Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢንቨስተሮች አዲሱን የልማት ባንክ የብድር መመርያ ተቃወሙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ በሰፋፊ እርሻ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ኢንቨስተሮች፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በቅርቡ ያወጣው የብድር አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ማንዋል አሠሪ አይደለም በማለት ተቃወሙ፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቅዳሜ መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በሒልተን አዲስ  በጠራው ስብሰባ፣ 200 ከሚጠጉ የሰፋፊ እርሻዎችና የኢንዱስትሪ ኢንቨስተሮች ጋር መክሯል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታሁን ናና በመሩት ስብሰባ ባንኩ በበጀት ዓመቱ ያከናወናቸውን ሥራዎች ሪፖርት ከማቅረቡ በተጨማሪ፣ በጥር 2009 ዓ.ም. ባወጣው የብድር አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ማንዋል ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

በውይይቱ ላይ በቀረበው የብድር አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ማንዋል ላይ ኢንቨስተሮቹ ከፍተኛ ተቃውሞ ማቅረባቸው ታውቋል፡፡ የተቃውሞው ማጠንጠኛ ሦስት ዋነኛ ጉዳዮች ናቸው፡፡

የመጀመሪያው የፖሊሲ፣ ሁለተኛው የአስተዳደርና ሦስተኛው ደግሞ በሥራ ክንውን ወቅት የሚያጋጥሙ ጉዳዮች የሚያሠራ ካለመሆናቸው ጋር የተያያዘ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የብድር ፖሊሲ አለው፡፡ በዚህ የብድር ፖሊሲ መሠረት አልሚዎች ከባንኩ ጋር የብድር ውል ፈርመው ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ፣ የፖሊሲ ለውጥ እየተደረገ አስቸጋሪ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑ በውይይቱ ወቅት ተነስቷል፡፡

የጋምቤላ ክልል እርሻ ባለሀብቶች የኅብረት ሥራ ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን ኃይሉ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባንኩ በሚያደርገው የፖሊሲ ለውጥ ሥራ ማካሄድ አልተቻለም፡፡ አቶ ሰለሞን ለአብነት ያህል እንደገለጹት ውል ሲገባ 8.8  በመቶ የነበረው የባንኩ ወለድ፣ ሥራ ውስጥ ከተገባ በኋላ 12.5 በመቶ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ውል ተገብቶ ከጋምቤላ ክልል መሬት ሲወሰድ የአንድ ሔክታር መሬት ሊዝ ዋጋ 30 ብር ነበር፡፡ አሁን ግን 110 ብር በሔክታር ገብቷል፡፡ ‹‹በዚህ ዓይነት የፖሊሲ ለውጦች እንዴት የእርሻ ሥራ ይካሄዳል?›› በማለት አቶ ሰለሞን ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአዲሱ የብድር መመርያ አንድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባንኩን ተጨማሪ ብድር በሚጠይቅበት ወቅት፣ የኩባንያው ባለድርሻ የሆነ ግለሰብ በኩባንያው ካለው ድርሻ ውጪ ሌላ የማስያዣ ዋስትና እንዲያቀርብ ይጠየቃል፡፡

ይኼን አሠራር በማመልከት ኢንቨስተሮቹ ባቀረቡት ቅሬታ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የራሱ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ሆኖ ሳለ፣ ተጨማሪ ዋስትና መጠየቅ ሕጋዊ አሠራር አይደለም በማለት ሊሻሻል እንደሚገባው ጠይቀዋል፡፡

ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከዚህ በኋላ ገንዘብ በቀጥታ ለኢንቨስተር አልሰጥም ማለቱ ነው፡፡

ኢንቨስተሮቹ ባንኩ የኢንቨስተሮችን ፕሮጀክት ለምን ያስተዳድራል? ፕሮጀክቱ ቢከስር ተጠያቂው ማነው? የሚል ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ አዲሱ የብድር ማንዋል ለተበዳሪው አካል ግዥ የሚፈጽመው ባንኩ እንደሆነ ይገልጻል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አንድ ኢንቨስተር ቀደም ሲል የራሱን ድርሻ ኢንቨስት ካደረገ ባንኩ ያፈሰሰውን መዋዕለ ንዋይ በዋስትና መልክ በመያዝ ብድር ይለቃል፡፡ በአዲሱ አሠራር ግን በመሬት ላይ ለፈሰሰ መዋዕለ ንዋይ የገቡ ማሽኖች ቢኖሩም ብድር እንደማይለቅ፣ ይልቁኑም ሌላ ተጨማሪ ገንዘብ በዝግ አካውንት ውስጥ ማስገባት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

ታማኝ መሆን ያለበት ደፍሮ መዋለ ንዋይ ያፈሰሰ ሆኖ ሳለ፣ የፈሰሰው መዋዕለ ንዋይ የብድር ዋስትና አይሆንም መባሉ አግባብ እንዳልሆነ አቶ ሰለሞን ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አሠራርን የተቃወሙ ኢንቨስተሮች ይህ አዲስ የብድር አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ማንዋል እንዲሻሻል ጠይቀዋል፡፡

በወቅቱ ስብሰባውን የመሩት አቶ ጌታሁን የቀረበውን ቅሬታ ከሰሙ በኋላ ባንኩ መፍታት ያለበትን ችግር ለመፍታት እንደሚሠራ፣ ከባንኩ አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ከመንግሥት ጋር እንደሚነጋገር ማስረዳታቸውን ስብሰባውን የተከታተሉ ኢንቨስተሮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከሳምንት በፊት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ በሰፋፊ እርሻ ሥራዎች የተሰማሩ ኢንቨስተሮችን ሰብስበው አነጋግረው ነበር፡፡

በዚህ ስብሰባ ለአገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃ የሚያቀርቡ ተዋናዮች ላይ የተፈጠሩ የመሬት ይዞታ፣ መልካም አስተዳደርና የብድር ችግሮች እንዲፈቱ አቅጣጫ ሰጥተው እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች