ተቃዋሚዎችና ኢሕአዴግ አሁንም ገና በማኮብኮብ ላይ ባለ፣ ወደ ቁምነገሩና ዋና ይዘቱ ውስጥ ባልገባ የድርድር ሒደት ላይ ናቸው፡፡ ውይይትም ድርድርም ይባል ማኮብኮብ ደረጃም ላይ ዘጭ እምቦጭ እያለም ቢሆን ከአሁኑ ማለም ያለበት የፖለቲካ ፀበኝነትን ለማዳከም፣ በጭፍን ጥላቻና ተቃውሞ ውስጥ የሚያንገታግትታቸውን ፖለቲካዊ መሬት ለማጥበብ፣ ተቃዋሚዎች እርስ በርሳቸውም ሆነ ከኢሕአዴግ ጋር በጠላትነት መፈራረጃቸው እንዲሟሽሽ ለማድረግ ነው፡፡ ኢወገናዊ በሆኑ ተቋማት ላይ ዴሞክራሲን ማቋቋም ነው፡፡ ኢትዮጵያን የጎደላት ይህ ነው፡፡
በዚህ ሒደትም ሆነ ገና ከጅምሩ ከኢሕአዴግ የሚጠበቀው መነሻ ቅድመ ሁኔታ የተቃዋሚዎችን አያያዝ የግድ መቀየር ያለበት መሆኑን ነው፡፡ የእሱ በጥልቀት መታደስ የተቃዋሚዎችን አያያዝ ከመቀየር በጭራሽ ሊነጠል አይችልም፡፡ በጠመንጃ ጎዳና ውስጥ ያሉትን ተቃዋሚዎች ወደ ድርድር ማምጣት ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰላም ትልቅ ጥቅም ያለው ቢሆንም፣ በአሁኑ ጊዜና ከተጓዝንበት ‹‹የባለ ብዙ ፓርቲ›› ዴሞክራሲ ያልተሳካ ተሞክሮ እንደተረጋገጠው ይህ ለኢትዮጵያ ለምን አይደረግላትም ብሎ መጠየቅ አጉል መሞላቀቅ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ እንኳን ይኼን ሊያደርግ በሰላማዊና በሕጋዊ መድረኩ ውስጥ ላሉት ተቃዋሚዎች ገና አልደላም፡፡ ከሰላማዊ ተቃዋሚዎች ጋር ግንኙነትን ማለስለስና የበለጠ መፈናፈኛ መስጠት የውጭ ጣልቃ ገብነትን ቀዳዳ ማሳጣትና ጦረኛ የትግል መንገድን ማምከን መሆኑን በማጤን ከለበጣ ባለፈ ደረጃ ቀና ለመሆን አለመቻል፣ ከፈለጋችሁ በጠመንጃ መንገድ ታገሉኝ ብሎ በተዘዋወሪ የመቀስቀስ ውጤትም የነበረውና ያለው ነው፡፡ ከተቀጠለበት ኢሕአዴግም ብልጫ ጥቅሜ ብሎ እያሽሞነሞነ ከገፋበት ተቃዋሚዎችም አላውቅበት ካሉ፣ በሰላማዊ የምርጫ መንገድ ለመወዳደር የተሰባሰቡትን ሁሉ ተስፋ አስቆርጦ ማመናመኑ ይቀጥላል፡፡ ሥውር የብተናና የመከፋፈል ተንኮሎችም ጥላቻ እያመረቱና ለሕገወጥ ትግል በመልማይነት እያገለገሉ ሒደቱን ያፋጥናሉ፡፡ እስከ ዛሬ ሲሆን ያየነው ይኼንኑ ነው፡፡
