Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የአንዱ ጩኸት የሌላው ማብረጃ ባይሆን ምን ይውጠን ነበር?

እነሆ ጉዞ! ከወሎ ሠፈር ወደ ቄራ ነን። ዱር እንዳደረ እረኛ ፈረቃዋ አብቅቶ ጨረቃ በፀሐይ ተተክታለች። የሠርክ ሽር ጉዱን ሊከውን ነዋሪው ማልዷል። በወትሮ ታክሲ መያዣ ሥፍራ ግራ የሚያጋባ ትዕይንት ይተወናል። ወያሎች ሥምሪታቸውን ይናገራሉ። ተራ አስከባሪዎች የሠልፍ ሥነ ሥርዓት ይቆጣጠራሉ። ዓይናችን ታክሲ የሚባል ማየት ተስኖታል። ‹‹የት አሉና ነው ታክሲዎቹ ሠልፍ የምሠለፈው?›› መንገደኛው ይነጫነጫል። ‹‹ይመጣሉ ነዳጅ ሊቀዱ ተሠልፈው ነው። እናንተም ተሠልፋችሁ ጠብቁ። አይዟችሁ የታክሲ ሠልፍ ነው ሰላማዊ ሠልፍ አይደለም የምናሰልፋችሁ›› ይላል አንድ ቀልቃላ ወያላ። ሁኑ፣ ተናገሩ፣ ሥሩ ከተባሉት ውልፍት ማለት እያስከተለ ያለው ጣጣ ነዋሪን ስላሰለቸው ይመስላል በዝምታ ላይጓዝ በሠልፍ መስመር ውስጥ ይገተራል። ‹‹እነሆ በመጨረሻው ዘመን ነዳጅ በሌላው ዓለም ሲረክስ በኢትዮጵያ ጠፍቶ መኪኖች እንደ ታክሲዎች ሠልፍ ይጀምራሉ’ የሚል ተንቢት ተጽፎ ሳናበው ቀርተን ይሆን ጎበዝ? እስኪ እናጣራ!›› ብላ አንዲት ወይዘሮ በአካባቢዋ ያለውን ሰው በጨዋታዋ ታዝናናለች። ትንሽ እልፍ ብሎ ደግሞ ማልዶ የተከፈተ ሙዚቃ ቤት ጥዑም ዜማ ይልክልናል። ‹‹ተው ማነህ ተው ማነህ፣ የተኛውን ልቤን ትቀሰቅሳለህ።  መንደርተኛው ሁሉ እሳት ጫሪ ነው፣ ያንን ገል አደራ ሰው እንዳይነካው፤›› ስትል እንሰማለን ዘፋኟ።

‹‹አይ ግጥም! አይ ጥበብ! እኔ ምለው ለምንድነው ጥበብም እንደ ዴሞክራሲ አንድ ዘመን ላይ ብልጭ ብሎ የጠፋብን?›› ስትል አንዲት ሠልፈኛ ነገር ትለኩሳለች። ‹‹መቼ ጠፉብን እነሱ? እኛ ነን እንጂ የጠፋንባቸው። በሰው አገር ልክ የተሰፋ ርዕዮተ ዓለም ለእኛ ካልሆነ ስንል እየተደነቃቀፍን፣ መንግሥት ልማቱ ላይ ተባበሩኝ ሲል እኛ የመልሶ መገንባትን ጽንሰ ሐሳብ ሙዚቃው ውስጥ ሳይቀር ደንጉረን በሰው ወርቅ መድመቅ ስንጀምር ነው ነገሩ ሁሉ እንዳይሆን የሆነው፤›› ይላታል ከኋላ የተሠለፈ ጎልማሳ። ይኼ ጨዋታ ሳይገባዳድ ደግሞ እዚያ ማዶ ከሠልፉ ጫፍ አካባቢ ፌዘኛ ወጣቶች ‹‹መቆማችን ካልቀረ ለምን ብሔራዊ መዝሙር አታዘምሩንም? ተማሪ ብቻ ነው ባንዲራ መስቀል ያለበት ያለው ማን ነው? አይደል እንዴ ሰዎች? ሠልፉ ካልቀረልን የዜግነት ክብሩስ ለምን ይለፈን?›› ሲባባሉ ተራ አስከባሪዎቹ፣ ‹‹ለዛሬ አልተሳካላችሁም፤›› እያሉ ያፌዛሉ። የጎዳናው ምስቅልቅል ትዕይንት ውኃ የማይቋጥር መስሎ ወንዝ እየገደበ ታሪክ ያጽፋል። አይገረምም ግን?

ወዲያው አንዲት ተባባሪ ሚኒባስ መጥታ ልትጭን ስትል ተራ አስከባሪዎቹ፣ ‹‹አይሆንም!›› ብለው ከለከሉ። መንገደኛው ከተራ አስከባሪዎች ጋር ሙግት ሲጀምር፣ ‹‹እናንተ ጉልበታችሁን የምታሳዩት እኛ ላይ ብቻ ነው? ሂዱና መንገድ ትራንስፖርት አቤት በሉ! እኛን ለቀቅ። የወደቀ ላይማ ምሳራችሁ ይበረታል፤›› ብለው ታክሲዋን ባዶዋን ሸኙዋት። ‹‹ቆይ ግን ታክሲዎቹ ነዳጅ ቀድተው የሚመጡት ከሱዳን ነው ከማደያ?›› ሠልፈኛው ብሶታል። ‹‹ኧረ ተውን እስኪ! አሁንማ ብለን ብለን ሳናጣ የሚቸግረን፣ ይዘን የሚርበን ሆንን እኮ!›› ይላል ከፊት ያለው። ድንገት ታክሲዎቹ ተከታትለው ሲመጡ ቆዝሞ ዘለሰኛ ያዳምጥ የነበረው ሠልፈኛ ወደ ጉዳዩ ለመሄድ ዘሎ ታክሲዎቹ ውስጥ መግባት ጀመረ። የተሳፈርንባት ታክሲ ከየዘርፉ፣ ከየዕድሜ እርከኑ፣ ከየኑሮ ደረጃው መራርጣ አሳፍራን ወዲያው መክነፍ ጀመረች። ‹‹ኡህ!›› መሀል መቀመጫ ላይ አንዲት አዛውንት በረጅሙ ይተነፍሳሉ።

አጠገባቸው የተመቀጠ ወጣት፣ ‹‹ምነው እማማ አመመዎ?›› ይጠይቃቸዋል። ‹‹እ! ይህቺን ያህል ቆምሽ ብሎ ይኼውልህ ይኼ እግሬ ማበጥ ጀመረ። ስቅስቃቱ ደግሞ አይጣል ነው!›› ሲሉት ‹‹አይዘዎት! ትንሽ ጊዜ ነው። ባቡራችንም እየደረሰ ነው። አውቶቡሱም ታክሲውም በቁጥራችን ልክ ሳይደረግልን አይቀርም፤›› ማለት። አዛውንቷ ታዝበውት ሽራፊ ፈገግታ ገጻቸው ላይ ተስሎ፣ ‹‹በምን አወቅክ?›› ብለው መጠየቅ። ‹‹አይ እማማ! ማወቅ ምን ዋጋ አለው? ማመን ነው እንጂ! ማወቅ ብቻውንማ መቼ በጀን? ይኼው እርስ በርሳችን እያደናቆረ ያስቸገረን አወቅኩ ባይነት አይደል?›› ብሎ ያልተጠየቀውን መለሰላቸው። እሳቸውም ሰምና ወርቁ ገብቷቸው፣ ‹‹አሃ! ሳያዩ የሚያምኑ ልማታዊ ናቸው እያልከኝ ነው?›› ሲሉት ገሚሱ ተሳፋሪ ሳቀ። ‘ከመፎከር መፈተል ‘ቦነስ’ ዕድሜ ሳያስጨምረን አይቀርም’ ያለ ይመስላል መንገደኛው!

 ጥቂት እንደተጓዝን ወያላው ሒሳብ አምጡ እያለ ሊሞት ደረሰ። ‹‹ምንድው ነገሩ? ነዳጅ ጠፋና ተሳፋሪም ‘ሳይከፍል ይጠፋል’ ብላችሁ ሠጋችሁ? ተረጋጋ ‘ፍሬንድ!›› አለው አንዱ። መጨረሻ ወንበር የተቀመጠ ተሳፈሪ ደግሞ፣ ‹‹ገና ሳይነጋ መስኮት ይከፍታል እንዴ? ‘ዝጋው!፣ ሲል ሌላው፣ ‹‹አልዘጋውም!’›› እየተባባሉ አንዱ ሌላ ላይ ይወርድበታል። ‹‹ውይ! ኧረ የመስኮት አምላክ ይኼን የዘመናት ንትርክ እባክህ ቋጨው? ዛሬም በመስኮት መዝጋትና መክፈት አልተስማማንም? እንኳን ይኼን ይኼን የአሰብን ነገር እርግፍ አድርገን ረስተን የለም ወይ?›› ትላለች አጠገቤ የተቀመጠች ዘመናይ። ‹‹አንቺ የመስኮቱ ይገርምሻል እንዴ? መቼ በባንዲራው፣ በሚከናወነው መሠረታዊ ለውጥ፣ በሚታይ በሚጨበጠው ነገርስ ተስማማን? መስማማት ሞታችን እኮ ነው!›› አላት ከአዛውንቷ አጠገብ የተቀመጠው ወጣት አንገቱን እስኪያመው ተጠምዝዞ።

‹‹ወደን መስሎህ ነው ልጄ? ባይልልን እኮ ነው! እሱ ባይልልን ነው!›› ቢሉ አዛውንቷ ጣልቃ ገብተው ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ ጎልማሶች እየተቀባበሉ፣ ‹‹‘አንድ ላንድ መታገል ሲያቅተው ሰው ሁሉ፣ አንተ ሰው በሰው ላይ ትጥላለህ አሉ…›› ብለው ይገጥሙ ጀመር። ‹‹እዚሁ እርስ በርሳችን መጠቋቆም ሳያንሰን ደገሞ ፈጣሪም መጨመሩ እኮ ነው የሚደንቀኝ፤›› ሲል አንደኛው የወዲኛው መልሶ፣ ‹‹ሁሉም ነገር እኛ ላይ ጀምሮ እኛ ላይ የሚጨረስ የሚመስለን ስለምንበዛ፣ ምናልባት ፈጣሪም ኢትዮጵያዊ ብቻ እየመሰለን ይሆናላ፤›› አለው። ይኼን ጊዜ ደግሞ መጨረሻ ወንበር ላይ የተሰየሙት ተሳፋሪዎች በአንዴው ፍቅር ሆነው ተገኝተው፣ ‹‹ታዲያስ! ሰው የምድሩን ትቶ ስለሰማዩ የማያውቀው እየገባ በሚፈላሰፍበት ዘመን፣ እኛ ስለማንቼዎችና ቼልሲዎች ስንቀድ ብንውል ለምን እንወቀሳለን?›› ማለት ያዙ። ዙሩ ከመክረሩ በፊት ግን የጆሮ ታንቡር የሚቀድ የስልክ ጩኸት ነገሩን አበረደው።

