Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉኢሕአዴግ የሚደራደረው በጠንካራ አቋም ላይ ሆኖ ነው

ኢሕአዴግ የሚደራደረው በጠንካራ አቋም ላይ ሆኖ ነው

ቀን:

አዲሱ ዓመት ከጠባ ጀምሮ በመካሄድ ላይ ካለው ጥልቅ ተሃድሶ ፍሬዎች ውስጥ አንዱ በኢሕአዴግና በ21 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተጀመረው ውይይትና ድርድር ነው። ፓርቲዎቹ ውይይትና ድርድር  በማድረጉ አስፈላጊነት ላይ ተስማምተዋል፣ ውይይትና ድርድሩ የሚመራበትን ረቂቅ ደንብም በጋራ አዘጋጅተው እየመከሩበት ነው፡፡ ሒደቱ እስካሁን ያስገኘው ተጨባጭ ውጤት ባይኖርም ፓርቲዎቹ በመደማመጥና በመግባባት መንፈስ የሚፈጽሙትና የቅድሚያ ትኩረታቸውን ያገኘ የጋራ አጀንዳ ሆኖ መቀጠሉን ማየት ይቻላል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ ይህን ውይይትና ድርድር አስመልክቶ የተሳሳቱ አስተያየቶች ሲሰጡ ይስተዋላሉ፡፡ አንዳንድ ወገኖች ኢሕአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር የሚያደርገው ውይይትና ድርድር ከፓርቲው መዳከም ወይም ከተሸናፊነት መንፈስ የሚመነጭ አድርገው ይመለከቱታል፡፡ ለዚህ መነሻቸው ደግሞ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተከሰተው አለመረጋጋትና ሁከት የተነሳ ኢሕአዴግን አጣብቂኝ ውስጥ የገባ ወይም የጨነቀው ፓርቲ አድርገው መውሰዳቸው ነው፡፡

ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎች እጃቸው ከምን?” በሚል ርዕስ በሪፖርተር ጋዜጣ አስተያየታቸውን ያሠፈሩ አንድ ጸሐፊ ኢሕአዴግ እየተደራደረ ያለው በደካማ አቋም ላይ ሆኖ እንደሆነ የሚያመላክት ጽሑፍ አውጥተዋል። አንዳንዶቹ እንዲያውም ተቃዋሚዎች ከኢሕአዴግ ጋር ወደ ሌላ ውይይት ከመግባታቸው በፊት አጋጣሚውን ተጠቅመው የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎችን እንዲያስቀምጡ ወትውተዋል፡፡

በመሠረቱ ካለፈው ዓመት ጀምሮ አገራዊ ሁኔታው ለኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን ለመላው የአገራችን ሕዝቦችም ፈታኝ ነበር፡፡ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች አንዳንድ ቦታዎች የተከሰቱ ግጭቶች ያስከተሉት ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት በኢሕአዴግ የመሪነት ዘመን ከተከሰቱት ሁሉ በስፋቱም በመጠኑም የላቀው ነው። ጉዳቱ ሁለንተናዊ እንቅስቀሴያችንን አደጋ ውስጥ የከተተ፣ የአገራችንንም ገጽታ ያጠለሸና በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም ዘርፉ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደረ እንደነበርም ይታወቃል፡፡ ከዚህም በላይ በኢሕአዴግ ውስጥ የተከሰተው የአመለካከት ዝንፈት አብዮታዊነቱን ስቶ የጥገኛ ዝቅጠት ባህሪዎችን አላብሶት ከርሟል። ከመጀመሪያው ተሃድሶ በኋላ በሰላ ትግል ተኮርኩመው አንገታቸውን የቀበሩት ትምክህትና ጠባብነት እንዲያንሰራሩ ዕድል ሰጥቷቸዋል። የውስጠ ድርጅት ትግሉ መዳከም አድርባይነትና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባሮች እንዲንሰራፉ ምቹ መደላድል ሆኗል፡፡ እነዚህ ድርብርብ ችግሮች በእርግጥም ኢሕአዴግን መስቀለኛ መንገድ ላይ አቁመውታል፡፡

