 

በግል አስተያየቴ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የጠቅላላ ጉባዔና የቦርድ አባላት፣ ደጋፊዎች፣ ሠራተኞችና አልፎ አልፎም የኤጀንሲው ተወካዮች በተገኙበት  የሚከናወነው ዓመታዊ ጉባዔ፣ የክንውንና የኦዲት ሪፖርቶች የሚቀርቡበት ወሳኝ ኩነት በመሆኑ ኤጀንሲው የጠበቀ ክትትልና ቁጥጥር ሊያደርግበት ይገባል እላለሁ፡፡ ከኦዲት ሪፖርት ጋር ተያይዞ በአብዛኛው ከሚስተዋሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሕገወጥ ተግባራት መካከል ሕግን ያልተከተለ የኦዲተሮች አመራረጥ፣ ይኼውም ለኤጀንሲው ቅጣት የማያጋልጥና የሚሰጠው የኦዲት አስተያየት ጠንካራ ያልሆነውን ኦዲተር አፈላልጎ መምረጥ፣ ኦዲተሮች አዋጁንና የኤጀንሲውን መመርያ ተከትለው የኦዲት ሥራውን አለማከናወን፤ ኦዲተሮች በምርመራ ሒደት የሚያገኙትን የሕግ ጥሰትና ፋይናንስ ነክ ግድፈቶች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሚያቀርቡት በገንዘብ ድለላ ማስቀልበስ፣ የኦዲት ሪፖርቱ በየድርጅቶቹ ቦርዶችና ጠቅላላ ጉባዔ በአግባቡ አለመመርመርና የይስሙላ ማፅደቅ፣ የኦዲት ሥራ ሒደታቸው ከዳይሬክተሮች ጋር በሚደረግ ምክክር ብቻ የተወሰነ እንዲሆንና ሌሎች ሠራተኞችን ሆን ብሎ ማግለል፣ ወዘተ በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የክንውን ሪፖርትንም በተመለከተ በአብዛኛው የድርጅቶቹን ጠንካራ ጎን ብቻ አጉልቶ የሚያሳይ፣ እውነታው ታቅዶ ከተፈጸመው ይልቅ ያልተከናወነው የሚልቅበት ቢሆንም የላቀ የአፈጻጸም ሪፖርት የሚቀርብበት፣ በየድርጅቶቹ በሚመለመሉ የተጠቀሚዎች ተወካዮች ነን ባዮች የሐሰት ምስክርነት  ድራማ የሚያከናውኑበት ሒደት ነው፡፡ በአብዛኛዎቹ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሚያከናውኗቸው ስብሰባዎች ላይ የኤጀንሲው ተወካዮች ሲገኙ አይስተዋልም፡፡ይህም ለብዙዎቹ ኃላፊነት ለጎደላቸው ድርጅቶቸ ሕገወጥ አሠራራቸውን አጠናክረው ያለ ከልካይ እንዲቀጥሉ የበለጠ የልብ ልብ ሲሰጣቸው ይስተዋላል፡፡

ከላይ ስሙን የጠቀስኩት ድርጅት ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የኤጀንሲው ተወካዮች ተገኝተው ቢሆን ኖሮ፣ አባራሪዎቹ ድርጊቱን ለመፈጸም ባልደፈሩ ወይም ኤጀንሲው የራሱን የዕርምት ዕርምጃ በወሰደ ነበር፡፡ ዓመትን ብቻ እየጠበቁ የሚገናኙትና የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነትም በተገቢው ሁኔታ የማይረዱና የማይወጡት የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ጥቂት ሊባሉ የሚችሉ አይደሉም፡፡ የተጣለባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት ወደ ጎን በማለት በወረቀት ላይ ተቀባብቶ የሚቀርብላቸውን ሪፖርት ብቻ እያዳመጡ፣ ምንም ጥያቄዎች ሳያነሱ ለሚቀጥለው ዓመት በሰላም ያገናኘን ብለው በዕለቱ የሚዘጋጀውን ድግስ ኮምኩመውና ዳጎስ ያለ የትራንስፖርት አበል ኪሳቸው ከተው የሚለያዩ ቀላል ቁጥር የላቸውም፡፡  ከዚህ ጋር በተያያዘም አልፎ አልፎም ቢሆን በታዛቢነት የሚገኙት ከኤጀንሲው ተወክለው የሚመጡ ግለሰቦች ያለውን ሁኔታ በተገቢው ሁኔታ ታዝበው የሚጠበቅባቸውን በተገቢው ከመወጣት ይልቅ፣ በየመድረኩ ከተለያዩ ግለሰቦች ጋር በመተዋወቅ በሚዘረጉት መረብ  የግል ጥቅማቸውን እንደሚያሳድዱ ይነገራል፡፡ ኤጀንሲው  በየዓመቱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያስገቡትን ሪፖርቶች ከመሰብሰብ ውጪ ትክክለኛና ተዓማኒነት ያለው ስለመሆኑ የሚከታተልበት ወይም የሚያረጋግጥበት የተጠናከረ ሥርዓት ባለመኖሩ የተነሳ ይመስላል፣ ዛሬ ዛሬ ሕገወጥ የሆኑ አሠራሮች በተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የሚስተዋለው፡፡

የጠቅላላ ጉባዔ አባላትና የቦርድ አመራሮች አመራረጥና ድብቅ ሚስጥሮቹ

በአብዛኛዎቹ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ለጠቅላላ ጉባዔና የቦርድ አባላትነት የሚመለመሉት ግለሰቦች ከየደርጅቶቹ የበላይ ኃላፊዎች፣ በተለይም ከዳይሬክተሮች ጋር ባላቸው ግለሰባዊ ግንኙነቶችና የጥቅም ትስስሮች ላይ ብቻ ሲያነጣጥር ይታያል፡፡ ፍላጎቱና ብቃቱ ያላቸው ግለሰቦች ቢኖሩ እንኳን የመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኃላፊዎች ለእነርሱ የሚመቹ ሆነው ካላገኙዋቸው ወይም አስገዳጅ ሁኔታ ካልተከሰተ በስተቀር፣  በምንም ሁኔታ ቢሆን የጠቅላላ ጉባዔ ወይም የቦርድ አመራርነት ቦታ ላይ እንዲመረጡ አያደርጉም፡፡ ብዙም የተለየ ጥናት ሳያስፈልግ ኤጀንሲው በእጁ ያለውን የተለያዩ ድርጅቶች የቦርድና የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ዝርዝሮችን ትኩረት ሰጥቶ ቢመረምር፣ እጅግ ብዙ አስደጋንጭ የሆኑ ሕገወጥ አሠራሮችን ሊመለከት ይችላል፡፡ ከላይ ስሙ የተጠቀሰው ድርጅት ዳይሬክተር የድርጅቱ የቦርድ ስብሳቢ በሚመሩት ሌላ ድርጅት ውስጥ የጠቅላላ ጉባዔ አባል ሆነው ውሳኔ የሚያሳልፉ ሲሆኑ፣ በሌላ የድርጅቱ የቦርድ አባል በሚመራ ድርጅት ውስጥ ደግሞ እሳቸው የቦርድ አባል እንደሆኑ አቤቱታ አለን የሚሉት ሠራተኞች በዝርዝር ነግረውኛል፡፡ ሌሎች ሁለት የቦርድ አባላትም የዳይሬክተሩ የቅርብ ወዳጆችና የቀድሞ የሥራ ባልደረቦች እንደሆኑም በተጨማሪ ይገልጻሉ፡፡ የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ባለው ሌላ መረጃ አራት የሚጠጉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች  ዳይሬክተሮች እርስ በእርስ የቦርድ አባላት ሆነው በመመራረጥ፣ የአራቱንም ድርጅቶች የቦርድ ስብሰባ በአንድ ላይ እንደሚያከናውኑና በአንድ ላይ ውሳኔ የሚያሳልፉ መሆኑን ያውቃል፡፡ አጅግ በጣም በሚያሳፈር ሁኔታ የተለያዩ ድርጅት ኃላፊዎች እርስ በርሳቸው የቦርድና የጠቅላላ ጉባዔ አባላት በመሆን ሚስጥራቸውንና ጥቅማቸውን በጋራ ለመጠበቅ የሚደርጉትን እንቅስቃሴን ኤጀንሲው እየተመለከተ በዝምታ ማለፉ ከተጣለበት ኃላፊነት አንፃር ከተጠያቂነት አያስመልጠውም፡፡ ይህንና መሰል የኤጀንሲውን ከፍተኛ ድክመቶች ጠንቅቀው የሚረዱት የተለያዩ የድርጅት ኃላፊዎች የሚፈልጉትን ሁሉ በሕጋዊነት ሽፋን ያለምንም ሥጋት እያከናወኑ እንዲቀጥሉ ምቹ ሁኔታዎችን ሲፈጥርላቸው ይታያል፡፡ ሕግና ሥርዓት ባለበት አገር በምንም ሁኔታ ቢሆን በደሀው በተለይም በሕፃናት ስም ተለምኖ በሚመጣ ገንዘብ ጥቂት ግለሰቦች በቦርድና በጠቅላላ ጉባዔ አባልነት ሽፋን በጥቅም ተሳስረው፣ ሕገወጥ አሠራሮችን እያራመዱ የሚቀጥሉበት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ልጓም ሊበጅለት ይገባል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በመግቢያዬ ላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በግዮን ሆቴል ያስተዋልኩት ክስተት በብዙዎቹ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ በቦርድ አመራርና በጠቅላላ ጉባዔ አባልነት የሚመረጡ ግለሰቦች ከድርጅታዊ ጥቅም ይልቅ፣ ለግለሰባዊ ጥቅሞች መጠበቅ ትኩረት ሰጥተው እንሚንቀሳቀሱ ጥሩ ማሳያ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ያ ባይሆንማ ኖሮ ቢያንስ የጠቅላላ ጉባዔው አባላት ባልተገደበ ሥልጣናቸው የሠራተኞቹን አቤቱታ ለማዳመጥ ዕድሉን ባልነፈጋቸው፣ እንዲሁም ሠራተኞቹ እንደ ሌባ ተገፍትረው ሲወጡ በአርምሞ ባላለፉት ነበር፡፡ በጊዜው እነዚህ ግለሰቦች የምንናገረው አቤቱታ አለን ብለው ሲወተውቱ እውነት የቦርድ አመራሩም ሆነ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ለድርጅቱ ቅድሚያ ሰጥተው በግልጽነት የሚንቀሳቀሱ ቢሆን ኖሮ፣ በመደነባበር አንደዚህ ዓይነት አፈና ለማድረግ ባልደፈሩ ነበር፡፡ በአጠቃላይ በሁለቱ በግለሰቦቹ ላይ የደረሰው ማዋከብ በብዙዎቹ መንግሥታዊ ያልሆኑ ደርጅቶች ውስጥ ያለውን የጠቅላላ ጉባዔ አባላትና የቦርድ አመራሮች ትስስርና ትክክለኛ የሆነ የውስጥ ባህርይ የሚያመለክት ነው ብዬ ለመናገር እደፍራለሁ፡፡ በጊዜው በጣም ያሳዘነኝ  ደግሞ በገለልተኝነት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በተገቢው መንገድ ይወጣሉ ተብለው የሚጠበቁት የድርጅቱ የቦርድ ሊቀመንበር  የሆኑት ግለሰብ በጊዜው የዚህ አፈና ሐሳብ አመንጪና መሪ ተዋንያን ሆነው መታየታቸው ነው፡፡ እንግዲህ እንደዚህ ዓይነት በጥቅም የተሳሰሩ ዳይሬክተሮች፣ የቦርድና የጠቅላላ ጉባዔ አባላቶች ናቸው ምስጥራቸው እንዳይወጣባቸው ንጹኃን ግለሰቦችን ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ለማሸማቀቅ የሚሞክሩት፡፡ ኤጀንሲውን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ሕግና ሥርዓት ባለበት አገር በማናለብኝነት የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ብቻ በንፁኃን ላይ ሥልጣናቸውን ተገን አድርገው የተለያዩ በደሎችን እየፈጸሙ ባሉት ላይ ሁሉ ጥብቅ ዕርምጃዎች ሊወስዱ ይገባል፡፡ ይህ ሳይሆን  ከቀረ ግን መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ወስጥ ተሰግስገው የሚገኙ ጥቂት የማይባሉ ኃላፊዎች በዕርዳታ ስም ተለምኖ የሚመጣውን ገንዘብ በመረባረብ  ለተለያዩ ሕገወጥ ሥራዎች ማዋሉን አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት ምንም አያጠራጥርም፡፡

የሰው ኃይል ቅጥርን በተመለከተ የሚከናወን ድራማ

አጅግ አስገራሚው ድራማ ደግሞ የሠራተኛ ቅጥርን በተመለከተ የሚስተዋለው  ነው፡፡ ሁሉም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ማለት ይቻላል፡፡ ክፍት የሥራ መደቦችን ለይስሙላ ያህል በጋዜጣ ላይ ከማውጣት ውጪ በግልጽነት ችሎታና የሥራ ልምድን መሠረት ባደረገ መንገድ ሲቀጥሩ አይስተዋልም፡፡ እስቀደመው የሚፈልጉትን ሰው መርጠው ስለሚያስቀምጡ ቅጥሩ በደፈናው ሕጋዊ መንገድን ተክትሎ የተከናወነ ለማስመሰል ሌሎችን ተወዳዳሪዎች ለአጃቢነት ፍጆታ ብቻ የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው፡፡ አንዳንድ  መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኃላፊዎችማ ልጆቻቸውን ጨምሮ ዘመድ አዝማዳቸውንና ጓደኞቻቸውን አሰባስበው የግል ጥቅማቸውንንና ሕገወጥ አሠራራቸውን ለመሸፋፈን እንደምቹ ሁኔታ እየተጠቀሙበት ነው የሚገኘው፡፡ ይህንንና ይህን በመሳሰሉት ዙሪያ ያሉትን ሥርዓት የለቀቁ አሠራሮች በተመለከተ በተደጋጋሚ ቢነገርም፣ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ሁሌም በቸልተኝነት ሲመለከቱት ይስተዋላል፡፡ አሁንም ከላይ በተጠቀሰው ድርጅት ላይ አቤቱታ አለን የሚሉት ሠራተኞች ከሚያነሱዋቸው ጉዳዮች  ውስጥ አንዱ የድርጅቱ ዳይሬክተር የቅርብ ዘመዳቸውንና ጓደኞቻቸውን በቅጥር መልክ መሰግሰጋቸውን፣ ይህም በአጠቃላይ የድርጅቱ የሥራ ሒደት ላይ ከፍተኛ እክል መፍጠሩን በማስረጃ ደርሰንበታል የሚል ነው፡፡

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በሌላ ድርጅት ውስጥ ሚስት ሥራ አስኪያጅ፣ ባል የፕሮግራሞች ኃላፊ፣ የሚስት እህት የፋይናንስ ኃላፊ፣ የባል እህት ልጅ ገንዝብ ያዥና የሚስት አጎት የአስተዳደር ኃላፊ ሆነው ድርጅቱን ከላይ እስከታች መቆጣጠራቸውን  ያውቃል፡፡ በሌላ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ደግሞ (ድርጅቱ የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው የሚኖሩ ሴቶችን እደግፋለሁ የሚል ነው) ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ሚስት አሜሪካ ለኮንፈረንስ ሄደው በዚያው ኮብልለው ሲቀሩ፣ የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት ባል በሥራ አስኪያጅነት ተተክተው አካውንታንት ከሆኑት የወንድም ሚስት ጋር ድርጅቱን መጠቀሚያ ማድረግ መቀጠላቸውን ያውቃል፡፡ ዛሬ ዛሬ ክፍት የሥራ መደብ በየጋዜጣው ላይ በወጣ ቁጥር ገንዘባቸውንና ጊዜያቸውን በመሰዋት በጉጉት እቀጠራለሁ በሚል ስሜት የሚንቀሳቀሱት ወጣት ባለሙያዎች ላይ እየደረሰ ላለው የሞራል ውደቀት፣ በቀዳሚነት ተጠቃሾች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸው፡፡ በመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ያለውን ግልጽነት የጎደለውን የቅጥር አሠራር ለመመልከት በሚያወጡት ክፍት የሥራ መደቦች ላይ ያመለከቱትን ግለሰቦች ዝርዝርና በመጨረሻ ላይ የሚመረጠውን/የምትመረጠውን ግለሰብ የትምህርት ደረጃና የሥራ ልምድ ሁኔታ መመልከት በቂ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ድርጅቶችማ በጣም አምባገነን ከመሆናቸው የተነሳ ስልክ በመደወል ለመከታተል መሞከር ራሱ በቀጥታ ከውድድር ውጪ ያደርጋል እያሉ ማሳሳቢያ ሲሲጡ ምንም ኃፍረት አይሰማቸውም፡፡ ስለሆነም የሚመለከተው አካል ሁሉ በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን ሕገወጥ የቅጥር ሁኔታ በቅርብ መከታታልና አስፋጊውን ዕርምጃ መውሰድ ይገባዋል፡፡

ግልጽነትና ተጠያቂነት መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች አጥብቀው የሚፈሩ መርሆዎች 

በብዙዎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መንገድ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲፈጸሙ አይስተዋልም፡፡ ከሚመደበው ገንዘብ ከ70 ከመቶ የማያንሰው በቀጥታ ለተጠቃሚው እንዲደርስ መንግሥት ሕግና መመርያ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ያለ ቢሆንም፣ አሁንም ቢሆን ወስጥ ለወስጥ እየተሠሩ ያሉት አሻጥሮች ሥፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ እንዲያውም ሕጉና መመርያው ለሕገወጦቹ እንደ ሽፋን እያገለገለ ይገኛል ለማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆኑት አቤቱታ አቅራቢዎች ከሚያነሱት ጉዳዮች መካከል የድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት  ከተጠቃሚዎቹ ጥቃት የደረሰባቸው ሴት ሕፃናት አፍ በመንጠቅ የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ቤት እያላቸው የቤት አበል መውሰድ፣ በግል የሚያሸከረክሩትን መኪና ያለጨረታ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ለሕፃናቱ የተመደበን ገንዘብ ወጪ በማድረግ ማሳደስ፣ የመኪና ነዳጅና የሞባይል ወጪ ያለገደብ፣ ለመስተንግዶ የሚወጣ ገንዘብ ያለገደብ እየወጣ እንዲከፈላቸው ማድረጋቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የሚያውቀው የአንድ ሌላ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ዳይሬክተር ደግሞ በልጃቸው ስም የተመዘገበ ቪላ ቤታቸውን ለሚመሩት ድርጅት በከፍተኛ ዋጋ አከራይተው ዳጎስ ባለ ገቢ ኪሳቸውን ያደልባሉ፡፡ የሌላ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ዳይሬክተር ደግሞ በየወሩ ወይም በየሁለት ወሩ ለገበያ ወደ ዱባይና መካከለኛው ምሥራቅ በድርጅቱ ወጪ በሥራ ሰበብ መመላለሳቸው ትዝብት ላይ እየጣላቸው ይገኛል፡፡ እንግዲህ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ዳይሬክተሮችን ገደብ አልባ ጥቅማ ጥቅም ለእነሱ በሚያመች መንገድ ማስፈጸሚያ ማኑዋሎችን እያዘጋጁ የሚያፀድቁት የቦርድ አባላት ተብዬ የጥቅም ተጋሪዎች መሆናቸው ልብ ይላል፡፡ ኤጀንሲውም  ቢሆን ይህን ያህል ዓይን ያወጣ ሕገወጥ አሠራርና ዝርፊያ ሲፈጸም እያወቀ ወይም ላለማወቅ በመፈለግ ዝምታን መምረጡ ያስተዛዝበዋል፡፡ የኦዲተሮች ገለልተኝነትና የምርመራቸውም አግባብነት ፈተና ላይ የሚወድቀው በእንዲህ ዓይነቱ ወሳኝ ጉዳይ ላይ ነው፡፡  

ከላይ ለመጥቀስ አንደተሞከረው በመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶቹ ዳይሬክተሮች፣ የቦርድ አመራሮችና የጠቅላላ ጉባዔ አባላት መካከል ያለው የተሳሰረ የጥቅም ግንኙነት ለእንዲህ ዓይነቶች ሕገወጥ አሠራሮች ምቹ ሁኔታዎችን ሲፈጥር ይስተዋላል፡፡ እንግዲህ በዚህ መሀል አሠራሮች ይስተካከሉ ብሎ የሚነሳ ሠራተኛ ሲያጋጥም፣ በእነዚህ ከላይ እስከታች በጥቅም በተሳሰሩ ግለሰቦች ምን ዓይነት የተቀናጀ የአፈና በደል ሊፈጸምበት  እንደሚችል መገመቱ የሚከብድ አይመስልም፡፡ ከላይ በጠቀስኩት ድርጅት ውስጥ ሲሠሩ የነበሩት ሁለት ግለሰቦች ላይ መሰል አቤቱታን በማቅረባቸው ብቻ በቦርዱና በድርጅቱ ዳይሬክተር አማካይነት በተቀናጀ መንገድ የተፈጸመባቸውን ድርጊት መጥቀሱ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ አንግዲህ እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ዋናው ነጥብ ይህ ዓይነቱን በደል የሚፈጽሙ ግለሰቦች ጥቂት ከማይባሉ የኤጀንሲውና ሌሎች አንዳንድ የሚመለከታቸው ሠራተኞችና ኃላፊዎች ጋር በፈጠሩት ግንኙነት የተነሳ እስከ መቼ ድረስ ነው የሚፈጽሙት በደል እየተሸፋፈነ የሚቀጥለው የሚለው ነው፡፡ በጣም በሚገርም ሁኔታ አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኃላፊዎች ኤጀንሲው ምንም አያመጣም ከሚል ንቀት የተነሳ በሚመስል እየፈጸሙዋቸው ያሉት በደሎች ከምን የመነጩ ነው የሚለው ራሱን የቻለ ጥልቅ ምርመራ የሚያስፈልገው ነው፡፡ በአጠቃላይ ኤጀንሲው ከላይ እስከታች  ራሱን መፈተሸና መንግሥት የጣለበትን ኃላፊነት በተገቢው መንግድ ሊወጣ ይገባል፡፡

ገደብ አልባው የዳይሬክተሮች የሥልጣን ዘመንና የሰፈነው የአምባገነንነት መገለጫ 

መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በተለይ አገር በቀል በሆኑት ወስጥ የኃላፊዎች  የሥልጣን ዘመን የጊዜ ገደብ የለውም፡፡ ይህም ለአብዛኛዎቹ አምባገነናዊ የሥልጣን ጊዜያቸውን፣ ጥቂት ለማይባሉት ደግሞ የጡረታ ዘመናቸውን ከመንግሥት በሚቆረጥ አበልና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ዳጎስ ያለ ደመወዝ በፍስሐ እንዲያሳልፉ ዕድል ሰጥቷቸዋል፡፡ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የዳይሬክተርነት ሥልጣን አንዴ ከተያዘ የዕድሜ ይፍታህ መንበር ነው፡፡ ምክንያቱም ተወዳዳሪና ጠያቂ የለበትማ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ  ጸሐፊው በቅርብ እንደሚያወቀው አንድ አኅጉራዊ ባህሪ ባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ዳይሬክተር የሆኑ አንድ ዕድሜያቸው ሰማኒያዎቹ መጨረሻ ላይ የሚገመቱ አዛውንት አሉ፡፡ እኚህ አዛውንት ላለፉት 20 የሚጠጉ ዓመታት ሥልጣንን የሙጢኝ ብለው በቅርቡ በልመናና በምልጃ መልቀቂያ ያቀረቡ ቢሆንም፣ ለማባበያ በቦታቸው ለሚተካው ዳይሬክተር ከፍተኛ አማካሪ የሚል ሹመት በቦርድ ተበጅቶላቸው ከፍተኛ ተከፋይነታቸውና በድርጅቱ ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ አቤቱታ የሚቀርብበት ድርጅት ዳይሬክተርም ያለ ውድድር ከተሾሙ ዘጠኝ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ የእርሳቸው ወንበር ሳይነካ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችንና ኃላፊዎችን ሲቀጥሩና ደስ ሳይላቸውም ሲያባርሩ እንደሚገኙ አቤቱታ አቅራቢዎች ይገልጻሉ፡፡ በሌላ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በሞት የተለዩትንና ለ18 ዓመታት በመሥራችነትና በሥራ አስኪያጅነት ሲመሩ የነበሩትን ሚስታቸውን የተኩት ባል እነሆ በአምባገነንነት ድርጅቱን መምራት ከጀመሩ ከሰባት ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ እንግዲህ ከላይ እስከታች ለይምሰል ብቻ የተደራጁት የጠቅላላ ጉባዔ አባላትና የቦርድ አመራሮች ለድርጅታዊ ጥቅም እምብዛም ግድ ስለሌላቸው ከጊዜው ጋር የሚሄድ አዲስ አስተሳሰብ ያላቸውና የበለጠ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉ የተሻሉ ሰዎች ቢኖሩም እንኳን  ለውጥ ለማድረግ ተነሳሽነቱ የላቸውም፡፡

በአጠቃላይ ብዙዎቹን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኃላፊዎችን እረፍት የሚነሳቸው የሥልጣናቸው ጉዳይ ብቻ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ እነዚህ ኃላፊዎች ትንሽ ለሥልጣናቸው ሥጋት መስለው የሚታዩዋቸውን ባለሙያዎች የተለያዩ ምክንያቶችን ፈጥረው ለማባረር የማይፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡ የሚያሳዝነው ግን ይህንን ሁሉ አኩይ ተግባር ሲፈጽሙ በየደረጃው ያሉ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ እውነታውን እየተረዱ ዝምታን መምረጣቸው ነው፡፡ በምንም ዓይነት ሁኔታ በዕርዳታ ስም በሚመጣ ገንዘብ ጥቂት ግለሰቦች በአምባገነንነት ንፁኃኖችን እየበደሉ የተደላደለ ኑሯቸውን የሚቀጥሉበት ሁኔታ ሊመቻቸች አይገባውም፡፡ ከድርጅታችን ኃላፊነት የሚለየን ሞት ብቻ ነው ብለው የማሉ የሚመስሉትን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን በሥልጣንና በጥቅም ዓይናቸው የታወሩትን ግለሰቦች ቆንጠጥ የሚያደርግ ግልጽ የአሠራር መመርያ ኤጀንሲው የማያስቀመጥ ከሆነ፣ እየታየ ያለው ብልሹ አሠራር  ተጠናክሮ ሊቀጥል ይችላል፡፡ 

የተፈራረሙዋቸው ፕሮጀክቶች ትዝ የማይሉዋቸው የሴክተር ቢሮዎች  

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ከተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ደርጅቶች በመጀመርያ የቀረቡለትን ፕሮጀክቶች ከተመለከተ በኋላ እንደፕሮግራሙ ይዘት ለሚመለከታቸው የተለያዩ ሴክተር ቢሮዎች በመላክ አስተያየት አንዲሰጥባቸው ማድርግ የተለመደ አሠራር መሆኑን ሁሉም ያውቀዋል፡፡ በመጨረሻም የተሰጡት አስተያየቶች ሁሉ መካተቱ ከተረጋገጠ በኋላ ብቻ ነው ከፕሮጀክቱ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር ስምምነት ተፈርሞ ወደ ትግበራ የሚገባው፡፡ እንደ ትክክለኛ አሠራሩ ከሆነ ተፈራራሚ አካላት የፕሮጀክቶችን ትግበራ በመደበኛነት በየሦስት ወራት ሪፖርት በመቀበልና በተለያዩ መንገዶች በአካል በመገኘት የአፈጻጸሙን ሁኔታ የመከታተል ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ዛሬ ግን እውነታው ከዚህ የራቀ መስሎ ይታያል፡፡ ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለባቸው በየደረጃው የሚገኙ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮዎችና  ሌሎችም ተፈራራሚ አካላት ጨምሮ በአግባቡ ሥራቸውን ሲወጡ አይስተዋልም፡፡ ከዚያ ይልቅ ከተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር የግል ጥቅማቸውን እያሳደዱ ያሉ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ቀላል ቁጥር የላቸውም፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በግምገማና በክትትል ስም በሚቀቡላቸው ጠቀም ያሉ ገንዘቦች የተነሳ የተለያዩ ጥቆማዎችና በተባላሹ አሠራሮች ላይ ሲደርሷቸው እንኳን ዓይናቸውን አጥበው ለአጥፊዎቹ ጠበቃዎችና ተከራካሪዎች ሲሆኑ በስፋት ይስተዋላል፡፡ እስከነተረቱም ‹‹ውሻ በበላበት ይጮሃል›› የሚባለው ለዚህ እኮ ነው፡፡ እንግዲህ እንደዚህ ዓይነት ግለሰቦች ናቸው መንግሥት ኃላፊነት ሰጥቷቸው በተለያዩ ቦታዎች ያስቀመጣቸው፡፡ በሚገርም ሁኔታ አንዳንዶቹማ ከሥራ በኋላ በየመጠጥ ቤቱና ሬስቶራንቱ ከተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኃላፊዎች ጋር በመገናኘት የተለያዩ ውሳኔዎችንና ሴራዎችን አስቀደምው አንደሚወጥኑ አንዳንድ ጥቆማዎች በግልጽ ያመለክታሉ፡፡ ስለሆነም የሚመለከታቸው ሁሉ እነዚህ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በጥቅም እየሸጡ ያሉትን ግለሰቦች በጥብቅ በመከታተል ዕርምጃዎችን መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው ግለሰቦችም ከኤጀንሲው ባለፈ አቤቱታቸውን ለአዲስ አበባ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ አስገብተው አሁንም ፍትሕን ለማግኘት ተስፋ ሳይቆርጡ በተለያዩ አቅጣጫዎች እያደረጉት ያለውን ጥረት እጅግ ላደንቅና ለሌሎችም አርዓያ መሆን የሚችሉ ናቸው በማለት በልበ ሙልነት ለመናገር እፈልጋለሁ፡፡ ግለሰቦቹ በቅርቡ የሚሰማ ጆሮ አግኘተው የሚፈልጉትን ፍትሕ አንደሚያገኙ አልጠራጠርም፡፡

መደምደሚያ

መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ግልጽና ተጠያቂ ለማድረግ፣ እንዲሁም በሕዝብ ስም የሚሰበሰብው ገንዘብን ለላቀ የተጠቃሚዎች አገልግሎት ብቻ እንዲውል በሚል ዓላማ ሕግና ደንብ ፀድቆ፣ መሥሪያ ቤት (ኤጀንሲ) ተቋቁሞ፣ የመንግሥት ሠራተኞችና በጀት ተመድቦ ሥራ ከተጀመረ ከስድስት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ ሆኖም የመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የግልጽነትና የተጠያቂነት ሁኔታ እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ መሆኑ ይታያል፡፡ ብዝብዛ፣ የጥቅም ትስስርና አምባገንነት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የጊዜው መገለጫ የሆነ ይመስላል፡፡ ኃላፊነት የተሰጠው ኤጀንሲም የተለመደውን የውጭ ኃይሎች ትችትን የፈራ በሚመስል ሁኔታ ይህንን የመሰለ የአደባባይ አዋጅን የሚፃረሩ አሠራሮችን በዝምታ ሲያልፍ ይታያል፡፡ ወይም የወሰዳቸው ዕርምጃዎች በግልጽ አይታወቁም፡፡ ወይም ደግሞ በኪራይ ሰብሳቢነት ትስስር መረብ ተጠልፍል፡፡ ለምሳሌ የዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆኑት ሠራተኞች እንደሚሉት አቤቱታቸውን ለኤጀንሲው በዝርዝር ካቀረቡ ሳምንታት ቢቆጠሩም፣ የሚመለከተው ኃላፊ አልተመቻቸውም  በሚል እጅግ ተራ ምክንያት ጉዳዩ ተገቢው ውሳኔ አልተሰጠውም፡፡ ምንም እንካኳን አቤቱታ አቅራቢዎቹ ኤጀንሲው ኃላፊነቱን ጊዜ ወስዶም ቢሆን ይወጣል ብለው ተስፋ ያልቆረጡ ቢሆንም፡፡ ለማንኛውም ኤጀንሲው የውጭ ኒዮ ሊበራል ኃይሎችን ትችት በመፍራትም ሆነ በሌላ ምክንያት በአዋጅ የተጣለበትን የሕግ ማስከበር ሥራ ላፍታም ቢሆን ቸል ሊል አይገባውም፡፡ ጥቆማዎችና አቤቱታዎች በወቅቱና በአግባቡ ተጣርተው ውሳኔ ካልተሰጠባቸው ሕግ ለዜጎች አለኝታነቱ ያበቃለታል፡፡ አምባገነኖችና ሕገወጦች በተጠያቂነት ፈንታ የጀግና ኒሻን ይሸለማሉ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት ሕግንና ሕጋዊ አሠራርን ይተካል፡፡ ደሃና ንፁኃን ይበደላሉ፡፡ ብሎም ሒደቱ ለሕገ መንግሥታዊው ሥርዓት አደጋ ይሆናል፡፡ ሕግ ይከበር፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሕግን ተከትለው ይንቀሳቀሱ፡፡ ኤጀንሲው ኃላፊነቱን በአግባቡ ይወጣ በማለት የዛሬው ጽሑፌን አጠናቅቃለሁ፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው m[email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles