በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በዘንድሮ ድርቅ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የተጎዱ ሲሆን፣ በሴፍቲኔት ፕሮግራም ደግሞ ከ1.6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ይረዳሉ፡፡ ድርቁ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው የክልሉ ዞኖች መካከል አንዱ የሆነው የሽንሌ ዞን ይጠቀሳል፡፡ በዚህ ዞን የተከሰተው ድርቅ በጣም የበረታ መሆኑን በቅርቡ በአካባቢው ከተደረገው የመስክ ጉብኝት ለመረዳት ተችሏል፡፡ በዚህ ጉብኝት የአውሮፓ ኅብረት አራት ኮሚሽነሮችና በቅርቡ የተሾሙት የሴቭ ዘ ችልድረን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የችግሩን ጥልቀት መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ለተከሰተው ችግር በአስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ይህንን በአካባቢው ነዋሪዎች ‹‹ሙልያ›› ወይም ሁሉንም ጠራርጎ የሚወስድ የሚባል ስያሜ የተሰጠውን ፅኑ ድርቅ በተመለከተ ነአምን አሸናፊ ያጠናቀረው ዘገባ ቀርቧል፡፡