ይህ ማለት ግን ኢሕአዴግ ችግሩም መፍትሔው የጠፋበትና በመላምት ዕርምጃዎችን የሚወስድ ነው ማለት አይደለም፡፡ በጊዜያዊ ችግሮች እጁን ተጠምዝዞ እነኛን ቀይ መስመሮቹን ያነሳል ማለትም አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ ያጋጠሙትን ጊዜያዊ ችግሮች ከነምንጫቸው መረዳት ብቻ ሳይሆን፣ የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ መፍትሔያቸውንም ጭምር ጠንቅቆ ያውቃቸዋል፡፡ ለዚያም ነው እነዚህ ችግሮች የሚቀዱት በራሱ በፓርቲው ውስጥ ካሉ የአመለካከትና የተግባር ዝንፈቶች መሆኑን በመገምገም መሠረታዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ንቅናቄ ውስጥ መግባት አማራጭ እንደሌለው በፓርቲ ደረጃ ታምኖበት ዳግም ጥልቅ ተሃድሶው የተጀመረው።

ተሃድሶው በተቀመጠለት አቅጣጫ መሠረት ከኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚና ከምክር ቤቱ አባላት ጀምሮ በየብሔራዊ ድርጅቶቹም ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ እስከ አባላት ድረስ ዘልቋል። በድርጅቱ ውስጥ ብቻም ሳይወሰን ወደ መንግሥት ሠራተኞችና መላው ሕዝብ ዘልቆ በመካሄድ ላይ ነው። በአፈጻጸም አቅጣጫው ብቻ ሳይሆን በይዘቱም ቀድሞ የተቀመጡለትን ግቦች በሚያሳካ መልኩ ነው ተሃድሶው እየተፈጸመ ያለው።

እዚህ ላይ በቅርቡ በወጣችው የድርጅቱ ልሳን አዲስ ራዕይ ላይ እንደሰፈረው ከአንዳንድ አመራሮች ስለተሃድሶውና ስለሚጠበቀው ውጤት የተሰጡ መግለጫዎች፣ ጉጉት የሚጨምሩና ከመግለጫዎቹ ማግሥት ተዓምር የሚመጣ የማስመሰል ዝንባሌ የሚታይባቸው ነበሩ፡፡ ይህ ሁኔታ በአንድ በኩል ተሃድሶውን ለሁሉም በሽታዎች መድኃኒት (Panacea) አድርጎ የመረዳት ችግር ሲያስከትል በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉም በሽታዎች አሁኑኑ (Now or Never) እንዲድኑ የመፈለግ ዝንባሌና በሒደቱ እዚህም እዚያም የመጡ ለውጦችን አሳንሶ የማየት ዝንባሌን ፈጥሯል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ገና በጅምር ጉዞ ላይ የሚገኘው የተሃድሶ ንቅናቄ ኢሕአዴግ እንደ ልማዱ ራሱን በራሱ አርሞ አንፀባራቂ ድሎችን ማስመዝገቡን እንደሚቀጥል ተስፋ የሰጡ ውጤቶችም የተመዘገቡበት ነው፡፡ የሥርዓቱ አደጋ ተብለው በተለዩ ጉዳዮችና የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄውን አስፈላጊ ባደረጉ መሠረታዊ ነጥቦች ላይ በሁሉም ደረጃዎች ግልጽነት እንዲፈጠርባቸው፣ መግባባት ላይ እንዲደረስና ከችግሮቹ ለመላቀቅ ቁርጠኝነት እንዲያዝ ማድረግ ተችሏል፡፡ በፌዴራልና በክልል ከፍተኛ አመራር ደረጃ ሥልጣንን የኑሮ መሠረት የማድረግ አመለካከትና ተግባርን የሚሰብር በብቃትና ልምድ ላይ የተመሠረተ ሹመት ተሰጥቷል፡፡

በየደረጃው ባሉ የአስተዳደር እርከኖችም በውጤታማነት ላይ የተመሠረተ የሰው ኃይል ምደባ ማስተካከያ ተደርጓል። የአመለካከት ብልሽታቸው በተጨባጭ ደረቅ ወንጀል ላይ እንዲሳተፉ ላደረጋቸው አመራሮች፣ ከፖለቲካዊና ከአስተዳደራዊ ዕርምጃዎች (ማስጠንቀቂያ፣ ከኃላፊነት ዝቅ ማድረግ፣ ከማዕከላዊ ኮሚቴ ወይም አባልነት ማገድ፣ ወዘተ…) በተጨማሪ ሕጋዊ ተጠያቂነት እያስከተለ ነው። የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በጊዜ የለንም መንፈስ የመፍታት፣ በተለይ ደግሞ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራን ቀዳሚ አጀንዳ የማድረግ ንቅናቄ ውስጥ ተገብቷል፣ ለውጦችም በመታየት ላይ ናቸው፡፡

የእነዚህና ሌሎች ማስተካከያዎች ድምር ውጤት ኢሕአዴግን ስቶት ወደነበረው ወደቀደመ አብዮታዊነቱ እንዲመለስ ዕድል የፈጠረ፣ በእሱ የሚመራውን መንግሥትም የሕዝቡን አንገብጋቢ የልማት ጥያቄዎች በተለይም የወጣቶችን የሥራ ዕድል ጥያቄ ለመመለሰስ ወደሚችልበት ቁመና የመለሰ ነው፡፡ እናም አሁን ኢሕአዴግ የሚገኝበት ቁመና እነሱ እንደሚሉት ደካማ አቋም ሳይሆን እንደ ወትሮው በፈተና (An Acid Test) ውስጥ ካለፈ በኋላ ለላቀ አገራዊ ተልዕኮ ራሱን ያዘጋጀበት ነው፡፡

በሌላ በኩል አገራዊ ወቅታዊ ሁኔታውን ታሳቢ በማድረግ ኢሕአዴግ ፈተና ውስጥ ገብቶ ነበር ሲባል፣ ፈተናው የመነጨው የሚመራው ሕዝብ ካነሳቸው ፍትሐዊና ተገቢ ጥያቄዎችና ይህንኑ የሕዝብ ጥያቄ እንዳይመልስ ቀይዶ ከያዘው የራሱ የድርጅቱ ውስጣዊ ችግር እንጂ ከተቃዋሚ ፓርቲዎቹ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ሕዝባዊ ተቃውሞው በሁከትና በረብሻ መልኩ በተገለጠበት ወቅትም ሆነ ከዚያ በፊት ተቃዋሚዎች የሚያነሱትና ሕዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ለየቅል ነበሩ፡፡ ሕዝቡ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ከሚችለው በላይ ሸክም እንደሆነበት ሲገልጽ፣ እነርሱ ግን ከውስጥ ንትርክ በተረፋቸው ጊዜ እንደ ወትሯቸው በሕግ ቁጥጥር ሥር ያሉ የፓርቲ አመራሮች እንዲፈቱላቸው ሲጠይቁ ነው የከረሙት፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ረብሻ በተነሳበት ወቅትም ብሶት ወደ አደባባይ ያወጣቸው ወጣቶች የፈጸሙትን ጥፋት ከማጃገን ያለፈ ሚና አልነበራቸውም፡፡

አሁን ባለንበት መድረክም ቢሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎች አገራችንንና ሕዝቦቿን ካሉበት ወቅታዊ ችግር የሚያወጣ ፍቱን መድኃኒት ይዘው ሊቀርቡ ይቅርና የችግሮች ሁሉ ምንጭ አድርገው የሚቆጥሩትን ኢሕአዴግን በተባበረ ድምፅ ለመሞገት የሚያስችላቸውን ኅብረት መፍጠር  አልቻሉም፡፡ በዚሁ ሳምንት 21 አገር አቀፍ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢሕአዴግን እንዴት ተቀናጅተው መሞገት እንደሚችሉ ለመምከር ቀጠሮ ቢይዙም፣ 12 ብቻ መገኘታቸውንና እነሱም ቢሆኑ ሳይስማሙ መለያየታቸውን ልብ ይሏል፡፡

በመሆኑም ወቅታዊ ሁኔታው ለኢሕአዴግ የህልውና ጥያቄ ሆኖበት ለለውጥ ሲያነቃንቀው ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን የፈጠረላቸው አዲስ ነገር የለም ማለት ይቻላል፡፡ በአጭሩ ኢሕአዴግ በመታደስ ላይ ሲሆን፣ ተቃዋሚዎች ግን ባሉበት እንደቆሙ ናቸው፡፡ በዚህ ዓይነት ነባራዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የሚደረግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ደግሞ በሰጥቶ መቀበል መርህ ይመራ ካልሆነ በቀር፣ የኢሕአዴግን እጅ በመጠምዘዝ ጠብ የሚል ነገር አይኖረውም፡፡

ከተጨባጭ ሁኔታው በመነሳት ጉዳዩን ለማብራራት በማሰብ እንጂ፣ ኢሕአዴግ በታሪኩም ቢሆን በፈታኝ ወቅቶች ለሚደረገቡት የውስጥም ሆኑ የውጭ ጫናዎች እጁን የመስጠት ታሪክ እንደሌለው ይታወቃል፡፡ ፓርቲው ሥልጣን ከያዘ ወዲህ ያሉትን ዓመታት ለፈተሸ እንኳን በምን ያህል ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ራሱን ብቻ ሳይሆን አገርና ሕዝብን እያዳነ የመጣ ፓርቲ መሆኑን መገንዘብ አይከብድም፡፡ በግንባሩ ውስጥ የተካሄደው የመጀመሪያው ተሃድሶ፣ አባል ብሔራዊ ድርጅቱ በሆነው ደኢሕዴን ውስጥ የተካሄደው ዳግም ተሃድሶ፣ በድኅረ 1997 ምርጫ በተለይ በከተሞች የተከሰተው ነውጥ መዳረሻዎች ለዚህ ዓቢይ ምስክሮች ናቸው፡፡

እነዚህን ፈታኝ ሁኔታዎች እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የውጭ መንግሥታትና ለጋሽ ድርጅቶች ከአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊው መስመሩ ሊያስወጡት ጥረዋል፡፡ ኢሕአዴግ ግን በሁሉም ክስተቶች ዴሞክራሲያዊ መድረኮችን በመክፈት፣ ችግሩን ወደ ውስጥ በማየት፣ ወቅታዊና ዘለቄታዊ መፍትሔዎችን በመተለም ቀድሞ ከነበረበትም ይበልጥ ጠንክሮ፣ ፈተናን ወደ መልካም አጋጣሚ የመቀየር ብቃቱን አስመስክሮ ወጥቶባቸዋል፡፡

በአንፃሩ በሌሎቹ የአገራችን ፓርቲዎች የተለመደው ግን ችግር ሲያጋጥማቸው ፀረ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እርስ በርስ መናከስና የችግሩን ምንጭ ከውስጣቸው ከመፈለግ ይልቅ ውጫዊ ሰበቦችን መደርደር ነው፡፡ ለዚያም ነው ከፈተና በኋላ መዳረሻቸው አንድም መጥፋት አሊያም መሰንጠቅ ሆኖ የኖረው፡፡ በዚህ ዓይነት በወቃሽ ከሳሽነት (Blame Shifting) አባዜ ውስጥ ያሉ ኃይሎች አሁን ኢሕአዴግ የገጠመውን ፈተና ለፓርቲው የዓለም መጨረሻ አድርገው ቢወስዱት ከባህሪያቸው የሚመነጭ ነውና አዲስ ተደርጎ አይወሰድም፡፡ ሆኖም እነዚህ አስተሳሰቦች የሚገዛቸው ካገኙ ውይይቱና ድርድሩ ፍሬ አልባ እንዲሆን በር የሚከፍቱ ናቸውና መጋለጥና መነቀፍ አለባቸው፡፡

ነባራዊ ሁኔታውም ሆነ ታሪካዊ ዳራው ይህ ሆኖ ሳለ ታዲያ ኢሕአዴግ ከፓርቲዎች ጋር ለመወያየትና ለመደራደር የፈለገበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ኢሕአዴግ መላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለ17 ዓመታት ያካሄዱትን የፀረ ደርግ አገዛዝ ትግል በመምራት ለፍጻሜ ባደረሰባቸው የመጨረሻዎቹ ቀናት እንኳን ሳይቀር የደርግ የኃይል ሚዛን መሽመድመዱን እያወቀም ቢሆን ከጠላቱ ጋር ለድርድር የተቀመጠ ድርጅት ነው፡፡ በ2002 ዓ.ም በተካሄደው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ከፍተኛ ውጤት (Landslide Victory) ተጎናፅፎ እንኳን የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጋብዞ ወራት የፈጀ ድርድር ማድረጉ ይታወሳል። ኢሕአዴግ እንዲህ በጦር ግንባርም ሆነ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ አሸናፊ ሆኖ ሳለ እንኳን ከተቀናቃኞቹ ጋር ለመደራደር ዝግጁ የሆነው፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ካለው ፅኑ እምነት በመነሳት ነው፡፡

ኢሕአዴግ በፕሮግራሙ ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕገ መንግሥቱና በአገሪቱ ሕጎች መሠረት ዓላማቸውን በሰላማዊ መንገድ እስካራመዱ ድረስ ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸውን በጥብቅ ማክበርና ማስከበር እንዳለበት፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ዓላማውን ለማሳካት ሲንቀሳቀስም ፓርቲዎቹን በዴሞክራሲያዊ፣ በሕጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ብቻ ሊታገላቸው እንደሚገባ አስቀምጧል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአንድም የምርጫ ጣቢያ ማሸነፍ ካልቻሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር ቁርጠኝነቱን ያሳየው፣ የፓርቲዎችን የኃይል ሚዛን ግምት ውስጥ በማስገባት ሳይሆን ለዚሁ ድርጅታዊ መርሁ ካለው ተገዥነት ነው፡፡

እንደሚታወቀው በ2007 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ኢሕአዴግ በተወዳደረባቸው የምርጫ ክልሎች ሁሉ አብላጫ ድምፅ በማምጣት አሸንፏል፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉም መራጭ ለኢሕአዴግ ድምፁን ሰጥቷል ማለት አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ ፍላጎቴን አያሟላልኝም ብለው የወሰኑ፣ ኢሕአዴግ ያሉበትን የአፈጻጸም ችግሮች መፍታት አይችልም ብለው ተስፋ የቆረጡ ወይም ተቃዋሚ ፓርቲ ፓርላማ ቢገባ ይሻላል ብለው ያመኑ ዜጎች ድምፃቸውን ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰጥተዋል፡፡ በአንዳንድ ትልልቅ ከተሞች እስከ 30 በመቶ የሚደርስ መራጭ ተቃዋሚዎችን መርጧል፡፡ ነገር ግን የመረጣቸው ፓርቲዎች በፓርላማ መቀመጫ አግኝተው ድምፁን ሊወክሉት አልቻሉም።

ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ የመረጠውን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ያልመረጡትንም መወከሉና ማገልገሉ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እነዚህ ወገኖች ይበጀናል የሚሉትን የፖለቲካና የኢኮኖሚ አላማዎች አንግቦ የሚንቀሳቀስላቸው፣ በሚወጡ አዋጆችና ደንቦችና በሚደረጉ ስምምነቶች ላይ ፍላጎታቸው እንዲደመጥ የሚገፋላቸው፣ አስፈጻሚውን አካል ከራሳቸው መብትና ጥቅሞች ተነስቶ የሚቆጣጠርላቸው እንደራሴ ቢኖራቸው የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ሁሉን አቀፍ (Inclusive) ያደርገዋል፡፡ ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በምርጫ 2002 ማግሥት ተቃዋሚዎች በፓርላማ ወንበር ቢኖራቸውም ባይኖራቸውም በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ተመካክረን እንሠራለን ማለታቸውም፣ ይህንኑ የተለዩ ሐሳቦች የሚደመጡበት መድረክ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ መጎልበት ያለውን ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡

በተጨማሪም ከፓርቲዎቹ ጋር የሚካሄደው ውይይት፣ ክርክርና ድርድር ለሰላማዊ የፖለቲካ ኃይሎች ሕጋዊ የመታገያ መድረክ ሆኖ ሲያገለግል እዚያው ሳለ ሕገወጥና የአመፅ አማራጭን ለመከተል የሚያማትሩ ኃይሎችን ፍላጎት የሚያመክን በመሆኑ፣ በሁለቱም ወገኖች እኩል ትኩረት ሊያገኝ የሚገባው ነው፡፡

በመጨረሻም በፓርቲዎቹ መካከል ለሚካሄደው ውይይት፣ ክርክርና ድርድር ሙሉ ፈቃደኝነቱን በማሳየቱ ኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን ሌሎቹም ተሳታፊ ፓርቲዎች ሊደነቁ ይገባቸዋል፡፡ በተለይም በውጭ ካለው ፅንፈኛ ኃይል የሚደርሳቸውን የአመፅ ጥሪና ሽንገላ ባለመቀበል ለሰላማዊ የትግል መድረክ ራሳቸውን ማዘጋጀታቸው ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው፡፡ ይሁንና ተቃዋሚዎች በእርግጥም አሁን አገራችን ያለችበት ሁኔታ የሚያሳስባቸው መሆኑን፣ ውግንናቸው በባሌም ሆነ በቦሌ ለሚመጣ ሥልጣን ሳይሆን ለሕዝብ ተጠቃሚነት መሆኑን የሚያረጋግጡልን ለሕዝብና ለአገር የሚበጅ የውይይት ሐሳብ ይዘው በመቅረብ ነው። በክርክርና ድርድር ወቅትም ኢሕአዴግ ከያዘው የተሻለ መደራደሪያ በማቅረብ ለሰላምና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው መጠናከር የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት አለባቸው፡፡ ኢሕአዴግ በተለይ ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸውን ሐሳቦች ለሕዝብና ለአገር ካላቸው ጥቅም አንፃር ብቻ መዝኖ፣ የሕግም ሆነ የአፈጻጸም ማስተካከያዎችን ለማድረግ ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...