የገንዘብ ቁጠባ ጠቀሜታው ለራስ ብቻም ሳይሆን ለአገርም ስለመሆኑ ትንታኔ አያሻውም፡፡ ሰሞኑን ‹‹ማርች 8›› የዓለም የሴቶች ቀን ሲከበር፣ በበዓሉ ሰበብ የተዘጋጀው የታላቁ ሩጫ መሪ ቃል ቁጠባን የሰነቀ እንደነበር እናታውሳለን፡፡
‹‹ማርች 8›› ሴቶችን በማወያየት ያከበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም ቆጥቡ ብለዋል፡፡ ቁጠባ ለሁሉም ነው፡፡ የሚቆጠብ ከተገኘ መቆጠቡ እሰየው ነው፡፡ መበረታታት የሚገባው ባህል ነው፡፡
‹‹እየሮጡ መቆጠብ›› የሚለው መሪ ቃል ጥሩ መልዕክት ያዘለ መሆኑም ግሩም ያሰኘዋል፡፡ አንድን በዓል ለማክበር እንደፋሽን የተያዘው የጎዳና ሩጫም ቢሆን መልካም ልማድ ነው፡፡ እየተዝናኑ፣ ሰውነትን እያፍታቱ ‹‹ቀኑን›› ማሰብ፡፡ በሰበቡም ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት አቋራጭ መንገድ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
እንዲህ ፕሮግራሞች በተዘጋጁ ቁጥር ግራ የሚያጋባኝ አንድ ነገር ግን አለ፡፡ ያማረ ካኔቴራ ለብሰን ጎዳናዎችን ሞልተን ስንሮጥ የመንገዳችንን ፅዳት፣ የከተማችን ውበት ማገናዘብ እየተሳነን መሆኑ ያናድዳል፡፡
ስንሮጥ ጎዳናዎቻችን ከማቆሸሽ መቆጠብ አለብን፡፡ እንደውም ‹‹ለፅዳት እንሩጥ›› የሚል ቋሚ የሩጫ ፕሮግራም ሊኖረን በተገባ ነበር ያስብላል፡፡ በየሩጫው ተሳታፊዎች የተጠቀሙባቸውን የውኃ ማሸጊያ ፕላስቲኮች እንዳሻቸው በየመንገዱ መጣላቸው፣ ጎዳናዎቹን በቆሻሻ እንዲሞሉ እያደረገ ነው፡፡ የተዘጋጁ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫቶች ውስጥ አስቦ የሚጥለው ሰው ጥቂት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የአዲስ አበባን የደረቅ ቆሻሻ አለአግባብ አወጋገድ ከፍ የማድረጋቸው ነገር ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ክረምት በመጣ ቁጥር ጭንቅ ጥብብ የሚላቸው ፈሳሽ ማስወገጃዎችም በእነዚህ ፕላስቲኮች ምክንያት ጭሩሱኑ እንዲደፈኑ ማድረጉ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ለበጎ እየሮጥን ሳለ በጎን እያጠፋን ነው ማለት ነው፡፡
እየተዘወተሩ ከመጡት በርካታ የጎዳና ሩጫዎች አኳያ እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች የንጽሕና አጠበበቅ አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ ፅዱና አረንጓዴ ከተማ የመፍጠር እንቅስቃሴን ይጎዳል፡፡ የፅዳት ልማዳችንን ወደኋላ ይመልሳል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለውን አጉል ልማድ ለመቅረፍ ‹‹ለፅዳት እንሩጥ››፣ ‹‹ከተማችንን እያፀዳን እንሩጥ›› የሚሉ ቋሚ ፕሮግራሞች ቢኖሩን በምን ዕድላችን፡፡
ከቆሻሻ የፀዳች ከተማ እንድትኖረን ድርሻችን ወሳኝ ነው፡፡ የፅዳት ነገር ከተነሳ ለቆሻሻ መጣያነት በከተማይቱ ጎዳናዎች ግራና ቀኝ የተቀመጡ ማጠራቀሚያዎች ጉዳይ ሊያነጋግረን ይችላል፡፡ እነዚህ ቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች ያለ አግባብ ብዙ ወጪ የሚወጣባቸው ብክነቶች ይመስላሉ፡፡
እነዚህን የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች ሠርቶ ለመትከል ሚሊዮን ብሮች ወጥተዋል፡፡ ተገልጋዩ በአግባቡ ይጠቀምባቸዋል ወይ? ስንል ያለማመንታት አይደለም ማለት ይቻላል፡፡ ብዙዎቻችን እነዚህን የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች ገላምጠን ከማለፍ ውጪ አልተገለገልንባቸውም፡፡ አንጠቀምንባቸውም ማለቱ ይቀላል፡፡ ማጠራቀሚያውን እያለልን በየሜዳው መጣል የሚቀናን ብዙዎች ነን፡፡ ቁጠባ ማለት ወጪ ያወጣንባቸውን ቁሳቁሶች በአግባቡ መገልገል እንደሆነም ልንረዳ ይገባል፡፡ እንቆጥብ እያልን መልሰን የምናባክን ከሆነ ምን ትርጉም ይኖረዋል?
በከተማችን ፅዳት ለማስጠበቅ ተብለው በየጎዳናዎቹ የተቀመጡትን የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች በአግባቡ አለመጠበቅና ነቃቅሎ መውሰድም ልንጠየፈው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ለከተማው የፅዳት ጉድለት ማዘጋጃ ቤት ላይ ጣት ከመቀሰር ይልቅ እኛ ነዋሪዎቿም ተጠያቂዎች ነን፡፡ የዘመናዊነት መገለጫ የሆነውን ተግባር በሕግ አስገዳጅነት ብቻ እንዲተገበርብን መጠበቅ የለበንም፡፡ የቆሻሻ መጣያዎችን በአግባቡ ለመጠቀም የግድ ሩጫ መዘጋጀት የለበትም፡፡ በተሮጠ ቁጥር ግን ጎዳናዎችን በፕላስቲኮችና በቆሻሻዎች ማዝረክረክ መልካም ምግባር አይሆንም፡፡
ዘመናዊ ነን ብለን ካሰብን እንቆጥብ፡፡ ዘመናዊ ነን ካልን በየትኛውም የሩጫ ፕሮግራም እየሮጥን ከተማችንን የማፅዳት ልምድ ይኑረን፡፡ ዘመናዊ ነን ከተባለ ብዙ ወጪ የወጣባቸውን አገልግሎት መስጫዎች በአግባቡ እንጠቀም፡፡ ይህንን ማድረግ መቆጠብ ነው፡፡ እንደልብ የሮጥንባቸው ጎዳናዎች በፕላስቲክ እየተሞሉ በጎርፍ ቢጥለቀለቁ ዕዳው የእኛው ነው፡፡ ውኃው መንገዱ እያበላሸ የሚያደርሰውን ጉዳት ለማስተካከል የሚጠይቀውን ወጪ ማሰብም ብልህነት ነው፡፡
ስለዚህ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የፅዳት ችግር በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ እኛው ነዋሪዎችም ለከተማዋ ፅዳት ማድረግ ያለብንን ያለማድረጋችን አንዱ ችግር ነው፡፡ በራስ ተነሳሽነት አለመሥራታችንም አስተዋጽኦ አለው፡፡ በዓላትን አሳበን እየሮጥን እንደምናደርገው ሁሉ ለከተሞቻችን ፅዳት የመሮጥ ባህል ቋሚ ፕሮግራም ወጥቶ በተደራጀና በተጠና መልኩ ለከተሞቻችን ፅዳት ለመሥራት እየሮጥንም ቢሆን የምንመክርበትን መንገድ እንፍጠር፡፡
ይኼንን ኃላፊነት የሚሸከሙ ጎበዞች ቢያንስ በየመንደራችን ለፅዳት እንሩጥ የሚል መፈክር እንዲኖረን፣ አንድ አካል ይህንን ኃላፊነት ወስዶ ይሥራ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ከተማችን የተስተካከለ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት እንዲኖራት አንዳንድ በዓላት ከመሪ መፈክራቸው ጎን ከተማን ማፅዳት አጀንዳቸው አድርገው ቢሠሩም ለውጡን ለማምጣት ይረዳልና ለከተማ ፅዳትም እንሩጥ፡፡ አስተዳደሩም የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቱን ያዘምን፡፡