እነሆ መንገድ። ጊዜና ሥፍራ ተጋግዘው በውስነንት ይዘውናል። መፍጠን ያቃተው ‘የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም’ እያለ እጁን ሰጥቶና አንገቱን ደፍቶ ይኖራል። ስለደጉ ጊዜ ይዘምራል፡፡ ክፉውን ይኮንናል። ጊዜን የቀደመው ደግሞ በእጆቹ ሥራ ኮርቶ ይጀግናል፡፡ አንዳንዱም ሰው ከማያየው ህሊናው ጋር እንደተሟገተ ‘የፍጥነት እንጂ የጊዜ ጀግና የለውም ያለው ሳይቲስት ለዘለዓለም ይኑር’ እያለ በወኔ ይጣደፋል። በመሀል በጊዜም በፍጥነትም ነገር ያልገባው፣ ቀኔም ውሎዬም ስሜም እኔም እንደተጻፈልኝ እንጂ እንደምጽፈው የምኖረው አይደለም በሚል ስሜት፣ የሚያየውንና የማያየውን ለአንድ ታላቅ አምላክ አስገዝቶ ውረድ ሲሉት ይወርዳል፣ ተሳፈር ሲሉት ይሳፈራል። አይስቅም፣ አያለቅስም፣ አይደሰትም፣ አያዝንም። ይህም እንደተጻፈለት እንጂ እንደጻፈው አይደለምና። ከላይ ሰማይ አለ። ከሰማዩ በታች አልፎ አልፎ ደመና፣ አልፎ አልፎ ብርሃን፣ አልፎ አልፎ ጨለማ፣ ከአልፎ አልፎዎቹ በታች ተራራ፣ ወንዝ፣ ባህርና የብስ አለ።
በወንዞቹ፣ በተራራዎቹ፣ በየብሳቱ መካከል ክልልና ኬላ፣ ከተማና ገጠር፣ ቀበሌና መንደር አሉ። አንዳንዱ የተጨናነቀ፣ አንዳንዱ ነፃ የሆነ መንገድ መኖሩ ሳይዘነጋ። አንዳንዱ ሕይወት፣ ትዳር፣ እምነት፣ ፅናት የሚያፈርስ ሌላው የልኬቱን ብቻ ታሪፍ የሚቀበል ጎዳና። ከእዚህ ጎዳና በአንዱ እንደ አበቃቀላችንና ኑሯችን የማናምን ተሰብስበን ታክሲ ይዘናል። አቀማመጣችን በሒሳባዊ ቀመር መገለጽ ቢችል ወይም ባይችል የማንደነግጥ የማንደመም፣ ብቻ ወያላው ‘ዛሬ ሒሳብ በእኔ ነው’ ቢለን ጮቤ የምንረግጥ ታካች መንገደኞች ነን። በቅርበትና በርቀት ከአዕምሮአችን በላይ በሆኑ ጥበቦችና ሐሳቦች ከተሠራው ዓለማችን በላይ ተጋፍተን ወንበር መያዛችን የሚያስፈነድቀን ምስኪን የሕይወት እስረኞች ነን። መንገድ የሌለበት የለምና ከደመናው በላይ ባንጓዝ ከደመናው በታችን መጓዝ አላቋረጥም። መንገድ ውሎ ይግባና!
