ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ እየተበራከተ የመጣው የውጭ ብራንድ ሆቴሎች ኢንቨስትመንትና የግንባታ ሒደት በፋይናንስ እጦት ምክንያት መጓተት እንደሚታይበት የእንግሊዙ ኩባንያ ጥናት አመለከተ፡፡
በያመቱ በአፍሪካና በሌሎች አኅጉሮች የሆቴል ፎረም በማዘጋጀት የሚታወቀው የእንግሊዙ ቤንች ኤቨንትስ ኩባንያ፣ በአፍሪካ እንዲገነቡ ስምምነት የተደረገባቸው ውሎች በታቀደላቸው ጊዜ እንዳይሳኩ የፋይናንስ ዕጥረት አስተዋጽኦ ማድረጉን ከትናንት በስቲያ ለሪፖርተር በላከው የዳሰሳ ጥናት መግለጫው አስታውቋል፡፡
ቤንች ኤቨንትስና ደብሊው ሆስፒታሊቲ ግሩፕ የተባለው አጥኚ ኩባንያ በጋራ ባሰራጩት መረጃ መሠረት፣ ዘንድሮ ለዘጠነኛ ጊዜ ይፋ የተደረገው የአፍሪካ ሆቴሎች ልማት ዳሰሳዊ ጥናት ሪፖርት፣ ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገሮች ውስጥ 30 ከመቶ የሆቴል ኢንቨስትመንት ጭማሪ መታየቱን አጥኚው ኩባንያ ደብሊው ሆስፒታሊቲ ግሩፕ አትቷል፡፡
በጥናቱ መሠረት ናይጄሪያ በአፍሪካ ትልቁን የሆቴል ኢንቨስትመንት በማካሄድ ከአሥር ዋና ዋና አገሮች ውስጥ ቀዳሚ ስትሆን፣ ኢትየጵያ ስምንተኛ ደረጃን በመያዝ 12 አዳዲስ ብራንድ ሆቴሎችን ወደ መስመር ለማስገባት እየተጠባበቀች እንደምትገኝ ጥናቱ ጠቁሟል፡፡
በኢትዮጵያ ስምምነት ተደርጎባቸው ወደ ግንባታ ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁ 12 ሆቴሎች ውስጥ በጣት የሚቆጠሩት ወደ ሥራ ለመግባት እየተዘጋጁ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ረማዳን ይጠቀሳል፡፡ አብዛኞቹ ባለሀብቶች የፋይናንስ ችግሮች እየገጠማቸው መሆኑን ሲገልጹ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የውጭ ፋይናንስ በማፈላለግ ሥራ ላይ የተጠመዱም አልታጡም፡፡
በአዲስ አበባ ሁለት ጊዜ በተከታታይ ከተካሄው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም ጎን በርካታ የብራንድ ሆቴሎች ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በሽርክና የሆቴል ኢንቨስትመንት ለማካሄድ ስምምነት ያደርጉ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህንን ተከትሎ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ የአብዛኞቹ ሆቴሎ ግንባታ ይጠናቀቃል ተብሎ ይገመታል፡፡
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ይፋ በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት በየወሩ አንድ ሆቴል በኢትዮጵያ ዕውን እየተደረገ ሲሆን፣ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ከ100 ያላነሱ ሆቴሎች ገበያውን እንደሚቀላቀሉም ማኅበሩ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ በየአፍሪካ አገሮች እየተዘዋወረ የሚካሄደው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም ዘንድሮ በቶጎ የሚካሄድ ሲሆን፣ ከቶጎ በመቀጠል በሩዋንዳ እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ ይፋ አድርገዋል፡፡