Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሆይ ስማ!

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሆይ ስማ!

ቀን:

በሮበሌ ነቢ

   በየሪፖርተር ጋዜጣ እሑድ መጋቢት 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ዕትም አስተያየት ገጽ ላይ፣ ‹‹የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ራሱን ይፈትሽ ወይም ይፈተሸ›› በሚል ርዕስ መንሹ ስ. የተባሉ ጸሐፊ፣ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ግንባታ የጥራት ችግርን በተመለከተ ያቀረቡት ጽሑፍ ማስተባበያ ሊቀርብበት የማይችል እውነት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የከተማው አስተዳደር የተቋሙን መሠረታዊ ችግር ለመቅረፍ ራሱን ዝግጁ ማድረግ ያለበት መሆኑን ማሳያ እንጂ፣ ሐሰት ነው በማለት እንደተለመደው ምክንያትና ማስተባበያ መደርደር መፍትሔ አይደለም እያልኩ የናፖሊዮን ሒል አባባል የሆነውን “Successes requires no explanations failure permits no alibis” በማለት ለመጻፍ የተነሳሁበትን ምክንያት ለማቅረብ ጥረት አደርጋለሁ፡፡

በቅድሚያ ጸሐፊው ያነሱት የከተማው ቤቶች ልማት ላይ የተገለጹ ችግሮች መንስዔ ዋናው የአመራሩ የማስፈጸም ችግር ነው የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ ይህ የማስፈጸም ችግር በዚህ ተቋም ያሉ አመራሮች ችግር ብቻ ሳይሆን የብዙ አመራሮች ችግር መሆኑ አይካድም፡፡ የከተማው አስተዳደር ለአመራርነት በዕጩነት የሚያቀርባቸው ከአመራሮች ትውውቅ በፀዳ መንገድ መሆን ነበረበት፡፡ አሁን ባለው እውነታ ግን በዚህ መንገድ ወደ አመራርነት የመጡ ስለሚበዙ ሳይላኩ ወዴት ሳይጠሩ አቤት በሚሉ የበታች አመራሮች የተሞላች ከተማ ሆናለች፡፡ ለዚህ እውነታ ከከተማ እስከ ወረዳ ያሉ አድርባይ አመራሮች ኃላፊነታቸውን ለማስጠበቅ እርስ በርስ የማይወቃቀሱ (የማይጋጩ)፣ ለበላዮቻቸው ታማኝነታቸውን ለመግለጽ ከመመርያ ውጪም ቢሆን የበላይን ተገቢነት የሌለውን ትዕዛዝ ያለማወላወል የሚፈጽሙ ስለመሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ለዚህ የፖለቲካ አመራሩ (ካድሬው) ከፍ ያለ ሥልጣን ያለውና የሚፈልገውን የሚሾም  የማይፈልገውን ደግሞ ስለሚሽር ይፈራል፡፡

ከዚህ ሌላ ብዙ አመራሮች አትንካኝ አልነካህም በሚል የተማማሉ ይመስላሉ፡፡ የራስንም ሆነ የሌላውን ድክመት ለማረም ወኔ ጠፍቷል፡፡ የግምገማ (አውጫጭኝ) ስብሰባዎች ችግር ፈቺ አይደሉም፡፡ ከዚህ የተለመደ ሁኔታ ውጪ የሆነ ግትር አመራር ከሌላው ጋር ይጋጫል፡፡ ውጤቱ ጥሩ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ብዙዎች ከሌላው ጋር ተመሳስሎ መኖር ይመርጣሉ፡፡ ደመወዛቸውና ጥቅማ ጥቅማቸው ያጓጓቸዋል፡፡ ተጋጭተው ከኃላፊነት የሚነሱ የሚጠብቃቸው ምን እንደሆነ አሳምረው ያውቁታል፡፡ የከተማው ስፖርት ኮሚሽን ምክትል የነበሩትን ማየት ብቻ ይበቃል፡፡ የሥራ ምደባቸውን በአስተዳደር ፍርድ ቤት ተሟግተው ያለደመወዝ የተሰቃዩትን ሥቃይ የውስጥ አዋቂዎች ያነሳሉ፡፡ እሳቸውን ለምሳሌ ያህል አነሳሁ እንጂ በግጭት ምክንያት ከአመራርነት የሚነሱ ወደቀድሞ ሥራቸውም ሳይመደቡ ተኮራምተው ከቤታቸው የዋሉና የተራቡትን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ ከአመራሩ ጋር ሳይጋጩ ከኃላፊነት በብቃት ችግር መነሳት መታደል ማለት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሁኔታ የተነሱ አመራሮች የምክትል ቢሮ ኃላፊ ደመወዝ እየተቆረጠላቸው አማካሪ እየተባሉ ተሽከርካሪ ከሾፌር ጋር የነበራቸው ጥቅማ ጥቅም ሳይቋረጥባቸው መደበኛ ትምህርት ቤት ገብተው እንዲማሩ የተደረጉትን ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ይቁጠራቸው፡፡

ስለዚህ በከተማው ያሉ አመራሮች ለበላዮቻቸው ታማኝ ብቻ ሳይሆኑ አጎብዳጅ ናቸው ቢባሉ አያንስባቸውም፡፡ ለምን ቢባል ከኃላፊነት እንኳን ቢነሱ ደመወዛቸው ሳይቀነስ ኃላፊነት ላይ እያሉ የተሰጣቸው መኪናና ቤትን ሳይነጠቁ በሹመት ምደባ በተድላ የሚቀጥሉ ‹‹ፀባይ›› ያላቸው ታዛዥ አመራሮች ባሉበት ከተማ ስለአመራሮች አድርባይነትና የተግባር ሰው ሳይሆኑ በአፋቸው ጤፍ የሚቆሉ ሆነው መገኘት መድረኩ የሚፈልገው ስለሆነ ነው ቢባል የተጋነነ ነው አይባልም፡፡ ይህ ሲባል ግን ያሉት አመራሮች ሁሉም ተመሳሳይ ባህሪ አላቸው ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ከጥቅመኞች ጋር የማይተባበሩ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡ መኖራቸው አይካድም፡፡ አብዛኛው አመራር ግን የሌላውን ድክመት ለማጋለጥ በተለይ ከላይ ያሉትን ለመናገር አይደፍርም በፍርኃት የተሸበበው ይበዛል፡፡ ያላግባብ የተጠቃ አመራርን መብት ለማስከበር የሚፈልግ አለ ማለት አይቻልም፡፡

በአንድ ቦታ ለረጅም ጊዜ በመሥራት የሚታወቁት በከተማችን የሚገኝ አንድ መንግሥታዊ ተቋም ሥራ አስኪያጅና ምክትል ሥራ አስኪያጅ የቅርብ ዝምድና አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው እውነታ ለከተማው አስተዳደር ጆሮ የራቀ አይመስለኝም፡፡ የግለሰቦቹ ዝምድና ችግር ሆኖ ሳይሆን በግምገማ (በአውጫጭኝ) መድረክ አንዱ ለሌላው ለማገዝና ለመተጋገዝ ግን ዕድል መስጠቱን መዘንጋት አይኖርብንም፡፡ ስለዚህ የዚህ ተቋም ሥራ አስኪያጅ ቦሌ መንገድ በውድ ዋጋ የሚያከራዩት የቤታቸውን ግንባታ አስመልክቶ ተቋሙ ለቢሮ ግንባታ ካወጣው ወጪ አንፃር እያያያዙ፣ ግለሰቡ ከገቢያቸው በላይ ቤት ገንብተው ማንም አልጠየቃቸውም የሚባለውን ለአስተዳደሩ ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች እንደሚሉት ተከራካሪ ወገን ያለው አመራር በግምገማ አይነሳም፡፡ ቢነሳ እንኳን ወድቆ አይወድቅም የሚለው አባባል እውነት ነው ያስብላል፡፡

የከተማው ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አመራሮችን በተመለከተ ቅዳሜ የካቲት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ለፕሮጀክቱ የተለያዩ አራት ኃላፊዎች ሹመት በተሰጠበት ቀን ማግሥት፣ ማታ የቢሮው ኃላፊና የፕሮጄክት ጽ/ቤቱ ኃላፊዎች በተገኙበት ለአዲሶቹ ተሿሚዎች ትልቅ የፈንጠዝያ ግብዣ ፕሮግራም በጦቢያ ጠጅ ቤት ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ግለሰቦቹ በቅርብ ትውውቅ የተሾሙ ለመሆናቸው በዕለቱ የነበረው የእንኳን ደህና መጣችሁ መገባበዝ የቅርብ ጓደኞች ግብዣ ያህል መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ የሚያሳየን በትውውቅ የመሾም አሠራር የከተማው አስተዳደር የተለመደ ችግር መሆኑን ነው፡፡ በዚህ አግባብ የተሰባቡ አመራሮች ያሉበት ተቋም ችግር የለበትም ብሎ ማን ደረቱን ነፍቶ ይናገራል?

ይህ ጽሕፈት ቤት ትልቅ የመንግሥት ሀብት የሚመደብለት እንደመሆኑ መጠን፣ የሚመደቡለትም የሥራ ኃላፊዎች ቢያንስ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ችሎታ ያላቸው፣ የምህንድስና ዕውቀትና የትምህርት ዝግጅት ያላቸው፣ ብሎም የተሻለ የማስፈጸም ብቃት ያላቸው ሊሆኑ ይገባ ነበር፡፡ የቴክኒክ ዕውቀት ለፕሮጀክት አመራሮች አያስፈልግም አይባልምና፡፡ የፖለቲካ ብቃት ብቻ መመዘኛ ተደርጎ ግለሰቦች የሚመደቡበት መሆን ባልተገባው፡፡

በየተቋሙ የሚገኙ የፖለቲካ አመራሮች ሙያተኞች ይሁኑ የሚል አቋም የለኝም፡፡ ግን ደግሞ የተወሰነ የቴክኒክ ዕውቀት ያለው ሰው ቢመደብ ከባለሙያዎች የሚያቀርቡትን ትንታኔን በወጉ መረዳትና መፍትሔ የማመንጨት የአመራር ሰጪነት ብቃትን ለመላበስ ያስችላል፡፡

የከተማው የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አመራሮችም ቢሆኑ፣ በፕሮጀክት ማኔጅመንትና የምህንድስና የትምህርት ዝግጅት የሌላቸው በመሆኑ ከእነሱ ሌላ አመራር የለንም ከተባለ ከፍተኛ ልምድ ባላቸው የቴክኒክ አማካሪዎች ሊታገዙ ይገባል፡፡ አማካሪ ሲባል ለደመወዝ ብቻ የምክትል ቢሮ ኃላፊነት ደረጃ እየተመደበላቸው በየቢሮው የሚመደቡ የፖለቲካ ተሿሚዎችን ማለቴ አይደለም፡፡

አሁን ያለው እውነታ ግን የምህንድስና ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎች ለጽሕፈት ቤቱ አመራሮች ታዛዦች እንጂ ድምፃቸው የሚሰማ ግለሰቦች አይደሉም፡፡ በፕሮጀክቱ ጽሕፈት ቤት የማቴሪያል አቅርቦት በትክክል በኦዲት ለማረጋገጥ የማይቻል ለብልሹ አሠራር በር የሚከፍት በመሆኑ፣ የከተማው አስተዳደር ለመፍትሔው መጨነቅ ይገባዋል፡፡ ከዚህ በላይ ከሥራ ተቋራጭ ጋር መቀራረብ ያላቸው ባለሙያዎች ጭምር ቁጥራቸው ትንሽ ነው ብሎ ማለት አይቻልም፡፡

የከተማው አስተዳደር በተለያዩ የኃላፊነት ቦታ የሚመድባቸው ከአንድ ኃላፊነት ወደሌላ እያገላበጠ በመሆኑ፣ የመሥሪያ ቤቱን ውስጣዊ ባህሪ ሳይረዱ ኃላፊ አድርጎ መመደብ ችግሩን ለመፍታት የቴክኒክ አቅም የሚያንሳቸው ይሆናሉ፡፡

የከተማው ትልቅ የፕሮጀክት ወጪ ከሚመደብለት ሌላ ተቋም የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን አንዱ ሲሆን፣ የዚህ ተቋም ኃላፊዎች በሥራው ላይ የነበራቸውን ልምድ ስናይ ብዙ ግንኙነት የሌለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ትምህታቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ ከተማው በኃላፊነት ተመድበው የሠሩ፣ ከዚያ ደግሞ ወደ ሌላ ሥራ ተመድበው ከቆዩ በኋላ አብረው ሲሠሩ በነበሩ የከተማው አመራሮች አማካይነት በድጋሚ በሹመት የመጡ እንጂ፣ የባለሥልጣኑን የውስጥ አሠራር በአግባቡ የሚያውቁ አይደሉም፡፡ ከሚመረተው ውኃ ከ49 በመቶ በላይ በሚባክንባት ከተማ መሠረታዊ ችግሩ ምንድነው ብሎ ስትራቴጂካዊ አመራር ለመስጠት ብቃት ያለማግኘት ያስከትላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የከተማችን የውኃ አቅርቦት ቢያድግም (አደገ ቢባልም) ባለሥልጣኑ ያልደረሰበት ትልቅ ብክነት እስካሁን መፍትሔ አላገኘም፡፡

ስለዚህ የከተማው አስተዳደር በቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ላይ በጸሐፊው የተነሱ መሠረታዊ ችግሮችን ለመቅረፍ መነሳት አለበት እንጂ፣ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ሊለን አይገባም፡፡ የሕዝብ ሀብት ነውና፡፡ የተቋሙ ኃላፊዎች ከሚመሯቸው ሠራተኞች ጋር ያላቸውን የጌታና የሎሌ ግንኙነት ለመለወጥ ኢሕአዴግ በእጅጉ ሊያስብበት ይገባል፡፡ የድርጅቱ አባላት አድርባይነት ችግር በብዙ አካባቢዎች ያለው ተመሳሳይና የተፈቀደ ሕጋዊ አሠራር መስሏል፡፡ የድርጅቱ አባላት የተለየ የተቃውሞ ሐሳብ በአለቆቻቸው ለማቅረብ ወኔ ይጎድላቸዋል፡፡ ከተጋጩ መጠመድ ይመጣል በሚል ይመስላል የሚያዩትን የሙስና ችግር የሚያጋልጡባቸው የውይይት መድረኮች ተቀዛቅዘዋል፡፡ ከተቋማት ኃላፊዎች ጋር ከተጋጩ ውጤቱ ጥሩ ስለማይሆንላቸው ‹‹ጎመን በጤና››ን መርጠዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ትልቅ የአድርባይነት ችግር ይታይባቸዋል፡፡ ከእነሱ ይልቅ ትንሽ ተስፋ የሚታየው አባል ባልሆነው የመንግሥት ሠራተኛ በኩል ይመስላል፡፡ ሠራተኛው ሐሳቡን እንዲገልጽ የሚያበረታተው ከተገኘ በግዢና በውል በሚፈጸሙ ክፍያዎች ላይ ስለሚሠራው ሙስና ሊያጋልጥ ይችላል፡፡

ለከተማውም አስተዳደር የግምገማ (አውጫጭኝ) መድረክ አመቻችቶ እቀንሰዋለሁ የሚለውን ኪራይ ሰብሳቢነት ለማጥፋት ባይቻልም፣ ለመቀነስ የመፍትሔው አካል እንዲሆን የሚያቀርበውን ተጨባጭ ጥቆማ የሚደመጥበት ሁኔታን መፍጠር ይጠቅማል፡፡ የሚፈጠሩ የግምገማ መድረኮች ችግርን ለመቀነስ ታስቦበት መዘጋጀት ያለበት እንጂ፣ የሚናገረውን ለይቶ ለማጥቃት መዋል የለበትም፡፡ በመሆኑም ሠራተኛው የጥቃት ሰለባ የማይሆንበትን የግምገማ ሥልት በመንደፍ ተግባራዊ ከተደረገ የአምባገነናዊ አመራሮች ቁጥርን በመቀነስ ብልሹ የሆኑትን በሥራቸው የሚመዘኑ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል፡፡ ግምገማው መመራት ያለበት ከተቋሙ ገለልተኛ በሆነ ወገንተኝነት በማይኖረው አመራር ነው፡፡ ይህ ከተደረገ በከተማው የቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት በኩልም ሆነ በተለያዩ ቢሮዎች የተደበቁ የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው አመራሮች እንዲጋለጡ በማድረግ ለከተማው ራስ ምታት የሆነው የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቀነስ ይችላል፡፡

ይህን ለመጀመር የከተማ አስተዳደሩ ከከፍተኛ ኃላፊዎች ጀምሮ ራሱን ያጥራ!! መሠረታዊ ችግር ላለባቸው የየተቋማት አመራሮች ጋሻ ጃግሬ የሆኑ ኃላፊዎችን ይዞ የትም አይዘልቅም፡፡ በየተቋሙ ደመወዛቸውን ብቻ የሚቆጥሩ የስም የሥነ ምግባር መኮንኖችን ምን ሠራችሁ የሚላቸውና የሚከታተላቸውም የለም፡፡ የከተማው ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ጥርስ የሌለው አንበሳ ነው፡፡ በኦዲት ጉድለት ጥፋተኛ የሆኑትን ለሕግ ማቅረብ አልቻለም፡፡ በአጭሩ የከተማዋ የህዳሴ ጉዞ ይቀጥል ብሎ ኢሕአዴግ ከልቡ ካሰበ ለዚህ እንቅፋት የሚሆኑ፣ የማስፈጸም ብቃት የሌላቸው፣ በዕውቀት የማይመሩና አስመሳይ አመራሮችን ሊያርም ይገባል፡፡ አስተያየቱ ለድርጅቱ ለራሱ ሊጠቅመው ይችላልን ይጠቀምበት ሲፈልግ እንደተለመደው በዝምታ ሊያልፈው ይችላል፡፡ መፍትሔ ነው ባይባልም፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አስተያየት ብዙ አመራሮችን የሚያስደስትም አይደለም፡፡ እርስ በርስ የሚተዋወቁና የሚደጋገፉ በርካታ አመራሮች ስላሉ በአንዴ ዕርምጃ መውሰድ በአስተዳደሩ ወቅታዊ አቅም የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ይሁን እንጂ ይህን አስተያየት ባለመቀበል ‹‹ውሾቹ ይጮሃሉ ግመሉ ግን ጉዞውን ቀጥሏል›› የሚለው ተረት ለዚህ መሰሉ የሕዝብ ሀብት ምዝበራ የሚሠራ መፍትሔ አይደለም፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሌሎች የአፍሪካ ከተሞች የማይታዩ ትልልቅ የልማት ሥራዎች መኖራቸውንና መገንባታቸው፣ እነዚህም የመሠረተ ልማት ሥራዎች የከተማውን አስተዳደር የሚያስመሰግኑ መሆናቸው ባይካድም፣ ከተማዋ አንዳንድ ግንባታቸው በችግር የተተበተቡ ፕሮጀክቶች ባለቤት መሆኗን ለማየት አበበ ቢቂላ ስታዲዮምንና የራስ ኃይሉ ስፖርት ጅምናዚየም የጥራት ችግር ማየት ይበቃል፡፡ የባህር ዳርና የመቐለ ስታዲየም ከአዲስ አበባ ከተማ ከኋላ ተነስተው ለአገልግሎት መዋላቸው ትልቅ ትምህርት ሊሰጥ ይችላል፡፡ የአዲስ አበባው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ግንባታው ሳይጠናቀቅ እየተንፏቀቀ 20 ዓመታት ሊደፍን ነው፡፡ 

በተረፈ ስህተትን ለማረም ቅን የሆኑት፣ ትሁትና ሰው አክባሪ የሆኑት የከተማዋ ከንቲባ ከዚህ በፊት በሠሩባቸው ቦታዎች የተበላሸ አሠራርን ለማስተካከል ቁርጠኛ ስለመሆናቸው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ በእኔ እምነት ግን አጋዥ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ በትውውቅ የተወሳሰበውን የመጠቃቀም ሰንሰለት ለመበጣጠስ ትልቅ አጋዥ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የፌደራል መንግሥትም አያገባኝም ብሎ እጁን አጣጥፎ መቀመጥ ያለበት አይመስለኝም፡፡ የተጠቆሙት ችግሮች እውነት ነው ወይስ ሐሰት ተብሎ ቢጣራ ጥሩ ነው፡፡ የሕዝብ ሀብትን የሚመዘብሩ (የሚያስመዘብሩ) አመራሮችን በጋራ ማስተካከል እንጂ የከተማው አስተዳደር ራሱ ይወጣው ማለቱ አይጠቅምምና!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...