Monday, May 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፓናማ ሰነዶች ለፀሐይ ያበቁት ስውር ደባና የታቦ ምቤኪ ሙግት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሰሞኑ የዓለም ሕዝብ መነጋገሪያ የሆነው ክስተት የአገር መሪዎችና ባለሥልጣናት፣ ታዋቂ ሰዎችና ሌሎችም በርካታ ግለሰቦች ከሕዝብ ጥቅም፣ ከታክስ ክፍያ ግዴታዎች ሰውረው በባለቤትነትና በባለአክሲዮን ድርሻነት ሲመሯቸው የነበሩና ስውር ገንዘብ ሲያጋብሱባቸው የነበሩ ኩባንያዎች ዝርዝራቸው ተጋልጧል፡፡

ከእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ጀምሮ አውሮፓን እያመሰ የሚገኘው የፓናማው የቅሌት ዶሴ ብዙዎችን ወደ አደባባይ እንዲወጡና የተቃውሞ ድምፃቸውን ዶሴዎቹ በጠቀሷቸው መሪዎች ላይ እያሰሙ ይገኛሉ፡፡ በአይስላንድ የተቀሰቀሰው የሕዝብ ሞገድ አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመሩ የነበሩትን ሲግሙንዱር ዴቪድን ከሥልጣን እንዲለቁ አስገድዷል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ስንብት በኋላም ቢሆን በአይስላንድ ዋና ከተማ ሬይኪያቪክ የተቃውሞ ሠልፈኞች ሌሎች ባለሥልጣናትም ከሥልጣን ይውረዱ፣ የተጭበረበረው የታክስ ገንዘብ ይመለስ የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎችን ሲያስተጋቡ ቆይተዋል፡፡

የዓለም የምርመራ ጋዜጠኞች ስብስብ (አይሲአይጄ) ያጋለጣቸው ከ11 ሚሊዮን በላይ ሰነዶች አደባባይ ካወጧቸው መካከል የተጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን፣ በእንግሊዝ ፓርላማ አባላት ዘንድ ቀርበው እንዲያስረዱ አስገድዷቸዋል፡፡ በፓናማ ሰነዶች እንደተጠቀሰው በአባታቸው በኩል ታክስ ያልተከፈለበት ገንዘብ ኢንቨስት አድርገዋል፣ ታክስ ሰውረዋል ተብለው ከሥልጣናቸው እንዲለቁ፣ የአሳማ ምስሎችን ሳይቀር በያዙ እንግሊዛውያን ሰልፈኞች ተቃውሞ የቀረበባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለፓርላማ አባላት ሐቀኛነታቸውን ለማረጋገጥ ተገደዋል፡፡ ከዚህም አልፈው የታክስ መረጃቻቸውን ለሕዝብ ይፋ በማድረግ ጭምር አለማጭበርበራቸውን ለማሳወቅ ጥረዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ተፅዕኖችን የፈጠሩት የፓናማ ዶሴዎች በአፍሪካም ሰባት ግለሰቦችን ነካክተዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ፣ የቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ፣ የሩዋንዳው ፖል ካጋሜ፣ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊኩ ሎሬት ካቢላ፣ የሞሮኮ ንጉሥ፣ የዚምባብዌን ባለሥልጣናት ጨምሮ 17 አገሮች ከአፍሪካ በታክስ ማጭበርበርና ስወራ ስልት ሕልውና የሌላቸው ነገር ግን ሕጋዊነትን ሽፋን ያደረጉ ኩባንያዎችን ከጀርባ በባለቤትነት፣ በልጆቻቸውና በዘመዶቻቸው እንዲሁም በበታች ሠራተኞቻቸው በኩል ሲያተዳድሩ እንደነበሩ የተደረሰባቸው ተብለው እየተብጠለጠሉ ይገኛሉ፡፡

የታቦ ምቤኪ ድምፅ

የዶሴዎቹን ይፋ መውጣት ተከትሎም የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡ የፓናማ ሰነዶች አደባባይ ያወጧቸው ሐቆች፣ ምቤኪ የሚመሩትና የአፍሪካ አገሮችን ሰለባ ያደረገ የታክስ ማጭበርበር ስልታዊ አካሄድን የሚቃወመው ከፍተኛ ፎረም፣ ከአፍሪካ በተለያየ የማጭበርበሪያ ስልት እየሸሸ የሚገኘው ገንዘብ መጠን በዓመት ከ60 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚገመት በፓነሉ ከአንድ ዓመት በፊት ይፋ የተደረገው ጥናት ይጠቁማል፡፡

ይሁንና ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ ከአፍሪካ ተጭበርብሮ የወጣው ገንዘብ ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ በአንፃሩ አፍሪካ ለመሠረተ ልማት ግንባታ ከ30 እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት በጀት ያስፈልጋታል፡፡ በመሆኑም ይህንን የበጀት ጥያቄ ለማሟላት ከውጭ በሚገኙ ዕርዳታዎችና ብድሮች ብቻ ለመደገፍ ስትገደድ ይታያል፡፡ ሆኖም ግን ከአኅጉሪቱ የሚሸሸው የገንዘብ መጠን የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን በአግባቡ ለማስተናገድ ያስችል እንደነበር ያሳያል፡፡

ከፍተኛ ፓነሉ ዓምና ይፋ ባደረገው ጥናት መሠረት፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ2010 ጀምሮ በየዓመቱ ከአሥር ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ በታክስ ማጭበርበር፣ በገቢና ወጪ ንግድ ማጭበርበር፣ የወጪና ገቢ ንግድ ደረሰኞችን ሆነ ብሎ በማዛባትና ወጪን በማናር እንዲሁም ሽያጭን በማሳነስ፣ በውጭ ህልውና ከሌላቸው እህት ኩባንያዎች ግዥ ስለመፈጸሙ፣ ዕዳ ስለመከፈሉ ወዘተ በሚጠቅሱ የተጭበረበሩ ተግባራት ሳቢያ አገሪቱ ከአሥር ቢሊዮን ዶላር በላይ እያጣች መሆኗን ‹‹ትራክ ኢት፣ ስቶፕ ኢት፣ ጌት ኢት›› በሚል ርዕስ ይፋ የተደረገው ጥናት ይጠቅሳል፡፡

በጥናቱ መሠረት ኢትዮጵያ እንዲህ ያለው የተጭበረበረ ተግባር ሰለባ ባትሆን ኑሮ፣ አብዛኞቹን የሚሊኒየሙ የልማት ግቦች ለማሳካት የፈጁባትን 13 ዓመታት ወደ ዘጠኝ ዓመት ያሳጥርላት እንደነበረም ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ በመሆኑም በጥናቱ መሠረት ናይጄሪያ ከፍተኛ ገንዘብ የምታጣ ቀዳሚ አገር ስትሆን፣ ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ አንጎላ፣ አልጄሪያ፣ ኮት ዲቯር፣ ሱዳን፣ ኢትዮጵያና ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ አሥሩ ዋና ዋና አገሮች ናቸው፡፡ በአንፃሩ ከእነዚህ አገሮች ተጭበርብሮ የሚሸሸውን ገንዘብ ከሚቀበሉ አገሮች አሜሪካ ቀዳሚዋ ሆናለች፡፡ ቻይና፣ ህንድ፣ ስፔን፣ ፈረንሳይ፣ ጃፓን፣ ጀርመን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሜክሲኮና የመሳሰሉት አገሮች ይከተላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በቅርቡ ለሚዲያ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት ደግሞ አገሪቱ ከ1996 እስከ 2006 ዓ.ም. በነበሩት አሥር ዓመታት ውስጥ አገሪቱ 26 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ማጣቷን አስታውቋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ደረሰኝ በማጭበርበር የታጣው ገንዘብ መጠን 19.7 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመትም ባለሥልጣኑ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህም አገሪቱ በዓመት ከአምስት እስከ አሥር ከመቶ የሚሆነውን የኢኮኖሚዋን ድርሻ በዚህ መንገድ እያጣች እንደምትገኝም ተጠቁሟል፡፡

በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አጥኝ ቡድንና በአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች ሙሉ ድጋፍ ይፋ የተደረገው ጥናትና ያስገኘው ውጤት ሰሞኑን የዓለም ቱባ ባለሥልጣናትና ኩባንያዎችን ካጋለጠው የፓናማ ዶሴዎች ይፋ ካደረጓቸው እውነታዎች ጋር መሳ ለመሳ ገጥመዋል ያሉት ምቤኪ፣ ከታክስ ስወራና ከታክስ ማጭበርበር ወንጀሎች በተጓዳኝ በታክስ እፎይታ ሰበብ በአፍሪካ መንግሥታት ለኩባንያዎች የሚሰጡ ግልጽነት የጎደላቸው ማበረታቻዎች ሊተኮርባቸው እንደሚገቡ አሳስበዋል፡፡

ጥላቸው እንጂ ህልውናቸው በማይታወቁ ኩባንያዎች ስም፣ በአካል በሌሉ ነገር ግን እንዳሉ ተመስለው ወጪ የሚደረግላቸው ኩባንያ ተብዬዎችን ጉዳይ በሚመለከት ታቦ ምቤኪ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአሜሪካ ተገኝተው የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ኃላፊዎችን ማነጋገራቸው ይታወሳል፡፡

በፓናማው የቅሌት ዶሴ ውስጥ ኢትዮጵያን በቀጥታ የሚመለከቱ ሰነዶች ስለመኖራቸው እስካሁን ማረጋገጥ ባይቻልም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ያደረጉ የውጭ ባለሀብት ስም መገኘቱ ተሰምቷል፡፡

ከአፍሪካ በልዩ ልዩ ዘዴ እየተካሄደ የሚገኘውን ገንዘብ የማሸሽ ተግባር ሊያስቆም የሚችልና በዓለም አቀፍ ደረጃ ቅስቀሳ የሚካሂድ ተቋም እንዲመሠርት ኃላፊነት የተሰጠው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከአምስት ዓመት በፊት በአፍሪካ የፋይናንስ፣ የዕቅድና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሮች አራተኛው የጋራ ጉባዔ ላይ በተወሰነው መሠረት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ባለፈው ዓመት ይፋ ያደረገው ጥናትም አገሮች እየደረሰባቸውን ጉዳት አመላክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች