በውጤቱ ሳቢያ ስድስት ድርጅቶች ቅሬታቸውን አቅርበዋል
የመንግሥት ግዥዎችና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በቀጣዩ ዓመት ለሚደረገው አገር አቀፍ የሕዝብ ቆጠራ አገልግሎት የሚውሉ 180 ሺሕ ታብሌት ኮምፒዩተሮችን ለመግዛት ባወጣው ጨረታ፣ ባክ ዩኤስና የቻይናው ሁዋዌ ኩባንያዎች ወደ ቀጣዩ ዙር እንዲያልፉ ወሰነ፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ በጨረታው ላይ ተሳትፈው የነበሩና ወደ ቀጣዩ ዙር አለማለፋቸው የተገለጸላቸው ስድስት ድርጅቶች ውጤቱን በመቃውም ቅሬታቸውን ለአገልግሎቱ አቅርበዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ዜድቲ፣ አይ-ላይፍ፣ ቴክኖ፣ ሲምቦ ሪሶርስ፣ ሌኖቮና መስቴክ አፍሪካ የተባሉት ድርጅቶች ይገኙበታል፡፡
‹‹በቀጣይ የሁሉንም ጉዳይ በተናጠል ተመልክተን ውሳኔያችንን እናሳውቃለን፤›› ሲሉ የአገልግሎቱ ኃላፊ አቶ ሰለሞን በትረ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ጂታይድ የተባለው ዘጠነኛ ድርጅት የቅድመ ግምገማውን ሳያልፍ መቅረቱም ታውቋል፡፡ ለመውደቁም ምክንያት ከሕጋዊነት ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል፡፡
አገልግሎቱ ባደረገው ውስን ጨረታ 18 ድርጅቶች ተጋብዘው የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ዘጠኙ ብቻ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
እንደ ሪፖርተር ምንጮች ይህ ሲሆን ጂታይድም አብሮ ተጋበዞ ነበረ፡፡ ነገር ግን በጂታይድ ስም ሰነድ ያስገባው ያልተጋበዘ የአገር ውስጥ ድርጅት ሆኖ በመገኘቱ ከጨረታው ሊሰረዝ ችሏል፡፡
ይህ ውጤት የመጀመሪያው የቴክኒክ ግምገማ ከተሰረዘ በኋላ የመጣ ነው፡፡ የተሰረዘውም የታብሌቶቹ ዝርዝር ዓይነት መሻሻል በማስፈለጉ እንደ ነበር ተገልጿል፡፡
መጀመሪያ በነበረው ጨረታ የታብሌቶቹ ባትሪ ዓይነት ተቀያሪ እንዲሆኑ ቢፈለግም፣ ነገር ግን ይኼ ተጫራች የሚጋብዝ ሆኖ አልተገኘም፡፡ በዚህም ምክንያት ጨረታው ሊደገም ችሏል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ምንጮች ጨረታው ለመሰረዙ ሌሎች ምክንያቶችን ያነሳሉ፡፡ የመጀመሪያው ጨረታ ከተደረገ በኋላ የተጫራቾች የቴክኒክ ሰነድ ውጤት በተጫራቾች መገኘቱን እንደ ምክንያት ይገልጻሉ፡፡
የጨረታው ግምገማ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ከመረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ በተወጣጡ ባለሙያዎች ነው የተደረገው፡፡
ታብሌት ኮምፒውተሮቹ በግንቦት 2009 ዓ.ም. ግዣቸው ተጠናቆ ይቀርባሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ በተፈጠረው የጨረታ መዘግየት አቅርቦቱ በአንድ ወር ተራዝሟል፡፡
የሕዝብ ቆጠራውን የሚያካሂደው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ለሕዝብ ቆጠራው በአጠቃላይ ወደ ሦስት ቢሊዮን ብር መድቧል፡፡ ታብሌቶቹ ደግሞ እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ያስወጣሉ ተብሏል፡፡
ግዥው ከተፈጸመ በኋላ ታብሌቶቹ በአውሮፕላን ተጓጉዘው የሚገቡ ሲሆን፣ የሕዝብ ቆጠራው ከተደረገ በኋላ ደግሞ ለሌሎች ተመሳሳይ ቆጠራዎች ይውላሉ፡፡
ከአሁን ቀደም ኤጀንሲው ለዋናው የሕዝብ ቆጠራ ዝግጅት እንዲረዳው የሙከራ ቆጠራ ሲያደርግ፣ በዚህም 220 የሚሆኑ የተመረጡ ቦታዎች በታብሌት ኮምፒዩተሮች የታገዘ ቆጠራ ተደርጎላቸዋል፡፡
በኅዳር 2010 ዓ.ም. ይደረጋል ተብሎ ለሚጠበቀው ብሔራዊ ቆጠራ ኮሚሽን ከአሁን ቀደም ተቋቁሟል፡፡ አገሪቱ ከዚህ በፊት የመጨረሻውንና ሦስተኛውን ቆጠራ በ1999 ዓ.ም. አድርጋለች፡፡ በዚህም ቆጠራ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 73.8 ሚሊዮን መድረሱ ይታወሳል፡፡ አሁን ባለው መረጃ መሠረት ደግሞ 100 ሚሊዮን ይጠጋል እየተባለ ነው፡፡