Sunday, July 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአለታ ወንዶ ዳዬ መንገድ በሰባት ዓመቱ ተጠናቀቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  ሥራው ኮንትራክተሩን አክስሯል ተብሏል

ዓለማየሁ ከተማ ኮንስትራክሽን በደቡብ ክልል በሲዳማ ዞን፣ ከአለታ ወንዶ እስከ ዳዬ ድረስ የገነባው 51 ኪሎ ሜትር የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ከሰባት ዓመታት በኋላ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተመረቀው ይህ መንገድ፣ በሦስት ዓመታት ይጠናቀቃል ተብሎ የተጀመረ ሲሆን አጠቃላይ ግንባታው ግን ሰባት ዓመታትን ወስዷል፡፡

መንገዱ ከተያዘለት ጊዜ በላይ ሊፈጅ የቻለበት ዋነኛ ምክንያት ግንባታው ከተጀመረ በኋላ የዲዛይን ለውጥ በመደረጉ ነው ተብሏል፡፡ ለመንገዱ ግንባታ በአጠቃላይ 426.9 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡ በ2000 ዓ.ም. የተጀመረው የዚህ መንገድ ግንባታ ኮንትራክተሩን ለኪሣራ እንደዳረገም ተጠቁሟል፡፡

የዓለማየሁ ከተማ ኮንስትራክሽን ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓለማየሁ ከተማ ድርጅታቸው ያለውን ሀብት አሟጥጦ የገነባው መንገድ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ አካባቢው በጣም ዝናባማ ስለሆነ ግንባታውን ለማካሄድ እንቅፋት ሆኖ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይህም ቢሆን ግን መጀመሪያ በተሠራው ዲዛይን መሠረት ወደ ሥራ ከተገባ በኋላ መንገዱ በአስፓልት ኮንክሪት ቢሠራ ይሻላል የሚል ሐሳብ ከአካባቢው ኅብረተሰብ በመቅረቡ፣ ለመንገዱ ግንባት መዘግየት ዋነኛ ምክንያት ነው ይላሉ፡፡ ከአካባቢው ኅብረተሰብ የቀረበውን ሐሳብ ዓለማየሁ ከተማ ኮንስትራክሽንም ተቀብሎት መንገዱ ከፍተኛ ቡና የሚመረትበት በመሆኑና ዝናባማ ስለሆነ በተሻለ ደረጃ መንገዱ በአስፓልት ኮንክሪት ቢገነባ ይሻላል የሚለውን ሐሳብ ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ማቅረቡን አቶ ዓለማየሁ ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም ባለሥልጣኑ ሐሳቡን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ ይህም በወቅቱ ከነበረው የባለሥልጣኑ ማኔጅመንት ጋር ጭቅጭቅ አስነስቶ እንደነበር አቶ ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡

ሐሳቡ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ቀደም ብሎ በነበረው ዲዛይን መሠረት ወደሥራ መግባታቸውን የገለጹት አቶ ዓለማየሁ፣ ሕዝቡ ግን በዚህ ደረጃ ከሚሠራ ይቁም ብሎ ግንባታውን በማስቆሙ የኮንስትራክሽን ግንባታው ለሦስት ዓመታት እንዲቋረጥ ምክንያት ሆኗል ይላሉ፡፡

በወቅቱ የነበሩ የደቡብ ክልል ባለሥልጣናት በጉዳዩ ጣልቃ ገብተው በአስፓልት ኮንክሪት ይሠራ፣ የሚለው ጉዳይ ላይ ብዙ ከተነጋገሩ በኋላ መንገዱ በአስፓልት ኮንክሪት እንዲሠራ በመወሰኑ ዲዛይኑ ተቀይሮ ወደ ሥራ ለመግባት ሦስት ዓመት መፍጀቱን ጠቅሰዋል፡፡

በ2005 ዓ.ም. ዲዛይኑ ተቀይሮ በአዲሱ ዲዛይን ወደሥራ እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ ግን በአዲሱ ዲዛይን የሚሠራው ሥራ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ድርጅቱ የተፈተነበትና ጥሪቱንም ያሟጠጠበት ነው ብለዋል፡፡

‹‹መንገዱን ሠርተን ብናስረክብም ከፍተኛ ኪሣራ ደርሶብናል፤›› ያሉት አቶ ዓለማየሁ፣ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ መክሰራቸውን ይገልጻሉ፡፡ ኪሣራው የኩባንያቸው ብቻ ሳይሆን በአዲሱ ዲዛይን መሠረት የሚያስፈልጉ እንደ አስፓልት ያሉ ምርቶችን በዱቤ ያቀረበው ናሽናል ኦይል ኩባንያና ብድር የሰጡን ባንኮች ጭምር ሆኗል ይላሉ፡፡ የእነዚህ ኩባንያዎች ገንዘብም ገና ወደፊት የሚከፈል ነው በማለት ገልጸዋል፡፡

በዲዛይን ለውጡ ምክንያት የመጣውን ከፍተኛ ወጪ በማስላት ባለሥልጣኑ የዋጋ ማካካሻ እንዲከፍላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውንም አቶ ዓለማየሁ ይናገራሉ፡፡ ጥያቄው ትክክል ነው የሚሉት አቶ ዓለማየሁ ዲዛይኑ ተቀይሮ እንዲሠራ የተደረገ በመሆኑ ቀድሞ በነበረው ዲዛይን መሠረት እንሠራበታለን ብለን በተዋዋልንበት ዋጋ ሊሠራ ስለማይችል የዋጋ ልዩነቱን የሚያሳይ ክፍያ እንዲከፈላቸው ለባለሥልጣኑ በማቅረብ ምላሽ እየጠየቁ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡

‹‹የዚህን ፕሮጀክት ሥራ በ2000 ዓ.ም. ስንጀምር የአንድ ቦቴ መኪና ነዳጅ 260,000 ብር ነበር፤›› ያሉት አቶ ዓለማየሁ፣ አሁን ግን የፕሮጀክቱን ማጠናቀቂያ ሥራዎች ለመሥራት ለአንድ ቦቴ ነዳጅ 900,000 ብር እየከፈሉ ሲሠሩ እንደነበር ጠቅሰው ያለው የዋጋ ልዩነት ምን ያህል እንደሆነ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ስለዚህ የልዩነቱን ክፍያ እየጠበቅን ነው ይላሉ፡፡

ይህም ቢሆን ግን የመንገዱ መጠናቀቅ በአካባቢው ሕዝብ ላይ የፈጠረው  ስሜት ትልቅ እርካታን ይሰጣል ብለዋል፡፡ ከአካባቢው ነዋሪዎች መረዳት እንደሚቻለውም መንገዱ ቢዘገይም የግንባታው የጥራት ደረጃ እንዳረካቸው ገልጸዋል፡፡ በምርቃቱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ የዚህ መንገድ መገንባት በአካባቢው ያለውን ምርት በፍጥነት ወደገበያ ለማቅረብ ያስችላል ብለዋል፡፡

የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ በታዳጊነታቸው በአካባቢው የሚመረተውን በቆሎ ለገበያ ለማቅረብ የነበረው ፈተና ከባድ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

አስቸጋሪ የነበረው መንገድ ተሽከርካሪዎች እንዳይገቡ ያገደ ሲሆን፣ ይገቡ የነበሩት ሁለት ተሽከርካሪዎች ብቻ እንደነበሩ በማስታወስ፣ የአዲሱ መንገድ ሥራ መጀመር ግን በቀን ከሁለት መቶ በላይ ተሽከርካሪዎች እንዲጓጓዙ አስችሏል ተብሏል፡፡ ነዋሪዎች ከእግር ጉዞ ወጥተው በመኪና እንዲጓጓዙ ዕድል ሰጥቷል፡፡ የዚህ መንገድ መገንባት ከፍተኛ ለውጥ የሚያስገኝ መሆኑን አቶ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡ ከዚህ የመንገድ ምርቃት ጎን ለጎን በዳዬ ከተማ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲን አዲስ ግቢ ለመገንባት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የመሠረት ድንጋይ አኑረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች