Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናመንግሥትን 18.3 ሚሊዮን ብር በማሳጣት የተጠረጠሩ የመሬት ባለሙያዎች ተከሰሱ

መንግሥትን 18.3 ሚሊዮን ብር በማሳጣት የተጠረጠሩ የመሬት ባለሙያዎች ተከሰሱ

ቀን:

– በክሱ ውስጥ የ80 ዓመት ባልቴት ተካተዋል

በልደታ፣ በቦሌና በቂርቆስ ክፍላተ ከተሞች የመሬት ልማት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ውስጥ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነት ላይ ይሠሩ የነበሩ በድምሩ 28 ተጠርጣሪዎች፣ መንግሥት ከ18.3 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲያጣ አድርገዋል ተብለው በተለያዩ መዝገቦች የሙስና ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

መንግሥት በተለይ ከመሬት ጋር በተያያዘ ተፈጥሯል ያለውን የመልካም አስተዳደር ዕጦት ችግር ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ከገለጸ በኋላ፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከ100 በላይ የሚሆኑ በመሬት ዘርፍ የሥራ መስክ የተሰማሩ በወጣትነትና በመካከለኛ ዕድሜ ላይ ያሉ ኦፊሰሮችን ‹‹በሙስና ጠርጥሬያቸዋለሁ›› በማለት እያሰረና እየከሰሰ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

- Advertisement -

ኮሚሽኑ በተለይም በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ አራዳ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ፣ ቦሌ፣ ልደታና የካ ክፍላተ ከተሞች የመሬት ዘርፍ በተለያዩ ሙያዎች ተሰማርተው ሲሠሩ በተለይ ለሰነድ አልባ ቦታ ያለምንም ማስረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በመስጠት፣ በመንግሥት የተወረሰን ቦታ የግል ይዞታ እንደሆነ በማስመሰል ካርታ ሠርቶና አቀላቅሎ በመስጠት፣ ከጂአይኤስ ዕይታ ውጪ የሆነን የመንግሥት ቦታ እንደሚታይና የቤቱ አካል እንደሆነ አድርጎ ሕገወጥ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በመስጠትና ሌሎችን ተገቢ ያልሆኑ ሕገወጥ ተግባራት በመፈጸም በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን፣ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በተለያዩ የክስ መዝገቦች ዘርዝሮ ያቀረባቸው ክሶች ያስረዳሉ፡፡

በልደታ ክፍለ ከተማ የ80 ዓመት ባልቴት ለሆኑት ወ/ሮ አስቴር ተሰማና አቶ ኤርሚያስ አበበ ሕገወጥ ጥቅም ለማስገኘት በማሰብ የሕግ ጉዳዮች አጣሪ ባለሙያና የወረዳ ፕሮሰሰር ካውንስል አስተባባሪ የሆኑት አቶ ሰንበት ገለቶ፣ የቴክኒክ ጉዳዮች አጣሪ ባለሙያ አቶ መሳይ ግርማና ሌሎችም ተመሳሳይ የሥራ ድርሻ ያላቸው አምስት የመሬት ሙያተኞች መንግሥትን ከ13.4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያሳጣ ቦታ ሕጋዊ ሰነድ አዘጋጅተው መስጠታቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ይገልጻል፡፡ ወ/ሮ አስቴር ተሰማ ግን ከ1961 ዓ.ም. ጀምሮ ይዘውት የቆዩት ይዞታቸው መሆኑን በመግለጽ እየተከራከሩ ነው፡፡

በዚያው በልደታ ክፍለ ከተማ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ልደታ ምድብ ፍርድ ቤት ዋና መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት የሚገኘው ባለስድስት ፎቅ ኑር ሕንፃ ካርታው ‹‹ለመኖሪያ›› የሚል ቢሆንም፣ ባለሙያዎቹ ‹‹የንግድ›› ብለው በመቀየር መንግሥት ከትራንዛክሽንና ከቦታ ግብር አገልግሎት በዓመት ሊያገኝ ይችል የነበረውን 23,408 ብር ማሳጣታቸውን ክሱ ያብራራል፡፡ በተለይ የቴክኒክ ጉዳዮች አጣሪ ባለሙያ የነበሩት ትዕግሥት አስፋው ካርታውን ማስተካከላቸውን ክሱ ይጠቁማል፡፡ የኑር ሕንፃ ባለቤት አቶ ኑረዲን አህመድም በክሱ ተካተዋል፡፡

የሰነድ አልባ ይዞታዎች መስተንግዶ ፕሮጀክት ዴስክ ተወካይ ኃላፊ ወይንሸት ሙላቱ፣ የሽንሻኖ ማስተካከል ጥናት ቡድን አስተባባሪ አበባው ደሳለኝ፣ የፕላን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ታደሰ ብርሃኔና የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢሳያስ ዘነበን ጨምሮ አሥር የመሬት ባለሙያዎች፣ በዚያው በልደታ ክፍለ ከተማ መንግሥት ለመልሶ ማልማት ካሳ የከፈለበትን ራሱን ችሎ የሚለማንና ለመንገድ ልማት የተቆረጠንና የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ንብረት የሆነን 198 ካሬ ሜትር ቦታ የግል ይዞታ ላለው ግለሰብ አቀላቅለው በመስጠት፣ መንግሥት 1,156,447 ብር እንዲያጣ ማድረጋቸውን በክሱ አካቷል፡፡ በተመሳሳይ በዚያው በልደታ ክፍለ ከተማ ራሱን ችሎ መልማት የሚችልን 179 ካሬ ሜትር የመንግሥት ቦታ ከግል ይዞታ ጋር አካተው በመስጠት መንግሥትን 769,621 ብር በማሳጣታቸው በቅየሳ ሙያ ላይ የተሰማሩት ከተማ ጅቦ፣ ሳሙኤል ሺበሺ፣ ዘሪሁን ደጄኔና ሌሎች አራት ሙያተኞችን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ከሷቸዋል፡፡ ቦታው ተካቶ ተሰጥቷቸዋል የተባሉት አቶ አወል አብደላ የተባሉ ግለሰብም በክሱ ተካተዋል፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት አስተዳደር የይዞታ አገልግሎት ኦፊሰር አቶ ፍቅረሰላም ወርቁ፣ የይዞታ ዴስክ ኃላፊው ሚካኤል ደረጀና የሕግ ጉዳዮች አጣሪ ባለሙያው አቶ ዳኛቸው ገረመው በሕገወጥ መንገድ በ175 ካሬ ሜትር የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ሠርተው በመስጠት፣ መንግሥት ከሊዝ ጨረታ ማግኘት የሚገባውን 3,844,915 ብር እንዲያጣ ማድረጋቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር የቅሬታ አፈታት የቴክኒክ ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳንኤል ደበበ በብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማኅበር ላይ ጉዳት ለማድረስና ሕገወጥ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ፣ ወ/ሮ መለይ ወልደ ሚካኤል ለተባሉ ግለሰብ ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ሳይኖራቸው እንዳላቸው በማስመሰልና በፊርማቸው በማረጋገጥ ሰጥተው ከባንኩ 3,600,000 ብር እንዲበደሩ በማድረጋቸው የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡

ሁሉንም ተጠርጣሪዎች በዋና ወንጀል አድራጊነት፣ በሕገወጥ ጥቅም ተካፋይነትና ሥልጣንን ያላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ 15 ዓመታት ሊቀጡ እንደሚችሉና ዋስትና እንደማይፈቀድ በመግለጽ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በመከራከሩ፣ ፍርድ ቤቱም የዓቃቤ ሕግን ክርክር በመቀበል የተጠርጣሪዎቹን ዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከራከሩ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛና 18ኛ ወንጀል ችሎቶች ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...