በኢትዮጵያ የመጀመርያው የጠለፋ ዋስትና ሰጪ ኩባንያ ለማቋቋም የምሥረታ ጉባዔውን ያካሄደው የኢትዮጵያ ሪኢንሹራንስ ኩባንያ አክሲዮን ማኅበር ፈቃድ ለማግኘት እንዲያሟላ የሚጠበቅበትን መረጃዎች አጠናክሮ ለብሔራዊ ባንክ አስገባ፡፡
ከኩባንያው የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ የኩባንያውን ህልውና የሚያረጋግጠውን የብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ለማግኘት ከኩባንያው የምሥረታ ጉባዔ ቀደም ብሎና ከዚያም በኋላ በተከታታይ የተጠየቀውን መረጃዎች ሲያስገባ ነበር፡፡ በዚህ ሳምንት መጀመርያ ላይም የመጨረሻዎቹን መረጃዎች ለብሔራዊ ባንክ አጠናቅቆ በማስገባቱ ወደ ሥራ የሚያስገባውንና የመጨረሻውን ፈቃድ ለማድረግ እየተጠባበቀ መሆኑ ታውቋል፡፡
በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት አንድ ሪኢንሹራንስ ኩባንያ ለማቋቋምና ወደ ሥራ ለመግባት የሚጠየቁ የተለያዩ ማረጋገጫዎች ስለሚያስፈልጉ፣ ይህንን የሚያሳዩ ከ30 ያላነሱ የተለያዩ መረጃዎች ለብሔራዊ ባንክ መቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከነዚህ ውስጥ የኩባንያው መሥራቾች ማንነት፣ የኩባንያው ካፒታል፣ የአዋጭነት ጥናት፣ አጠቃላይ የኩባንያውን ይዘት የሚያሳዩና ፈቃድ ለማግኘት ያስችላሉ የተባሉ የተለያዩ ሌሎች መረጃዎችን የሚያጠቃልል ነው፡፡ አሁን ሙሉ በሙሉ አስፈላጊ የተባሉ መረጃዎች ገብተው የሚጠበቀው የብሔራዊ ባንከ ፈቃድ ብቻ ሲሆን፣ ይህም ፈቃድ በአንድ ወር ውስጥ ይሰጣል ተብሎ ተገምቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኩባንያውን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሊመራ የሚችል ባለሙያ በመገኘቱ፣ የኩባንያው ዳይሬክተሮች ቦርድ የሪኢንሹራንስ ኩባንያውን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ይመሩልኛል ብሎ ያጫቸውን ባለሙያ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት መሪዎችን ሹመት ማፅደቅና መሻር ሥልጣን የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲያፀድቅለት ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ኩባንያው የዕጩውን ሥራ አስኪያጅ ለጊዜው ለመግለጽ ፈቃደኛ ባይሆንም፣ ኩባንያውን በሥራ አስፈጻሚነት የሚመራ ባለሙያ መታጨቱን ገልጿል፡፡
የኩባንያው ምሥረታ ጉባዔ ከመካሄዱ ቀደም ብሎ ኩባንያውን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚመራ ባለሙያ ለመቅጠር የተደረጉ ጥረቶች ሳይሳኩ መቅረታቸው ይታወሳል፡፡ ኩባንያውን ለመምራት በኢትዮጵያ የመጀመርያውን የጠለፋ ዋስትና ሰጪ ኩባንያን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚመራ ባለሙያ ባለመገኘቱ፣ የማፈላለጉ ሥራ በአዲሱ ቦርድ ከቀጠለ በኋላ በቅርቡ ለቦታው የተጠቀመውን መሥፈርት የሚያሟላ ባለሙያ ሊያገኝ ችሏል፡፡
ለኩባንያው ሥራ አስፈጻሚ ለመሰየም የተደረጉ ጥረቶች እልህ አስጨራሽም ነበር ተብሏል፡፡ በተደጋጋሚ የተደረጉት ጥረቶች ሳይሳኩ በመቅረታቸው፣ ብሔራዊ ባንክ ለሥራ መደቡ በመመርያው ያስቀመጠውን መሥፈርት ካላሻሻለ ለቦታው የሚመጥን ባለሙያ ለማግኘት ያስቸግራል ተብሎ ተሠግቶ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመርያው የሆነው የኢትዮጵያ ሪኢንሹራንስ ኩባንያ በአንድ ቢሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው 10 ሺሕ ብር ዋጋ ያላቸው 100 ሺሕ አክሲዮኖች አሉት፡፡
በዚሁ መሠረት ከአንድ ቢሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል ውስጥ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ፈራሚ ኩባንያዎቹና ግለሰብ ባለአክሲዮኖች 699 ሚሊዮን ብር ክፍያ በመፈጸማቸው፣ በዚሁ ካፒታል መጠን ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት አንድ ሪኢንሹራንስ ኩባንያ ለመመሥረት የሚጠየቀውን የተከፈለ 500 ሚሊዮን ብር ማሟላት ችሏል፡፡ ይህን ኩባንያ ለማቋቋም ሲታሰብ ከኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ሌላ የባንኮች ተሳትፎ የጎላ እንዲሆን ቢፈለግም፣ የባንኮች ተሳትፎ የተጠበቀውን ያህል ሊሆን አልቻለም፡፡
በዚህ ኩባንያ ውስጥ ባንኮች 200 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች የገዙ ሲሆን፣ ከባንኮች ከፍተኛውን የአክሲዮን ግዥ የፈጸመው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ የኩባንያው ባለአክሲዮን ሆነው ከተመዘገቡት ውስጥ 17ቱም የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ሰባት ባንኮች ይገኙባቸዋል፡፡ ግለሰቦቹም የአክሲዮን ኩባንያው አባላት ሆነው እንደተካተቱበት ይታወቃል፡፡ የኩባንያው መመሥረት አገሪቱ ለጠለፋ ዋስትና በየዓመቱ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓመት ከሚሰበሰቡት ዓረቦን ውስጥ 30 በመቶውን በውጭ ምንዛሪ ለውጥ የጠለፋ ዋስትና ኩባንያዎች ሲያውሉ ቆይተዋል፡፡