Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በቆላማ ሥፍራዎች የግብርና ምርታማነትን ለማሻሻል ስምምነት ተደረገ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ቆላማና ደረቃማ ሥፍራዎች የግብርና ምርትን በተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችና የምርምር ሥራዎች በማገዝ ምርታማነትን ለማሳደግ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና ዓለም አቀፍ የሰብል ምርምር ተቋም በአጋርነት ለመሥራት ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡

ሁለቱ ተቋማት ዓርብ ሚያዝያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. እንዳስታወቁት፣ በኢትዮጵያ ቆላማ ቦታዎች የሚስተዋለውን ዝቅተኛ ምርታማነት ለማሳደግ ያስችላል ባሏቸው አራት መስኰች ላይ ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡

በተለይ የባቄላ ምርታማነትን ማስፋፋት፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚውሉ የጥራጥሬ ምርቶችን ማሳደግ በማሽላ፣ በዘንጋዳና በጤፍ ሰብሎች ለተሻለ የእርሻ አጠቃቀም የሚውል የመሬትና ውኃ ጥበቃ እንዲሁም ከአየር ፀባይ መቀያየር ጋር የገበሬዎችን ግንዛቤና ክህሎት ማሳደግ የስምምነቶቹ ይዘቶች ናቸው፡፡

‹‹እነዚህን መሰል ችግሮቻችንን ለመፍታትና የተሻለ ምርታማነትን ለማምጣት እንዲህ ዓይነቱ የጋራ ጥምረት የጎላ ጠቀሜታ ሲኖረው፣ የእሴት ሰንሰለት ያለው ሥራ እንድንሠራ ያግዘናል፤›› ሲሉ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ፋንታሁን መንግሥቱ ከስምምነቱ በኋላ ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የሰብል ምርምር ተቋም በቆላማና በደረቃማ ቦታዎች በሚመረቱ የሰብል ዓይነቶች፣ በምርትና በአዳዲስ የቴክኖሎጂ ፍብረካዎች ላይ በ55 አገሮች ውስጥ የሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡

ድርጅቱ የሚታወቅባቸውን የፈጠራና የምርምር ሥራዎች ወደ ኢትዮጵያ አምጥቶ በአገሪቱ የእርሻ ዘርፍ የራሱን አስተዋፅኦ ለማድረግ ከመንግሥት ጋር የደረሰበት ስምምነት እንዳስደሰታቸው የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዴቪድ በርግቪንሰን ገልጸዋል፡፡

‹‹ዋናው ፍላጎታችን በኢትዮጵያ ላሉት መልካም አጋጣሚዎች ተጨማሪ እገዛ ሊሰጡ የሚችሉ የፈጠራ ውጤቶችና ክህሎቶች ማምጣት ነው፡፡ በመሆኑም ረዘም ላሉ ጊዜያት የሚቆይና ቀጣይነት ባለው ጥረት የግብርና ንግድ ሥራዎች መፈልፈያ፣ የተሻለ የንግድ ፈጠራ ክህሎትና አቅም በኢትዮጵያ እንዲዳብር ያደርጋል፤›› ሲሉም የዓለም አቀፉ ተቋም ኃላፊ ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ ተቋማት በአዲስ አበባ ባደረጉት የአንድ ቀን ስብሰባ የሁለቱም የቦርድ አመራሮችና ባለሙያዎች በተገኙበት የተካሔደ ሲሆን፣ የልምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች