መንግሥት የሞጆ ደረቅ ወደብን የአገሪቱ የሎጂስቲክስ ማዕከል ለማድረግ ለነደፈው ዕቅድ ማስፈጸሚያ፣ የዓለም ባንክ 150 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለመስጠት ተስማማ፡፡
ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 130 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው ሞጆ ደረቅ ወደብ የአገሪቱ የሎጅስቲክስ ማዕከል ለሚያደርጉ ግንባታዎች፣ አሥር ሚሊዮን ዶላር ለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አውታሮች ግንባታና ቀሪው አሥር ሚሊዮን ዶላር ለሎጂስቲክስ ዘርፍ ተዋናዮች አቅም ግንባታ ሥራዎች ይውላል፡፡
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ተፈራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከዓለም ባንክ ጋር ሲካሄድ የቆየው የብድር ድርድር ተጠናቋል፡፡
‹‹የቀረው የዓለም ባንክ ቦርድ ብድሩን ማፅደቅ ብቻ ነው፤›› ሲሉ አቶ መስፍን የኢንተርፕራይዙን ቀጣይ ትኩረት ሞጆ ደረቅ ወደብን የሎጂስቲክስ ማዕከል ማድረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኢንተርፕራይዙ የዓለም ባንክ በሚፈቅደው ብድር ሞጆ ደረቅ ወደብን አሁን ካለበት 60 ሔክታር መሬት ይዞታ ወደ 140 ሔክታር ለማስፋፋት አቅዷል፡፡
ይህ ግንባታ እስካሁን ሞጆ ደረቅ ወደብ ትኩረቱን አድርጎ ከቆየው ገቢ ንግድ ወደ ወጪ ንግድ ማድረግ ላይም እንዲያተኩር ያደርገዋል ብለዋል፡፡
በዚህም የማቀዝቀዣ ማሽኖች በመትከል አትክልት፣ ፍራፍሬና የሥጋ ውጤቶችን በባቡርና በመርከብ ወደ ውጭ ለማጓጓዝ ታቅዷል፡፡
ተጨማሪ ተርሚናሎችንና መጋዘኖችን በመገንባትም ብትን ዕቃዎችን፣ ለአብነትም ማዳበሪያና የመሳሰሉትን በጥቅል አገር ውስጥ በማስገባት በሞጆ ሎጂስቲክስ ማዕከል በማሸግ ወደተለያዩ አገሮች ለማጓጓዝም ታቅዷል፡፡
‹‹ብረት ወደ ደረቅ ወደብ አናስገባም ነበር፡፡ በአዲሱ ፕሮጀክት ብረት በሎጂስቲክስ ማዕከሉ ይስተናገዳል፤›› ሲሉ አቶ መስፍን ተግባራዊ የሚደረገው ፕሮጀክት ሞጆ ደረቅ ወደብን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀይር አስረድተዋል፡፡
ሞጆ ደረቅ ወደብ ደቡብ በምሥራቅ አቅጣጫ ከአዲስ አበባ በነባሩ መንገድ 76 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ይኼ ግዙፍ ፕሮጀክት በመታቀዱ ለከተማውና ለአገሪቷ ኢኮኖሚ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ተብሏል፡፡
በቅርቡ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የባቡር ሐዲድ ግንባታ ፕሮጀክት፣ ቀደም ሲል ባይካተትም የባቡር ሐዲዱ የግድ በደረቅ ወደቡ ውስጥ ማለፍ ስላለበት ሁለት ኪሎ ሜትር መስመር በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ አቶ መስፍን እንዳሉት በደረቅ ወደቡ ቅጥር ግቢ ውስጥ ተጨማሪ የባቡር ሐዲድ ግንባታዎች እየተካሄዱ ነው፡፡ የሥራ አፈጻጸሙም 50 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል፡፡
መንግሥት ከሞጆ ደረቅ ወደብ በተጨማሪ በአገሪቱ ሰባት ደረቅ ወደቦችን ገንብቷል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ኢንተርፕራይዙ ገላን ተርሚናል ሞጆ ደረቅ ወደብንና የመርከበኞች ማሠልጠኛ ተቋም ያሉበትን ደረጃ ለመገናኛ ብዙኃን አስጎብኝቷል፡፡
በዚህ ወቅት የኢንተርፕራይዙ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደሳለኝ ገብረ ሕይወት እንደተናገሩት፣ አሁን ያሉትን ሰባት ደረቅ ወደቦች ከማስፋፋት ጎን ለጎን በኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ ደረቅ ወደቦች ይገነባሉ፡፡
‹‹በደቡብ ክልል ሐዋሳ፣ በአማራ ክልል ወረታ አካባቢ ደረቅ ወደቦች ለመገንባት ጥናት እየተካሄደ ነው፤›› ሲሉ አቶ ደሳለኝ ዕቅዳቸውን ገልጸዋል፡፡