Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኦማን ባለገንዘቦች ኢትዮጵያን ለአፍሪካ ገበያ መግቢያ በር እንድትሆናቸው መርጠዋታል

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኦማን መንግሥት የኦማን ኩባንያዎች ለሚያመርቱት ምርት ገበያ ለማፈላለግና ከተለያዩ አገሮች ኩባንያዎች ጋር በጥምረት ለመሥራት የሚያስችል ዕድል ለመፍጠር ተንቀሳቃሽ ኤግዚቢሽኖችን ያዘጋጃል፡፡

ኦሞኒ ፕሮዳክት ኤግዚቢሽን (UPEX) የሚል መጠሪያ ያለው ይህ የንግድ ትርዒት፣ በርካታ የኦማን ኩባንያዎችን በመያዝ በተመረጡ አገሮች ላይ ይካሄዳል፡፡ አምስተኛ ዓመቱን የያዘው ይህ የንግድ ትርዒት፣ የመጀመሪያዎቹን አራቱን የንግድ ትርዒቶች ዝግጅቶች ያካሄደው በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ባሉ አገሮች ነው፡፡ ከንግድ ትርዒቱ አስተባባሪዎች መረዳት እንደተቻለው የመጀመሪያዎች ሁለት የንግድ ትርዒቶች በሳውዲ ዓረቢያ፣ ጂዳና ሪያድ ከተሞች የተደረጉ ናቸው፡፡ ሁለቱ ደግሞ በዱባይና በዶሃ መካሄዳቸውን የንግድ ትርዒቱ አስተባባሪዎች ይገልጻሉ፡፡

አምስተኛውን የኦማን አምራቾች የንግድ ትርዒት ዝግድት ግን ከመካከለኛው ምሥራቅ ወጥቶ አፍሪካ ውስጥ ለማካሄድ ሲወሰን፣ ለዝግጅቱ ዕጩ ከሆኑ አሥር አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ተመራጭ ሆናለች፡፡ በዚሁ መሠረት 115 የሚደርሱ የኦማን ኩባንያዎች ተሳታፊ የሆኑበት አምስተኛው የኦማን አምራቾች ኤግዚቢሽን፣ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ባለፈው ሰኞ ሚያዚያ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ሊከፈት ችሏል፡፡   

ኦማኖች የማኑፋክቸሪንግ ምርታቸውን በተለያዩ አገሮች ገበያ ለማግኘትና ተጨማሪ ኩባንያዎችን በማፈላለግ በጋራ ኢንቨስት ለማድረግ የሚያስችላቸውን ዕድል ለማግኘት የሚጠቀሙት ይህ የንግድ ትርዒት፣ በአብዛኛው አምራች ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ነው፡፡

ኦማኖች ኢትዮጵያን ለንግድ ትርዒታቸው ቀዳሚ ምርጫ ያደርጉዋት በጥናት ላይ የተመሠረተ የገበያ ዕድል ያላት በመሆንዋ ነው ተብሏል፡፡ እንደ አዘጋጆቹ ገለጻ ኢትዮጵያ የተመረጠችበት ዋነኛ ምክንያት፣ እያደገ የመጣው ኢኮኖሚና በተለይም በቀጣዩ አሥር ዓመታት የዜጐቿ የመግዛት አቅም እያደገ ይመጣል የሚለውን ማረጋገጫ በመያዛቸው ነው፡፡

ኢትዮጵያ ቀጣይ የሆነ ዕድገትና የመካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ትገባለች የሚለውን መረጃ የኦማን መንግሥት በባለሙያዎች ጭምር በማስጠናቱ፣ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የንግድ ትርዒት አዲስ አበባ ላይ እንዲካሄድ ተደርጓል፡፡ ከዚህም ሌላ ኢትዮጵያን የአፍሪካ መግቢያ በር በመሆንዋ ተመርጣለች ተብሏል፡፡

በቀጣዩ ዓመት የሚካሄደው ስድስተኛው የንግድ ትርዒት አዲስ አበባ ላይ እንዲካሄድ ተወስኗል፡፡ በስድስተኛው የንግድ ትርዒት ከ200 እስከ 250 ኩባንያዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እንደ አዘጋጆቹ ገለጻ ይህ የንግድ ትርዒት የኦማን ባለሀብቶች ከኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ጋር በጥምረት ወደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ መንገድ የሚከፍት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በቀጥታ የኢትዮጵያውያን አስመጪዎች የኦማንን ምርት በማስመጣት በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቱን ወደ ገበያ ለማስገባት የሚያስችል የንግድ ትስስር ይፈጥራል ተብሏል፡፡

ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሸጡ የኦማን ምርቶች ተገዝተው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት ከዱባይ ገበያ መሆኑን የሚገልጸው መረጃ፣ አስመጪዎች በቀጥታ ከኦማን አምራቾች ቢገዙ ከዱባይ ገበያ ካለው ዋጋ እንደሚቀንስላቸውና የውጭ ምንዛሪ ወጪን በመቀነስ ዕድል ስለሚሰጥ፣ እንዲህ ዓይነቱ ስምምነቶች በሁለቱ አገሮች ኩባንያዎች መካከል ይፈጠራሉ ተብሏል፡፡

ንግድ ትርዒቱ ከተከፈተ በኋላም ወደ አራት የሚሆኑ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ከአራት የኦማን ኩባንያዎች ጋር በጥምረት ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነቶች ተፈራርመዋል፡፡

እስካሁን አራት የኦማን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ሲሆን፣ የኢትዮጵያውያን ኩባንያዎች ከኦማን ኩባንያዎች ጋር በጥምረት ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሁኔታዎች ለማመቻቸትም አፕስተርም ኢንቨስትመንትስ የተባለ ኩባንያ በኢትዮጵያ ውስጥ እየሠራ ነው ተብሏል፡፡ 

በተለይ ዊንዶ 2000 የተባለው የሕንፃ መሣሪያዎች ማምረቻ ከኢትዮጵያ ኩባንያ ጋር በመጣመር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሕንፃ መሣሪያዎች ማምረቻ ለመገንባት መፈራረማቸው በምሳሌነት ተጠቅሷል፡፡   

በኦማን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ዶ/ር አሊ ቢን አሊ ሱንዴይ የተመራው የንግድ ትርዒቱ ተካፋይ ቡድን፣ የንግድ ትርዒቱ እስከሚዘጋበት ዕለት ድረስ ተጨማሪ ስምምነቶችን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኦማን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከንግድ ትርዒቱ ባሻገር በሁለቱ አገሮች መካከል ስለሚኖረው የንግድ ግንኙነት ከፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ጋር መወያየታቸው ታውቋል፡፡ እንዲህ ዓይነት የንግድ ትርዒቶች በተለይ በኢትዮጵያና በኦማን መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ያጠናክራል የሚል እምነት እንዳለም ተጠቁሟል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች