Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምየፓናማው ሚስጥራዊ ሰነድ የተፅዕኖ አድማስ እየሰፋ ነው

የፓናማው ሚስጥራዊ ሰነድ የተፅዕኖ አድማስ እየሰፋ ነው

ቀን:

ከቀናት በፊት 11.5 ሚሊዮን ሚስጢራዊ ሰነዶችን ይፋ ያደረገው የፓናማው ሰነድ አሁንም አነጋጋሪ መሆኑ ቀጥሏል፡፡ ሰነዱ በፓናማ የሚንቀሳቀሰውና በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች፣ ሀብትና ንብረታቸውን እንደፈለጉ መደበቅ የሚያስችል የሕግ አገልግሎት ከሚሰጠው ሞሳክ ፎንሴካ የተገኙ መረጃዎችን የያዘ ነው፡፡

ሰነዱ የባለድርሻዎችንና የቦርድ ዳይሬክተሮችን ማንነት የያዘ ነው፡፡ የዓለም ባለፀጐችና ባለሥልጣናት ገንዘብና ንብረታቸውን እንዴት ከሕዝብ ሸሽገው ከግብር አርቀው እንደሚያስቀምጡ ሁሉ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ መረጃዎች ከግዙፉ የፓናማ ሰነድ ቀስ በቀስ ተቀንጭበው እየተለቀቁ ሲሆን፣ ለጊዜው ይፋ እንደሆነው የአርጀንቲና፣ የአይስላንድ፣ የሳዑዲ ዓረቢያ፣ የዩክሬንና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የቀድሞ መሪዎች፣ ከአርባ የሚበልጡ አገሮች የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የባለሥልጣናቱ የቅርብ ዘመዶች በሞሳክ ፎንሴካ አማካይነት ያሸሹትን ገንዘብ ሸሽገዋል፡፡ ከግብርም አምልጠዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በሕገወጥ መንገድ የተገኙ ገንዘቦችን ሕጋዊ ማድረግ ተችሏል፡፡ ገንዘቦቹ ከአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ጋርም ግንኙነት እንዳላቸው በመረጃ ተመልክቷል፡፡

የፓናማው ሰነድ በሰባ ስድስት አገሮች ተጨማሪ ምርመራና ትንተና ይደረግባቸው ዘንድ ለ400 ጋዜጠኞች፣ እንዲሁም ለ107 ሚዲያ ተቋማት ተሠራጭቷል፡፡ ሕጋዊ ሆነው እስከተመዘገቡ ድረስ እንደ ሞሳክ ፎንሴካ ያሉ ተቋማትን መገልገል ወንጀል ባይሆንም፣ እንደዚህ ያሉት ተቋማት ለሕገወጥ ተግባርም እየዋሉ መሆኑ ይነገራል፡፡

- Advertisement -

የእንግሊዙ ቨርጅን አይላንድ በሰነዱ ከተጋለጡ ኩባንያዎች ከግማሽ የሚበልጡት ከትመውበታል፡፡ ሆንግ ኮንግም ከሞሳክ ፎንሴካ ጋር የሚሠሩ ባንኮች፣ የሕግ አማካሪ ድርጅቶችና ደላሎች መቀመጫ መሆኗ ተጠቅሷል፡፡ ሞሳክ ፎንሴካ ከ300,000 በላይ የሚሆኑ ኩባንያዎች እንደራሴ ሆኖ ተንቀሳቅሷል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆኑ እንደ ደች ባንክ፣ ኤችኤስቢሲ፣ ኮሜርዝ ባንክና ከሌሎችም ጋር ሠርቷል፡፡

በፓናማው ሰነድ በርካታ የቀድሞም ሆነ አሁን በሥልጣን ላይ ያሉ መሪዎች ተጠቅሰዋል፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ፕሬዚዳንት ካሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን፣ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ፣ የሳዑዲ ንጉሥ ሳልማን፣ እንዲሁም የአይስላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር አሪሀን በሥልጣን ላይ ካሉት ተጠቅሰዋል፡፡ ከቀድሞዎቹ የኳታር አሚር ሀማድ ቢን ካሊፋ አል ታኒ፣ የጆርጂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢዲዚና ኢቫ ኒሽቢል፣ የኢራቅ አያድ አላዊ፣ የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር ፓቭሎ ላዛሬንኮና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

የፓናማው ሰነድ 61 የፕሬዚዳንቶች፣ የንጉሦችና የጠቅላይ ሚኒስትሮች የቤተሰብ አባላትንም ለይቷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን አባት ተጠቅሰዋል፡፡ ዴቪድ ካሜሮንም ሟች አባታቸው ከላይ በተገለጸው መንገድ ሸሽገው ያስቀመጡት ገንዘብ ተጠቃሚ ናቸው በመባሉ፣ ስለዚሁ ጉዳይ ማብራሪያ ለመስጠት ከፓርላማ አባላት ፊት መቆም ግድ ሆነባቸው፡፡   

በሰነዱ የካሜሮን አባት ለእንግሊዝ ግብር የማይከፍል የኢንቨስትመንት ኩባንያ ማቋቋማቸው ተገልጿል፡፡ ዴቪድ ካሜሮንም በእርግጥም እ.ኤ.አ. በ2010 በአባታቸው ኩባንያ ያላቸውን አክሲዮን በመሸጥ መጠቀማቸውን አምነዋል፡፡ ቢሆንም ግን እንቅስቃሴያቸው ሕግን የተከተለ መሆኑን ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ በውጭ አገሮች የባንክ ሒሳብ መክፈትን ጨምሮ በተለያዩ ዘዴዎች ግብር የማይከፍሉ የእንግሊዝ ኩባንያዎች ላይ ዕርምጃ መውሰድ የሚያስችል አሠራር እንዲኖርም ፓርላማውን ጠይቀዋል፡፡

‹‹የሕግ ማስፈጸም ሒደት ማን ሁሉንም ኩባንያዎች በሞኖፖሊ እየተቆጣጠረ እንደሆነ ማየት አለበት፤›› ያሉት ዴቪድ ካሜሮን ግን ከወቀሳ አልዳኑም፡፡ ለምሳሌ ከተቃዋሚው ሌበር ፓርቲ ጠንካራ ትችት ሲሰነዘርባቸው የፓርቲው መሪ ጀርሚ ኮርባይን፣ ‹‹እንግሊዝ የታክስ ሥወራ ኢንዱስትሪ ልብ ነበረች፤›› ብለዋል፡፡ ስለዚህም ዴቪድ ካሜሮን ስለቤተሰባቸው ሀብት ቀጣይ ጥያቄዎችን መመለስ ይኖርባቸዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡ መንገድ አፅጂዎች፣ መምህራንና ነርሶች ግብር ሲከፍሉ ከላይ ያሉ እንዴት ይህ የግብር ሕግ እነሱን እንደማይመለከት ሊያስቡ ይችላሉ? ሲሉም ይጠይቃሉ ኮርባይን፡፡

የፓናማው ሰነድ ያስነሳው ማዕበል አገሮችንና እንደ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ጭምር እየደረሰ ነው፡፡ የአይኤምኤፍ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክርስቲን ላጋር ዓለም አቀፍ ግብርን በሚመለከት ከተለመደው ውጪ ማሰብ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት መቀመጫውን እንግሊዝ ያደረገው በጎ አድራጐት ድርጅት ኦክስፋም የዓለም ድሀም ሆኑ ሀብታም አገሮች በግብር ላይ ያላቸው አመለካከት እኩል መሆኑን የሚያረጋግጥ ዓለም አቀፍ ነፃ ተቋም እንደሚያስፈልግ ያቀረበው ሐሳብ እንዳይደናቀፍ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኦክስፋም አቅርቦት የነበረው ሐሳብ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር ታክስን የሚመለከት ድርጅት እንዲቋቋም ነው፡፡

ክርስቲን ላጋር አገሮች በግብር ላይ ያላቸውን ኃይል አሳልፈው ለተመድ ለመስጠት ፈቃደኛ እንደማይሆኑ ይገልጻሉ፡፡ ላለፈው ምዕተ ዓመት ግብር ምን ማለት ነው የሚለው ከተለያየ አቅጣጫ ሲታይ፣ ሲተነተን፣ ዲዛይን ሲደረግና ሲተገበር የኖረው የአገሮችን ሉዓላዊነት መሠረት አድርጐ መሆኑ የሥጋታቸው መሠረት ነው፡፡ ስለዚህም የተገለጸው ዓይነት ዓለም አቀፍ የታክስ ተቋም የተወሰነ ሥልጣን ይውሰድ ቢባል፣ በርካታ አገሮች ፈቃደኛ አይሆኑም የሚለው ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ፡፡

የፓናማው ሰነድ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁነቶች ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው እየተባለ ነው፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው፡፡ በኅብረቱ ጉዳይ ላይ ወጣ ገባ እያለች ያለችው እንግሊዝ በፓናማው ሰነድ ዋነኛ ተዋናይ ተደርጋ መቀመጧ ደግሞ የተፅዕኖውን አንድምታ ያገዝፈዋል፡፡

በፓናማው ሰነድ ግብር ባለመክፈል የሀብት መሠረታቸውን ካሰፉ መካከል አንዱ አባታቸው የሆኑት ዴቪድ ካሜሮን፣ በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ ኅብረትን በጥርጣሬ እያዩ ያሉ እንግሊዛዊያንን በአውሮፓ ኅብረት ጉዳይ ማሳመን እጅግ ይከብዳቸዋል እየተባለ ነው፡፡ የአውሮፓ ኅብረት አባልነትን በሚመለከት ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ቅስቀሳ በጀመረችው እንግሊዝ የፓናማው ሰነድ ካሜሮን ላይ ፈተና ደቅኗል፡፡

ፓናማ ታክስ የሌለባት ምድረ ገነት ነች እየተባለች ስትገለጽ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ከታክስ ጋር በተያያዘ ግልጽነትን ከሚያረጋግጡ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ ባለመሆንም ስሟ እየተነሳ ነበር፡፡

ከጥቂት ቀናት በፊት ዓለም የፓናማ ሰነዶች ከሚባለው ሚስጥራዊ ጉዳይ ጋር ተዋውቋል፡፡ ይህ ሰነድ 2.6 ቴራ ባይት ሲሆን፣ በዚህ ሰነድ ይፋ መሆን ከባድ ትስስር ያለው የኃያላንና የባለሥልጣናት ሙስናና ግብር አለመክፈል እየተጋለጠ ነው፡፡ ከዚህ ጀርባ ያለው ደግሞ መቀመጫውን ፓናማ ያደረገውና የውጭ አገር ዜጐች የሽፋን ኩባንያዎችን በማቋቋም ገንዘባቸውን ከግብር እንዲሸሽጉ የማድረግ ድጋፍ የሚሰጠው ሞሳክ ፎንሴካ የተሰኘው የሕግ ምክር አገልግሎት ድርጅት ነው፡፡     

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...