Monday, May 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ70 ሺሕ በላይ ያልተፈቀዱ አምፖሎች በማስገባት የተጠረጠሩ ነጋዴዎች ተከሰሱ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

 ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የጋላፊ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ጋር በመመሳጠር፣ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ክልከላ የተጣለባቸውን ከ70 ሺሕ በላይ ባለ 60 እና 40 ዋት አምፖሎች በማስገባት የተጠረጠሩ ነጋዴዎችና ሠራተኞች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዓርብ መጋቢት 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ተከሳሾቹ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ፈቃድ የወሰዱት ፒፒማት (ምንጣፍ) ነበር፡፡ ነገር ግን ከጉምሩክ ሠራተኞች ጋር በመመሳጠርና የማስተላለፊያ ሰንሰለት በመፍጠር፣ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ያልተፈጸመባቸው 2,000 ኪሎ ግራም የአርጀንቲና ሥሪት ፈንድሻ፣ የቻይና ሥሪት 22,800 ጥንድ የአዋቂ ሴት ቱታዎችና ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ክልከላ የተጣለባቸው 593 ካርቶን (59,300) ባለ 60 ዋትና አሥር ካርቶን (10,000) ባለ 40 ዋት አምፖሎች ማስገባታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

ተከሳቹ አቶ ከድር ሁሴን (ሾፌር)፣ አቶ ይርሳው የሺወንድም (ያልተያዘ)፣ አቶ አህመድ ይሳቅ (ያልተያዘ) እና አቶ አህመድ አያሌው (የጉምሩክ ሠራተኛ) ሲሆኑ፣ ድርጊቱን የፈጸሙት አቶ አህመድ ቀደም ብሎ የጉምሩክ ሠራተኛ መሆኑን እንደ መሣሪያ በመጠቀምና በሁሉም የጉምሩክ መተላለፊያ መስመሮች የወንጀል ቡድን ሰንሰለት በመመሥረት መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ባልተያዘው ተከሳሽ በአቶ አህመድ ይሳቅ ስም በተመዘገበ ዲክላራሲዮን የትራንዚት ፈቃድ በመጠቀም የወንጀል ድርጊቱን መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡ በሾፌርነት የተሳተፈው አቶ ከድር ሁሴን የተባለው ተከሳሽም አቶ ይርሳውና አቶ አህመድ የተባሉት ተከሳሾች የሰጡትን  ተልዕኮ ለመፈጸም የተጠቀሱትን ዕቃዎች በማጓጓዝ ላይ እያለ በቁጥጥር ሥር መዋሉንም ዕቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ በጋላፊ የመንግሥት ሥራን ለሚሠራው አቶ ዮሴፍ ብርሃኔ ለሚባል ግለሰብ 100,000 ብር ጉቦ መስጠታቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡

ፍርድ ቤቱ ክሱን ካነበበላቸው በኋላ የዋስትና መብታቸው እንዲፈቀድላቸው አቶ ከድርና አቶ አህመድ ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ከአገር እንዳይወጡ ለብሔራዊ ኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ እንዲጻፍ ትዕዛዝ ሰጥቶ አቶ ከድር በ35,000 እና አቶ አህመድ በ60,000 ብር ዋስ እንዲለቀቁ ፈቅዷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች