መንግሥት በውጭ በስደት ላይ ባሉ ዜጐች ላይ የተፈጸመውንና እየተፈጸመ ያለውን ጉዳት ከማውገዝ ባለፈ፣ ችግሩን ለመቅረፍ ወይም ለመቀነስ በቂ ጥረት እያደረገ አይደለም ሲል የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) ወቀሰ፡፡
ሰመጉ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ውስጥ ባለው ከፍተኛ ድህነትና ሥራ አጥነት፣ የከፋ የኑሮ ውድነትና የፖለቲካ ጫና ምክንያት ከአገራቸው በመሰደድ በተለያዩ አገሮች አስከፊ የስደት ኑሮ በመግፋት ላይ መሆናቸውን ገልጿል፡፡
በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ በስደት በሚኖሩባቸው አገሮች የሚደርስባቸው ድብደባ፣ ማሰቃየትና አሰቃቂ ግድያ አስደንጋጭና አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ እየቀጠለ በመሄድ ላይ ነው ብሏል፡፡
ኢትዮጵያውያን በግፍ ሰለባ የሆኑበትን የደቡብ አፍሪካውን የዘረኝነት ጥቃት፣ እንዲሁም በየመን፣ በሊቢያ፣ በሳዑዲ ዓረቢያና በሌሎችም የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በሕገወጥ አዘዋዋሪዎችና ሰብዓዊነት በጐደላቸው አሠሪዎች የተፈጸመውንና እየተፈጸመ ያለውን ኢሰብዓዊና ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት እንደሚያወግዝ ሰመጉ ገልጿል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ አገር በስደት ላይ ባሉ ዜጐቻችን ላይ የተፈጸመውንና እየተፈጸመ ያለውን እጅግ ዘግናኝ ግድያ፣ ዝርፊያ፣ ድብደባና ሕገወጥ እስራት ለማስቆም ወይም ለመቀነስ ድርጊቱን ከማውገዝ ባለፈ፣ በተግባር ዜጐቹን ከጥቃት ለመጠበቅና ለመከላከል በቂና የተቀናጀ ሥራ ሲሠራ አይታይም፤›› ብሏል፡፡
በመሆኑም መንግሥት ዜጐች በአገራቸው ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተከብሮላቸውና በቂ የሆነ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው በአገራቸው በእኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ እንዲያመቻች ጥሪ አቅርቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት በችግር ላይ የሚገኙና ሕይወታቸው ላይ አደጋ የተጋረጠባቸው ዜጐች በፍላጐትና በሰላም ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን እንዲያመቻች፣ መመለስ የማይችሉትን በተመለከተ መብታቸው የሚከበርበትንና የሕግ ጥበቃ የሚያገኙበትን መንገድ እንዲያመቻች ጥሪ አቅርቧል፡፡
በዚህ መሰሉ ችግር ሰለባ የሆኑና የሚሆኑ ወገኖች አስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲያገኙ፣ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ በመላው ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ሌሎችም የተቻላቸውን እንዲያደርጉ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
መንግሥት በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካ ያሉ የተጐዱ ኢትዮጵያውያንን ችግር ለመቅረፍ፣ እንዲሁም በሊቢያ አሁንም ችግር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን በግብፅ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል እንዲጠቀሙ እያደረገ መሆኑን በመግለጽ ላይ ይገኛል፡፡