Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ​​​​​​​ፌዴራል ፖሊስ በአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ላይ የጠየቀው ይግባኝ ውድቅ ተደረገ

​​​​​​​ፌዴራል ፖሊስ በአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ላይ የጠየቀው ይግባኝ ውድቅ ተደረገ

ቀን:

 

  • በሥር ፍርድ ቤት የተፈቀደው ዋስትና በከፍተኛውም ፀና
  • ለዋስትና 1.1 ሚሊዮን ብር አስይዘዋል

የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት መጋቢት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ለአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር መሥራችና የቦርድ አባል ለአቶ ኤርሚያስ አመልጋ የፈቀደውን የ500 ሺሕ ብር ዋስትና በመቃወም፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መመርመር ዳይሬክቶሬት ለከፍተኛው ፍርድ ቤት አቅርቦት የነበረው የይግባኝ አቤቱታ፣ ማክሰኞ ሚያዝያ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ውድቅ ተደረገ፡፡

አቶ ኤርሚያስ ከአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ቤት ለመግዛት ውል ከፈጸሙ ቤት ገዥዎችና የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በቦሌ ክፍለ ከተማ 22 ማዞሪያ አካባቢ በሚገኘው የሸማቾች መሰብሰቢያ አዳራሽ ተሰብስበው እያሉ፣ ጥር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው በእስር ላይ ቆይተዋል፡፡

ለሰባት ጊዜያት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እየተፈቀዱለት ከሁለት ወራት በላይ በምርመራ ላይ የከረመው የፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ቡድን፣ ለስምንተኛ ጊዜ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሲጠይቅ፣ ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ አድርጐ አቶ ኤርሚያስ በ500 ሺሕ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም፣ መርማሪ ቡድኑ ባቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ለ17 ቀናት ዋስትናው ታግዶ ከርሟል፡፡

ጊዜያዊ ዕግዱን የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት መርማሪ ቡድኑ ለምን ይግባኝ እንደጠየቀ እንዲያስረዳ ጠይቆት፣ አቶ ኤርሚያስ የተጠረጠሩበት ወንጀል ውስብስብ መሆኑንና ምርመራውን ሳያጠናቅቅ የሥር ፍርድ ቤት ዋስትና መስጠቱ ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ፣ ከአቤቱታው ጋር የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔን ማያያዙን አስረድቷል፡፡  

የተጠርጣሪው የአቶ ኤርሚያስ ጠበቆች በበኩላቸው፣ የሥር ፍርድ ቤት ከበቂ በላይ ጊዜ ሰጥቶትና የመጨረሻ ቀጠሮ መሆኑን በሰባተኛው ቀጠሮ ላይ ነግሮት እያለ፣ መርማሪ ቡድኑ ለስምንተኛ ጊዜ ተጨማሪ ቀናት እንዲፈቀድለት መጠየቁ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውም ውሳኔ አግባብነት መሆኑን በመጥቀስ እንዲፀናላቸው ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በተጠርጣሪ ላይ ፍርድ ቤቶች ዋስትና ሲፈቅዱ ፖሊስ ዋስትናን በመቃወም የይግባኝ አቤቱታ ሊያቀርብ የሚያስችለው፣ የወንጀል ሕግም ሆነ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አለመኖሩን በመግለጽ፣ ይግባኙ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀው ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም ወገኖች ክርክር ከተገቢው ሕግ ጋር በማገናዘብ በሰጠው ውሳኔ እንደገለጸው፣ መርማሪ ቡድኑ በሥር ፍርድ ቤት ለሰባት ጊዜያት አሥር፣ አሥር ቀናት ተፈቅዶለታል፡፡ ፖሊስ በተፈቀደለት ጊዜ ሥራውን በአግባቡ አለመሥራቱን ፍርድ ቤቱ ከምርመራው ሰነድ መገንዘብ መቻሉን አስረድቷል፡፡ ጠበቆች መርማሪ ቡድኑ ይግባኝ ማለት እንደማይችል በመግለጽ የተከራከሩበትን ሒደት እንዳልተቀበለውም ፍርድ ቤቱ አክሏል፡፡

ነገር ግን የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን የምርመራ ጊዜና የፈቀደውን የዋስትና መብት በተመለከተ የሚነቀፍ ሆኖ እንዳላገኘው በማስረዳት፣ ተጠርጣሪው በስር ፍርድ ቤት የተከበረላቸው የዋስትና መብት መጽናቱን አረጋግጧል፡፡ በመሆኑም አቶ ኤርሚያስ ከተጠረጠሩበት የማታለል ወንጀል በ500 ሺሕ ብር ዋስትና ይፈታሉ፡፡ አቶ ኤርሚያስ በባንክ የሚያዙበት በቂ ስንቅ (ገንዘብ) ሳይኖራቸው ለስድስት ግለሰቦች በድምሩ 4.9 ሚሊዮን ብር ደረቅ ቼክ በማውጣት (መጻፍ) ወንጀል ተጠርጥረው ከተመሠረተባቸው ክስ በ600 ሺሕ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ ውሳኔ መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በአጠቃላይ በ1.1 ሚሊዮን ብር ዋስትና እንዲለቀቁ ተወስኗል፡፡

ሚያዝያ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. የአራዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው ውሳኔ የአቶ ኤርሚያስ ቤተሰቦች በለቅሶና በሳቅ ደስታቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል፡፡ የሕግ አማካሪና ጠበቃቸው አቶ ሞላ ዘገዬ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ መደሰታቸውንና ትክክለኛ ፍትሕ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ አቶ ኤርሚያስ የሥር ፍርድ ቤት የፈቀደላቸውን የ500 ሺሕ ብር ዋስትና አስይዘው በዕለቱ ለመለቀቅ ያደረጉት ጥረት፣ የቢሮ ሠራተኞች የተለያየ ምክንያት በመስጠት የመፈቻ ትዕዛዝ ሊጽፉላቸው ባለመቻላቸው በፌዴራል ፖሊስ እስር ቤት ለማደር መገደዳቸው ታውቋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...