- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም ያብራራሉ
- በሶማሊያና በኦሮሚያ ክልሎች ስለተነሳው የድንበር ግጭት ያነሳሉ
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቡዕ መጋቢት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ያቀርባሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግሥታቸው የሥራ አፈጻጸም በየዘርፉ ምን ይመስል እንደነበር፣ የወደፊት አቅጣጫዎችን፣ ሊጠናቀቅ አንድ ወር ያህል ስለቀረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸምና ያስገኛቸው ውጤቶች ሪፖርት እንደሚያቀርቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ድንበሮች ላይ እየታየ ስላለው ግጭት ማብራሪያ እንደሚሰጡ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በጥር ወር መጨረሻ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ድንበሮች ላይ የተነሳው ግጭት አሳሳቢ እንደሆነ ገልጸው፣ በሁለቱም ክልሎች ውስጥ የሚገኙ የበታች አመራሮችን ተጠያቂ ማድረጋቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ከሳምንት በፊት የኦሮሚያ ክልላዊ ምክር ቤት (ጨፌ) በዚሁ የድንበር ግጭት ላይ ተወያይቶ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታና የክልሉ ፖሊስ በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች ደኅንነት እንዲጠብቅ ውሳኔ ማሳለፉን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሪፖርት በጠዋት ፕሮግራም የሚያዳምጠው ፓርላማው፣ ከቀትር በኋላ ውሎው ደግሞ የጂቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኡመር ጊሌ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያደርጉትን ንግግር ያዳምጣል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ንግግራቸውን የሚያደርጉት ለሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኡመር ጊሌ በኢትዮጵያና በጂቡቲ መካከል ስለተፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ቁርኝትና ኢኮኖሚያዊ ውህደት አፅንኦት ሰጥተው ያብራራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በጂቡቲ ፓርላማ በመገኘት ለጂቡቲ ሕዝብ ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያና የጂቡቲ ሕዝቦች ወደፊት አንድ ሆነው ማየት ህልማቸው እንደሆነ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በንግግራቸው ማስታወቃቸው ሪፖርተር ከሥፍራው መዘገቡ ይታወሳል፡፡