“ሾፌር ንዳዋ ጊዜያችንን ገደልከው እኮ፤” ጋቢና የተቀመጠ ወጣት ሾፌራችንን ይጠዘጥዘዋል። “ምን ጊዜ አለ ደግሞ እዚህ አገር?” አለው ከጎኑ የተቀመጠ ሌላ ተሳፈሪ። “እንዴት?” ግራ ተጋብቶ ዞሮ አየው። ሾፌሩ ወያላውን እየጠቀሰ ትርፍ እንዲጭን ያበረታታዋል። “ኧረ ተወኝ አንዳችንም የለንም፤” መለሰ ‘ምን ጊዜ አለ’ ባዩ። “ከማንና ከማን?” ጠየቀው የቸኮለው ወጣት። “ከጊዜና ከእኛ አንዳችን እዚህ አገር ላይ የለንም ብዬ ነው የማምነው፤” አለው ኮስተር ብሎ ሐሳቡን ለምጡቅ የፊዚክስ ሊቅ እንደሚያቀርብ ታታሪ ተማሪ። “ታዲያ እንደሱ አትለኝም። መጀመርያውኑም ‘ብዬ ነው የማምነው’ ብለህ ሐሳብህን አቅርበህ ቢሆን ኖሮ ይኼው ገና አሁን ቁርሴን በልቼ ከመውጣቴ ደንግጨ ረሃብ አይሰማኝም ነበር፤” አለ በጎን ሾፌሩን እንሂድ እያለ እየወተወተው።
“አልገባኝም” አለው ደግሞ በተራው ያኛ ግራ ተጋብቶ። “ጊዜ የሚባል ነገር እኛ ዘንድ የለም አልክ። ቀጠልክና ወይ እኛ ወይ እሱ አንዳችን የለንም አልከኝ። ማስረጃ ያለህ መስሎኝ ደግሞ ምን ተዓምር አመለጠኝ ብዬ እህ ብዬ ሳዳምጥም አገር፣ ጊዜና ሕዝብ የመገነጣጠል መላምታዊ ሐሳብህ በእምነት ላይ እንደተመሠረተ ነገርከኝ። እንኳን በተጨበጠ የፍጥረት ሕግና ቁጥር ላይ አልተመሠረተ እንጂ፣ በሐሳብና በእምነት ላይ የተመሠረተ የመነጠልና የመገንጠል ቲወሪ ፍርኃት አይዞህ ለቆናል፤” እያለ ይባስ ግራ አጋባው። “ማነው ስለ አንቀጽ 39 የሚያወራው?” ብሎ ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠ ሳቂታ ሰውዬ ጣልቃ ሲገባ፣ “ምናለበት አንቀጽ መቁጠሩን ትታችሁ ዕድሜያችሁን ብትቆጡሩ? አዳሜ ከ39 ዓመት በላይ መኖር በማይችልበት አገር አሁንም አንቀጹ ላይ ነው?” ብላ ከሰውዬው አጠገብ የተሰየመች ወጣት ሳቀች። እንዲያው የአንዳንዱን ሳቅ ዓይነት ለመግለጽ የሆነ የሳቅ መለኪያ ‘ዩኒት’ በኖረ ያስብላል፡፡ አንዳንዴ!
ወያላው ሒሳቡን ሰብስቦ መልስ ያከፋፍላል። መጨረሻ ወበር የተየሰመ ወጣት ስለሰብዓዊነት ይተረተራል። “ሌላው ቢቀር ጓደኛዬ ሠፈር ውኃ የለም እያልን እኛ ሁለት ሰዓት ሙሉ ሻወር ስንወስድ ትንሽ አናፍርም?” አለ። “ማነን እኛ?” አለች መሀል መቀመጫ ላይ ወይዘሮዋ። “ኧረ ቆይ ተይው! አሁን ይኼን ከሰብዓዊ አስተሳሰብ ጋር ምን ያገናኘዋል? ውኃ የሚጠፋው ስለማያልፍልን። ሻውር የምንወስደው ስላለፈልን። ቆይ ምን ለማለት ነው?” ብሎ ሦስተኛው ረድፍ ላይ አጠገቤ የተሰየመው ጎልማሳ አፈጠጠበት። “በሉ በሉ ውኃ ፈረቃ ገባን ብለን ያልተጣላን ሰዎች በሻወር ልንጣላ ነው?” ሲል አንዱ፣ “ካላችሁስ ዘመኑ ብዙ ሻወር የሚያስወስድ ነው፤” አለ ሌላው። “እንዴት?” ሲባል “ታጥቦ የማይጠራው በዝቷላ። ተነግሮት የማይለወጠው፣ ተመክሮ የማይሰማው፣ ተለምኖ የማይራራው እኮ ነው መንገዱን አጓጉል እያደረገ ፍዳችንን የሚያሳየን። ዛሬ ብንነቃ ነገ ፈዘን እንውላለን። እውነቱና ሀቁ እዚህ አፍንጫችን ሥር ተኝቶ አናስተውለውም። ሙሰኛው አጠገባችን እየበላ እየጠጣ ቆይቶ ጋባዥ እኛው ነን። እንዲያው በአጠቃላይ አይደለም የሁለት የ24 ሰዓት ሻውር ብንወስድ ያንሰናል?” ብሎ እንዳበቃ፣ “የምሩን ነው? በውኃ እጥረትና በመዋጮ ባበደች አገር ተቀምጦ 24 ሰዓት ሻወር ሲል አያፍርም?” ይለኛል። ወዬው በሆነልና ውኃው በባከነ ብዬ በልቤ ዝም። አያሰኝም እንዴ? የአስተሳሰብ ውዝግባችን ብዛቱ?
