Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊትውስታና ተስፋ በለገሀሬ

ትውስታና ተስፋ በለገሀሬ

ቀን:

መነሻችን አዲስ አበባ ለገሀር ከሚገኘው የምድር ባቡር ጣቢያ ነበር፡፡ የድሬዳዋ አዲስ አበባ የባቡር ጉዞ መዳረሻ የነበረው ቃሊቲ አካባቢ ያለው የባቡር ሐዲድ ሥራ አልባ በመሆኑ ዝጓል፡፡ ሐዲዱ አቅራቢያ የተሠሩ ሱቆች ወደ ቃሊቲ መናኸሪያ ለሚገቡ ተጓዦች ይሆናሉ ያሏቸውን ሸክፈዋል፡፡ ቃሊቲን አልፈው ከወጡ በኋላም ሐዲድ ማየት በሚቻልበት አካባቢ ሁሉ መስመሩን ድንጋይ ከቦታል፡፡ ተቆራርጠው የተነሱ የሐዲድ ክፍሎችም ይታያሉ፡፡

ከአዲስ አበባ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ድሬዳዋ ከተማ እስከምንደርስ የባቡር ሐዲዱን መመልከት በሚቻልበት አካባቢ ባጠቃላይ ከጥቅም ውጪ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ የድሬዳዋ ምድር ባቡር ጣቢያ ቅጥር ግቢ (ለገሀሬ) ስንዘልቅም ያስተዋልነው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡

በግቢው ብዙም የሰው እንቅስቃሴ አይስተዋልም፡፡ አልፎ አልፎ የሚዘዋወሩት የባቡር ጣቢያው ሠራተኞችም በሥራ ተጠምደው አይታዩም፡፡ ቀድሞ በተጓዦች የሚሞሉ ባቡሮች አቧራ ለብሰው ቆመዋል፤ የሐዲዱ ዳርቻም ሳርና ሙጃ በቅሎበታል፡፡ በባቡር ጣቢያው የነበሩ ሠራተኞች ከጣቢያው እስከ ሸኒሌ ድረስ ባቡር ተሳፍረን እንድንጎበኝ ጋብዘውን ተሳፈርን፡፡

ባቡሩ ውስጥ ያሉ መቀመጫዎች ተጠቃሚ ስለሌላቸው አድፈዋል፡፡ ወንበሮቹ ጀርባ ላይ በባቡሩ የተጓጓዙ ሰዎች ያሰፈሯቸው ጽሑፎችና ሥዕሎች ይገኛሉ፡፡ ባቡሩ ከተማዋን አቋርጦ ሲጓዝ፣ ለበርካታ ሙዚቃዎች እንዲሁም ጽሑፎች መነሻ የሆነውን አስገምጋሚ ድምፁን እያሰማ ነበር፡ ድምፁ በተለይ በድሬዳዋ ነዋሪዎችና ባቡሩ አዲስ አበባ እስኪደርስ ባለው መንገድ ባሉ ከተሞች ተወላጆችም ሳይቀር ልዩ ስሜት ይፈጥር እንደነበር ይነገራል፡፡

ባቡሩ ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ በማጓጓዝ የሚሰጠው ግልጋሎት እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ የሐዲዱን መስመር ተከትለው የጦፈ ንግድ ያካሄዱ ግለሰቦች ጥቂት አልነበሩም፡፡ በትውስታ ወደ ኋላ ተመልሰው ስለ ወቅቱ የነገሩን ቀድሞ በባቡር ጣቢያው ጥገና ክፍል ይሠሩ የነበሩት የ58 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ አዘዘ መርሻ ናቸው፡፡

ያገኘናቸው በባቡሩ ወደ ሸኒሌ ስንጓዝ ነበር፡፡ በወጣትነታቸው ባቡር ጣቢያ ውስጥ የመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበራቸው ይናገራሉ፡፡ ጥገና ክፍል ሥራ ከመጀመራቸው አስቀደሞ የባቡር መለወዋጫዎች ፅዳት ክፍል ሠርተዋል፡፡ ባቡር ስለሚገለገልባቸው ቁሳቁሶች ባጠቃላይ ጠንቅቀው ከተገነዘቡ በኋላ ጥገና ጀመሩ፡፡ የባቡር ጥገና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ በመሆኑ የጥገና ክፍል ሠራተኞች ትልቅ ኃላፊነት ነበረባቸው ይላሉ፡፡ አንዳች ስህተት እንዳይፈጠርና ባቡሩ እየተንቀሳቀሰ አደጋ እንዳይገጥመው የመከላከል ኃላፊነት ተሸክመው ለ35 ዓመታት ሠርተዋል፡፡

‹‹ባቡሩ የሚሻውን ጥገናና ጥበቃ መስጠት ከባድ ኃላፊነት ያለበትና እጅግ አስደሳች ሥራ ነበር፤›› በማለት የቀድሞ ሥራቸውን ይገልጹታል፡፡ ከድሬዳዋ እስከ አዲስ አበባ ባለው መስመር ላይ ያሉ ነዋሪዎች ያገኙ የነበረው ጥቅም የትየለሌ ነበር፡፡ ባቡሩ ውስጥና በሚያርፍባቸው ጣቢያዎች ምግብና መጠጥ በመሸጥ ይተዳደሩ የነበሩ ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ አዋሽና ሞጆ አካባቢ የነበረውን የፍራፍሬ ገበያ አቶ አዘዘ ያስታውሱታል፡፡ ባቡሩ ከድሬዳዋ የሚነሳበትን ሰዓት ተከትለው በየከተማቸው የሚጠባበቁ ሰዎች ዛሬ ትዝታው ብቻ ቀርቷቸዋል፡፡

ሦስት ማዕረግ ያለው የባቡር ጉዞ ክፍያ ከ20 ብር ጀምሮ በየደረጃው ይጨምራል፡፡ ተደብቀው የሚጓጓዙም ነበሩ፡፡ የኮንትሮባንድ ንግድ ያካሂዱ የነበሩ ነጋዴዎች የባቡር ጉዞ አንድ ክፍል ናቸው፡፡ ዕቃቸውን ኬላ ለማሳለፍ የሚጠቀሟቸው መንገዶች  አሏቸው፤ ብዙ ሺሕ ብሮች ቢከስሩም ተመልሰው ወደ ንግዱ ይመለሳሉ ይላሉ አቶ አዘዘ፡፡

አሁን ከድሬዳዋ ደወሌ የሚወስደው መስመር ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ የበርካታ ከተሞች ኢኮኖሚ በባቡሩ መቋረጥ ሳቢያ መጎዳቱን ያምናሉ፡፡ ‹‹ከድሬዳዋ ተነስቶ ውርሶ፣ ኤረር፣ ኤረር ጎታ፣ ዲኬ፣ አፍደም፣ ሞሉ፣ ሚኤሶ፣ ኮራ፣ አዋሽ፣ መተሐራ፣ መልካችሌ፣ ወለንጪቴ፣ ናዝሬት፣ ሞጆ፣ ደብረዘይት፣ ዱከም፣ አቃቂ፣ ቃሊቲና አዲስ አበባ ላይ ባቡሩ ይፈጥረው የነበረው ድባብ ተዳፍኗል፡፡ በተለይ ለድሬዳዋ ከተማ የባቡር ድምፅ የተለያየ ጣዕመ ዜማ ነበር፤›› ይላሉ፡፡

የባቡሩ ሥራ ማቆም በቀጥታ የጎዳው ሠራተኞችን እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በርካታ ባለሙያዎች ከሥራ ከወጡ በኋላ መቸገራቸውን ይገልጻሉ፡፡ አሁን አዲስ የባቡር ሐዲድ መስመር እየተዘረጋ ነው፡፡ ከቀድሞው ባቡር ጣቢያ ሠራተኞች መሃከል በአዲሱ ተቋም የሚሠሩ ባለሙያዎች አሉ፡፡ የቀድሞው ባቡር ጣቢያ ውስጥ ሥራቸውን የቀጠሉ ጥቂት ሠራተኞችም አጋጥመውናል፡፡ በቦታው ተገኝተን ያነጋገርናቸው ሠራተኞች እንደሚናገሩት አዲሱ ባቡር ለብዙዎቹ የቀድሞ ሠራተኞች ተስፋ ነው፡፡

አቶ አዘዘ የቀድሞ ሠራተኞች በአዲሱ ፕሮጀክት ተሳታፊ የመሆን ፍላጎት ይኖራቸዋል ብለው ያምናሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ የዓመታት ልምድ ያካበቱና በተለያየ ዘርፍ የሠሩ ባለሙያዎች የመሥራት አቅም እስካላቸው ድረስ በአዲሱ ባቡር ቢሳተፉ ጠቀሜታ ይሰጣሉ፡፡ እሳቸውም ባቡሩ ሙሉ በሙሉ ማጓጓዝ በሚጀምርበት ወቅት የመሥራት ዕቅድ አላቸው፡፡ አዲሱ ባቡር ላይ ተስፋ የጣሉ የቀድሞ ሥራ አጋሮቻቸው ዕድሉን ቢያገኙም ምኞታቸው ነው፡፡

በሌላ በኩል ባቡሩ ከመጓጓዣነት ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳና ማኅበረሰቡን የማስተሳሰር ሚና ነበረው፡፡ አዲሱ ባቡር በፍጥነት ስለሚጓዝ እነዚህን ጠቀሜታዎች መልሶ ለማግኘት ያስቸግራል ይላሉ፡፡ የባቡሩ መዳረሻ ከተሞችን የቀድሞ ድባብ ለመመለስ ቢከብድም ተስፋቸው እንደሚለመልም በአፅንኦት ይናገራሉ፡፡

ሌላው በጉዟአችን ወቅት ያገኝናቸው አቶ ሙሉጌታ ከበደ ለ27 ዓመታት የባቡር ሹፌር ነበሩ፡፡ ከባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ ተመርቀው ምድር ባቡሩን በ1972 ዓ.ም. ተቀላቀሉ፡፡ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ባቡር እየነዱ ጡረታ እስኪወጡ ድረስ አገልግለዋል፡፡ ሲሾፍሩ ምንም የከፋ አደጋ ገጥሟቸው ስለማያውቅ የሚሰማቸውን ደስታ ይገልጻሉ፡፡

ቢሆንም በ1983 ዓ.ም. አካባቢ የነበረውን ውጥረት ሳይናገሩ አያልፉም፡፡ ኢሕአዴግ በገባበት ወቅት የገጠማቸውን አካፍለውናል፡፡ በወቅቱ ከባቡሩ መነሻ ጀምሮ ባሉ ጣቢያዎች ላይ ውጥረት ነግሦ ነበር፡፡ እሳቸው ከድሬዳዋ ተነስተው ሲጓዙ ሚኤሶ ላይ በአማጺዎች ይታገታሉ፡፡ የጫኑት ሕዝብ ለአደጋ በመጋለጡ ይጨነቃሉ፡፡

‹‹ሁሉም ለሚያምነው አምላክ ይፀልይ ነበር እኔም ‹ነአምን በአሐዱ አምላክ› እል ነበር፤›› በማለት ውጥረታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ሚኤሶን እንዲያልፉ ሲፈቀድላቸው እፎይታ ቢሰማቸውም መንገዳቸው ላይ ቦንብ እንደተጠመደና የባቡር ሐዲድ የተቆረጠበት ቦታም እንዳለ ይነገር ስለነበር ደስታቸው አልዘለቀም፡፡ እውነትም መንገዳቸው ላይ ከአንዴም ሁለቴ የባቡር ሐዲድ ተቆርጦ ጠበቃቸው፡፡ ሐዲዱን መልሰው ከቀጠሉ በኋላ ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡ ባሰቡበት ቀን ባይሆንም በሰላም መድረሳቸው ‹‹ዕድለኛ ነበርን›› ያስብላቸዋል፡፡

ያኔ ባቡሩ ወደ አዲስ አበባ ይጓዝ የነበረበትን ወቅት በሕይወታቸው ትልቅ ቦታ ይሰጡበታል፡፡ ‹‹ለሙያው ትልቅ ፍቅር አለኝ፤ ሰዎችን በሰላም ከሚፈልጉት ቦታ ማድረስ ትልቅ ስኬት ነው፤›› ይላሉ፡፡ ባቡሩ ሲቋረጥ የብዙዎች የዕለት ከዕለት ኑሮና የሠራተኛውም ሕይወት እንደተስተጓጐለ ከሥራ ባልደረባቸው አቶ አዘዘ ጋር ይስማሙበታል፡፡ ከሠራተኞቹ ጥቂቱ ዳግም ወደ ሥራ መመለሳቸው መልካም ቢሆንም አዲሱ ባቡርም ትልቅ ተስፋ ነው ይላሉ፡፡

ካለፈው ከመስከረም ጀምሮ ለጥቂት ወራት በአዲሱ የባቡር ሐዲድ ግንባታ ላይ ቢሠሩም፡፡ ከቀድሞው በተለየ ከቻይናዎች ጋር ከመሠራታቸው ውጪ ብዙም አዲስ ነገር እንዳልገጠማቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹በርግጥ በአዲሱ ባቡር ግንባታ የተሻለ ደሞዝ ቢኖርም ሥራ የጀመርኩበትና እንደቤቴ የምትቆጥረው የቀድሞው ምድር ባቡር መሥራት ስለመረጥኩ ተመልሻለሁ፤›› ይላሉ፡፡

በቀድሞው ባቡር ጣቢያ ልምድ ያካበቱ ሠራተኞች በአዲሱ ባቡር መሥራትን  ተስፋ እንደሚያደርጉ ይናገራሉ፡፡ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም የተወሰኑ ሠራተኞች መካተት አለባቸው ይላሉ፡፡ ለማስተማር ወይም ለመሥራት አቅም ያላቸው በርካቶች ስለሆኑ ችላ መባል እንደሌለበት ያስረዳሉ፡፡

በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የተዘረጋው የባቡር መስመር በፈረንሳያውያን ባለሙያዎች በመቆርቆሩ በባቡር ጣቢያው ግቢ ሲዘዋወሩና ባቡሩ ላይም የፈረንሳይኛ ቃላት መመልከት አያስገርምም፡፡ የባቡር መስመር ዝርጋታው በውጣ ውረድ እንዳለፈ ይነገራል፡፡ እ.ኤ.አ. 1902 ከጂቡቲ ወደ ድሬዳዋ የመጀመሪያው ጉዞ የተደረገ ሲሆን፣ የድሬዳዋ ድምቀት ተያይዞ መጥቷል፡፡ በመቀጠል ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ ያለው ጉዞ ይጠቀሳል፡፡

ባቡሩ አሁን መጠነኛ እንቅስቃሴ ቢኖረውም ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ ያለውን ጉዞ ማቋረጡ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ አሁን እንደ ተስፋ የሚታየው አዲሱ የባቡር መስመር በመጪው ዓመት ተጠናቆ ሥራ ይጀምራል ተብሏል፡፡

አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው፣ ባቡሩ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ የኤሌክትሪክ ባቡሮች በሰዓት 120 ኪሎ ሜትር ፍጥነት እንደሚጓዝ ይጠበቃል፡፡

በቀድሞው ባቡር ጣቢያ በመካኒክነት እየሠሩ ያሉት አቶ መሳይ አዳሙ ሌላው አስተያየት ሰጪ ናቸው፡፡ እሳቸው ለ23 ዓመት በድርጅቱ ሠርተዋል፡፡ ባቡሩ ሥራ ሲያቆም ለጥቂት ጊዜ ቢቸገሩም ሥራ ሲጀምር በድጋሚ ተቀጥረዋል፡፡ ከእሳቸው ጋር ሥራ የቀጠሉ ባልደረቦቻቸው ጥቂት እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ አብዛኞቹ ወደተለያየ ሥራ ተበትነዋል፡፡

‹‹አዲሱ የባቡር ፕሮጀክት በፍጥነት እየተጠናቀቀ ነው፡፡ አሁን የምንሠራው በብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ሥር ሲሆን፣ ባቡሩ ሥራ ሲጀምር ተቀጥረን እንደምንሠራ እገምታለሁ፤›› ይላሉ አቶ መሳይ፡፡

ወደ ጂቡቲና ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ጉዞ አማካይ ድሬዳዋ በመሆኑ እዛ ያሉ ሠራተኞች የዓመታት ልምድ እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡ አሁን ወደተለያዩ አገሮች በመጓዝ ትምህርት ከወሰዱ ባለሙያዎች በተጨማሪ ቀደምቱ ዕውቀታቸውን ማካፈል የሚችሉበት መንገድ እንደሚፈጠር ያምናሉ፡፡

ከቀደመው ባቡር አንፃር አዲሱ ከጣቢያ ወደ ጣቢያ የሚያደርገው ጉዞ ፈጣን በመሆኑ እንደቀድሞው ሞቅ ያለ ድባብ ባይኖርም በኢኮኖሚ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ፈጣን ነው ባቡሩ ፈጣን ያልሆናችሁ እንዳትሳፈሩ፤›› እየተባለ መሆኑንም ነግረውናል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...