Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኦሮሚያ ክልል ወጣት ባለሀብቶችን ለማፍራት የ2.4 ቢሊዮን ብር አዲስ ፕሮጀክት ይፋ አደረግኩ...

የኦሮሚያ ክልል ወጣት ባለሀብቶችን ለማፍራት የ2.4 ቢሊዮን ብር አዲስ ፕሮጀክት ይፋ አደረግኩ አለ

ቀን:

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በ2.4 ቢሊዮን ብር በጀት ወጣት ባለሀብቶችን ለማፍራት አዲስ ፕሮጀክት ማፅደቁን አስታወቀ፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙክታር ከድር ሚያዝያ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ ፕሮጀክቱን ይፋ አድርገዋል፡፡

መክረሚያውን ተከስቶ ከነበረው መጠነ ሰፊ ግጭት በኋላ፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ከሕዝቡ ጋር የሰላም ኮንፈረንሶች ማካሄዱ ይታወሳል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮና የካቢኔ አባል አቶ ፈቃዱ ተሰማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከተካሄዱት ሰፋፊ ውይይቶች መንግሥት ከተረዳቸው ነጥቦች መካከል ለግጭቱ መንስዔ አንዱና ዋነኛው የሥራ አጥነት ችግር ነው፡፡

የክልሉ ገዥ ፓርቲ ኦሕዴድ ለግጭት መንስዔ የሆኑ ችግሮች በሚፈቱበት መንገድ ላይ መሰንበቻውን ሲመክር ቆይቶ፣ በአገሪቱ ባልተለመደ ሁኔታ ወጣቶችን ባለሀብት የሚያደርግ አዲስ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ለኦሮሚያ ወጣቶች ሥራ ከመፍጠር ባሻገር፣ በቀጥታ ወደ ሀብት የሚጓጓዙበት መንገድ የቀየሰ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ አቶ ፈቃዱ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ ከሌሎች ሥራዎች ሁሉ ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲካሄድ በመወሰኑ ሌሎች ፕሮጀክቶች ታጥፈው ለመጀመሪያው ዙር 300 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዟል፡፡

‹‹ከታጠፉ ፕሮጀክቶች ውስጥ የመንገድ ግንባታ፣ የጤና፣ የትምህርትና የውኃ ፕሮጀክትን አይጨምርም፤›› ያሉት አቶ ፈቃዱ፣ ሌሎች ፕሮጀክቶች ታጥፈው ይህ አዲስ ፕሮጀክት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ከሁለት ሳምንት በኋላ በይፋ ወደ ሥራ ይገባል፤›› በማለትም የፕሮጀክቱን አጣዳፊነት ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን ግጭቱን ካበረደ በኋላ በስፋት ከሕዝብ ጋር ምክክር መደረጉን፣ በክልሉ የሥራ አጥነት ችግር፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና የመሳሰሉት ችግሮች በስፋት መነሳታቸውን አቶ ፈቃዱ አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሠረት የክልሉ መንግሥት ካቢኔ ከመከረ በኋላ በክልሉ የሚገኙ 8.3 ሚሊዮን ሥራ አጦች ሥራ እንዲያገኙ ብቻ ሳይሆን፣ ሀብት ሊይዙ የሚችሉበትን ዕቅድ ማፅደቁም ተገልጿል፡፡

ይህ ዕቅድ በኦሮሚያ ከተሞችና የገጠር አካባቢዎች የሚተገበር ነው ተብሏል፡፡ ወጣቶቹ የታሸገ ውኃና የምግብ ማቀነባበሪያ የመሳሰሉ ማምረቻዎች ባለቤት የሚሆኑበትና በማዕድን ማውጣት የሚሰማሩበት ዕቅድ መዘጋጀቱን አቶ ፈቃዱ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ወጣቶቹ ከመንግሥት ጋር በጋራ ማምረቻዎችን ያቋቁማሉ፡፡ በሒደት መንግሥት ባለድርሻነቱን በመልቀቅ ወጣቶቹ የማምረቻዎቹ ባለቤት የሚሆኑበት አሠራር ተዘርግቷል፤›› በማለት አቶ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች ክልሎች ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው አሠራር፣ ሥራ አጥ ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ተደራጅተው በአነስተኛ ሥራዎች እንዲሰማሩ ማድረግ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

አቶ ፈቃዱ እንደገለጹት፣ የክልሉ መንግሥት መለስ ብሎ የጥቃቅንና አነስተኛ ድርጀቶችን ሁኔታ በሚገመግምበት ወቅት በርካታ ችግሮች መኖራቸው ተረጋግጧል፡፡ ‹‹የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም ያበደረው ሳይመለስ ብድር አይሰጥም ነበር፡፡ ይህ አሠራር እንዲቀር ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከታክስ ለመሸሽ አንዳንድ ነጋዴዎች በጥቃቅን ዘርፍ ተከልለው የሚገኙም አሉ፤›› በማለትም የክልሉ መንግሥት በቀጣይነት በዘርፉ ስለሚወስደው ዕርምጃም ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል 14 ሺሕ ትምህርት ቤቶች፣ ዘጠኝ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በርካታ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችና የግል ኮሌጆች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ተቋማት በየዓመቱ ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ግን በቂ ሥራ እንዳልተፈጠረላቸው የክልሉ መንግሥት ባለሥልጣናት መግባባት ላይ መደረሱ ተጠቁሟል፡፡ በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የወጣቶችን ጥያቄ መመለስ ተገቢ በመሆኑ፣ ይህ አዲስ ዕቅድ ተግባራዊ መደረጉ ተገልጿል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ ተከስቶ የነበረውን ግጭት በዘላቂነት ለመቅረፍ፣ መንስዔ ነበሩ በተባሉ ችግሮች ላይ ተከታታይ ዕርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ እየገለጸ ነው፡፡

ከእነዚህ ውስጥም የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን መሰረዝ፣ የከተሞች አዋጅን ሦስት አንቀጾች መሰረዝና ለተጎጂዎች ካሳ ለመክፈል ያለውን ዝግጁነት መግለጹ ተጠቃሾች መሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...