‹‹ምናለበት እንዲህ ራሳችንን ከመቃብር በላይ እንደምናፈቅረው ቢያንስ ‘ይህቺን ታጥል’ ሌላውን ብናፈቅር?›› ራሰ በራው የአዛውንቱን ጨዋታ ሲያደምጥ ቆይቶ ነው መናገር የጀመረው። ‹‹በቃ እስከ መቃብር እየተዋደድን ተያይዘን ማለቅ ሆነ የእኛ ታሪክ?›› ማንም አይመልስለትም ብቻውን ያነበንባል። ‹‹ምንድነው ሰውዬው የሚነጫነጭብን? አግብቶናል እንዴ?›› ትለኛለች ከጎኔ ሹክክ ብላ። ይኼን ስትል የሰማት ያ መጨረሻ ወንበር የተቀመጠ ጠይም ጎልማሳ፣ ‹‹ምናልባት ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ‘ፌስቡክ’ ሲጠቀም ቆይቶ ይሆናል የተሳፈረው፤›› አላትና ሳቀ። ‹‹ታዲያ እኛ የእንካ ሰላንትያ ሰሌዳ ነን እንዴ? አንዳች ደህና ነገር አይታየውም?›› ብላ አፏን እንደከፈተች አዛውንቱ፣ ‹‹ልይስ ቢል ማን ያሳየዋል ልጄ? ጠማማ ነው ብለሽ የተውሽውን እንጨት ‘የቀና ነው’ ብለው ወስደው ማገር አድርገውት ያሳዩሻል። ‘የቀና ነው’ ያልሽውን ደግሞ ጎባጣ ነው ብለው ይተቹብሻል። ከጠማማው ጋር ስትጣመሚ ከቀናው ጋር ስትቀኚ እንዲቺው አንቺ ራስሽን ሳትሆኝ ታልፊያለሽ። እህ ታዲያ? ስታስቢው ገና መንገድሽን ሳታጋምሽው አጨራረሱን እያሰብሽ አጀማመርሽን ታበላሺውና ታርፊያለሽ፤›› ሲሉዋት ክው አልን። ገና በጅማሬው እንዲህ ከባሰብን መጨረሻችን ይሆን እንዴ ጎበዝ?!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ከወዲያ፣ ‹‹እኮ የዓለም መንግሥታት ምን እያሰቡ ይመስላችኋል?›› ብሎ ጥያቄ ያነሳል። ‹‹ምንስ ቢያስቡ ምን አገባን? እዚህ የጓዳችንን ረሃብና ችግር አንድ ነገር ሳናደርግ ምን ‘ኬላ’ ያሻግረናል?›› ትላለች ከወዲህ። ‹‹እንዴ ዘመኑ እኮ የግሎባላይዜሽን ነው፡፡ ኬላ አይደለም ህዋም ያሻግራል ጊዜው›› ይላል ሌላው። ‹‹የፍሳሽ ቦይ ተደፍኖ ያቆረውን ውኃ መሻገር ያቃተንን አትርሱን ፕሊስ?›› ትላለች ከወደ ጋቢና። ‹‹አሽሟጣጭ ሰውና ጋሬጣ አንድ ናቸው፣ የሚያልፈውን ሁሉ በመቦጨቃቸው፤›› ይላል ከወደ ስፒከሩ ከተማ መኮንን። ‹‹እኛን ያስቸገረን እኮ ታዲያ የሚያልፈው አይደለም። እኔም አላልፍም እናንተም አታልፉም ብሎ መንገዱን የዘጋው ነው፤›› ራሰ በራው ይቀጥላል። ‹‹በስንቱ ይሆን ይኼ መንገድ የሚዘጋው?›› ትላለች ከአጠገቡ። ‹‹የዛሬ ጓደኛ ዋንጫ አገናኘው፣ መለኪያ አገናኛው፣ ሸርተት ሸርተት ይላል መከራ ሲያገኘው፤›› ከተማ ቀጥሏል። ‹‹እውነት ነው! ይኼው የመከራ ለትማ አለሁ ባዩ ሁሉ ቤቱን ዘግቶ ተቀመጠ።›› ትላለች ከጎኔ፡፡

ወይዘሮዋ አጉል ነገር ጠመዘዘች መሰል፣ ‹‹የምን መከራ ነው የምታወሩት?›› ከወደ መጨረሻ ይጠየቃል። ‹‹ኧረ ባትሰማ ይሻልሃል። እኛስ ሰምተን ምን ፈየድን?›› ወይዘሮዋ ቀጥላለች። ‹‹እስካሁን መደመር አልተማርንም እንዴ?›› ነገር ያልገባው ነገር ሊያቦካ ድንጉር ይላል። ‹‹እንጃ! እስካሁን መቀነስ ላይ ነበርን። መሸፋፈን ላይ ነበርን። አሁን ግን ይኼው እንደምራለን፤›› ይላል መሀል መቀመጫ ላይ ያለው። ‹‹ብቻ እነዚህ አይሲስ የሚባሉትን አንድ ነገር ካላደረግናቸው እንጃልን፤›› ይላል ደግሞ ከወዲያ። ‹‹እኛ ስንት ሆነን ነው እነሱን አንድ የምናደርጋቸው?›› ብለው አዛውንቱ ጣልቃ ሲገቡ፣ ‹‹እንዴት?›› የሚል ጥያቄ ተከተላቸው። ‹‹ምን እንዴት አለው? ይኼው እንደ ባቢሎን ሰዎች ቋንቋችን ተደበላልቋል እኮ? አንዱ የሚናገረውን ሌላው አይሰማም። ወዲያ የፈለገውን ሲል ወዲህ የፈለገውን ይቀጥላል። ችግሮቻችን ውስብስብ። ቋንቋችን ውስብስብ…›› ብለው ሳይጨርሱ ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ ማስወረድ ጀመረ። ‹‹ኧረ መላ መላ . . .›› የከተማ እጆች ክራር ማክረሩን ተያይዘውታል። የእኛ ሐሳቦች ደግሞ በተለያዩ አቅጣጫዎች ያዋክቡናል፡፡ ግን የአንዱ ጩኸት የሌላው ማብረጃ ባይሆን ምን ይውጠን ነበር? መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት