Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አየር መንገድ በ100 ሚሊዮን ዶላር ያስገነባውን የጥገና ማዕከል ሊያስመርቅ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያስገነባውን አዲስ የጥገና ማዕከል በመጪው ወር እንደሚያስመርቅ አስታወቀ፡፡

አየር መንገዱ ከሚያዝያ 3 እስከ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ዓመታዊ የሥልጠና ሲምፖዚየም አስተናጋጅ መሆኑን አስመልክቶ የአየር መንገዱ ከፍተኛ አመራሮች ማክሰኞ መጋቢት 5 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ አየር መንገዱ በ100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያስገነባው ዘመናዊ የጥገና ማዕከል ሲምፖዚየሙ በሚካሄድበት ወቅት እንደሚመረቅ ገልጸዋል፡፡

የጥገና ማዕከሉ ሁለት የአውሮፕላን መጠገኛ ሃንጋሮች እያንዳንዳቸው 8,000 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው ናቸው፡፡ አንደኛው የጥገና ሃንጋር ለአውሮፕላን አካላት ጥገና የሚያገለግል ሲሆን፣ ሁለተኛው ሃንጋር ለአውሮፕላን ቀለም ቅብ ሥራ የሚውል ነው፡፡ የጥገና ሃንጋሮቹ እንደ ቦይንግ ቢ747 እና 777 ያሉ ግዙፍ አውሮፕላኖችን ማስተናገድ የሚችሉ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የሃንጋሮቹ ግንባታ የሚያካሄደው ኢቪክ ኢንተርናሽናል የተባለው የቻይና ኩባንያ ነው፡፡ ግንባታው የተጀመረው በሰኔ 2006 ዓ.ም. ነበር፡፡ የገንዘብ ምንጩ የቻይና ኤግዚም ባንክ ነው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጸሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም እንደተናገሩት፣ የአየር መንገዱ የጥገና ማዕከል በየጊዜው ሰፊ የማስፋፊያ ሥራ አካሂዷል፡፡ አዲስ የተገነቡት ሃንጋሮች ማዕከሉ ለአየር መንገዱ አውሮፕላኖችና ለሌሎች አየር መንገዶች የሚሰጠውን የአውሮፕላን ጥገና አገልግሎት አቅም በከፍተኛ መጠን ያሳድገዋል፡፡

የዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን የሥልጠና ሲምፖዚየም ከ500 በላይ የድርጅቱ ተወካዮች፣ የአቪዬሽን ሥልጠና ተቋማት ኃላፊዎች፣ አውሮፕላንና የአውሮፕላን ሞተር አምራች ኩባንያዎች ተወካዮች፣ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣናት፣ የኤርፖርት አስተዳደር ድርጅቶች፣ የቱሪዝም ድርጅቶችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚካፈሉበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በአፍሪካ ሲምፖዚየሙ ሲዘጋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የገለጹት አቶ ተወልደ፣ አዲሱን የጥገና ማዕከል ለማስመረቅና ጥገና የማዕከሉን አቅም ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አየር መንገዱ ግዙፍና ዘመናዊ የሆነ የካርጎ ተርሚናል በማስገንባት ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ በሰኔ 2009 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ በሚካሄው የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የካርጎ ጉባዔ ላይ እንደሚመረቅ ገልጸዋል፡፡  

አየር መንገዱ በ100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የአቪዬሽን አካዳሚ ገንብቶ ማስመረቁን ከራሱ አልፎ በርካታ የአፍሪካ አየር መንገዶች አብራሪዎች የአውሮፕላን ጥገና ቴክኒሽያኖችንና ኢንጂነሮች፣ የበረራ አስተናጋጆችንና የማርኬቲንግ ባለሙያዎችን የማሠልጠን አቅም እንዳለው ገልጸው፣ የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የሥልጠና ሲምፖዚየም የአቪዬሽን አካዳሚው የደረሰበትን ደረጃና ብቃት ለዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ማኅበረሰብ ለማስጎብኘት መልካም ዕድል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹የአፍሪካ አገሮች ይህንን ዘመናዊ የሥልጠና መሣሪያዎች የተገጠሙለትን ትልቅ የማሠልጠኛ ተቋም ሊጠቀሙበት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

አየር መንገዱ ዘመናዊ የምግብ ማደራጃ ማዕከል ገንብቶ በቅርቡ ያስመረቀ ሲሆን፣ 370 የመኝታ ክፍሎች ያሉት ባለአራት ኮከብ ሆቴል ግንባታ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ አየር መንገዱ ለማስፋፊያ ፕሮጀክቶቹ 500 ሚሊዮን ዶላር፣ ለዘመናዊ አውሮፕላኖች ግዢ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ማውጣቱ ተገልጿል፡፡

የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የሥልጠና ሲምፖዚየም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ፣ ለሌሎች አየር መንገዶች የሚሰጣቸውን የተለያዩ አገልግሎቶች ለማስጎብኘትና የአገሪቱን የቱሪዝም ዕምቅ ሀብት ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ተነግሯል፡፡  

በተያያዘ ዜና የበረራ አድማሱን በማስፋት ላይ የሚገኘው አየር መንገዱ በመጋቢት ወር መጨረሻ ወደ ቪክቶሪያ ፎልስ ዚምባብዌ፣ አንታናናሪቮ ማዳጋስካርና ኦስሎ ኖርዌይ አዲስ በረራዎች እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም አየር መንገዱ በቅርቡ ወደ ቼንዱ ቻይናና ጃካርታ ኢንዶኔዥያ አዳዲስ በረራዎች እንደሚጀምር፣ አቋርጦት የነበረውን የሲንጋፑር በረራ እንደ አዲስ እንደሚጀምር ታውቋል፡፡

አየር መንገዱ ወደ ቻይና እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ በረራ በመጀመር ከአፍሪካ ቀዳሚ አየር መንገድ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ አራት የቻይና ከተሞች (ቤዥንግ፣ ቫንጋይ፣ ሆንግ ኮንግና ጓንዢ) በሳምንት 28 በረራዎች ያደርጋል፡፡ በሳምንት 4,000 ያህል ቻይናዊያን በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በኩል ወደ ተለያዩ አገሮች የሚጓዙ በመሆኑ፣ አየር መንገዱ ቻይናዊያን የበረራ አስተናጋጆች ከመቅጠሩም በላይ ሠራተኞቹን የቻይና ቋንቋ (ማንዳሪን) እያሠለጠነ ይገኛል፡፡ አየር መንገዱ በሚያስገነባው ሆቴል ውስጥም ከአፍሪካ ትልቁ የቻይና ምግብ ቤት በመገንባት ላይ ነው፡፡     

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትም ሠራተኞችን ከቻይና ኤምባሲ ጋር በመተባበር ቋንቋ በማስተማር ላይ ሲሆን፣ በኤርፖርት ውስጥም በቻይና ቋንቋ የተጻፉ አመልካቾች እንደሚሰቀሉ ታውቋል፡፡ በየዓመቱ ከ120 ሚሊዮን በላይ ቻይናዊያን ቱሪስቶች የተለያዩ አገሮችን እንደሚጎበኙ የተናገሩት አቶ ተወልደ፣ እስካሁን ቻይናዊያን በአብዛኛው ወደ አፍሪካ ለሥራ እንደሚመጡ ጠቁመው ወደፊት ግን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የቻይና ቱሪስቶች ወደ አፍሪካ ለጉብኝት ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ ከዚህም ገበያ ለመጠቀም አየር መንገዱ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች