Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሌላኛው መኖሪያ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሌላኛው መኖሪያ

ቀን:

የሰው ልጅ ሦሶት መሠረታዊ ፍላጎቶች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ፡፡ እነዚህ መሠረታዊ ፍላጎትች ሲሟሉ ሰው በሕይወት ይኖራል፡፡ ዘሩንም ይተካል፡፡ ከዚህም በላይ የእነዚህ ፍላጎቶች መሟላት ደስተኛ ሕይወት እንዲመራ ያደርገዋል፡፡ ሰው ያለ ምግብ ከባህር እንደወጣ ዓሳ ነው፡፡ ዓሳ ከባህር ሲወጣ እስትንፋሱ ቀጥ እንደሚል ሁሉ ሰውም እንደዚያው ነው፡፡ ይሁን እንጂ በምግብ እጥረትና በድህነት የተነሳ የሰው ልጅ ለተለያዩ ችግሮችና ፈተናዎች ሲጋለጥ ይታያል፡፡

 በተለይ አፍሪካዊያን የዚህ ችግር ዋነኛ ገፈት ቀማሾች ናቸው ሲል ሰሞኑን አፍሪካ ክራድል የተሰኘው የመረጃ መረብ ዘግቧል፡፡ በመረጃ መረቡ መሠረት አፍሪካ ረብ ባለው መልኩ ከድህነት ልትወጣ እንዳልቻለችና መንግሥታትም ዜጎቻቸውን መመገብ በሚያስችል ደረጃ ላይ መድረስ አለመቻላቸውን አስነብቧል፡፡ ያልተነካ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት የሆነችው አፍሪካ በድህነት የተነሳ ዜጎቿን ከሞት፣ ከስደትና ከተለያዩ ችግሮች የሚታደጋቸው አካል እንደሌለና ችግሩ አሁንም ድረስ የቀጠለ መሆኑን ገልጿል፡፡

ይህ ችግር በተለይ በአሁኑ ወቅት በዚምባብዌ እየተባባሰ መምጣቱን ዘግቦ፣ አገራችን ኢትዮዽያንም እስካሁን ድረስ ራሷን ያልቻለች ሲል ፈርጇታል፡፡ ለዚህና ሌሎች ችግሮች እንደ ምክንያትነት የሚያስቀምጠው ደግሞ በአፍሪካ የተማረ የሰው ኃይል አለመኖር፣ የየአገሮቹ ገዥዎች ብልሹ አሠራርና በሙስና መዘፈቅ፣ ራስ ወዳድነትና ሌሎች ምክንያቶችን ያስቀምጣል፡፡ ይህ ከላይ ያነሳሁት ሐሳብ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ውስጥ ያለውን ድህነትና ከዚሁ ጋር ተያይዞ እየተስፋፋ የመጣውን የጎዳና ተዳዳሪነት ሕይወት ለመዳሰስ፣ እንደ መነሻ ወይም መግቢያ ያገለግለኝ ዘንድ ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት የድህነት ቡትቶዋን አሽቀንጥራ ለመጣል ደፋ ቀና እያለች ነው፡፡ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የከተማ ባቡር ባለቤት ሆናለች፡፡ ታላላቅ ሕንፃዎች እዚያም እዚህም እየታዩባት ነው፡፡ የውስጥ ለውስጥ መንገዶቿ ኮብልስቶን መልበስ ጀምረዋል፡፡ ኑዋሪዎቿ በጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) መኖር ጀምረዋል፡፡ ይህ ደግሞ የከተማዋን ውበት ጨምሯል፡፡ የተወሰኑ ፋብሪካዎች እየተቋቋሙ ነው (በዚህም ብዙ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል)፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር የተማረ የሰው ኃይል በውስጧ ይዛለች፡፡ አዳዲስ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ታክሲዎችና ሚኒባሶች ባለቤት ሆና ዜጎቿ የተሳለጠ ባይባልም አገልግሎት ማግኘት ጀምረዋል፡፡ ሌሎችም ለውጦች በአዲስ አበባ እየታዩ ነው፡፡

በተቃራኒው አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት ሊሠሩ የሚገባቸውና እስካሁን ድረስም ብዙ ያልተሠራባቸው ጉዳዮችን በውስጧ እንደ ዶሮ ጫጩት ታቅፋ የያዘች ከተማ በመሆኗ፣ ዜጎቿ ለከፋ ችግርና ረሃብ ብሎም ለጎዳና ተዳዳሪነት ሲዳረጉ ማየት ብርቅ አይደለም፡፡

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሌላኛ መኖሪያቸው ጎዳና ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ አዲስ አበቤዎች መዋያቸውም ሆነ ዞሮ መግቢያቸው ጎዳና ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ይህ የጎዳና ሕይወት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ደግሞ በዙሪያችን ያሉ ጎዳናዎችን ዞር ዞር ብሎ መመልከቱ በቂ ይመስለኛል፡፡

እነዚህ ወገኖቻችን በዜግነታቸው ከአገራቸው መጠቀም ያለባቸውን እየተጠቀሙ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ብናነሳ መልሱ አይደለም የሚል ይሆናል፡፡ ለምን? ለሚለው ጥያቄ ወደፊት የምመለስበት ሆኖ ለዛሬው ግን ጎዳና ላይ ስለሚኖሩ ወገኖቻችን ሕይወትና ስለ አኗኗር ዘይቤያቸው ትንሽ ለማለት ፈልጌያለሁ፡፡ በተወጠረ ሸራ ውስጥ የሚኖሩ የጎዳና ተዳዳሪዎች እን’ኳ ብርቅ  በሆኑባት አዲስ አበባችን አብዛኛው የጎዳና ተዳዳሪ ሰማይ ዳሱ፣ ድንጋይ ትራሱ፣ አፈር ቁርሱ ሆኖ ነው የሚኖረው፡፡

ዘወትር ከቤቴ ወደ ሥራ ቦታ፣ ከሥራ ቦታ ወደ ቤቴ በምመላለስበት ወቅት ከአየር ጤና እስከ ሜክሲኮ፣ ከሜክሲኮ እስከ ቦሌ ባሉ ጎዳናዎች የማያቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች ሕይወት ልብን የሚነካ ነው፡፡ እናት ከልጆችዋ፣ ሕፃን ልጅ ያለ እናት (አባት)፣ እናትና አባቶች ያለጧሪና ቀባሪ፣ የአዕምሮ ችግር ያለባቸው ዜጎችና ሌሎች ወገኖቻችንን በአዲስ አበባ ጎዳና ላይ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡

ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ የመጣው የጎዳና ተዳዳሪ ዕጣ ፈንታም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ቁጥሩ በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ አዲስ አበባችን ብርቅየዋና ብቸኛዋ የአፍሪካ የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎች ማዕከል መሆኗ የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ ኢኮኖሚያችን በአሁኑ ወቅት በ11 በመቶ ያደገውን ያህል የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥርም በዚሁ ልክ ያደገ ይመስለኛል፡፡

ለአብነት ያህል በቦሌ የሚኖሩትን ብናይ ጥሩ ማስረጃ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የቦሌ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን ተገን አድርገው የሚኖሩ ወገኖቻችን ቁጥራቸው የበዛ ነው፡፡ ዘወትር ምሽት ከቦሌ ድልድይ ወደ ቦሌ መድኃኔዓለም ወይም ከቦሌ መድኃኔዓለም ወደ ቦሌ ድልድይ ለሥራም ሆነ ለሽርሽር ጎራ ሲሉ ከላይ እስከ ታች ተሠልፈው ‹‹እራቴን አብላኝ (አብይኝ)›› የሚሉ ልጆችን ማየት ወይም መስማት የተለመደ ነው፡፡ እናት ጨቅላ ልጇን ይዛ ባዶ አስፋልት ላይ ስትውልና ስታድር ማየት ሌላው የዚህ አካባቢ ትዕይንት ነው፡፡ የአካል ጉዳተኞችና ሌሎች ወገኖቻችንም በዚሁ ሠፈር ወይም አካባቢ በስፋት ይታያሉ፡፡

ሌላው ደግሞ ለሆነ ጉዳይ ወደ ቆሼ እግር ጥሏችሁ ጎራ ካላችሁ ቀለባቸውን ከዚሁ ቆሻሻ ቦታ ያደረጉ ወገኖቻችንን ታገኛላችሁ፡፡ በተለይ በተለይ ትናንሽ ልጆችን፡፡ የእነዚህና ሌሎች መሰል ልጆች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ስናስብ ጉዳዩ ከባድ ይሆናል፡፡

ኢትዮዽያዊነት ባህሉ ይይዘንና ሽርፍራፊ ሳንቲሞችን ሰጥተን እናልፋለን፡፡ ይህ ዕርዳታ ለእነዚህ ወገኖቻችን ዘላቂ መፍትሔ ይሆናል? የሚል ጥያቄ ብናነሳ መልሱ አይሆንም የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም እስከ ዛሬ ድረስ ሳንቲሞችን ሰጥተን ወገኖቻችንን ከዚህ ሕይወታቸው ልንታደጋቸው አልቻልንምና፡፡

ለዚህ ሁሉ ችግር ምንጩ ምንድነው? የሚል ጥያቄ እናንሳ፡፡ ምንም’ኳ የችግሮቹን ምንጮች በጥናት አስደግፎ ማቅረብ ተገቢ ቢሆንም፣ በእኔ እምነት የሚከተሉት ሊሆኑ እንደሚችሉ ይሰማኛል፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ እየፈለሰ ያለው ሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ በሚመጣ ቀውስ፣ የኑሮ ውድነት ባስከተለው ጫና፣ በፖለቲካዊ ቀውስ፣ በማኅበራዊና ሌሎች ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

አሁን ደግሞ ለእነዚህ ችግሮች ዋነኛው መፍትሔ ምንድነው? የሚል ጥያቄ እናንሳ፡፡ ይህ ጥያቄ ተገቢና በስፋት መዳሰስ ያለበት ይመስለኛል፡፡ በመሆኑም እንደሚከተለው ለመዳሰስ እሞክሩለሁ፡፡ ‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው ሆኖ መገኘት በቂ ነው›› የሚል አገርኛ አባባል አለን፡፡ ይህ አባባል ጠቅለል ባለ መልኩ አንድ መልስ ብቻ ይሰጠናል፡፡ የመፍትሔው አካል ግለሰብ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ መንግሥት ወይም ሌላ አካል ሳይሆን ሰው ሆኖ መፈጠር ብቻ በቂ ነው የሚል ምላሽ፡፡ ይህ አባባል መንግሥትን፣ አንድን ግለሰብን ወይም ሌላ ተቋምን ከተጠያቂነት የሚያሸሽ ነው፡፡ የመፍትሔው አካል መንግሥት ነው ወይም ግለሰብ ነው የሚል ጥያቄ እንዳናነሳ ያስገድደናል፡፡

ሰው ስለሆንን ብቻ እነዚህን ወገኖቻችንን መርዳትና ከዚህ ችግራቸው ማውጣት እንዳለብን ይነግረናል፡፡ አባባሉ ትክክል ነው፡፡ ሰውን ለመርዳት ሰው ሆኖ መገኘት በራሱ በቂ ነው፡፡ ነገር ግን የችግሩ አሳሳቢነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞና ከዚህ በፊት እነዚህን ወገኖቻችንን ከዚህ ሕይወታቸው ለማውጣት የሄድንባቸው መንገዶች ዘላቂ መፍትሔ ስላላመጡልን፣ ለጉዳዩ ኃላፊነት መስጠት ተገቢ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ አለበለዚያ ለምሳሌ በፖለቲካ ምክንያት ጎዳና ላይ የወጡ ወገኖቻችንን ከዚህ አባባል ተነስተን መንግሥትን ተጠያቂ ላናደርገው ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ለእነዚህ ችግሮች ዋነኛ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ባለድርሻ አካላት ግዴታቸውን ሲወጡና ሁላችንም የኃላፊነት ስሜት ሲፈጠርብን ነው፡፡

በግለሰብ ደረጃ የሚቋቋሙ የመርጃ ማዕከላት ለምሳሌ እንደ መቄዶኒያ ዓይነትና ሌሎች መሰል ድርጅቶች ሊስፋፉና ሊበረታቱ ይገባል፡፡ አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው፣ አርቲስት ዳንኤል ተገኝ፣ ድምፃዊ ሀመልማል አባተና ሌሎች ባለሙያዎች፣ ባለሀብቶች ወዘተ. ዓይነት ግለሰቦች የወሰዱትን የሰብዓዊ ድጋፍና ዕርዳታ ግዴታ ሁላችንም መውሰድ  አለብን፡፡ እነዚህ ወገኖቻችንን ከዚህ ሕይወት ለማውጣት ቅን ልቦና ኖሮን የየድርሻችንን መወጣት አለብን፡፡

የሃይማኖት ተቋማት ሕዝቡን በማስተማር ለእነዚህ ወገኖቻችን ዘላቂ መፍትሔ እንዲመጣ የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ የአንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን ምሳ ወይም እራት መጋበዝ ሳይሆን፣ ባላቸው ተሰሚነት አዳዲስ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ለችግሩ የመፍትሔ አካል መሆን አለባቸው፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ መንግሥት ይህንን ችግር ለመፍታት እጀ ረጅም  በመሆኑ ትልቁንና ዋናውን ሚና መጫወት አለበት፡፡ ራሱን ከሙስናና ብልሹ አሠራር ነፃ አድርጎ ለዜጎቹ ዘብ መቆም አለበት፡፡ ቆሼንና ሌሎችን መሰል ቦታዎች አለኝታቸው አድርገው የሚኖሩ ዜጎቹን ነፃ ማውጣት አለበት፡፡ ሕፃናት ለዚህ ችግር ተጋላጭ እንዳይሆኑ ከፍተኛ ሥራ መሥራት አለበት፡፡ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር አለበት፡፡ በአንድ ወቅት ተጀምረው የነበሩ እንቅስቃሴዎች ቀጣይነት ይኑራቸው፡፡ የእያንዳንዱ ዜጋ ሕመም የመንግሥትም ሕመም መሆን አለበት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

                                        

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...