Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አለ በጅምላን የሚተካው የግል ዘርፍ ይመጣ ይሆን

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት በአገሪቱ ያለውን ገበያ ለማረጋጋት በአማራጭነት ተግባራዊ ካደረጋቸው ዕርምጃዎቹ መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ንግድ ድርጅት ወይም አለ በጅምላ የተባለውን ኩባንያ መፍጠር ነው፡፡ የአለ በጅምላ የቦርድ አባልና የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሊ ሲራጅ በሐዋሳ ከተማ የአለ በጅምላ ቅርንጫፍ መክፈቱን አስመልክቶ በተካሔደው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳምለከቱት፣ በአገሪቱ ውስጥ የታየውን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተከትሎ የዋጋ ግሽበትና የሸቀጦች ዋጋ አለመረጋጋትን ለማስተካከል መንግሥት የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅድ አውጥቷል፡፡ በአጭር ጊዜ  ውስጥ እተገብረዋለሁ ብሎ ከያዘው ዕቅድ ውስጥ አንዱ አለ በጅምላን መፍጠር እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

በሸቀጦች ጅምላ ንግድ ውስጥ እንዲሳተፍ የተደረገው አለ በጅምላ፣ መንግሥታዊ ተቋም ሲሆን፣ የመመሥረቱ ጥንስስ ከሁለት ዓመታት በላይ ቆይቶ ነበር ወደተግባር የገባው፡፡ ሥራውን ከጀመረ አንድ ዓመት አስቆጥሯል፡፡

ባለፉት 12 ወራት ውስጥ በአዲስ አበባ ሦስት፣ ከአዲስ አበባ ውጭ ሁለት ቅርንጫፎቹን ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ተጨማሪ ቅርንጫፎችንም በክልል ከተሞች ለመክፈት እየተዘጋጀ ነው፡፡ ተረኞቹ ከተሞች ባህር ዳርና ደሴ መሆናቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የሐዋሳው ቅርንጫፍ ሲከፈት፣ የአለ በጅምላ ቦርድ አባልና የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሊ ሲራጅ፣ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መርከቡ ዘለቀ፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ብርሃኑና የአለ በጅምላ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኑረዲን መሐመድ አለ በጅምላን በተመለከተ ሰፋ ያለ ገለጻ አድርገው ነበር፡፡

አለ በጅምላ ዛሬና ነገ

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከተሰጠባቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ የአለ በጅምላ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምንድነው? እስካሁንስ ምን የተጨበጠ ውጤት አምጥቷል? የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡ የአለ በጅምላ አመሠራረትና ጉዞን የተመለከቱ ጥያቄዎችም ተካተው ነበር፡፡

አቶ አሊ ሲያብራሩ፣ የአለ በጅምላ አመሠራረትን ወደኋላ መለስ ብለው በማስቃኘት ሲሆን፣ አለ በጅምላ ሲቋቋም የግል ዘርፉን ሥራ ለመተካት ተብሎ እንዳልሆነ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

በተለይ ወሳኝ የተባሉ መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦችን ከአገር ውስጥና ከውጭ በመግዛት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ታስቦ የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ መንግሥት በዚህ ሥራ እጁን ሊያስገባ የቻለው የንግዱ ዘርፍ ግልጽነትና ፍትኃዊ አሠራር የሰፈነበት ባለመሆኑ፣ የዘመናዊነት ጉድለትና ተወዳዳሪነት ያነሰው ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ መንግሥት ይህንን በጥናት በማረጋገጡ የጅምላ ንግድ ችግሮችን በሒደት ሊቀረፍ የሚችልበትን መንገድ ለመፍጠር ሲባል አለ በጅምላ ተቋቁሟል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ዘርፍ ያለውን ችግር በመቅረፍ ምቹ ሁኔታ መፍጠር የነበረበት የግል ዘርፉ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ለአለ በጅምላ መፈጠር ምክንያት ብለው ያቀረቡት ሌላው ነጥብ በአገሪቱ የተከሰተው የሸቀጦች ዋጋ እየናረ መምጣት ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ጥሪት ላይ ሊያስከትል የሚችለው ችግር በመታሰቡ ተቋሙ ሊፈጠር ችሏል ተብሏል፡፡ የዋጋ ንረቱ በልማትና በኢንቨስትመንት ላይ ያልተረጋጋ ማክሮኢኮኖሚ እንዲኖር በማድረግ ሊያስከትል የሚችለውን ችግር ከግምት በማስገባት መንግሥት የገበያ ጉድለቶችን እያጠና ክፍተቶችን ለማሟላት የሚያደርጋቸውን ጥረቶች ለማሳካት የአለ በጅምላ መፈጠር ተገቢ እንደነበርም ሚኒስትር ዴኤታው ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

የገበያ የሸቀጦች ዋጋን ማረጋጋትና የጅምላ ንግዱን ዘመናዊ ማድረግ የሚሉትን መሠረታዊ ዓላማዎች ይዞ የተነሳው አለ በጅምላ፣ የገበያ ተደራሽነቱን እያሰፋ ወደ ኅብረተሰቡ እየቀረበ አማራጭ የንግድ ሥርዓት የመፍጠር ሥራውን እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡

አቶ ኑረዲንም የአለ በጅምላ መፈጠር ለሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች መፈጠር በር ይከፍታል ይላሉ፡፡ ከዚህ የንግድ ድርጅት እንቅስቃሴ ሌሎች የንግድ ዘርፉ አባላት ትምህርት በመውሰድ ዘመናዊ የጅምላ ንግድን ኢትዮጵያ ውስጥ ያስፋፋሉ በሚል ተስፋ እንደተቋቋመ አስረድተዋል፡፡

አቶ መዝገቡም አለ በጅምላ አማራጭ ገበያ እንዲሆን እንጂ የነጋዴውን ሚና እንዲተካ ታስቦ የተቋቁመ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በነፃ ገበያ ፖሊሲ ሥርዓት በሚተዳደር አገር ውስጥ ነጋዴው ወደ ዘመናዊነት እንዲመጣ ንግድ ውድድርን ማለማመድና ማስተማር ዓላማ አድርጐ የተቋቋመ እንጂ ዘላቂ ያለመሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ተልዕኮውን ካሳካ በኋላ አለ በጅምላ ወደ ግል ይዞታነት እንደሚዛወር ሁሉም የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡  

የወደፊት ዕጣ ፈንታው እንዴት ይሆናል የሚለው ጥያቄ ላይ ሁሉም የሥራ ኃላፊዎች ተመሳሳይ ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡ ‹‹አለ በጅምላ ተልዕኮውን ካሳካ ፕራይቬታይዝድ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ኑረዲን በዚሁ ጉዳይ አክለው እንደገለጹትም አለ በጅምላ የዕውቀት ማዕከል ይሆናል ስንል ችርቻሮ እንዴት እንደሚሸጥ፣ የጅምላ ሥርዓት እንዴት እንደሚሠራ፣ የአለ በጅምላን ሞዴል ቀድቶ  መሥራት የሚፈልግ የግል ዘርፍ እንደገባበት ነው፡፡ ለዚህም በራችንን ክፍት አድርገን የአሠራር ሥርዓታችንን አዘጋጅተን በዚህ መልክ እንደ አለ በጅምላ ዓይነት 10 እና 20 ከተፈጠረ በመንግሥት አቅጣጫ መሠረት አለ በጅምላ ወደ ግል ይዞራል››

‹‹በመንግሥት እምነትና ፍልስፍና ገበያ ፍትሐዊ አይደለም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ኢኮኖሚ ባለው አገር ውስጥ ገበያ ሁልጊዜ ሠፊ ጉድለት አለበት ብሎ ይምናል፤›› በማለት የገለጹት አቶ አሊ ደግሞ ከሌሎች የምንለየውም ገበያ በራሱ ፍትሐዊነት በውስጡ የተፈጠረውን ችግር ራሱ ይፈታዋል የሚል እምነት ስለሌለ ነው ብለዋል፡፡ ይህንን ጉድለት በሁለት መንገድ መፍታት እንደሚችል ሲያስረዱም፣ አንዱ ለራሱ ለገበያው መተው፣ ሁለተኛው በተመረጠ አኳኋን መንግሥት ጣልቃ እየገባ የገበያ ጉድለቶቹን እያሟላ ይሒድ የሚል ነው ብለዋል፡፡ እነዚህ የገበያ ጉድለቶች መሟላታቸውን ሲያረጋግጥ ደግሞ ለግል ዘርፉ እየተወ እንዲወጣ የሚደረግበት ዕድል መኖሩን በመጥቀስ እስከዚያ ግን አለ በጅምላ የገበያ ጉድለቱን እያሟላ የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አለ በጅምላ በእስካሁን ጉዞው እንዲህ ዓይነት ውጤት አስገኝቷል ማለት ባይቻልም ገበያን በማረጋጋት አስተዋጽኦ ስለማድረጉ ግን ተገልጿል፡፡ ትክክለኛ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ በማድረግ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ አለው ያሉት አቶ መርከቡ፣ ለምሳሌ በልኬትና በጥራት ዙሪያ ችግር ሳይኖር ሸማች ያለ ሥጋት እንዲሸምት ማስቻሉ አንዱ ነው ይላሉ፡፡ መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ የሚያሠራጫቸው ምርቶች ጤናማና በትክክለኛ ልኬት የሚቀርቡ መሆናቸው ትልቅ ጥቅም ነው ብለዋል፡፡ በእስካሁን ሒደቱ የተገኘ ውጤት ምንድነው ለሚለው ተጠየቅ ‹‹አሁን ስለውጤት ልንናገር የምንችልበት ጊዜ ላይ አይደለንም፤›› የሚል ምላሽ የሰጡት አቶ ዓሊ፣  ይህንን ያህል ውጤት አግኝተናል ማለት ባይቻልም ኅብረተሰቡ ወደፊት የበለጠ የሚጠቀምበትን ነገር መፍጠር ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ሥራው ሲጀመር በጥናት ላይ ተመሥርቶ ቢሆንም፣ ለኅብረተሰቡ በስፋት ተደራሽ እየሆነ በመሄድ ከመሥራት ውጭ አሁን ባለው ሁኔታ አጥጋቢ ውጤት አምጥተናል፡፡ ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን ነገር በተሟላ ሁኔታ ሠርተናል ብዬ ለመናገር ሥራው ጅምር ነው፤›› በማለት መልሰዋል፡፡  አሁን ዋናው ሥራ የኅብረተሰቡን ፍላጐት ማሟላት ኅብረተሰቡን በተሻለ ዋጋ እንዲገበያይ ማስቻል ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

አለ በጅምላ ምን ውጤት አስገኝቷል በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ተስፋዬ፣ ደግሞ የንግዱ ሥርዓት ለረጅም ጊዜ ችግር ውስጥ የቆየ ዘርፍ በመሆኑ አለ በጅምላ ከመጣ ገና ሁለት ዓመቱ በመሆኑ በገበያ ውስጥ ተዓምር ይፈጥራል ማለት እንደማይቻል ይናገራሉ፡፡ ውጤት እያስገኘ ስለመሆኑ ግን መናገር ይቻላል ብለው ከዚህ ውጤት አንዱ ሸማች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸምት ማስቻሉ ነው ብለዋል፡፡

አለ በጅምላና አዳዲስ ቅርንጫፎቹ

አለ በጅምላ ተጨማሪ ቅርንጫፎችን ይከፍታል? በጅምላ ንግድ ውስጥ ያለውን ድርሻ የማሳደግ ዕቅድ አለው ወይ? የመደብሮቹ አከፋፈት ምንን መሠረት ያደረገ ነው? የሚሉት ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ይነሳሉ፡፡ የቅርንጫፍ አከፋፈቱ በጥናት ላይ የተመሠረተ ነው ያሉት አቶ ኑረዲን፣ ‹‹መደብሮቹን ሲከፍት መጀመሪያ የክልሎቹን አውጭነት ጥናት ወስዶ ነው፡፡ የሻሸመኔ መደብር ከመከፈቱ በፊት የአለ በጅምላ የገበያ ጥናት ቡድን በሻሸመኔ አካባቢ ምን ምን ምርቶች ይፈለጋሉ የሚለውን አጥንቶ በዚያ ጥናት መሠረት የተከፈተ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከ555 በላይ ምርቶች  ይከፋፈላሉ፡፡ ሻሸመኔ ላይ ግን 162 ምርቶችን ማከፋፈል እንደሚቻል አረጋግጠን ከ115 በላይ ምርቶችን ይዘን ጀምረናል፤››  በማለት አቶ ኑረዲን ተናግረዋል፡፡

የሐዋሳው ገበያ ከሻሸመኔው ገበያ የተሻለ ስለሆነ የሚያከፋፍለው የምርት መጠን ከ150 በላይ ሆኖ ሥራው ተጀምሯል፡፡

በሁሉም አካባቢዎች ምን ዓይነት ምርቶች ያስፈልጋሉ ተብሎ የተደረገው ጥናት እንደ ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ዱቄት፣ ስኳር፣ ዘይት የመሳሰሉት ምርቶች ተፈላጊ ናቸው ይላል፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉት ደግሞ እንደ አካባቢው ፍላጐት እየታየ አካባቢውን መሠረት ያደረገ አገልግሎት ለመስጠት የሚታሰብበት ነው፡፡

አለ በጅምላ በየክልሉ መደብሮቹን እያስፋፋ በሚሔድበት ጊዜ በክልሉ ያለውን የገበያ ክፍተት ለመሸፈን ብቻ ሳይሆን ‹‹በዚያ ክልል ውስጥ ሌሎች ተወዳዳሪዎች ላይ ተፅዕኖ በማሳደር በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ጭምር የሚሠራ ተቋም ነው ተብሏል፡፡

የቸርቻሪዎች መዘና

ከአለ በጅምላ ምርት ተቀብለው የሚቸረችሩ ነጋዴዎች የሚመረጡት በግልጽ መመዘኛ ላይ ተመሥርቶ ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡ ወደ ሥራ ሲገባ ባስቀመጠው መስፈርት መሠረት ቸርቻሪዎችን ሲመለምል ቆይቷል፡፡ አመላመሉም መስፈርት አለው፡፡ የአለ በጅምላ ቸርቻሪዎች በዋናነት የሚመረጡት ከዚህ ቀደም ለሸማቹ ሲሰጡ ከነበረው አገልግሎት ላይ በመነሳት ነው፡፡ ይህ አገልግሎታቸው የሚፈተሽ ስለመሆኑ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ‹‹የግላቸውን ንግድ ሥራ ሲሠሩ አላስፈላጊ የምርት እጥረት ሲፈጥሩና ወደቀውስ ሲመሩ የነበሩት ቸርቻሪዎች ጋር ጋር ለመሥራት ፍላጐት የለንም፤›› ብለዋል፡፡

የቀድሞ አገልግሎታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ቸርቻሪዎች ንግድ ፈቃድና የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር (ቲን) ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከእነዚህ ባሻገር በግልጽ በተቀመጡ ዘዴዎች ከመተለመሉት ነጋዴዎች በተጨማሪ መመዘኛዎቹን አሟላለሁ ብሎ ለሚመጣ ነጋዴም በሩ ክፍት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ከዚህ ቀደም ቸርቻሪዎችን ለመመልመል ይሠራበት የነበረው አሠራር በተወሰነ ደረጃ መቀየሩን ያመለክታል፡፡

በዚህ መንገድ የአለ በጅምላ ቸርቻሪዎችን በማብዛት ወደ ኅብረተሰቡ የመድረስ ዕቅድ እንዳላቸው ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ ቸርቻሪው ትርፋማ እንዲሆን እንፈልጋለን ብለዋል፡፡ አለ በጅምላ ባስቀመጠው የትርፍ ህዳግ መሠረት እንዲሠሩ ከማድረግ በላይ ከአለ የሚወስዱትን ምርት በምን ያህል የትርፍ ህዳግ መሸጥ እንዳለባቸው ሸማቹም እንዲያውቀው ይደረጋል፡፡

እነዚህ ሱቆች በትክክል የሚታወቁ ባለመሆናቸው ‹‹አለ በችርቻሮ›› የሚል ታፔላ እንዲለጥፉ እንደሚደረግም ጠቅሰዋል፡፡ የአለ በጅምላ ቸርቻሪዎችን ቁጥር ለማብዛት ሸማቾች በብዛት ይኖራሉ ተብሎ በሚታመንባቸው የኮንዶሚኒየም መንደሮች ውስጥ ያሉ መደብሮች ላይ ትኩረት የማድረግ ዕቅድም ተይዟል፡፡

አለ በጅምላ በአሁኑ ወቅት ከሦስት ሺሕ በላይ ቸርቻሪ ነጋዴዎችን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በ2007 በጀት ዓመትም አንድ ቢሊዮን ብር በመመደብ የምርትና የቅርንጫፍ ስርጭቱን ለማስፋት እየሠራ ይገኛል፡፡ እንደ ኃላፊዎቹ ገለጻ፣ በተለይ መሠረታዊ የሚባሉ ሸቀጦች ከገበያ ዋጋ ባነሰ እንዲሸጡ እያደረገ ነው፡፡ በራሱ ስያሜ የታሸጉ የተለያዩ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ እያስገባ ሲሆን፣ የአለ ምልክት ያለባቸው ደብተርና የዘይት ምርቶችን አስመጥቶ እያሠራጨ ይገኛል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች