Friday, May 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ስንፍና መድኃኒት የታጣለት የአገር በሽታ ሆኗል!

አመርቂ ውጤት የሚያስመዘግቡ ሥራዎች ይበልጥ እንዲጠናከሩና የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖራቸው ይበረታታሉ፡፡ ለአገር ትልቅ ጠቀሜታ ያላቸው ውጤታማ ሥራዎች በተያዘላቸው ዕቅድ መሠረት የሚከናወኑት ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል ስለሚደረግባቸው ነው፡፡ ውጤታማ ሥራዎችን የሚመሩ ደግሞ የሙያ ብቃትን ከሥነ ምግባር ጋር ያዋሀዱና ይኼ ነው የሚባል ጥያቄ ስለማይነሳባቸው፣ ሁልጊዜም በስኬት መሰላል ላይ ይረማመዳሉ፡፡ በተቃራኒው ያሉ ግን የረባ አቅም የሌላቸው፣ በሙያ ሥነ ምግባራቸውም ሆነ በጥረታቸው የማይታወቁ ናቸው፡፡ የሚመሩትን ተቋምም ሆነ ሙያተኞችን በአግባቡ ካለማወቃቸውም በላይ እንኳን አቅደው ለማስፈጸም፣ ታታሪዎች የሚሠሩትን ሲያበላሹ ይውላሉ፡፡ በስንፍና፣ በግዴለሽነትና በሙስና የናወዙ በመሆናቸው ከዘመኑ ጋር እኩል ለመራመድ ይቸግራቸዋል፡፡ አቅደው በሠሩት ሥራ ውጤት ከማሳየት ይልቅ ‹‹አይሆንም›› ማለት ይቀላቸዋል፡፡ እነሱ የሚያውቁት አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ስንፍናቸውን ለመሸፈን ሰበብ መደርደር፡፡ በድርጅትና በኔትወርክ ውስጥ መሸጎጥ፡፡ ከሥራ ይልቅ መፈክር ማነብነብ፡፡ በእነሱ የተነሳ ሕዝብ ምሬት ውስጥ ይገባና  አገርን ችግር ውስጥ የሚከት ፈተና ይፈጠራል፡፡ ጦሱ ለንፁኃን ይተርፋል፡፡

በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ልዩ ልዩ ሕጎች ይወጣሉ፡፡ እነዚህን ሕጎች በአግባቡ የሚያስፈጽም እየጠፋ በሕዝብ ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት ይደርሳል፡፡ በደረሰው ጉዳት ተጠያቂ ስለማይኖር ስንፍና የአገር በሽታ ይሆናል፡፡ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ሲመዘበር፣ መሬት በጠራራ ፀሐይ እየተወረረ ሲቸበቸብ፣ የመንግሥት ግዥና ኮንትራቶች በሕገወጥ መንገድ ሲፈጸሙ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ከጥራት ደረጃ በታች ሲሠሩ፣ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ያለከልካይ ገበያውን ሲወሩ፣ ግብር ማጭበርበርና መሰወር ፋሽን ሲሆን፣ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን በጉቦ መስጠት ግዴታ ሲመስል፣ ፍትሕ በገንዘብ ሲሸቀጥ፣ የመንግሥት ሥልጣን የሕገወጥ ሀብት ማፍሪያ ሲሆን፣ ወዘተ ሃይ ባይ ሲጠፋ ከስንፍና በላይ ምን ሊጠቀስ ይችላል? ግልጽነትና ተጠያቂነት ማስፈን ሲያቅት ከስንፍና በላይ ምን ስያሜ ይሰጠዋል? ሕዝብን የሚያማርሩና አገርን የሚያሰቅቁ ድርጊቶችን በአግባቡ መቆጣጠርና ፈጣን ዕርምጃ መውሰድ ሲገባ ዝም ተብሎ ይቆይና የዘመቻ ሥራ ይጀመራል፡፡ ዘመቻ ደግሞ በጥድፊያና በሁካታ ስለሚታጀብ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት አይጠቅምም፡፡ ብዙ ጉዳት ሲያደርስ ነው የሚታወቀው፡፡ የሰነፎች ተግባር ነው፡፡

መንግሥትን የሚመራው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ያለፉትን 15 ዓመታት ስንክሳሮች በ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› አስተካክላለሁ በማለት ከላይ እስከ ታች ሲገማገም ከርሟል፡፡ ተሃድሶው ጓዙን ጠቅልሎም መንግሥት መዋቅር ውስጥ ገብቷል፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎም ወደ ኅብረተሰቡ ውስጥ እየዘለቀ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ መንስዔው በአገሪቱ ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል የዘለቀው ደም አፋሳሽ ነውጥ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ችግርን ከሥር ከመሠረቱ የመመልከት አዝማሚያ አለ ወይ? ተብሎ ጥያቄ ሲቀርብ፣ መልሱ ግን በጉልህ የሚታይ አይደለም ነው፡፡ እዚህም እዚያም መጠነኛ የማረጋጋት ዕርምጃዎች ቢወሰዱም ደፈር ተብሎ በላይኛው አካል አካባቢ  የሚወሰድ ዕርምጃ የለም፡፡ በከፍተኛ፣ በመካከለኛና በዝቅተኛ ደረጃ ከኃላፊነት ማንሳትና ሽግሽግ ቢታይም፣ በላይኛው መዋቅር ላይ ጨከን ያለ ዕርምጃ መውሰድ አልተቻለም፡፡ በመካከለኛውና በዝቅተኛው እርከን የተወሰዱ ዕርምጃዎችም ቢሆኑ ያን ያህል የሚያረኩ አይደሉም፡፡ ይልቁንም በጥገናዊ ለውጥ አለባብሶ ለማለፍ የሚደረግ ሙከራ መስሏል፡፡ ዘለቄታዊ ሰላምን ለማስፈን የሚረዱ አሳማኝ ዕርምጃዎች ከመውሰድ ይልቅ መልመጥመጥ ይታያል፡፡ የሰነፎች ሥራ፡፡

በመልካም አስተዳደር፣ በሙስና፣ በፍትሕ ዕጦትና በመሳሰሉት የሚታየው የአገር ችግር መሠረታዊ ለውጥ ያስፈልገዋል ሲባል መጠራጠር መዘዝ ያመጣል፡፡ መንግሥት ለራሱ ሲል ሰነፎችንና አስተሳሰባቸውን ወደ ጎን በማለት ለብቃትና ለዘመናዊ አሠራሮች በሩን ክፍት ማድረግ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ መጀመሪያ በአገር ውስጥ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያግዙ በዓይን የሚታዩ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ ደፋር መሆን ያስፈልገዋል፡፡ ተቃርኖ ካላቸው የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ሰላማዊ ውይይቱና ድርድሩ በሕዝብ ፍላጎት መሠረት እንዲከናወን በማድረግ፣ ለፖለቲካዊ ምኅዳሩ መከፈት ጥርጊያውን ማመቻቸት ይገባል፡፡ ዴሞክራሲ የተለያዩ ሐሳቦችና ፍላጎቶች በነፃነት የሚስተናገዱበት ዓውድ መፍጠሪያ እንጂ፣ አሁን እንደሚታየው የተዘጋጋና አስከፊ አዙሪት መሆን የለበትም፡፡ ሕግ በአግባቡ የሚከበርበትና ሁሉም ዜጋ በነፃነት የሚኖርበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚፈጠረው በተዘጋጋ ምኅዳር ውስጥ አይደለም፡፡ ሰነፎች እያጭበረበሩ የሚከብሩበትና አገር የሚያበላሹበት ሥርዓት ለአገር አይጠቅምም፡፡ አምባገነንነት ዘመኑንም ሆነ ትውልዱን አይመጥንም፡፡ በሕዝብ ይሁንታ የሚገኝ ሥልጣን ለአገር ዘለቄታ ሰላምና ለሕዝብ ብልፅግና ይበጃል፡፡ ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ ሲሆን የሕዝብ እርካታ ይፈጠራል፡፡ ዴሞክራሲ እያነበነቡ ፀረ ዴሞክራሲ ተግባር ማከናወን ጊዜ ያለፈበት ነው፡፡ ለውጥን እየሸሹ እግርና እጅን አሳስሮ መቀመጥ ለአገር ጠንቅ የሚሆን ስንፍና ነው፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አልድን ያለው በሽታ ስንፍና ነው፡፡ ስህተትን በስህተት ለማረም እየተሞከረ ከማይወጡት አዘቅት ውስጥ መግባት ልማድ ሆኗል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰጥቶ መቀበል መርህ አማካይነት ለመነጋገርም ሆነ ለመደራደር ከመሞከር ይልቅ፣ በቅድመ ሁኔታዎች የታጠሩ እንቶ ፈንቶዎችን በመደርደር ጊዜ ማባከን የተለመደ ተግባራቸው ነው፡፡ ከተቃራኒ ወገን ጋር የሚደረግ ንግግርም ሆነ ድርድር ብልጠት ይፈልጋል፡፡ ይኼ ብልጠት ግጭትን በማስወገድ የጋራ ተጠቃሚነትን ያስገኛል፡፡ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ የትርፍ ሰዓት ሥራ ይመስል የትም ተኝተው ይከርሙና የሚነጋገሩበት ጉዳይ በቅጡ ሳይገባቸው ከመግባባት ይልቅ ለመጣላት መቸኮል የዓመታት የአገር በሽታ ነው፡፡ የተናጠል ትግሉ ሲከብዳቸው ልዩነታቸውን አቻችለው ተጠናክረው መውጣት ሲገባቸው፣ በማይረቡ ጉዳዮች ላይ ይነታረካሉ፡፡ አንዳንዶቹ ከዘመኑ ጋር እኩል መራመድ ተስኗቸው ዛሬም የተረሱ አጀንዳዎች ላይ ተቸክለዋል፡፡ የባሰባቸው ደግሞ እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ሳይሠሩ ራሳቸውን ከመጠን በላይ አሳብጠው ሌሎችን  ይንቃሉ፡፡ በስንፍናቸው ምክንያት ብቻ የራሳቸውን አጀንዳ መቅረፅ ተስኗቸው የሌሎችን ዓላማ ተሸክመው የሚባዝኑም አሉ፡፡ እነዚህ በራሳቸው ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ሳያካሂዱ እንዴት አገር ለመምራት ያስባሉ? ግራ የተጋቡ፣ አቅመ ቢስና ቀቢፀ ተስፋ ሆነው መኖራቸው በራሱ የስንፍናቸውን ጣሪያ ያመላክታል፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡

ስንፍና የአገር በሽታ ለመሆኑ ሌላው ማሳያ ሰሞኑን ለበርካታ ዜጎች ሕልፈት ከሆነው የረጲ ቆሻሻ ማስወገጃ ጀምሮ በርካታ ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ አዋጅ በአግባቡ ቢሠራበትና ክፍተቶቹ ደግሞ በማሻሻያ ሕጎች ቢሞሉ፣ ሰው ሠራሽ ተራራ የሠራው ቆሻሻ ተንዶ ሕዝብ አይፈጅም ነበር፡፡ ቆሻሻ ሀብት ነው፡፡ ለኤሌክትሪክ ኃይል፣ ለማዳበሪያ ማምረቻ፣ ለፋብሪካ ጥሬ ዕቃ፣ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ነዳጅ፣ ወዘተ በመሆን በዘመናዊ መንገድ በርካታ የሥራ ዕድሎችን ይፈጥር ነበር፡፡ በአግባቡ ማስተዳደር ባለመቻሉ ግን ዜጎቻችንን ፈጀ፡፡ ሕግ ባለመከበሩ ብቻ በርካታ ጥፋቶች ይታያሉ፡፡ በአገሪቱ ውስጥ በዓመት በትንሹ ከሦስት ሺሕ በላይ ዜጎችን የሚፈጀው የትራፊክ አደጋን መቀነስ ለምን አልተቻለም? በየቦታው እየተከፈቱ የሚተው ጉድጓዶች እስከ መቼ ዜጎችን ይገድላሉ? አካለ ጎዶሎ ያደርጋሉ? በሰዎች ጤናና በአካባቢ ላይ ብክለት የሚያደርሱ በካይ ፋብሪካዎች በሕጉ መሠረት እንዲሠሩ ማድረግ ለምን ያቅታል? አድሎአዊነት፣ ኢፍትሐዊነት፣ ሙስና፣ ሕገወጥነትና የመሳሰሉት የአገር ጠላቶች ሕዝብ ላይ ሲፈነጩ የማያዳግም ዕርምጃ የማይወሰደው ለምንድነው? የሕግ የበላይነት አለ በሚባልባት አገር ውስጥ ሕጎች ባለመከበራቸው ብቻ በርካታ ሕገወጥ ድርጊቶች ሕዝብ ያማርራሉ፡፡ ቆፍጠንና ጠንከር ብሎ በሕገወጥነት ላይ የበላይነት መያዝ ሲቻል ቸልተኝነትና ደንታ ቢስነት ተበራክተዋል፡፡ ስንፍና መድኃኒት የታጣለት የአገር በሽታ ሆኗል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...

ያልነቃ ህሊና!

ከሽሮሜዳ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ነቀፋ አንሶላው፣ ትችት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...