ኢሕአዴግ ጊዜያዊ መንግሥት ከነበረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ምን ያህል በፖለቲካ ሾኬና በመሰሪ ፕሮፓጋንዳ፣ በተቃዋሚ ውስጥ እየሰረገ አናጭቶ በመበተን፣ በስልክና አፍኖ በማስፈራራት፣ በድብደባና ደብዛ በማጥፋት፣ ማጥመጃ እየፈለጉ በማስገደድ፣ የሐሰት ምስክር በመግዛት፣ በሸፍጠኛ ውንጀላና እስራት ስሙ ሲነሳ ኖሯል? ከሽብር ጋር በመተባበርና በሕገወጥነት ወንጀል ተፈርዶባቸው በምሕረት የተለቀቁት የስዊድን ጋዜጠኞች ከወጡ በኋላ “የእጅ ከፍንጅ” የቪዲዮ ማስረጃ እንደምን እንደተቀናበረባቸው ያቀረቡት ታሪክ ምን ያህል የመንግሥትን ተዓማኒነት ጎድቷል? ለዓቃቤ ሕግ “የከሳሽ (የመንግሥት) ጠበቃ” የሚል ስም እስኪወጣለት ድረስ ሕግና ፍትሕ ተገን ስለማጣቱ ምን ያህል ተወርቷል/ተጽፏል? ይህንን መሳዩ ገጽ ብዙ ገመና የሚያመርተው ብግነትና አደገኛ ስሜት ምን ያህል ቅን መንፈስና ህሊናን አኝኮ ጨርሷል? ፖለቲካው ወላልቆ የተበታተነውን ኦነግ እንደገና ለማሰባሰብ የተጣጣሩ ሰዎች በአደባባይ “የትጥቅ ትግል ዛሬም ይሠራል፣ እንዲያውም በኢትዮጵያ ውስጥ ተስፋ የሌለው ሰላማዊ ትግል ነው፣ ሕጋዊ ተቃዋሚዎች ከመወገዝና ከመታሰር በቀር ምን አተረፉ . . .?” እያሉ ለመቀስቀስ ያበቃቸው ማነው? እነዚህ ጥያቄዎች መሠረተ ቢስ ውንጀላዎች፣ ተራና ርካሽ ስም ማጥፋቶች ተብለው የማይገላገሏቸው ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ ውድ መፈክርና ተልዕኮ ላነገበው ለኢሕአዴግ ደግሞ መታደስና ‹‹በአዲስ መልክ ሥራ ጀምረናል›› ምክንያት የሆኑትም እነሱ ናቸው፡፡
የተቃዋሚ አንድ ግለሰብ እንኳ ያላስደረሰ የ2007 ዓ.ም. “እንከን የለሽ” የምርጫ ውጤትም በሰላማዊ ትግል ውስጥ የመቆየትን ተስፋና ፍላጎት የሚያዳክምና ይህንኑ የኃይል መንገደኞችን መከራከሪያና አቋም የሚያግዝ ነበር፡፡
ከምርጫው ሒደትና ውጤት የበለጠ ደግሞ የአንድነትና የመኢአድ ክፍፍል የተስተናገደበት አኳኋን የበለጠ ጠንቀኛ ነበር፡፡ ለምሳሌ አንዱን አንጃ ለመጥለፍ ማጣደፍ፣ ሌላውን አንጃ እንዲደሰኩር መልቀቅ የታየበት ‹‹የልማታዊ ጋዜጠኞች›› አድሎኛ ቃለ መጠይቅ ማስተዛዘቡ ሳያንስ፣ “የፖለቲካ ምኅዳሩን የሚያሰፋ፣ በገለልተኛነት የተካሄደ፣ ለማንም ያላዳላ፣ ወዘተ” እየተባለ በ‹‹ሕዝብ አስተያየት›› ስም ውዳሴ ሲጎርፍለት የቆየውና በአንድነትም ሆነ በመኢአድ ውስጥ የተከፋፈሉት ወገኖች “ሁሉም ሕገወጦች ናቸው… በተናጠል ጠቅላላ ጉባዔ መጥራት አይችሉም . . .” ሲል የነበረው ምርጫ ቦርድ የሰጠው ውሳኔ የ”ቅንጅት”ን ስም ለአየለ ጫሚሶ ቡድን ከሰጠበት ውሳኔ የማይሻል ነበር፡፡ ሌላው ቢቀር ጊዜ ማጓተት ሳያስፈልግ ገና በፊት፣ አንድ ላይ ጠቅላላ ጉባዔ እየጠራችሁ ለውዝግቦቻችሁ እልባት ስጡ ወይ ከሁለት አንዳችሁ ወይም ሁላችሁም ስማችሁን ቀይራችሁ እንቅስቀሴያችሁን መቀጠል ትችላላችሁ፣ እስከዚያ ታግዳችኋል የሚል ውሳኔ መስጠት የተሻለ ፍትሐዊ በሆነ ነበር፡፡ በድርጅቶቹ ውስጥ ተፈጸሙ የተባሉት የሕገ ፓርቲ ጥሰት ችግሮች የቆዩ ሆነው ሳለ ምርጫ ሲደርስ መወዛገቢያ መሆናቸውም የሚያስተዛዝበው እነሱን ብቻ አይደለም፡፡ ምርጫ በደረሰ ቁጥር ተቃዋሚዎችን የሚያምስ ነገር የሚለቅባቸውስ ምን ሰይጣን ነው? የሚለው ጥያቄ ያላንዳች ማቅማማት ሁነኛ መሽከርከሪያ አድርጎ የከሰሰው የኢሕአዴግን “ሥውር እጅ” ነው፡፡
‹‹የልማታዊ ጋዜጠኞች›› ቃለ መጠይቅ፣ የምርጫ ቦርድ ውሳኔና በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሊቪዥን ለምርጫ ቦርድ የጎረፈው የአድናቆት ፕሮፓጋንዳ አንድ ላይ ተደጋግፈው እንኳ ሐሜቱንና ክሱን ማደናገር አልተሳካላቸውም፡፡ “ሁሏም የኢሕአዴግ ሥውር ተንኮል ነች! የተፈለገው በቅዋሜ ሠልፍና በፀረ ሽብር አዋጁ ላይ ፊርማ በመሰባሰብ አላርፍ ብለው ያስቸገሩትን ወገኖች አስወግዶ የአዛውንቱን ወገን ሕጋዊ ማድረግ ነው…” ሲባል የነበረው ገና ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት ነበር፡፡ ከፋፍሎ የማናጨት መጪ ተራ ደግሞ የሰማያዊ ፓርቲ ስለመሆኑም ተተንብዮ አብቅቷል፡፡ ትንቢቱም የያዘለት መሆኑን በዕለት ዕለት ዜናዎች እያስመዘገበ ነው፡፡ የፓርቲው የውስጥ ሽኩቻ እንዳለ ሆኖ፡፡
‹‹በጥልቅ መታደስን›› ግድ ካደረገው የ2008/2009 በውድመት ጭምር የጨቀየ ተቃውሞ በኋላ፣ ኢሕአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር ለመነጋገር በጀ ብሏል፡፡ በዚህም የከዚህ በፊቱን ድፍን እምቢተኝነትና ቅድመ ሁኔታ ያዘለ አዛዥና ናዛዥነት ያሻሻለ ይመስላል፡፡ ከዚህ ቀደም እንኳንስ ብቻዬን አሸንፌ ባላሸንፍም ከተቃዋሚ ጋር አልሠራም፣ ከዕለታት አንድ ቀን ረግጠህ የወጣኸው ስብሰባ አለብህ፣ የሥነ ምግባር ድንብ አልፈረምክም እያለ ራሱ ‹‹የመብትና የወግ የማዕረግ ማጣት ፍርድ›› ከወሰነባቸው ፓርቲዎች ጋር የፈጠረውን አንደራረስም አቋም ቀይሬያለሁ ብሏል፡፡
