Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቆሻሻ ክምር ተደርምሶ ያደረሰው አደጋ

የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ ያደረሰው አደጋ

ቀን:

እስከ ማክሰኞ ምሽት 72 ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል

  በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ውስጥ የሚገኘውና በተለምዶ ቆሼ ወይም ቄስ ሠፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ፣ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ መጋቢት 2 ቀን ከምሽቱ 1፡30 ላይ በተደረመሰው የቆሻሻ ክምር ሕይወታቸው ያለፈ ወገኖች ቁጥር 72 ደርሷል፡፡ ይህ ቁጥር እስከ ማክሰኞ ምሽት ድረስ የነበረውን የሞት መጠን የሚገልጽ ሲሆን፣ የሟቾች መጠን ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

      ለደረቅ ቆሻሻ መጣያ በተከለለው 37 ሔክታር ቦታ ላይ ተከምሮ የነበረው ቆሻሻ ከምድር ወደ ላይ ከ13 ሜትር በላይ ሲሆን፣ ከምድር ወደታች ጥልቀቱ ደግሞ 40 ሜትር ነው፡፡ አደጋው ከደረሰበት ዕለት ጀምሮ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ መጥቶ ሪፖርተር ማተሚያ ቤት እስገባበት ድረስ የማቾች ቁጥር 72 ደርሷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

      የቆሻሻ ክምሩ ባለበት አጠገብ የሚኖሩት ዜጎች ለጊዜው ምን ያህል እንደሆኑ ባይታወቅም፣ አደጋው የደረሰባቸው ወይም የተደረመሰባቸው ነዋሪዎች ግን በርካታ እንደሆኑ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ከአደጋው የተረፉ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ ወረዳው በተለየ ሁኔታ አደጋው በደረሰበት ቦታ ላይ ምን ያህል አባወራዎች ወይም ነዋሪዎች ይኖሩ እንደነበር በማጣራት ላይ መሆኑን ገልጾ፣ ሰሞኑን እንደሚያሳውቅ ተናግሯል፡፡

      በአካባቢው ሕጋዊ ሰነድ ያላቸው ከ15 በላይ ቤቶችና ቁጥራቸው ያልታወቁ የጨረቃ ቤቶች የአደጋው ሰለባ መሆናቸውን የሚናገሩት የአካባቢ ነዋሪዎች፣ አደጋው በምሽት በመድረሱና በአንድ ቤት እስከ ስምንት የሚደርሱ ተከራዮች የሚኖሩ በመሆናቸው የሟቾቹን ቁጥር በትክክል ማወቅ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው ቆሻሻ መጣል ከተጀመረ ከ50 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም፣ ሕጋዊና ሕጋዊ ያልሆኑ (ጨረቃ) ቤቶችን በመሥራት ከ20 ዓመታት በላይ እንደኖሩ የሚናገሩት ከአደጋው የተረፉ ነዋሪዎች፣ ሥጋታቸው አንድ ቀን ቆሻሻ ሊለቃቅም የመጣ አውሬ ልጆቻቸውን እንዳይነጥቃቸው እንጂ ቆሻሻ ተደርምሶ በአንድ ላይ ያጠፋናል የሚል እንዳልነበር የሚናገሩ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ለዓመታት የቆሻሻው ክምር አንድ ቀን ይናዳል በማለት አቤት ማለታቸውን የሚናገሩም አሉ፡፡

ቆሻሻው ከመደርመሱ አስቀድሞ የኤሌክትሪክ ፖል ፍንዳታ በመስማት ከቤታቸው ሲወጡ፣ የቆሻሻ ክምሩ ወደታች ሲናድ በመመልከታቸው በተቃራኒ አቅጣጫ ሮጠው መትረፋቸውን የሚናገሩት አቶ ኃይሌ በቀለ (የአባታቸው ስም ተቀይሯል) ከ20 ዓመታት በላይ በአካባቢው መኖራቸውን ተናግረው፣ ‹‹ልጆቻችንን ከቆሻሻና ከዝንብ ጋር ማሳደጋችን ሳያንስ መጨረሻችን በቆሻሻ መቀበር መሆኑ ያሳዝናል፤›› ብለዋል፡፡ የእሳቸው ቤተሰቦች በጊዜ ወደ ቤታቸው ሳይገቡ በመዘግየታቸው ቢተርፉም ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ እናቶችና አባቶች ከወለዷቸው ልጆች ጋር ቆሻሻ ተጭኗቸው ሕይወታቸው  እንዳለፈ እያነቡ ገልጸዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚናገሩት አደጋው መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ከመድረሱ አንድ ቀን በፊት አንዲት ላም በቆሻሻ ክምሩ አናት ላይ ወጥታ የበቀለውን ሳር በመጋጥ ላይ እያለች፣ የቆመችበት የቆሻሻ ክምር ተንዶ ይዟት ወርዷል፡፡  በእነሱ ግምት የከተማ አስተዳደሩ አስቀድሞ ዕርምጃ መውሰድ እንደነበረበት አመላካች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የወረዳው ኃላፊዎች መጋቢት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በአካባቢው ተገኝተው በተለይ ሰነድ አልባ (የጨረቃ) ቤቶችን ይለኩ እንደነበር አስታውሰው፣ ምናልባትም ይደረመሳል የሚል ጥርጣሬ ሳይኖራቸው እንደማይቀር አመላካች መሆኑን ነዋሪዎች አክለዋል፡፡

በተለምዶ ቆሼ የሚባለው ቦታ ከ50 ዓመታት በላይ በመቆየቱና በመሙላቱ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በቢሊዮን የሚቆጠር ብር መድቦ ሰንዳፋ የቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ መገንባቱን ነዋሪዎቹ አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን ከከተማ ወደ ሰንዳፋ የሚወሰደው ቆሻሻ በአካባቢው ነዋሪዎች በተነሳ ተቃውሞ በመቆሙ የከተማው ቆሻሻ ተመልሶ ወደ ቀድሞ ቦታው መድፋት ሲጀመር ከፍተኛ ሥጋት አድሮባቸው እንደነበር ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

የቀን ሥራም ሆነ ሌሎች የሥራ መስኮች በመሀል ከተማ በመሆናቸው ሙሉ ቀን ሲሠሩ ውለው አቅማቸው በሚፈቅደው መሠረት ወደ ተከራዩበት ቤት ከገቡ በኋላ፣  ወጣቶችና እናቶች በአደጋ ሕይወታቸው ማለፉን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ ከአደጋው የተረፉ ወገኖች ሌላ አደጋ እንዳይደርስባቸው መንግሥት አስቸኳይ ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

እስከ መጋቢት 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ መሞታቸው ከተረጋገጡት ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች ናቸው፡፡ በአካባቢው ከተከሰተው አደጋ የተረፉ ነዋሪዎች በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ወጣቶች ማዕከል የተጠለሉ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርና ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዕርዳታ እያደረጉላቸው መሆኑም ታውቋል፡፡

ሕይወታቸው ያለፈው ወገኖች በአዲስ አበባ በሚገኙ እምነት ተቋማት እንደየ እምነታቸው የቀብር ሥርዓታቸው መፈጸሙም ታውቋል፡፡ ነዋሪነታቸው በክልል የሆኑት ደግሞ አስከሬናቸው ወደየመጡበት ክልል መሸኘቱን ከንቲባ ድሪባ ኩማ ተናግረዋል፡፡ ከ13 ሜትር በላይ ከፍታና 40 ሜትር ጥልቀት ያለው የቆሻሻ ክምር የተደረመሰበት ምክንያት ገና እየተጣራ መሆኑን ከንቲባው አክለዋል፡፡ የሟቾች ቁጥር ግን ከተገኙት በላይ ይሆናል የሚል ግምት በመኖሩ ፍለጋው መቀጠሉም ታውቋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደግሞ አደጋው በደረሰ በአራተኛው ቀን መጋቢት 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ባደረገው መደበኛ ስብሰባው፣ ከረቡዕ መጋቢት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት ብሔራዊ የሐዘን ቀን እንዲሆን አውጇል፡፡ 

በታምሩ ጽጌና በዘመኑ ተናኘ

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአብዮቱ ያልተዘጉ ዶሴዎች

‹ዳኛው ማነው› ሒሳዊ ንባብ - ሐሳብና ምክንያታዊነት በዚያ ትውልድ...

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

በዚያን ሰሞን የሹክሹክታ ወሬ ደርቶ ነው የሰነበተው፡፡ የአገራችን ልጆች...