– ከስምንት ሺሕ በላይ የሚሆኑት ሙሉ ክፍያ ፈጽመዋል
የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅፈር ይፋ ከተደረጉት አራት ፕሮግራሞች አንዱ በሆነው 40/60 ከተመዘገቡ 165 ሺሕ ተመዝጋቢዎች ውስጥ ሰባት ሺሕ ያህሉ ውላቸውን ሲያቋርጡ፣ 8,329 ተመዝጋቢዎች ደግሞ ሙሉ በሙሉ ክፍያ ፈጽመው ቤታቸውን ለመረከብ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ሙሉ ክፍያ ከፈጸሙት ተመዝጋቢዎች በተጨማሪ 20,973 የሚሆኑት 40 በመቶና ከ40 በመቶ በላይ መቆጠባቸው ታውቋል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ ለተጠቃሚዎች ይተላለፋሉ ተብለው የሚጠበቁት 1,992 የ40/60 ፕሮግራም ቤቶች ሙሉ በሙሉ ለከፍሉ ተጠቃሚዎች፣ በተለይም ምዝገባ በተጀመረበት ወቅት ሙሉ ክፍያ ለፈጸሙት ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክንዴ ብዙነህ ባለፈው ዓርብ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ዕጣ የሚወጣላቸው ተመዝጋቢዎች በከፈሉት መጠን ቅደም ተከተል ነው ካሉ በኋላ ለተጠቃሚዎች የሚተላለፉት ቤቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ይኖራል ብለዋል፡፡ ይደረጋል የተባለው ጭማሪ ግን እየተሰላ በመሆኑ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ በዕጣ ለተጠቃሚዎች በሚተለለፉት ቤቶች ሴቶችና የመንግሥት ሠራተኞች ልዩ ተጠቃሚ ይሆናሉ ወይስ አይሆኑም የሚለው እየታየ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በመጪው ሰኔ ወር ለተጠቃሚዎች ይተላለፋሉ ተብለው የሚጠበቁት ቤቶች በሠንጋ ተራና ቃሊቲ በሚገኘው በክራውን ሆቴል አካባቢ የተገነቡ ናቸው፡፡ ክራውን ሆቴል አካባቢ የተገነቡት 14 ብሎኮች በጠቅላላው 882 ቤቶች ሲኖሩዋቸው፣ በሠንጋ ተራ የተገነቡት አምስት ብሎኮች ደግሞ 340 ቤቶች አሉዋቸው፡፡ እነዚህ ግንባታዎች በአሁኑ ወቅት በመጠናቀቅ ላይ ሲሆኑ፣ የሚቀራቸው የማጠናቀቂያ (ፊኒሺንግ) እና የመሠረተ ልማት ግንባታ ብቻ ነው፡፡
የቤቶቹ ከፍታ ባለ ዘጠኝና ባለ 12 ፎቅ ነው፡፡ እነዚህ 1,992 ቤቶች እኩል ባለአንድ፣ ባለሁለትና ባለሦስት መኝታ ክፍሎችን ያካተቱ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የቅርንጫፍ አንድ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ታዬ ገልጸዋል፡፡ ኢንተርፕራይዙ በቅርቡ ለተጠቃሚዎች ከሚተላለፉት ከእነዚህ ቤቶች በተጨማሪ ቦሌ፣ አያትና በመሳሰሉ አካባቢዎች 14,300 ቤቶችን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡
አቶ ክንዴ እንደገለጹት በቤቶቹ ግንባታ 100 ኮንትራክተሮች፣ አሥር አማካሪ ድርጅቶች፣ 200 ጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ተሳታፊ ናቸው፡፡ ኢንተርፕራይዙ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግንባታ የማካሄድ አቅሙ እያደገ ቢመጣም፣ መንግሥት በፍጥነት የመኖሪያ ቤቶችን ችግር ለመፍታት የውጭ አገር ኩባንያዎችን ለማስገባት ፍላጎት ያሳዩ ኩባንያዎችን እያለየ ነው፡፡
‹‹በውጭ ኩባንያዎቹ ለሚካሄዱት ግንባታዎች ቦታ መረጣ ተጀምሯል፤›› ያሉት አቶ ክንዴ፣ የውጭ ኩባንያዎችን ለማስገባት መንግሥት እያካሄደ ያለው ሥራ ያለበትን ደረጃ ገልጸዋል፡፡
እየተካሄደ ያለው የ40/60 ቤቶች ፕሮጀክት ግንባታ እስካሁን 3.7 ቢሊዮን ብር የወጣበት ሲሆን፣ በሰኔ ወር የሚተላለፉት ቤቶች ከዚህ ውስጥ ምን ያህል ድርሻ እንዳላቸው አልተገለጸም፡፡ አቶ ክንዴ ለ1,992 ቤቶች የወጣው ወጪ እየተሰላ መሆኑን ገልጸው፣ ቤቶቹ ለተጠቃሚዎች ሲተላለፉ የሚኖረው ጭማሪ በሚገለጽበት ወቅት አብሮ ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