Friday, February 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጨሞጋ ይዳ የኃይል ማመንጫ ለኢንቨስተሮች በጨረታ ሊሰጥ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በግብፅ መንግሥት ተፅዕኖ የተጓተተውና 27.8 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ የተገመተው ጨሞጋ ይዳ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት፣ ኃይል አመንጭተው ለመንግሥት መሸጥ ለሚፈልጉ የግል አልሚዎች በጨረታ ሊሸጥ ነው፡፡

ጨሞጋ ይዳ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአማራ ክልል የሚገኝ ሲሆን፣ የውኃ ምንጩም የዓባይ ወንዝ ገባር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህንን የኃይል ፕሮጀክት ዕውን ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት ባወጣው ጨረታ አማካይነት፣ ሲኖ ኃይድሮ የተባለው የቻይና ኩባንያ በቬንደር ፋይናንሲንግ (ራሱ ለፕሮጀክቱ በሚያቀርበው የብድር ገንዘብ) ለመገንባት እ.ኤ.አ. በ2009 ውል ተፈራርሞ ነበር፡፡

ፕሮጀክቱን ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ የሚያስችለውን 555 ሚሊዮን ዶላር ከቻይና ኢምፖርትና ኤክስፖርት (ኤግዚም) ባንክ የረዥም ጊዜ ብድር ለኢትዮጵያ መንግሥት አቅርቦ የነበረ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ የግብፅ መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች በቻይና መንግሥት ላይ በፈጠሩት ጫና ለፕሮጀክቱ የተገኘው ብድር እክል ሊገጥመው ችሏል፡፡

ማክሰኞ ሚያዚያ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. የስምንት ወራት የሥራ አፈጻጸማቸውን ለፓርላማ ያቀረቡት የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አመራሮችም የፕሮጀክቱ መዘግየትን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ፣ ይህንኑ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡

ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ ወንድሙ ተክሌ በሰጡት ምላሽ፣ ፕሮጀክቱን ለመገንባት ኮንትራት ፈርሞ የነበረው ሲኖ ኃይድሮ የተባለ ኩባንያ ወደ ሥራ ለመግባት እንቅስቃሴ ላይ እያለ፣ ለመንግሥት ያቀረበው ጥያቄ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚገዳደር በመሆኑ ፕሮጀክቱ እንዲቋረጥ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ሲኖ ኃይድሮ የተባለው ኩባንያ ይህንን ፕሮጀክት ከመጀመሩ በፊት የግብፅ ይሁንታን የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲጠይቅና እንዲያሳውቀው በመጠየቁ ሊቋረጥ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን ‹በኢንዲፔንደንት ፓወር ፐርቼዝ› ሥርዓት፣ ማለትም የግል ኩባንያዎች ኃይል አመንጭተው የኤሌክትሪክ ኃይሉን ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጡበት ሥርዓት አማካይነት ለመገንባት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ የሰጡት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት የተወሰነ ጨረታ ለማውጣት የኩባንያዎች ቅድመ ምዘና ሥራ ላይ ነን፤›› ብለዋል፡፡

ጨረታውን ለማለፍም ሆነ የመነጨውን ኃይል ለመንግሥት በሚያቀርብበት ታሪፍ ላይ ከፍተኛ ድርድር እንደሚካሄድ ጠቁመዋል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ የተካተቱ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች 50 በመቶ የሚሆኑት በተመሳሳይ ለግል አልሚዎች የሚሰጡ መሆናቸውን ያስታወሱት ኢንጂነር አዜብ፣ ጨሞጋ ይዳ ፕሮጀክት የመጀመሪያው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች