ከመጋቢት 1 እስከ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. መደበኛ ስብሰባውን ሲያካሂድ የነበረው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) 1,091 በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ የነበሩ አመራሮችን ከኃላፊነት በማገድ ተጠናቀቀ፡፡
ሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2009 ዓ.ም. የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለምነው መኰንን በጽሕፈት ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ክልሉ ካሉት አመራሮች መካከል 1091 የሚሆኑትን በብልሹ አሠራር፣ በአቅም ውስንነትና በሌሎች ጉድለቶች ተገምግመው ከኃላፊነት እንዲነሱ ተደርጓል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ እነዚህ ግለሰቦች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ እንደሠሩት ጥፋት ታይቶ በሕግ ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡
ከኃላፊነት የመታደግ ዕርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ጌትነት አማረ፣ የአዊ ዞን የቀድሞ አስተዳዳሪና በኋላም የአማራ ክልል የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ባዘዘው ጫኔ እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡
ድርጅቱ በክልሉ ውስጥ በተለይም ከባህር ዳር ከተማ ማደግ ጋር ተያይዞ የተከሰተውን የቤት ችግር ለመፍታት፣ የተለያዩ አሠራሮችን ለማስፈን መወሰኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ከብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ መጠናቀቅ ማግሥት የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ከመጋቢት 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እየተካሄደ ነው፡፡ በዚህ ጉባዔም ለክልሉ ለውጥ ያመጣሉ ተብለው የሚጠበቁ አዳዲስ አዋጆች እንደሚፀድቁ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