Saturday, June 15, 2024

ኢትዮጵያዊነት የጋራ መገለጫ ይሁን!

ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በሚገኙ የኢትዮጵያ ግዛቶችና በመላው ዓለም ተበትነው ያሉ ኢትዮጵያውያን፣ የዚህች አገር ውድ ልጆች ናቸው፡፡ አንዳቸው ከአንዳቸው አይበልጡም ወይም አያንሱም፡፡ የባህል፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የዘር፣ የፆታ፣ የፖለቲካ፣ ወዘተ ልዩነቶች ቢኖሩን እንኳ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ናት፡፡ ይህች አገር የጋራ መኖሪያቸው ብቻ ሳትሆን መቀበሪያቸውም ናት፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከልዩነቶቻችን ይልቅ አንድነታችን እጅግ በጣም የጐላ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያዊነትን የጋራ መገለጫ ማድረግ አለብን፡፡

ኢትዮጵያዊነት የጋራ መገለጫ መሆን የሚችለው በአገራችን ጉዳይ ሁላችንም ሲያገባንና ለዚህም አስፈላጊውን አስተዋጽኦ ስናበረክት ነው፡፡ አገራችን የሁላችንም ናት ስንል አክብረናት ልናስከብራት ይገባናል፡፡ ሊያዋርዱዋት የሚፍጨረጨሩ ካሉ በጋራ ማውገዝ አለብን፡፡ በአገር ቀልድ የለም፡፡ በኢትዮጵያዊነት ቀልድ የለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት መከበር አለበት ሲባል ለግል ጥቅምና ለቡድን ጥቅም ብቻ ሲሉ የሚሯሯጡ ወገኖች አደብ ይግዙ ማለት ነው፡፡ ለአገራቸው ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ የሚያደርጉ፣ በክፉ ጊዜ ደራሽ የሆኑና ለአገራቸው እንደ አያት ቅድመ አያቶቻቸው ቀናዒ የሆኑ ወገኖች ያስፈልጉናል፡፡ የኢትዮጵያዊነትን እሴት ላቅ ያለ ደረጃ የሚያደርሱ ትጉኃን ያሹናል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ የሚያስከብሯት የታላላቅ ገድሎች ባለቤት ናት፡፡ ለዘመናት ሲያናጥሩባት ከኖሩት ድህነት፣ በሽታ፣ ኋላቀርነትና ተስፋ መቁረጥ በላይ የምትኮራባቸው ታሪኮች የተከናወኑባት አገር ናት፡፡ አንገታችንን ሲያስደፉን ከቆዩት መከራዎች በላይ፣ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌትነትዋ የላቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያችን እንደ መርግ ይከብዱ ከነበሩ ቀንበሮቿ በላይ፣ ታሪኮቿና ገድሎቿ አንፀባራቂ ናቸው፡፡ በዚህም ክብር የሚገባት ታላቅ አገር ናት፡፡

ሕዝባችን በውስጡ ያሉትን ልዩነቶች ጥበባዊ በሆነ መንገድ ይዟቸው በእርስ በርስ መስተጋብሩ ተምሳሌታዊ አንድነቱን ይዞ በመቆየቱ፣ ለዘመናት የዘለቀው ይኼው አስደሳች አብሮነት ዛሬም ቀጥሏል፡፡ በልዩነት ውስጥ አንድነትን አጉልቶ በማውጣት በደስታውም ሆነ በሐዘን አብሮ አለ፡፡ ለአገሩ ቀናዒ የሆነው ሕዝባችን በደስታውም ሆነ በመከራው ጊዜ አብሮ በሰላም ኖሯል፡፡ አሁንም ይህንን አስመስጋኝ ልምዱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ይህ የኢትዮጵያዊነት ክብር መገለጫ ነው፡፡

ኢትዮጵያችን ከኮሎኒያሊስቶች ጋር በመፋለም በአፍሪካ አኅጉር ፀረ ኮሎኒያሊስት ትግል ግንባር ቀደም ፋና ወጊ ስትሆን፣ አፍሪካውያን ወገኖቻችን ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር እንዲላቀቁ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች፡፡ ከዚያም አልፋ ተርፋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላም በማስከበር ለረጅም ዓመታት የዘለቀ አኩሪ ስም አላት፡፡ የአፍሪካውያን መሰባሰቢያ የሆነውን የአፍሪካ ኅብረት በመመሥረት ረገድ ከፊት ረድፍ ነበረች፡፡ አሁንም አለች፡፡ ኢትዮጵያ ከዜጐቿ በተጨማሪ አፍሪካውያን ወንድሞችና እህቶችን አስተምራለች፡፡ አስጠልላለች፡፡ በዚህም ከፍተኛ ክብር ተጐናጽፋለች፡፡ ኢትዮጵያዊነት ማለት ይህ ነው፡፡

ይህንን ታላቅ እሴት የማስከበር ኃላፊነት ወር ተራው የዚህ ትውልድ ነው፡፡ ይህ ትውልድ ያለበት ዘመን እጅግ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በርካታ ተስፋ የሚፈነጥቁ አጋጣሚዎችም አሉት፡፡ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያውያን በተለይ በፖለቲካው ከባቢ ውስጥ የሚገኙ እከሌ ከእከሌ ሳይሉ ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው፡፡ ከምንም ነገር በፊት የአገሪቱና የሕዝቧ ጥቅም መቅደም አለበት፡፡ ይህ ጥቅም መቅደም የሚችለው ደግሞ በመከባበርና በወዳጅነት መንፈስ ለዓመታት የተበላሸውን ግንኙነት ማደስ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ የመፈራረጅና የመጠላላት ፖለቲካ ለአገሪቱ ፋይዳ እንደሌለውና የሕዝባችንን ሥነ ልቦና እንደማይገልጸው እያየን ነው፡፡ ‹‹ከእኔ በላይ ለአሳር›› የሚለው የጀብደኝነት አካሄድ የኢትዮጵያ ሕዝብን ጥቅምና የአገሪቱን ህልውና አደጋ ውስጥ ስለሚከት፣ ሁሉም የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ከአሉታዊ ድርጊታቸው ይታቀቡ፡፡

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው ጽንፍ በያዙና የማይታረቅ ቅራኔ ባነገቡ ኃይሎች በሚደረግ ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር አይደለም፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ከግለሰባዊና ከቡድናዊ ጥቅምና ፍላጐት በላይ የአገርን ጉዳይ ማገናዘብ ከተሳናቸው፣ ይህንን ኩሩ ሕዝብ እንዴት ሊወክሉ ይችላሉ? የነገዋ ኢትዮጵያ ዛሬ በብሔራዊ ወሳኝ ጉዳዮች በሚግባቡ ልጆቿ መገንባት አለባት ሲባል እኮ፣ የኢትዮጵያዊነትን የጋራ መገለጫ ባህርይ አንፀባርቁ ማለት ነው፡፡ የዚህን ኩሩ ሕዝብ በመከባበርና በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተና ለዘመናት የኖረውን አንፀባራቂ አርዓያነት በመከተል፣ በአገር ጉዳይ ላይ የጋራ መግባባት መኖር አለበት ማለት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በሚያግባባው እየተግባቡ፣ ልዩነቶችን ደግሞ እያቻቻሉ የኢትዮጵያዊነትን ከፍታ መጨመር ያስፈልጋል፡፡

በፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች ትልቁ ግባቸው የሕዝባቸውና የአገራቸው እርካታ መሆን አለበት፡፡ ከሕዝብ ድምፅ በላይ ምንም ወሳኝ ነገር የለምና ኃላፊነታቸውም ሆነ ተጠሪነታቸው ለሕዝብና ለአገር ብቻ ይሁን፡፡ ከቡድን ፍላጐትና ጥቅም በላይ የሕዝብና የአገር ጥቅም ይቅደም፡፡ ለኢትዮጵያ ክብርና ዕድገት ሲባል የተለያዩ አመለካከቶችና አስተሳሰቦች በተገቢው መንገድ ይንፀባረቁ፡፡ ልዩነቶችም ለዘለዓለም ይኑሩ፡፡ ከፀብና አላስፈላጊ ከሆኑ ዕርምጃዎች ይልቅ ውይይቶችና ድርድሮች ትልቅ ቦታ ይሰጣቸው፡፡ የነገዋን የተከበረችና የታፈረች አገር እናስብ፡፡

አሁን እየተስተዋለ ያለው የፖለቲከኞችና የደጋፊዎቻቸው ጭፍንና ጽንፈኛ አቋም ኢትዮጵያዊነትን እየገዘገዘው ነው፡፡ ወዳጆቻችንን የሚያሳቅቅ ተግባር እየፈጸምን የጠላት መጫወቻ እንዳንሆን እንጠንቀቅ፡፡ ለዓለም ብሎም ለአገራችን ደመኛ ጠላት የሆኑት አሸባሪዎች ወገኖቻችንን በአሰቃቂና አረመኔያዊ መንገድ ከፈጁ በኋላ እየታዘብን ያለነው በፍፁም ኢትዮጵያዊነትን አይገልጽም፡፡ ይህ ሕዝባችንን የማይገልጽ ደባል የሆነ ባህሪ መታረም አለበት፡፡ በጽንፈኝነትና በጥላቻ የታጀቡ የቃላት ልውውጦች አደገኛና መርዛማ ወደሆነ አዘቅት እንዳይገፉን መጠንቀቅ ብልህነት ነው፡፡ ይህ ኩሩና ጀግና ሕዝብ በልጆቹ ሐዘን ምክንያት ቅስሙ በተሰበረበት ወቅት፣ ለፖለቲካ ትርፍ የሚሯሯጡ ወገኖች ራሳቸውን ያቅቡ፡፡ ሕዝባችን ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይበግረው ለዘመናት የዘለቀውን አንድነቱን ይዞ እየተጓዘ በመሆኑ ይህ መብቱ ይከበርለት፡፡ የኢትዮጵያዊነት የጋራ መገለጫ የሆነው አንድነቱና አብሮነቱ ለዘለዓለም አብሮት ይቀጥል ዘንድ ታሪካዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ክብር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ሰላም ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት አርቆ አሳቢነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የጋራ መገለጫችን ይሁን!   

         

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...

የ‹‹ክብር ዶክትሬት›› ዲግሪ ጉዳይ

በንጉሥ ወዳጅነው ‹‹የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ግልጽ የሆነ መመርያ እስኪወጣ ድረስ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...

ከግጭት አዙሪት ውስጥ የሚወጣው በሰጥቶ መቀበል መርህ ነው!

የኢትዮጵያን ሰላም፣ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ማዕከል በማድረግ መነጋገር ሲቻል ለጠብ የሚጋብዙ ምክንያቶች አይኖሩም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚደረጉ ክንውኖች በሙሉ ከጥፋት የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ዘርፈ...