Friday, July 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የህንድ ኩባንያ ለሚገነባቸው ሆቴልና ሆስፒታል 40 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ እንዲዘጋጅ ታዘዘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የህንዱ ግዙፍ ኩባንያ አርትሜትስ ካፒታል በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገነባቸው ባለአምስት ኮከብ ሆቴልና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሆስፒታል 40 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ እንዲዘጋጅ ታዘዘ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ ቦታው በመሀል ከተማ በሚካሄደው መልሶ ማልማት ክልል ውስጥ እንዲዘጋጅ፣ ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ፣ የተለያዩ የዘርፍ መሥሪያ ቤቶች የህንዱ ኩባንያ የጠየቀው መሬት እንዲሰጠው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ እሸቱ ደሴ ተፈርሞ ለከንቲባ ድሪባ ኩማ የተላከው ደብዳቤ፣ ‹‹ኩባንያው ያቀረበው ፕሮጀክት የሚኖረው አገራዊ ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ባለው ሕግ መሠረት አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግለት እናስታውቃለን፤›› በማለት የፕሮጀክቶቹ ጠቀሜታ የጎላ በመሆኑ መሬት እንዲሰጠው አስገንዝቧል፡፡

ከንቲባ ድሪባ ከኩባንያው በቀጥታ ከተላከላቸው ደብዳቤና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ድጋፋቸውን የሰጡትን የአርትሜትስ ካፒታል ፕሮጀክቶች ከገመገሙ በኋላ፣ በሥራቸው የሚገኘው የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ቦታ እንዲያዘጋጅ ትዕዛዝ መስጠታቸው ታውቋል፡፡

ከንቲባው ለመሬት ቢሮው በጻፉት ደብዳቤ አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ለእነዚህ ፕሮጀክቶች በአስቸኳይ መሬት ተዘጋጅቶ ለውሳኔ፣ ለካቢኔ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ አርትሜትስ ካፒታል በህንድ ታዋቂ የሆነው የጂያን ግሩፕ እህት ኩባንያ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ በህንድ ሙንባይ፣ በታንዛኒያና በፈረንሣይ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ተሰማርቷል፡፡ በተለይ በሪል ስቴት፣ በግብርናና በኢኩቲ ኢንቨስትመንት በሰፊው እንደተሰማራ ተገልጿል፡፡ ይህ ኩባንያ በአንድ ቢሊዮን ብር ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ለመገንባት አቅዷል፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት 20 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ በመሀል አዲስ አበባ እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡

አርትሜትስ ካፒታል ፕሮጀክቱን ከዚህ በላይ በማስፋት 40 የመኝታ ክፍሎች ያሉት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሆስፒታልና የጤና ማዕከል ለመገንባት አቅዷል፡፡ ለዚህ ፕሮጀክትም በተመሳሳይ አንድ ቢሊዮን ብር በጀት መያዙን ኩባንያው ለከንቲባ ድሪባ የላከው ደብዳቤ ያመለክታል፡፡

ለእነዚህ ሁለት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ታደለች ዳለቾ ለከንቲባ ድሪባ በላኩት ደብዳቤ፣ አዲስ አበባ በርካታ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን የምታስተናግድ በመሆኗ ከተማዋ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ካላት ሰፊ ዕድል ምክንያት ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች መኖራቸው ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ ሚኒስትሯ በደብዳቤያቸው እንዳብራሩት የህንዱ ኩባንያ የውጭ ምንዛሪን ወደ አገር የሚያመጣ በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ በበኩላቸው፣ የጤና ቱሪዝምን ከማስፋፋት አንፃር የሆስፒታሉ መገንባት ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ በተለይም ኩባንያው የሚያቋቁመው ሆስፒታል የልብ፣ የኩላሊትና የስኳር በሽታዎችን ለማከምና ከእናቶችና ከሕፃናት ክብካቤ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች የሚሰጥ በመሆኑ፣ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ሚኒስትሩ ጨምረው አብራርተዋል፡፡

የአርትሜትስ ካፒታል የኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መሠረት መኮንን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያው ያቀረበው የመሬት ጥያቅ መልስ እንዳገኘ ወደ ግንባታ ይገባል፡፡

የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ እንዲያዘጋጅ የታዘዘውን መሬት አዘጋጅቶ ካቀረበ፣ በከንቲባው የሚመራው የአስተዳደሩ ካቢኔ ቦታው ለኩባንያው እንዲሰጥ ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኩባንያው ያቀረባቸው ፕሮጀክቶች በሊዝ አዋጁ መሠረት በልዩ ሁኔታ እንዲስተናገዱ፣ ከከተማው ከንቲባና ከፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ድጋፍ አግኝቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች