Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ከሳሪስ አቦ ወደ መገናኛ የሚያመራው ሃይገር ባስ ውስጥ ተሳፍሬያለሁ፡፡ ረዳቱ ‹መገናኛ፣ መገናኛ› እያለ ይጣራል፡፡ ሃይገሩ ውስጥ ያለነው ተሳፋሪዎች አሥር አንሞላም፡፡ ከፊቴ ያለው መቀመጫ ላይ ሁለት ወጣት ሴቶች ተቀምጠዋል፡፡ እየተንሾካሾኩ ይሳሳቃሉ፡፡ ምን ዓይነት የሚያስቅ ቀልድ ቢሆን ነው እንዲህ የሚያሳስቃቸው እያልኩ በመገረም አያቸዋለሁ፡፡ በዚህ መሀል የአንደኛዋ የሞባይል ስልክ አንቃጨለ፡፡ አነሳችው፡፡ ድምጿ እየተርገበገበ ‹‹ወይኔ ጉዴ፣ ወይኔ ጉዴ….›› እያለች ስትጮህ ቀደም ሲል የነበረው ስሜት በአንዴ ተቀየረ፡፡ ድንጋጤ ተፈጠረ፡፡

ጓደኛዋ ስልኩን ተቀብላት ከደዋዩ ጋር መነጋገር ጀመረች፡፡ ‹‹በቃ ኮንትራት ታክሲ ይዘን እንመጣለን…›› ብላ ጓደኛዋን ደግፋ ከሃይገሩ ላይ ወረዱ፡፡ ተሳፋሪዎች በየተራ ‹ምንድነው የገጠማችሁ?› እያሉ ሲጠይቁ ማን ይመልስ? የመጀመሪያዋ እዬዬዋን ታስነካዋለች፡፡ ሁለተኛዋ እንባዋ እየተዝረበረበ ጓደኛዋን ደግፋ መናገር አቃታት፡፡ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ታክሲ እየተጣሩ አጅበው ወሰዷቸው፡፡ የሃይገሩ መሙላት ተረጋግጦ ሾፌሩ ሞተር ሲያንቀሳቅስ ረዳቱ ገባ፡፡ በጥያቄ እናጣድፈው ጀመር፡፡

ረዳቱ አንገቱን በሐዘን እየነቀነቀ፣ ‹‹ሊቢያ በአረመኔዎቹ ከተገደሉት መካከል ሦስተኛው ታውቆ ነው፤›› ሲለን ሃይገር ባሱ በፀጥታ ተዋጠ፡፡ ጥቂት ቆይቶ አንዲት እናት፣ ‹‹ወይ ልጆቼ እንደወጣችሁ በባዕድ አገር አለቃችሁ…›› እያሉ ማልቀስ ሲጀምሩ፣ ተሳፋሪዎች በሙሉ ማለት ይቻላል በህቅታና በሳግ እንባቸው ፈሰሰ፡፡ ሾፌሩ አቦ ቤተ ክርስቲያንን አለፍ ብሎ ሃይገሩን ዳር ካስያዘው በኋላ ‹‹ወይኔ ወንድሞቼን…›› እያለ ሲንሰቀሰቅ በብሶት የታጀበው የታመቀ ለቅሶ ተጀመረ፡፡ በጣም ልብ የሚነካ ነበር፡፡ ለቅሶው ትንሽ መለስ ሲል እርስ በርስ ‹‹አይዞን›› ተባብለን ጉዞው ተጀመረ፡፡ በሕይወቴ እንዲህ ያለ አጋጣሚ ገጥሞኝ ስለማያውቅ በጣም ነበር የገረመኝ፡፡ ይህንን የመሰለ ኢትዮጵያዊነት፣ ዘር፣ ሃይማኖትና አመለካከትን የማይጠይቅ አብሮነት ውስጥ በመገኘቴ ወገኖቼን አፈቀርኳቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ኩሩና አዛኝ ሕዝብ የፈጠረን አምላክ አመሰገንኩት፡፡ ሕዝባችን እንዲህ ነው፡፡

ይኼንን ገጠመኜን የነገርኳቸው የሥራ ጓደኞቼ በጣም ተገረሙ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ማለት ምን ያህል የከበረ ትልቅ ነገር እንደሆነ ተነጋገርንበት፡፡ ሃይገር ባሱን የሐዘን ቤት ያደረገው አጋጣሚ ድንገት ገጥሞን ነው እንጂ ሰሞኑን በየመን፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በተለይ ደግሞ በሊቢያ በአረመኔዎች አጅ የወደቁት ወገኖቻችን ጉዳይ የሕዝባችንን አንጀት እንደበላው እናውቃለን፡፡ ከቤተሰቦቻቸውና ከወዳጆቻቸው እኩል መላ ኢትዮጵያዊያን በሐዘን ተቆራምደዋል፡፡ በተለይ በሊቢያ የተፈጸመው አሰቃቂና አረመኔያዊ ተግባር እናት አገርን የሐዘን ከል አልብሷታል፡፡ ይህ ዓይነቱ የአውሬ ተግባር እንዳይፈጸም ፀሎትና ምህላ ያስፈልገናል፡፡ ፈጣሪን አጥብቀን እንለምን እላለሁ፡፡ ይህንን ደግና አዛኝ እንዲሁም ኩሩ ሕዝብ እያመሰገንኩ፣ መታረም ያለባቸውን ደግሞ መጠቃቀስ እፈልጋለሁ፡፡

ይህ ዘመናችን ማኅበራዊ ድረ ገጾች በተለይ ደግሞ ፌስቡክ በከፍተኛ ደረጃ የመረጃ መለዋወጫ እየሆነበት ነው፡፡ አንድ ቦታ የተከሰተ ጉዳይ በደቂቃዎች ውስጥ ዓለምን በሚያዳርስበት በዚህ ዘመን ለፌስቡክ ምሥጋና ይግባው መባል አለበት፡፡ የመረጃውን ተዓማኒነት የማረጋገጥ ጉዳይ ለተጠቃሚዎች እንተወውና የአንድ ክስተት ዕውን መሆን በጥሬውም ቢሆን መጀመሪያ የሚሰማው በአብዛኛው በፌስቡክ በመሆኑ እኔ በበኩሌ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን የመገናኛ ዘዴ በአግባቡ ከተጠቀምንበት ደግሞ ለማመን የሚከብዱ ነገሮችን እናገኝበታለን፡፡ አጠቃቀማችን ግን ኃላፊነት ይኑርበት ነው የምለው፡፡

በሰሞኑ ብሔራዊ ሐዘናችን ላይ መረጃዎችን ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ያስተላልፉ የነበሩ ወገኖች የመኖራቸውን ያህል፣ አይኤስ በተባለው ጭራቅ ፍጡር የተገደሉ ወገኖቻችን መታየት የሌለባቸው ምሥሎች ሲለጥፉ የታዩ አሉ፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የተለጠፉ ምሥሎች ጉዳይ ያሳሰባቸው ወገኖች ‹‹ኧረ ተው!›› እያሉ እያሳሰቡ በድርጊታቸው የቀጠሉበት አሉ፡፡ አረመኔዎቹ ወገኖቻችንን ከመጨፍጨፋቸው በላይ የሚፈልጉት ነገር አለ፡፡ የጭካኔያቸው መጠን በሚዲያዎችም ሆነ በማኅበራዊ ድረ ገጾች እየታየ እንዲፈሩ ነው የሚፈልጉት፡፡ በእነዚህ ጭራቆች ለምን እንበለጣለን? ያስለቀሱን አንሶ ጭራሽ የእነሱ ተባባሪ እንሁን? ወገኖቼ እባካችሁ ከዚህ ድርጊት ተቆጠቡ፡፡ በሌላ በኩል ወላጅ እናቶችንና አባቶችን አስቡ፡፡ በቃ ተውት፡፡

በሌላ በኩል በዚህ ወሳኝ ወቅት ሐዘናችንን በጋራ መወጣት ሲገባን፣ የተሰውትን ወገኖች ደም ዋጋ የሚያሳጣ ቁማር ተጀምሯል፡፡ ይኼ የፖለቲካ ቁማር የአገራችንን ሕዝብ አይመጥንም፡፡ ሰማዕታቱ ነፍሳቸው በሰላም ይረፍ፡፡ ቤተሰቦቻቸውም ይፅናኑ፡፡ አገሪቱም ከደረሰባት ሐዘን ታገግም፡፡ ሁላችንም ውስጣችን ያለው ሰቀቀን ይልቀቀን፡፡ በታሪካችን በደረሱብን መከራዎች ምክንያት የጠላት መሳለቂያ የሆንባቸው ጉዳዮች ተረት መሆን ሲገባቸው፣ በሐዘን መሀል ምንድነው የሚያባላን? በእርግጥ ይህ የጥቂቶች መረን ያጣ ነገር ቢሆንም በፌስቡክ ገጾች ላይ የሚታየው አፀያፊ ድርጊት ይታሰብበት፡፡ አረመኔዎቹ ያስለቀሱን አንሶ፣ በአረመኔያዊ ድርጊታቸው ያቆሰሉን አንሶ፣ እንዴት እርስ በርሳችን እንዲህ እንሆናለን? ኧረ በውዲቷ ኢትዮጵያ አምላክ ረገብ በሉ፡፡ ተው እናንተ ጥቂቶች ሕዝብ አታሳዝኑ? ተው የጠላት መቀለጃ አታድርጉን፡፡ ተው ይህንን ኩሩ ሕዝብና ይህቺን ታላቅ አገር አታዋርዱ፡፡ በቀደም ዕለት መስቀል አደባባይ የታየውን አጓጉል ተግባር የታዘቡ እናት፣ ‹‹በግፍ ለተገደሉት ልጆቻችን እናልቅስ? ወይስ የእናንተን የማይረባ እንኩሮ እናንኩር?›› ያሉት ምሬቱን የሚገልጽ ይመስለኛል፡፡

(አያሌው ኩራባቸው፣ ከለገጣፎ)

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...