Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉበኮንዶሚኒየም ዕጣ የመክፈል አቅም ለሌለው የመንግሥት ሠራተኛ የተሰጠው ትርጉም አልባ የ20 በመቶ...

በኮንዶሚኒየም ዕጣ የመክፈል አቅም ለሌለው የመንግሥት ሠራተኛ የተሰጠው ትርጉም አልባ የ20 በመቶ ዕድል

ቀን:

በአሻም አዲስ

ክብርና ሞገሥ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትራችን አቶ መለስ ዜናዊ ይሁንና አገራችንን ዘመናዊ ለማድረግ፣ በዚያውም ደሃውን ጨምሮ ሁሉም በየአቅሙ የቤት ባለቤት የሚሆንበትን የቤቶች ልማት ዕቅድ ነደፉልን፡፡ የዛሬውን አያድርገውና። በሕይወት እያሉም በርካታ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ተገንብተው ፍትሐዊ በሆነ ዋጋ በርካታ ሕዝብን ተጠቃሚ አድርገዋል። በ1998 ዓ.ም. ዕጣ የወጣላቸው ሰዎች ባለሁለት መኝታ ቤት በ50,000 ብር ተረክበዋል። ዛሬ ይኼ ዋጋ 340,000 ብር ደርሷል። እስኪ አስቡት የማንኛውንም ሸቀጥ ዋጋ ወስደን በ1998 እና በ2007 ዓ.ም.  መካከል ያለውን ልዩነት ብናነፃፅር ይኼን ያህል ዋጋ ጨምሮ አናገኝም።

በደመወዝ ጭማሪ ሰሞን ነጋዴዎች የተጋነነ ዋጋ እንዳይጨምሩ ሲዝትና ሲቀጣ የነበረውስ የሸማቾች ደኅንነት የተባለ ተቋም፣ በቤቶች ላይ በመንግሥት ይኼን ያህል የተጋነነ የቤቶች ዋጋ ጭማሪ ሲደረግ ምነው ድምፁ ጠፋ? ወይስ ጡንቻው የደረጀው ነጋዴው ላይ ብቻ ነው? ይኼንን ሁሉ የምለው ለአሥር ዓመታት ቤት ይደርሰኛል ብዬ ስጠብቅና በመንግሥት የ20 በመቶ ቅድሚያ ዕድል ተሰጥቶሃል ተብዬ ስደሰት ቆይቼ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተስፋዬን ያጨለመ የመንግሥት ሠራተኛ ነኝ። በእኔ እምነት ይኼ ድርጊት የቤቶች ልማት ፖሊሲው ዓላማውንም ሆነ መንግሥት ለደሃው ቆሜያለሁ፣ ወግኛለሁ ሲል ሁሌም ከሚነግረን እውነታ ተቃራኒ ነው።

የመንግሥት ሠራተኛው አቅምና የቤቶቹ ዋጋ አራምባ ቆቦነት

የቤቶች ልማቱ እንደተጀመረ ዓላማ ተደርጎ የተቀመጠው በዝቅተኛ ዋጋ ቤቶችን በመገንባት ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ነበር። ዛሬ ግን የአዲስ አበባ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ልማት ቢሮ የቤት ዋጋ ማነፃፀሪያ የዜጎች አቅም ሳይሆን ነጋዴው ሆኗል። የቢሮው ኃላፊ ሁሌም ስለዋጋው መወደድ ሲጠየቁ ምላሻቸው በሪል ስቴት እኮ የአንድ ቤት ዋጋ ይኼን ያህል ነው ብለው ነው እንጂ፣ የዜጎች አቅም ለሳቸው ጉዳያቸውም አይደለም። ነጋዴ ሆኑ እንዴ እኚህ ባለሥልጣን? በጣም ያሳዝናል። ለምሳሌ አሁን በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት በሾፌርነት ነው የማገለግለው፡፡ ደመወዜም 1,035 ብር ነው፡፡ ከዚህ ላይ ታክስ፣ ጡረታና የህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዥ ተቆራርጦ 795 ብር ነው የሚደርሰኝ። አስቡት አሁን ባለ አንድ መኝታ ቤት ደርሶኛል። ቅድሚያ ክፍያው  35,000 ብር ነው፡፡ ይኼን ከእኔ አቅም ጋር አነፃፅሩትየቱ የመንግሥት ሠራተኛ ከየት አምጥቶ ይኼ ብር ይኖረዋል?

እሺ ይኼን እንደምንም ብዬ ተበድሬም ተለቅቼም ልክፈል፡፡ ከዚያ ደግሞ በባንክ ወለድ የተሞላ በየወሩ 1,300 ብር አካባቢ መክፈል ይጠበቅብኛል። ደመወዜ 800 ብር፡፡ ምግብ የለ፣ ልብስ የለ፣ ልጅ ወልዶ ማሳደግ የለ ብዬ እንኳን ልከፈል ብል ከየት ሞልቶልኝ? ያሳዝናል፡፡ በዚህ ሁኔታ እንኳን 20 በመቶ፣ 100 በመቶ ቅድሚያ ዕድል ቢሰጠንስ የማንጠቀምበት ዕድል ምን ያደርግልናል? ለመሆኑ ይህን ውሳኔ ያሳለፉት ለደሃ ተቆርቋሪ ነኝ የሚለው ኢሕአዴግ አባል የሆኑ ባለሥልጣናት? ወይስ ትርፍ እያሰሉ የሚጓዙ ነጋዴዎች? አጠያያቂ ነው።

በጣም አሳዛኙ ነገር ደግሞ ሰሞኑን መግለጫ የሰጡት የአዲስ አበባ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊዎች ጭፍን ያለ አነጋገር ነው። እንደነሱ አገላለጽ የቤት ዋጋው ፍትሐዊ ነው። ሩቅ ሳይሄዱ የክፍያ መጠኑን ከራሳቸው ገቢ ጋር ቢያነፃፅሩት መልሳቸው ለደሃ ምን ያህል መራር እንደ ሆነ በተረዱት ነበር። ለነገሩ ሳያውቁት ቀርተው ነው ብዬ አላስብምምን ያድርጉ እነሱ? ዕድሜ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በነፃ የመኖሪያ ቤት ተሰጥቷቸዋል። ስለዚህ እውነታውን እንዳይረዱ ወይም ጨፍነው እንዲክዱ አደረጋቸው።

ምክንያት የሌለው የዋጋ ጭማሪ

በአሁኑ ወቅት የኮንስትራክሽን ዋጋን ያናረ ምንም ተጨባጭ ነገር በገበያው ውስጥ አይታይም። በግንባታው ወቅት ሲሚንቶው፣ ብረቱ፣ ድንጋዩ ያን ያህል የተለየ ጭማሪ አልታየባቸውም። ምናልባት ዋጋውን ያስወደደው በዓመት ውስጥ እንዲያልቅ ተብሎ የተጀመረው ሥራ በአስተዳደሩ የማኔጅመንት አቅምና ቁጥጥር ልልነት፣  ሥራው ሦስት አራት ዓመት በመውሰዱ ነው። ይኼ ደግሞ የእኛ የተጠቃሚዎች ችግር አይደለምእኛ ድጋሚ ተመዝገቡ ሲባል ተመዝግበናል፡፡ ቆጥቡ ሲባልም ቆጥበናል። የቤቶቹ ግንባታዎቹ በመጓተታቸውም በቤት ኪራይ ፍዳችንን ስናይ ቆይተናል። ለመሆኑ በምን ጥፋታችን ነው ከአስተዳደሩ ችግር በመጣ እኛ ጭማሪ ከፋይ የምንሆነው?

የቤቶቹን ዋጋ በተመለከተ እየተደረገ ያለው የተሳሳተ ንፅፅር

ከላይ እንደገለጽኩት የከተማዋ የቤቶች ልማት ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ ሁሌም የቤቶቹን ዋጋ ፍትሐዊነት ሊነግሩን የሚሞክሩት ከግል ሪል ስቴት አልሚዎች ጋር አነፃፅረው ነው። ይኼ እጅግ በጣም የተሳሳተ አካሄድ ነው። በእኔ እምነት የቤቶቹ ዋጋ ከመንግሥት ሠራተኛውም ሆነ ከሌላው ደሃ የኅብረተሰብ ክፍል የመክፈል አቅም ጋር ነው መገናዘብ ያለበት። አንድ ጥሩ ደመወዝ ያገኛል የሚባል የመንግሥት ሠራተኛን ደመወዝ እንውሰድ። ለምሳሌም ያህል ከፍተኛ ተከፋይ የሚባሉት የዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሮች ደመወዝ ግፋ ቢል 6,000 ብር ነው። ከዚህ ላይ 35 በመቶ ታክስ ተጨርግዶለት የተጣራ ደመወዝ ቢደርሰው 4,000 ብር ቢሆን ነው። ይኼ ሰው እንዲያው የተሻለ ብሎ ተመዝግቦ የባለ ሁለት መኝታ ቤት ዕድለኛ ቢሆንና በየወሩ 2,800 ለቤት ቢከፍል ቀሪው 1,200 ብር ምግብ፣ ጤና፣ ልብስና የልጆች ትምህርት ሆኖ እስኪ አስቡት? ካልዘረፈ ወይም ካልሞሰነ በጭራሽ የዚህ ቤት ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም። ሌላውና በጣም በሚያሳፍር ሁኔታ ቤቶች ልማት አካባቢ ያሉ ሠራተኞች ሲናገሩ የሰማሁት ደግሞ አታከራየውም ወይ? ወይም ብትሸጠው እኮ ይኼን ያህል መቶ ሺዎች ብር ያወጣልሃል የሚል ነው። ይኼ እኮ ቤቶቹ ሲጀመሩ ዓላማ ተደርጎ ከተወሰደው ዜጎችን የቤት ባለቤት የማድረግ አካሄድ ተቃራኒ ነው።

ልዩነት የሌለው የክፍያ ዋጋ

የቤቶቹ ዋጋ የተገለጸው በደፈናው በካሬ ሜትር ይኼን ያህል ተብሎ ነው እንጂ፣ ከከተማ ያለው ርቀትና ከወለሉ ዓይነት ጋር አለመዛመዱ ኢፍትሐዊነቱን የሚያጎላ ሌላ ምክንያት ነው። ለምሳሌ ያህል በመሀል ከተማ የሚገኘው ልደታም ሆነ ባሻ ወልዴ ችሎትና በጣም በርቀት ያሉት የካ አባዶና ቱሉ ዲምቱ የመሳሰሉ ሳይቶች ዋጋ በምን መሥፈርት ተመሳሳይ ይሆናል? በተመሳሳይ ምድርና አንደኛ ፎቅ የደረሰውና አራተኛ፣ ሰባተኛ ወይም 12 ፎቅ እንዴት በካሬ ሜትር ተመሳሳይ ዋጋ ይወጣላቸዋል? በፎቆቹ መጨረሻ የደረሳቸው ደግሞ የውኃው ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ ኮርኒስ ለማሠራትና የጣሪያውን ፍሳሽ ለማስቆም የሚያወጡት ወጪስ እንዴት ታሳቢ ሊሆን አልቻለም? ይኼ የሚያሳየው የቤቱ ዋጋ የሚተመነው ሳይንሳዊ መንገድን ተከትሎ ሳይሆን በግምት እንደሆነ ነው። ይኼም ፍትሐዊነቱ ላይ ትልቅ ጠባሳ የሚያሳርፍ ጉዳይ ይመስለኛል።

በአጠቃላይ ከአሥር ዓመት በላይ በትልቅ ተስፋ ስንጠብቀው የነበረውና በመንግሥት ተሰጠን ብለን ደስ ብሎን የነበረው የ20 በመቶ የቅድሚያ ተጠቃሚነት ዕድል፣ የአዲስ አበባ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ አጨልሞታል ለማለት እወዳለሁ። እውነት ግን መንግሥት ይኼን ጉዳይ እንዴት ተመልክቶት ይሆን? በሌለ አቅማችን ታክስ እየከፈልን ያለንና ለአገራችን ልማት ደፋ ቀና ለምንል፣ በዓባይ ግድብ ዙሪያ ግንባር ቀደም አስተዋጽኦ ላበረከትን የመንግሥት ሠራተኞችና ድሆች የሚሰማና የሚመልስልን መንግሥት ይኖረን ይሆን?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው    [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...