በአገራችን ውስጥ በጣም ከማይመቹ ልማዶች መካከል አንዱ ለግልጽነት የሚሰጠው ዝቅተኛ ደረጃ ነው፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ኅብረተሰብ ብሎም መንግሥት ድረስ በስፋት የግልጽነት ችግር ይታያል፡፡ የግል ገመናን ከመደባበቅ ጀምሮ እስከ ብሔራዊ ጉዳዮቻችን ድረስ ለግልጽነት የተሰጠው ዋጋ በጣም የወረደ በመሆኑ፣ ሕዝብም አገርም እየተጎዱ ነው፡፡ በቤተሰብ ደረጃ በአብዛኛው ልጆችና ወላጆች ያላቸው ግንኙነት በግልጽነት ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ኅብረተሰቡ ውስጥ ሲገባ ግልጽነት እንደ ቅንጦት ይወሰዳል፡፡ መንግሥት ዘንድ ሲደረስ የብዙዎቹ ተቋማት ሠራተኞችና አመራሮቻቸው ግልጽነትን ይሸሻሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ገመና ከታችነትና መደባበቅ ውስጥ ግን ለአገር የማይጠቅሙ በርካታ ጉዳቶች ይከሰታሉ፡፡ ጉዳቶቹ በስፋት ይታያሉ፡፡ አንዳንድ ዋና ዋና ጉዳዮችን እያነሳን እንነጋገርባቸው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአበረታች ንጥረ ነገር ምክንያት አገራችን ፈተና ገጥሟታል፡፡ ይህ ፈተና በግል ለአትሌቶች የበለጠ አሥጊ ቢሆንም፣ እንደ አገር ግን ሁላችንንም ይመለከታል፡፡ የወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የተለያዩ የስፖርት ፌዴሬሽኖች፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ክለቦች፣ የስፖርት ማኅበራት፣ ስፖርተኞች፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ በአጠቃላይ ሕዝቡ፣ ወዘተ በግልጽነት በአንድ ላይ መቆም ካልቻሉ ፈተናው ከባድ ነው፡፡ አንድ ስፖርተኛ ከበስተጀርባው ቤተሰቦቹ፣ ጓደኞቹ፣ አሠልጣኞቹ፣ ማናጀሮች ወይም ሌሎች አካላት አሉ፡፡ ውጤት ለማግኘትና ዝና ለመጎናፀፍ፣ እንዲሁም በሀብት ለመንበሽበሽ ሲባል አላስፈላጊ ድርጊት ውስጥ ይገባል፡፡ በዚህም ሒደት ስፖርተኛውን የሚገፋፉት ብዙ ናቸው፡፡ በእነዚህ ሁሉ አካላት መካከል በግልጽነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ከሌለ ግን ለአገር ከፍተኛ አደጋ ነው፡፡ አንድ ሯጭ ወይም የእግር ኳስ ተጫዋች በወሰደው አበረታች ንጥረ ነገር ምክንያት ራሱን ችሎ ቢቀጣም፣ ሁኔታው እየተደጋገመ ሲሄድ አገርን ከበርካታ ውድድሮች የሚያሳግድ ችግር ይፈጠራል፡፡ አሁንም ምልክቱ እየታየ ነው፡፡ ነገር ግን የሚመለከታቸው አካላት ከዓመታት በፊት በግልጽነት በዚህ አሳዛኝ ድርጊት ላይ ቢሠሩ ኖሮ ይህ አንገት የሚያስደፋ ተግባር፣ ይህችን በአረንጓዴ ጎርፍ ልጆቿ የምትታወቅና በተፈጥሮ ላይ ብቻ የምታተኩር አገርን አንገት አያስደፋም ነበር፡፡ በግልጽነት መጓደል ምክንያት ግን ግንዛቤ ማስጨበጥ እንኳን አልተቻለም፡፡ ከሌሎች ውድቀት መማር አልተፈለገም፡፡
የአገሪቱ ሕገ መንግሥት የመንግሥት አሠራር በግልጽነትና በኃላፊነት መከናወን እንዳለበት በማያወላዳ መንገድ አስቀምጧል፡፡ ነገር ግን የግልጽነት ባህል የተለመደ ባለመሆኑ ብዙዎቹ አሠራሮች ይሸፋፈናሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ የተለያዩ ሕጎች ሲረቀቁ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች መደረጋቸው በስፋት ሲነገር ይሰማል፡፡ ነገር ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች በረቂቆቹ ላይ ውይይት ሲጠራ ይመለከታቸዋል የተባሉ አካላት ለተረቀቀው ሕግ እንግዳ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ብዙዎቹ ሕጎች ጥራት የሌላቸውና ለአሠራር የማይመቹ በመሆናቸው ብዙ ጊዜ ማሻሻያ ሲደረግባቸው ይታያል፡፡ በአንድ ወቅት ፍትሕ ሚኒስቴር ለፓርላማ ሪፖርት ሲያቀርብ የተወቀሰበት አንዱ ጉዳይ ይኼው የጥራት መጓደል ነው፡፡ በግልጽነት መርህ ላይ ተመሥርቶ ለመሥራት ፍላጎት ስለሌለ አገሪቱ በሚፐወዙና በሚከለሱ ሕጎች ምክንያት ትቸገራለች፡፡ ሕዝብ ደግሞ ለከፍተኛ ብስጭት ይዳረጋል፡፡ በተደጋጋሚ ከሚታዩ ችግሮች መካከል አንዱ የሆነው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በዋስትና የሚወጡ ሰዎችን አግቶ ማቆየት ነው፡፡ ሰባራና ሰንካላ ምክንያቶች እየተፈጠሩ ዜጎች የሚጉላሉት በግልጽነት መጥፋት ነው፡፡ ግልጽነት ባህል ባልሆነበት አገር ውስጥ የሚገኘው ውጤት ኪሳራ ብቻ ነው፡፡
ሰሞኑን በኢትዮ ቴሌኮም አማካይነት የቴሌኮም መገልገያ መሣሪያዎችን ለመመዝገብ፣ እንዲሁም በቫይበርና መሰል የጥሪ አገልግሎቶች ላይ ክፍያ ለመጣል በመንግሥት በኩል ዝግጅት እንዳለ ተሰምቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በኢንተርኔት አማካይነት የድምፅና የምሥል ጥሪዎችና መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ አፕሊኬሽኖች፣ ኢትዮ ቴሌኮም ከውጭ ጥሪዎች ማግኘት የሚችለውን ከፍተኛ ገቢ በማስቀረታቸው ነው ተብሏል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያዊያን ተጠቃሚዎች ዘንድ በስፋት የሚታወቁትን ‘ቫይበርና ዋትስአፕ’ የመሳሰሉትን ለመቆጣጠር፣ በአገልግሎቶቹ ላይም ክፍያ ለመጣል የኢትዮ ቴሌኮም ቦርድ፣ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የተለያዩ የመንግሥት አካላትን ውሳኔ እንደሚጠበቅም ተነግሯል፡፡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች የሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ፍላጎት ያማከለ ውሳኔ ላይ እንዲደረስ፣ ውይይቱም ሆነ ምክክሩ ለሕዝብ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ግልጽነት የጎደላቸው ውሳኔዎች ሕዝብን ያስኮርፋሉና፡፡
እዚህ ላይ መንግሥት የሕዝብ ኃላፊነትና ተጠሪነት እስካለበት ድረስ የሕዝብን ፍላጎት ማዳመጥ አለበት፡፡ ገና ከድህነት ማጥ ውስጥ ለመውጣት የሚታገልና በአገሪቱ በተጀመረው ልማት ውስጥ ሁነኛ ተሳታፊ የሆነን ሕዝብ ለመጫን ከማሰብ ይልቅ፣ ሌሎች አማራጮችን ማየት ይጠቅማል፡፡ ከተቻለ እንደተባለው ከአፕሊኬሽኖቹ ባለቤቶች ጋር በመደራደር ጥቅም ለማግኘት መሞከር፣ ወይም በሚገባ ጥናት ሠርቶ ሌሎች አማራጮችን ማየት የግድ ይላል፡፡ ይልቁንም በግልጽ የሕዝቡን ስሜት አውቆ የአገልጋይነት ኃላፊነትን መወጣት የተሻለ ይሆናል፡፡ በዓመት በርካታ ቢሊዮን ብሮችን በትርፍ የሚያገኘውና ዘርፉን በሞኖፖል የተቆጣጠረው ኢትዮ ቴሌኮም የአገልግሎት ተደራሽነቱን እያሰፋ ደንበኞቹን ያርካ፡፡ ከደንበኞቹ ጋርም በግልጽ ውይይት እያደረገ እርካታ ይፍጠር፡፡ ግልጽነትን ባህሉ ያድርግ፡፡
የግልጽነት ጉዳይ ሲነሳ በርካታ መንግሥታዊ ተቋማት በራፋቸው ላይ ‘የሥነ ምግባር መርሆ’ የሚባሉ ሰሌዳዎችን ሰቅለዋል፡፡ እነዚህን ሰሌዳዎች አንብቦ የሚያረካ አገልግሎት አገኛለሁ ብሎ ወደ ውስጥ የሚዘልቅ ተስተናጋጅ ግን የሚጠብቀው ሌላ ነው፡፡ ብዙኃኑ ታማኝና ቅን ሠራተኞች በመልካም ሥነ ምግባርና በኃላፊነት ስሜት ተገልጋዮችን ሲያስተናግዱ፣ ወሳኝ የተባሉ ኃላፊነቶችን የያዙ ጥቂት ሠራተኞችና አመራሮች በአካባቢው ካሰማሩዋቸው ደላሎች ጋር በመሆን ተገልጋዮችን የሙስና ሰለባ ያደርጋሉ፡፡ የያዙትን ኃላፊነት ያላግባብ በመጠቀም ግብር ከፋዩ ሕዝብ ያለምንም ክፍያና መንገላታት ማግኘት ያለበትን አገልግሎት የግል ጥቅም ማግበስበሻ ያደርጉታል፡፡ ጠያቂና ገላማጭ ስለሌለባቸው ኃላፊነታቸውን በትጋት የሚወጡትን ጭምር ያሸማቅቃሉ፡፡ ተቋማቱን እንደ ግል ንብረት ስለሚቆጥሩ ብልሹ አሠራሮችን ያስፋፋሉ፡፡ እያንዳንዱ ሰው ኃላፊነቱን እንዴት እንደሚወጣ መመርያ ቢቀመጥም፣ ለግልጽነት የተሰጠው ዋጋ ዝቅተኛ በመሆኑ ተቋማቱ የምሬት ጎተራ ይሆናሉ፡፡ ብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ከላይ እስከ ታች ያለው የሥራ አፈጻጸም በግልጽ ስለማይገመገምና በአጥፊዎቹም ላይ ፍትሐዊ የሆነ ዕርምጃ ስለማይወሰድ ምን ቸገረኝነት በስፋት ይታያል፡፡ ግልጽነት ቢኖር ግን ተቋማትና ሠራተኞች በአደባባይ እየተመሰገኑ አርዓያነታቸው ለሌሎችም በምሳሌነት እንዲቀርብ ይደረግ ነበር፡፡ ግን የትም ቦታ ቢሆን በአርዓያነት እየተወደሱ የሚጨበጨብላቸው ለማየት አልተቻለም፡፡ ግልጽነት የናፈቃቸው በጣም ብዙ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ የግልጽነት መጥፋት የሚጎዳው አገርና ሕዝብን ነው፡፡ በተለይ መንግሥት የግልጽነት ችግር በስፋት ሲታይበት የሚጠየቀው በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሥራውን እንዲያከናውን ነው፡፡ ለብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት ከሚፈጥሩ ጉዳዮች በስተቀር፣ ሕዝቡ የሚያስፈልጉትን ማናቸውንም የመንግሥት ሰነዶች የማግኘት መብት አለው፡፡ መንግሥት ተቋማቱም ሆኑ ሠራተኞቹ አሠራራቸው ለሕዝብ ግልጽ እንዲሆን ማድረግ አለበት፡፡ መደባበቅና ማድበስበስ የተለመደ በመሆኑ ብቻ አገር መጎዳት የለባትም፡፡ ‹‹ግልጽነት ባህላችን አይደለም›› እየተባለ አገሪቱ ዝግ መሆን የለባትም፡፡ መልካም አስተዳደር የጠፋው በግልጽነት መጥፋት ነው፡፡ ፍትሕ የሚዛነፈው ግልጽነት ባለመኖሩ ነው፡፡ ሙሰኞች የሚፈነጩት ግልጽነት በመጥፋቱ ነው፡፡ መብት የማይከበረው ግልጽነት ቦታ ስላልተሰጠው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከሥልጣኔ ይልቅ ኋላቀርነት፣ ከሰላምና መረጋጋት ይልቅ ፍጥጫ፣ ከመስማማት ይልቅ ጠብ፣ በጋራ ጉዳዮች ላይ ከመቀራረብ ይልቅ መራራቅ፣ ወዘተ. በስፋት ይታያሉ፡፡ ግልጽነት ለአገር ብልጽግና፣ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለዘለቄታዊ አብሮነት የሚጠቅም ስለሆነ በእጅጉ ይታሰብበት፡፡ ግልጽነት የአገር ባህል ይሁን!