በአገሪቷ በተለይም ድኅረ ምርጫ 2007 ያፈጠጠው ለሕዝብ እሪታ ምላሽ የመስጠት አደራና ኃላፊነት ኢሕአዴግን የሚሰማው ከሆነ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታውንም ሆነ፣ እውነትን፣ ትክክለኛነትን፣ ሥልጣንን፣ የእኔና የእኔ ብቻ ከሚል አባዜው መውጣት፣ ተቃዋሚዎች እርባና ኖራቸው አልኖራቸው፣ ፈየዱም አልፈየዱም የሥርዓቱ ግንባታ አካል መሆናቸውን መቀበል አለበት፡፡ እርባና ቢሶቹን፣ ፋይዳ የለሽ ፓርቲዎችን አንጓሎ መጣል ያለበት ራሱ ሥርዓቱ እንጂ የኢሕአዴግ የቅድሚያ ፈቃድና ምርመራ መሆን የለበትም፡፡ ይህ ፀረ ዴሞክራሲና በዴሞክራሲ ላይ ግፍ መዋል ነው፡፡
ኢሕአዴግ ለሕዝብና ለዘላቂ ጥቅም እታመናለሁ ካለ፣ እንደሚለውም ‹‹የመስዋዕትነት›› ድርጅት ሆኖ ድል ማስመዝገብ ከፈለገ ካለታማኝ ጭፍራ በቀር ማንንም ሳያስጠጋ፣ ሥልጣን ለብቻው ይዞ ረዥም ዘመን ለመቆየት ካቀደው ግብና ህልም መንቃት አለበት፡፡ በትጥቅ ትግል የጀመረውንና ሽግግሩ መጀመሪያ ላይ ራሱ ያጨናገፈውን እንደገና እንዲያንሰራራ ከፈለገ ተቃዋሚነትን በፀጋ መቀበል፣ ባለፉት 25 ዓመታት ያለተቃዋሚ ሥራውን ለማካሄድ አለመቻሉን ልዩ ሴራና ተንኮል በእሱ ላይ እንደተጋረጠበት አድርጎ ከመቁጠር ቅዠቱ መንቃትና መውጣት አለበት፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ አየር አልጠራ ያለው ብሎም ወደ ሰከነ የፖለቲካ ኃይሎች ሰላማዊ ግብግብ ሳይሸጋገር የቀረው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ይህን ስህተቱን ኢሕአዴግ አሁን በተጀመረው ድርድር ውስጥ ማረምና መጠገን አለበት፡፡ መንግሥትነቱንና ፓርቲነቱን ‹‹እያጣቀሰ›› ከሚወስደው አፍራሽ አቋም መታገድ አለበት፡፡ ይህ ከማንም በላይ በተለይም ከተቃዋሚዎች በላይ ኢሕአዴግን ይጠቅማል፡፡ አገርንም ከሚያስደነግጥና ከሚያተራምስ አማራጭ ያድናል፡፡ ከጠብ ፖለቲካ መውጣት ከተቃዋሚ በላይ ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ይበልጥ ይጠቅማል፡፡ በመዘርጠጥ ጭንቅ ተጠምዶ ሁሉን ነገር ሚስጥራዊ ከማድረግና የተቃዋሚ የተቃውም ንፋስ ከማሳደድ አዙሪት ይላቀቃል፡፡ እንዳይፈነዳ የሚያስፈራራ እምቅ ብሶት ያስቀራል፡፡
ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎች በፓርቲነታቸው በነፃ መደራጀትን በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ሕዝብ ማነሳሳትንና ከሰላማዊ ባለጋራዎቻቸው ጋር ፊት ለፊት መጋፈጥን ባህል ከሚያደርግ አዲስ ጅምር መነሳት አለባቸው፡፡ ፓርቲዎች ሐሳባቸውን በሰፊው ለሕዝቡ አስረድተውና ተከታይ አበጅተው ሥልጣን የመረከብ ትግል እንዲያካሂዱ ግን መጀመሪያ የአገሪቷ የሥልጣን መንበር ከየትኛውም ፖለቲካዊ ቡድን ታማኝነት መፅዳትና መላቀቅ አለበት፡፡
ለኢሕዴግም ሆነ ለተቃዋሚዎች ዋናው ቁምነገር ዴሞክራሲንና ልማትን በማጎዳኘት ከአምባገንነት በተቃራኒ የመቆም ጉዳይ ነው፡፡ በአሁኒቷ ኢትዮጵያ እውነታ ከዴሞክራሲ ጎን ቆሞ የመታገል ጉዳይ የፀደቀው ሕገ መንግሥት ውስጥ የተቀመጡት፣ የዴሞክራሲ መብቶች ሕይወት እንዲያገኙ (ለሕገ መንግሥቱ መቆም) ነው፡፡ በዚህም ትግል ውስጥ መጀመሪያ መጤን ያለበት ጥሩ ነገር በአሁኑ ጊዜ ዴሞክራሲያዊ ሥልጣን የማቋቋም ዕድል ሙሉ ለሙሉ በኢሕአዴግ መፍቀድ አለመፍቀድ ውስጥ መሆኑ ነው፡፡
በሌላ አባባል ከሕገ መንግሥቱ ጎን ቆሞ የዴሞክራሲ ሻምፒዮን መሆን ማለት ለዴሞክራሲ ታማኝ የሆነ ተቃዋሚነትንና ለገዢው ፓርቲ የ“ተቃዋሚ” ታማኝ መሆንን አምታትቶ፣ “ለኢሕዴግ ታማኝ ተብለን ዘመቻ ተካሂዶብን ሕዝብ ጋ እንዳንደርስ ተደረግን” የሚል (ግረፍልን ብሎ ከማመልከት የማይሻል) አቤቱታ እስከ ማቅረብ መጥመልመል አይደለም፡፡ ይህንን መሳዩ “ተቀዋሚነት” ፍርፋሪ ያስገኝ እንደሆን እንጂ ለዴሞክራሲ ቅንጣት ያህል አያዋጣም፡፡ ከዚህ በተቃራኒም እየተቅበጠበጡ በመንገድ ላይ ተቃውሞ ገዥውን ክፍል ለማጣደፍ ወይም አብዮት አደባባይን ለመቆጣጠር መሞከርም የዴሞክራሲ ሻምፒዮንነትን አያስገኝም፡፡ ለአገር መታመንና ለኢሕአዴግ መታመን፣ አንድ የሆነበት አገዛዝ ሥጋቴ ያላቸውን ተቃዋሚዎች በነውጠኝነት እየጠለፈም ሆነ እርስ በርስ እያናቆረ የሰባበረበት ልምድ፣ የፓርቲ ደንብን እንኳ ስቶ ቀለበት ውስጥ ላለመግባት በከፍተኛ ደረጃ መጠንቀቅን የሚያስተምር ነው፡፡ መኢአድና አንድነት በሚባሉት ቡድኖች ውስጥ በ2007 ዓ.ም የደረሰው የመከፋፈል ቀውስ ይኼን ትምህርት በቅጡ ካለመጨበጥ ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ እነ አንድነት ላይ የደረሰው እንዳይደርስበት የሚሻ ተቃዋሚ ጠለፋና ሸርን እንደምን ባለ ፖለቲካና ንቁነት መብለጥ እችላለሁ የሚል ጥያቄን መመለስ ግድ ይለዋል፡፡
ገዢው ኢሕአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር ያለበትን መጠማመድና መሸካከር በድርድርና በመቀራረብ ለማድከም ያለመጨነቁ ተግባራዊ ትርጉም በፀጥታ ኃይሌ ታማኝነትና ብርቱነት እተማመናለሁ፣ እንኳን ፊት ለፊት ግልበጣና ኅቡዕ ትግል ቢከጅላችሁ ወይም በሻጥር ብትመጡብኝ እበልጣችኋለሁ እንጂ አትበልጡኝም የሚል ነው፡፡ የልማታዊነት ዝና ማግኘት በተጨመረበት በቀድሞው ሁኔታ ውስጥ ሆነ ዛሬ በቅዋሜ ጋጋታ ለመከንበል የሚደረግ ሙከራ ተደፍጥጦ ከመጥፋትና ለአመል ተከፍታ ያለችውን ቀዳዳ ከማስደፈን ያለፈ ውጤት እንደማያስገኝ፣ በምርጫ አሸንፌ እገላገለዋለሁ ማለትም ደጋፊዎቹ አያዳሉብኝም ብሎ ከመቀበል እኩል መሆኑን ማስተዋል ለሚያዋጣ መፍትሔ የማዕዘን ድንጋይ ነው፡፡ የቅርቡ በውድመት የታጀበው አመፅ ያመጣው ተስፋን ብቻ አይደለም፡፡ ማነቆውን አጥብቆብናል፡፡ በትግል መሸነፍንም አስከትሏል፡፡
አሁን ባለንበት ደረጃ እንደ ልብ ተዘዋውሮ ቅስቀሳ ለማሞቅና ያለሸፍጥ ምርጫ ለማካሄድ የሚፈቅድ ሁኔታ ቢከፈት አንዳንድ የተቃዋሚ ሰዎች ኢሕአዴግን በዝረራ የሚያሸንፉት ይመስላቸዋል፡፡ ግን ከዚህ ይልቅ የመሆን ምናልባት ያለው ኅብረተሰቡንና አካባቢዎችን በኢሕአዴግና በፀረ ኢሕአዴግ ረድፍ ያሠለፈ፣ (በፀረ ኢሕአዴግነት ውስጥም ሌሎች ፍንግጥግጦሾች ወለል የሚሉበት) መከፋፈል ፈጥጦ መውጣት ነው፡፡
ዛሬ መንግሥታዊ አውታራቱ፣ ምርጫ አስፈጻሚ ሠራዊቱ፣ የሕዝብ ታዛቢዎቹ ሆኑ የሲቪክ ማኅበራት ታዛቢዎች በ‹‹ልማታዊ›› ወገንተኛነት አመለካከት የተገሩ በሆኑበት፣ የ1997 ዓ.ም. ዓይነት ቅዠት እንኳ መቃዠት የማያስችል ሁኔታ በለማበት ተቃዋሚዎች አምስት ዓመት እየጠበቁ የምርጫ ፍር ፍር ስለአደረጉ ጠብ የሚል ነገር አይኖርም፡፡ ተዓምረኛ ሁኔታ ተፈጥሮ አሸነፍን ብሎ የመቃዠት ዕድል ቢከሰት እንኳ የለም እናንተ አደላችሁም ያሸነፈችሁት ብሎ በ‹‹ማስረጃ›› መብለጥ ቢያስፈልግ፣ በድጋሚ ቆጠራና የግድፈት አቤቱታ አቅርቦ የማረሚያ ምርጫ እንዲካሄድ በማድረግ አሸናፊነትን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
ኢሕአዴግ ሳት ብሎት ተቃዋሚዎች የተወሰነች ብልጫ ወይም ተጋግዞ ጥምር መንግሥት ለማቋቋም የሚያስችል ድምፅ አገኙ የሚል ዓይነት ውጤት አፈትልኮ አደባባይ ቢወጣ እንኳ፣ ማን እማን ላይ ተቀምጦ ሊገዛ? ካስፈለገ አሸነፍኩ ባዮቹን ራሳቸውን ከጀርባ “በሉ ኮሽ ሳይልባችሁ” ብሎ በልጓም መንዳት ይቻላል፡፡ በዚህ ባይሆን ታፍኖ የኖረ ሕዝብ ሲፈታ የጉርምስና ዝላይ እንዳመለጠው ባለግርሻ የሚፈጥረውን የሁሉ አይቅረኝ ጫጫታ አጋግሎ ሥርዓተ አልባነትን በማራባት፣ እንዲሁም ሕገ መንግሥቱ አደጋ ላይ ስለሆነ እንገነጠላለን፣ ወዘተ በሚል አዙሪት ናላ አዙሮ አገር ለማዳን አስቸኳይ አዋጅ ፀጥ ለጥ ማድረግ ሌላ መንገድ ነው፡፡ አሸነፍኩ ባዩ ተቃዋሚ ይኼንን የመሳሰለውን መሰናክል ሁሉ ጥሶ ወደ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ሊያመራ የሚችልበት ቀዳዳ የሚኖረው ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ አነቃናቂ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሁኔታ እንደ መንግሥተ ሰማያት መንገድ የራቀ ሆኗል፡፡ አንድ ፓርቲ/ግንባር ሰፊ ድጋፍ የሚያገኝበት ዕድል ዕውን ቢሆን እንኳ፣ ያ ቡድን መንግሥት ሲሆን ዴሞክራሲን ማራመድ ሊሳነውና መንበር ላይ ያወጣውን የሕዝብ ድጋፍ አባክኖ ሊንሳፈፍና የአምባገነንነት ዕራት ሊሆንም ይችላል፡፡
የዚህ ሁሉ ሀተታ መሰባሰቢያ ሐሳብ ዋናው የዴሞክራሲ ትግል ያለው በየአምስት ዓመቱ በሚመጣ ምርጫ ላይ ሳይሆን መሠረት የመጣል ሥራ ላይ ነው የሚል ነው፡፡ ጠላትነትና ልማቱ ያለ አንድ ፓርቲ የማይቀጥል የሚያስመስል አስተሳሰብን መፈርከስና በበጎ መተያየትንና ተቀራርቦ መወያየትን ማዳበር፣ ማነቆዎች እንዲላሉና ሸሮች እንዲደክሙ የሚያደርጉ ተግባራት ላይ ማተኮር፣ በደሎችና ጥፋቶች በተለያየ መንገድ እየተገለጡ እንዲታረሙ የማድረግ ዴሞክራሲያዊ አኗኗርን መለማመድና ማለማመድ፡፡ ይኼንን መሳይ ጥርጊያ ሳያበጁ ምርጫ ጠብቆ ድምፅ ለማፈስ መጓጓት ጉምን ለመዝገን ከመሞከር አይሻልም፡፡
የዚህ ሁሉ መፍትሔውና የጥበብ መጀመሪያው የአገሪቷን የሥልጣን መንበር ከየትኛውም ፖለቲካዊ ቡድን ታማኝነት ማላቀቅ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታዎችንና ተቋማትን ማጎልበት ማለት ይኼ ነው፡፡ በድምፅ ካርድ ብልጫ የተመረጠ መሪ ወታደሩንና ደኅንነቱን ለመያዝ ሳይጨነቅ ቢሮ ሲገባ ሥልጣኑንም መቀዳጀት የሚችልበት፣ የሥልጣኑም ቀጣይነት በሕገ መንግሥቱና በተግባሩ ብቻ የሚወሰንበት ሥርዓት ሀ ብሎ የሚጀምረው ወታደሩ፣ ፖሊሲና ደኅንነቱ የምርጫ አስፈጻሚና ሌሎች ተያያዥ አካላት ከግለሰብና ከፓርቲ ታማኝነት ጋር ሳይጣበቁ በሕጋዊ ጎዳና በኩል ማንም መጣ ማን፣ እንደ ተቋም በገለልተኝነት የሚቀበሉና አገራዊና ሙያዊ ተልዕኳቸው ላይ የሚያተኩሩ አድርጎ ከማደራጀት ነው፡፡ የፖለቲካ ትርምስ ሳይፈጠር፣ የመፈነቃቀልና የሙያ ብክነት እገጭ እገው ሳይኖር፣ ከሕዝብ ጋር በእርጋታ እዚህ ሒደት ውስጥ ለመግባት አሁን ያለንበት ምዕራፍ ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡
የፀጥታ ኃይሎችና ሌሎች ገለልተኛ መሆን የሚያሻቸው ተቋማት ከቡድን ታማኝነት እስካልተላቀቁና በፓርቲዎች መካከል ያለው ግንኙነት በጠላትነት ጎራዎች ውስጥ እሰከቀጠለ ድረስ ዴሞክራሲን የመገንባት፣ ሙስናን የማሸነፍና መልካም አስተዳደርን የማስፈን ትግሉ በዓለትና በዓለት መሀል እንደተቀረቀረ ይቆያል፡፡ የኢሕአዴግ የለውጥ “ንቅናቄ”ም ከሕግ በላይ ሆኖ ሕግ ተላላፊነትን እንደ መታገል፣ ከተጠያቂነት በላይ ሆኖ ተጠያቂነትን እንደ ማረጋገጥ፣ ከተሸፋፍኖ ኑሮ ሳይወጡ ለግልጽነት እንደ መዋደቅ፣ ተንኮል እያፈለቁ ተንኮልን እንደ መታገል እየፈጩ ጥሬ ከመሆን አይዘልም፡፡
እዚህ ሒደት ውስጥ ሲገባ መልካም አስተዳደርን የማስፈን ትግል ከገባበት አጣብቂኝ ይላቀቃል፣ ታጥቦ ጭቃነቱ ይቀየራል፡፡ የአካባቢ ተወላጅነትንም ሆነ የድርጅት አባልነትን መሠረት በማድረግ “የሥርዓቱ ታማኝና ልዩ ጠበቃ” እየተባለ ጣት መጠቋቆሚያ የሚሆን (ለደግም ይሁን ለክፉ ነገር ብቻውን ተነጥሎ የሚታይ) የመኖሩ ዕድል ይጠባል፣ ይዳከማል፡፡ የትምክህትንም ሆነ የብሔርተኝነትን ጠባብ የአዕምሮ ሙሽት የሚያሰፉና ተዛማጅ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ተጨማሪ ማስተከካያዎች ሲደረጉ ደግሞ ጉዞው ይበልጥ ይቃናል፡፡ ይህ ጉዞ ቢጀመር እንኳ ንቅዘት አዲስ መጦችን እየቀረጠፈ ራሱን የሚያባዛበትን ፋብሪካ (ብቃት የለሽነት፣ አልምጥነት፣ ደንታ ቢስነት፣ ዓይነጥፉ ራስ ወዳድነት፣ ሰብቀኝነት፣ መሰሪነት፣ ለመጥማጣነትና ጎሰኛ ጥቅቅም የለሙበትን ማኅበራዊ አካባቢ) ነቃቅሎ የሥራ ብቃት፣ ለሥራ መታመን፣ ትጋት፣ ቅንነት፣ ተቆርቋሪነትና በሥራ ብቻ መለካት በሚላወሱበት ማኅበራዊ አካባቢ መተካትን ይጠይቃል፡፡ ይኼ ማኅበራዊ አካባቢ ከተፈጠረ ራሱ በራሱ የምግባረ ብልሹነት መገለጫዎችን እንደ ተባይ እያዋከበ ይታገላቸዋል፡፡ እነ ሙስናንና ጎሰኛነትን ማሸነፍ ማለት ይህ ነው፡፡ እንዲህ ያለው አሸናፊነት የሚገኘው ደግሞ በጥዝጠዛና በማባረር ሳይሆን የተማረውን ክፍል፣ የወጣቱን፣ የፓርቲዎችንና የሕዝብን ውዴታና ወኔ ያስተባበረ የባህል ለውጥ ሰዎችን እያሳደደ የሚደቁስ ሳይሆን ወደ አዲስ የአኗኗር ዘይቤ የሚያስገባ ለውጥ በማካሄድ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