ጉዟችን ቀጥሏል። መሀል ረድፍ ላይ ከወይዘሮዋ ጋር የተሰየመች ሠርቶ አዳሪ ከት ብላ ሳቀች። “እንዴ ምንድነው እንዲህ ያለማስጠንቀቂያ የምትስቂው?” ስትላት ጨመረችው። “ወይ አዲስ አቤ አያ! ሳቅም በማስጠንቀቂያ ነው ደግሞ? ኧረ…!” እያለች ከላይ እስከ ታች እያንዳንዳችንን ታነሳ ትጥለን ጀመር። “የየት አገር ልጅ ነሽ?” ወይዘሮዋ ናት የምትጠይቃት። “ባህር ዳር። ፓስፖርት ላወጣ መጥቼ ነፍሴ ልትወጣ ነው፤” ብላ ታከተች። “ወዴት ልትሄጂ ነው?” ከማለቷ ሴትዮዋ፣ “አልተማርኩ አልነገድኩ፣ አቅም የለኝ ዘመዴ የለኝ። እዚያው ዓረብ አገር ሄጄ የ40 ቀን ዕድሌ እንደሚያደርገኝ ለመሆን ነዋ፤” ስትላት ወይዘሮዋ ቆጣ ብላ፣ “እኛ ምንሽ ነን? ይኼ አገር ምንሽ ነው? ቤትሽ እኮ ነው። እኛም ዘመዶች ነን። ለምን ስደት?” ብላ ሰቀዘቻት። “ኧረ ይተውኝማ። ‘መኒ’ ነው አሉ ጨዋታው ዘንድሮ። ያለ ‘መኒ’ የለም ‘ፈኒ’ ይላሉ። በዛ ላይ ሴት ነኝ። ወንድ ብሆን ባጃጂቷንም ቢሆን ተበዳድሬ ገዝቼ እሯሯጥ ነበር። ማጀት ለማጀት ለመሯሯጥ ለመሯሯጥ ሸጋ ጥቅም ያለበት አገር ሄጄ ጭስ የማያውቀው ማጀት ብገባ እመርጣለሁ። ይተውኝማ፤” ብላ ቆዘመች። “ወይ አንቺ አገሬ። አንድ አገር ውስጥ ሆነን ለካ ማዶ ለማዶ ነን፤” ሲል ጎልማሳው፣ “ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም” ብላ ወይዘሮዋ መልካሙን ሁሉ ተመኘችላት። ከመመኘት በቀር መከወንማ የጥቂቶች ፀጋ ሆኗል እንግዲህ!
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ወጣቶች መካከል ስለሰብዓዊነትና ስለመተዛዘን ሲሰብክ የነበረው ወራጅ ብሎ አስቆመን። ሲወርድ መሀል መቀመጫ በአነጋገር ዘዬዋና በቀናነቱዋ ቀልባችን ስትስብ የቆየችውን ምስኪን ሠርቶ አዳሪን ረገጣት። “ኧረ ኡኡኡኡ! ኧረ ገደለኝ እናንተ! ኧረ እኔስ እንጃልኝ ወዬው! ኡሁሁሁሁ!” እያለች አቀለጠችው። ተሳፋረዎች ከመደንገጥና ምንሆንሽ ከማለት ይልቅ ባደገችበት ሥፍራ ባህልና የቋንቋ አገላለጽ ልማድ አጋና ስታቀርበው እንደ ቴአትረኛ ፈዘው እያዩዋት በሳቅ አሽካኩ። እሷም አፍራ በነጠላዋ ዓይኗን ሸፈነች። ያ ቆሞባት የሄደው ወጣት ግን መለስ ብሎ ‘እኔን’ ሳይል ‘ይቅርታ’ ሳይል ቀጥ ብሎ፣ ሄደ። “አይዞሽ” አለች ወይዘሮዋ። “ኧረ እኔስ ተርፌያለሁ እሱ ነው እንጂ ቀደም እንዲያ ሲደሰኩር እንዳልነበር እንደ ሰባ ኮርማ መለስ ብሎ ሳያየኝ የሄደው። ኧረ! ወይ አዲስ አበባ አያ!” እያለች ንፅፅር ጀመረች። “እንዴ ቅድም እንዲያ ስለሰውና ሰብዓዊነት ሲደሰኩር እንዳልነበር ምናለበት አሁን ቢያንስ ትዝብቱን ፈርቶ ይቅርታ ብሏት ቢወርድ?” ወይዘሮዋ ነገር ለኮሰች።
“ካወራን አይበቃም ብለሽ ነው። ዘመኑ እኮ የወሬ እንጂ የተግባር አይደለም። ከማን አንሼ ‘በቶክ’ ሆኗል። እንጂ ሥራ ድሮ ቀረ፤” እያለ ተሳፋሪው መቀባበል ጀመረ። “ያም ሆነ ይህ ቃል የእምነት ዕዳ ነው። መቼም ልናበዛው፣ ልናሳንሰው እንችላለን እንጂ ምንም ነገር እንዲያው ሳናምንበት አናወራም። አይደለም እንዴ?” ሲል ጎልማሳው “ተወው እሱን። ዘንድሮ ከልብ ሳይሆን ከፌስቡክና ከዩቲብ የቃረመውን ነው ሰው የሚያወራው። ለዚያም እኮ ነው በተግባር የማያሳየውን ነገር ሲዘባርቁ መዋል የበዛው። ሙስና ይባል የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የፍትሕ ይሁን የዴሞክራሲ ዕጦት የመሳሰሉት አላስኖሩን አሉ እያለን ስንትና ስንት የአገር ሸክም በእኛው በግለሰቦች ደረጃ ሊቃለሉ የሚችሉ እያሉ፣ ወሬያችንና ትችታችን እንዳበቃ ሀሞታችን ይፈሳል። ደግሞ ለሌላ የቃል የዲስኩር ሀሜትና ትችት አጠራቅመን እንመለሳለን፤” ብሎ ከመጨረሻዎቹ አንዱ የልቡ እስኪደርስ አወራ። ወያላው “መጨረሻ” ብሎ በሩን ከፈተው። እኛም ‘የወሬ ማብቂያ የተግባራዊነት መጀመርያ ዘመን የትኛው ፌርማታ ላይ ይሳፈርብን ይሆን?’ እየተባባል ወረድን። አንዳችን በሌላችን ላይ እያላከክን ዘመኑ እንዴት ይገፋ ይሆን? ያ ወጣት እንዳለው አንድ አገር ውስጥ ሆነ ማዶ ለማዶ መሆናችን አይገርምም? ኧረ አንገፋፋ! መልካም ጉዞ!