Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናዶ/ር መረራ የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጎ በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከራከሩ ተወሰነ

ዶ/ር መረራ የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጎ በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከራከሩ ተወሰነ

ቀን:

‹‹ለተራ ወንጀለኛ የሚሰጥ የዋስ መብት በመከልከሌ ጥልቅ ሐዘን  ተሰምቶኛል››                                                                                                                                                                                                                          የተመሠረቱባቸው ክሶች ዋስትና እንደማይከለክሉ ሕገ መንግሥቱንና ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ ሕጎች በመጥቀስ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ፍርድ ቤትን ጠይቀው የነበሩት ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ የዋስትና መብት ጥያቄያቸው ታልፎ በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከራከሩ ዓርብ መጋቢት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ውሳኔ ተሰጠ፡፡

ከሳሽ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በዶ/ር መረራ ላይ ያቀረባቸው ሦስት ክሶች ዋስትና እንደማይከለክሉ በጠበቆቻቸው በኩል ዶ/ር መረራ መከራከሪያቸውን ማቅረባቸውን ያስታወሰው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ ዓቃቤ ሕግ የዋስትና ጥያቄውን በመቃወም ያቀረበውን መልስ በንባብ ለችሎቱ ታዳሚዎች አሰምቷል፡፡

ዶ/ር መረራ የሕገ መንግሥቱን አንቀጾች 9፣ 19 እና 20 በመጥቀስ ዋስትና እንዲከበርላቸው ያቀረቡት በጊዜ ቀጠሮ ወቅት የፖሊስ ምርምራ ሳይጠናቀቅ ስለዋስትና መጠየቃቸውን ከማስታወስ በስተቀር፣ ክሱን ለሚያየው ፍርድ ቤት የማይቀርብና የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግን ያልተከተለ መሆኑን ዓቃቤ ሕግ ማስረዳቱን ገልጿል፡፡ ዶ/ር መረራ ሌላው ያቀረቡት መቃወሚያ የተመሠረተባቸው ክስ ግንቦት 21 ቀን 1997 ዓ.ም. ፀድቆ ሥራ ላይ በዋለው ሕግ መሆኑን ጠቁመው፣ ዓቃቤ ሕግ ግን ክስ የመሠረተባቸው በ1996 ዓ.ም. የወጣውን ሕግ ተላልፈዋል በማለት መሆኑንና ‹‹የማይታለፍ ጉድለት›› ያሉትን በሚመለከትም ዓቃቤ ሕግ ምላሽ መስጠቱን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ ዶ/ር መረራ ሥራ ላይ ባልዋለ ሕግ ሊከሰሱ እንደማይችሉ የጠቀሱት ሕግ ለዋስትና ክርክር መቃወሚያ የሚጠቀስ ባይሆንም፣ ‹‹ለግንዛቤ ያህል ለመግለጽ የወንጀል ሕጉ የፀደቀው በአዋጅ ቁጥር 414/1996 ነው፤›› ማለቱን ጠቁሟል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የወንጀል ሕግ 1997 የሚለውን ሽፋን ተመልክቶ ባልፀደቀ ሕግ ሊባል ስለማይችል መቃወሚያቸው የሕግ መሠረት እንደሌለው ዓቃቤ ሕግ በመልሱ መግለጹንም ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(2) መሠረት ማንኛውም ዜጋ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የማክበርና የማስከበር፣ እንዲሁም ለመንግሥቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት እንዳለበት መደንገጉን ዓቃቤ ሕግ በመልሱ አስታውሷል፡፡ በንዑስ አንቀጽ (3)ም በሕገ መንግሥቱ ከተደነገገው ውጪ በማንኛውም አኳኋን የመንግሥትን ሥልጣን መያዝ መከልከሉንም አክሏል፡፡ ነገር ግን ዶ/ር መረራና ግብረ አበሮቻቸው ላይ የቀረበው ክስ በአድማ ስምምነት በማድረግ ሽብርና ሁከት እንዲቀጥል በማስደረግ፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማስወገድ ሙከራ መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ በመቃወሚያው መግለጹን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 1/2009 እና የዕርምጃ አፈጻጸም መመርያን መጣሳቸውን ገልጾ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(6)ን መተላለፋቸውንና በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 63(1) መሠረት ዋስትና ሊፈቀድላቸው እንደማይገባ መቃወሙን ፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ላይ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት በመውደሙ፣ ሰዎች በመሞታቸውና ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት በመድረሱ የወንጀል ድርጊቱን ከባድ ስለሚያደርገው ተከሳሹ ከአገር አይወጡም፣ መረጃ አያጠፉም ለማለት ስለማይቻል በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 67(ሀ፣ ለ እና ሐ) መሠረት የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ እንዲደረግለት መጠየቁንም ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም በቅጽ 12 በመዝገብ ቁጥር 59304 አስገዳጅ ውሳኔ መስጠቱንም ዓቃቤ ሕግ በመቃወሚያው ጠቅሶ ማቅረቡን ፍርድ ቤቱ ጠቁሟል፡፡

ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ተከራካሪ ወገኖች ክርክር ሲመረምር በዶ/ር መረራ አንደኛ ክስ ላይ የተጠቀሰው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 238 (1 እና 2) ከሦስት ዓመት እስከ ሞት የሚያስቀጣ መሆኑን ገልጿል፡፡ ዋስትና ሕገ መንግሥታዊ መብት ቢሆንም እንደ ወንጀል ድርጊቱ በተለያዩ ልዩ የሕግ ድንጋጌዎች ዋስትና ሊነፈግ እንደሚችል በሕገ መንግሥቱ በመጠቀሱ፣ ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብት የሚለው ፍፁም እንዳልሆነም አስረድቷል፡፡

ዶ/ር መረራ የቀረበባቸው አንደኛ ክስ ላይ ንብረት መውደሙን፣ ሰው መሞቱንና የአካል ጉዳት መድረሱን የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 63(1) እና አንቀጽ 67 (ሀ፣ ለ እና ሐ) ጠቅሶ መቃወሙን ፍርድ ቤቱ ጠቁሞ፣ ከክሱ አንፃር አንቀጾቹ ሲተረጎሙ ዶ/ር መረራ የጠየቁትን የዋስትና መብት የሚከለክሉ ሆነው ስላገኛቸው ክሳቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ መወሰኑን አስታውቋል፡፡

የክስ መቃወሚያ መቼ ማቅረብ እንደሚችሉ ፍርድ ቤቱ ለዶ/ር መረራ ጠበቆች ጥያቄ አቅርቦ ለሚያዝያ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደሚያቀርቡ ጠበቆች ተናግረዋል፡፡ የፍርድ ቤቱ ውሎ ሊጠናቀቅ ሲል ዶ/ር መረራ ሁለት ነገሮች እንዲናገሩ እንዲፈቀድላቸው ፍርድ ቤቱን ሲጠይቁ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

ዶ/ር መረራ ሲፈቀድላቸው፣ ‹‹ከጄኔራል መንግሥቱ ነዋይና ከጄኔራል ታደሰ ብሩ ዘመን ጀምሮ ከአንድ ትውልድ በላይ ገዳዮችና ሟቾች፣ አሳሪዎችና ታሳሪዎች በበዙበት የአገራችን ድራማ ውስጥ በመቆየት አንድ ከሆዱ በላይ ለአገሪቱ የሚያስብ ምሁር ማድረግ እንዳለበት ሁሉ፣ ከ45 ዓመታት በላይ ለአገሬ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ በታማኝነት መታገሌ እየታወቀ ወደ ጎን ተገፍቻለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ቀጥለውም፣  ‹‹ለሁላችንም የምትሆንና በእኩልነት የምታስተናግደን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትፈጠርና ነፃ የፍትሕ ሥርዓት በአገራችን እንዲሰፍን ላለፉት 25 ዓመታት በመታገሌ መከሰሴና የአገሪቱ የፓርላማ አባል ጭምር የነበርኩ ሰው ለተራ ወንጀለኛ የሚፈቀድ የዋስ መብት በመከልከሌ የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን ለራሴ ብቻ ሳይሆን፣ እኛም ሆንን ልጆቻችን በሰላም ይኖሩባታል ለምንላት መከረኛ አገራችንና አላልፍለት ብሎ ሲታመስ ለሚኖረው መከረኛ ሕዝባችን ጭምር መሆኑን እንዲታወቅልኝ ነው፤›› በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...