Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናጣና ፎረም በወቅታዊ የሰላምና የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ሊመክር ነው

ጣና ፎረም በወቅታዊ የሰላምና የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ሊመክር ነው

ቀን:

– ለፖል ካጋሜ የክብር ዶክትሬት ሊሰጥ ነው

አምስተኛው ዙር ጣና ፎረም ከሚያዝያ 8 እስከ 9 ቀን 2008 ዓ.ም. አፍሪካ በዓለም አቀፍ ወቅታዊ የደኅንነት አጀንዳዎች ላይ ያላት ሚና ላይ ይመከራል፡፡ የጣና ከፍተኛ ደረጃ የአፍሪካ የደኅንነት ፎረም ሚያዝያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. በአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት መቀመጫ በባህር ዳር ከተማ በሚደረግ ሥነ ሥርዓት፣ ለሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ የክብር ዶክትሬት ሊሰጥ መሆኑ ታውቋል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ካጋሜ የሩዋንዳ ልማታዊ መንግሥትን ልምድ በተመለከተ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ጣና ከፍተኛ ደረጃ የአፍሪካ የደኅንነት ፎረም በየዓመቱ በባህር ዳር ከተማ የሚካሄድ ሲሆን፣ የአፍሪካ አኅጉር በሰላምና በደኅንነት ዙሪያ የሚገጥመውን ተግዳሮት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ መሪዎች ግምገማ እያቀረቡና እየተከራከሩበት የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲቀርፁ ለማስቻል ያለመ መድረክ ነው፡፡ የጣና ፎረም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት ጥናቶች ተቋምና በዕውቅ አፍሪካውያን አነሳሽነት ከአምስት ዓመት በፊት የተቋቋመ ነው፡፡

ከጣና ፎረም ዝግጅቶች ንቁ ተሳትፎና ክርክር በመጋበዝ የተሳካለት የመለስ ዜናዊ ዓመታዊ የተከታታይ ሌክቸር መድረክ፣ ዘንድሮ በፓትሪክ ሉሙምባ ትሩፋቶች ላይ ክርክር ይደረግበታል፡፡ ባለፈው ዓመት ታንዛኒያው ባለሀብት ዓሊ ሙፍሪኪ የቀድሞው የጋና ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህ የአፍሪካ ጀግና ሳይሆኑ መጥፎ የውድቀት ምሳሌ ናቸው በሚል ጭብጥ ያቀረቡት ጥናት፣ ተሳታፊዎችን ለሁለት የከፈለና በከፍተኛ ስሜት ክርክር የተካሄደበት ነበር፡፡

እንዳለፉት አራት ዙር ዝግጅቶች ሁሉ ዘንድሮ በጣና ፎረም ትልቅ ኃላፊነት የያዙና ዝና ያተረፉ መሪዎችና ባለሙያዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡ በዝግጅቱ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ማረጋገጫ ከሰጡት መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የአፍሪካ ኅበረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶ/ር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ፣ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንትና የጣና ፎረም ቦርድ ሊቀመንበር አሉሴጉን አባሳንጆ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪና የጣና ፎረም ቦርድ ምክትል ሊቀመንበር ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ የቀድሞው የተመድ ዋና ጸሐፊና የኖቬል አሸናፊ ኮፊ አናን፣ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ካርሎስ ሎፔዝ፣ የሙኒክ የደኅንነት ኮንፈረንስ ሊቀመንበር አምባሳደር ወልፍጋንግ ኢስችንገር፣ በአፍሪካ የልማት ጉዳይ ላይ ከተቀዳሚ ተመራማሪዎች የሚመደቡት የለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር ታንዲካ ምካንዳውሬና የኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ ፕሬዚዳንት ጂያንማር ጉዌኖ ይገኙበታል፡፡

‹‹የአፍሪካ ኅብረትና የአመራሩ ጉዞ ወደ 2063›› በሚል ርዕስ የጣና ፎረም ከፍተኛ ደረጃ ተሳታፊዎች የምክክር መድረክ እንደሚኖርም ተጠቁሟል፡፡ የጣና ፎረም በሁለት ቀናት ውሎው የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ በአገር መሪዎች፣ በምሁራንና በተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች ውይይት እንደሚያካሂድ ይጠበቃል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ኢትዮጵያ እያስተናገደች ባለችው የፀጥታና የደኅንነት ተግዳሮት ላይ ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...