ኢትዮጵያ ወደ አንድ ፓርቲ ሥርዓት በይፋ የተሸጋገረችው በ1980 ዓ.ም. ነው፡፡ ከዚያ በፊት በአገሪቱ ፓርቲ ማቋቋም በራሱ እንደ ከባድ ወንጀል የሚታይ ጉዳይ ነው የነበረው፡፡ በዚህ የተነሳ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ጽንሰ ሐሳብ ከ1983 ዓ.ም. በፊት ለነበረው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕይወት እንግዳ ነገር ነበር፡፡ የተደራጀና ተቋማዊ ተቃውሞን ማስተናገድ ለቅድመ ኢሕአዴግ የፖለቲካ ልሂቃን የማይታሰብ ነበር፡፡ ዛሬ ቢያንስ ከፎርማሊቲ አንፃር የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት፣ ከሥርዓቱ መገለጫዎች አንዱ ሆኗል፡፡ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግም ይህንኑ ሥርዓት ለመጀመሪያ ጊዜ በአገሪቱ በማስተዋወቁ ምሥጋናውን ይወስዳል፡፡
ይሁንና ከ2002 ዓ.ም. በኋላ በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ የለም የሚያስብል ደረጃ ላይ መድረሱ ክርክር የሚቀርብበት ጉዳይ አይደለም፡፡ ባለፉት ሁለት ጠቅላላ ምርጫዎች በፓርላማው የታየው የአንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ ምሥል ብቻ መሆኑ፣ ለዚህ ስምምነት ዋነኛ ማሳያ ሆኖም ያገለግላል፡፡ ይህም በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ኢትዮጵያ አንድ ደረጃ ወደኋላ በማለት ወደ አንድ ፓርቲ ሥርዓት ተሸጋግራለች ብለው እንዲሞግቱ ዕድል ሰጥቷቸዋል፡፡
ለእነዚህ አስተያየቶች ሩቅ ያልሆነው ገዢው ፓርቲ መሬት ላይ ያሉ ክርክሮችን ወደጎን በመተው፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ የአንድ ፓርቲ ሥርዓትን እንደማይፈቅድ ሲከራከር ይሰማል፡፡ ከዚህ ይልቅ በአገሪቱ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ የአውራ ፓርቲ ሥርዓት እየጎለበተ በመምጣቱ የሚገለጽ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪዎች በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት ሲገልጹ፣ በአንድ ፓርቲ ሥርዓት ሌሎች ፓርቲዎች ተደራጅተው በምርጫ እንዳይሳተፉ በሕግ ጭምር የሚከለከሉ እንደሆነና በአውራ ፓርቲ ሥርዓት ግን ሕጋዊና ሰላማዊ ፓርቲዎች በነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ቢሳተፉም ሁሌም የሚያሸንፈው ግን አንድ ፓርቲ ብቻ እንደሆነ ያሰምሩበታል፡፡ ኢሕአዴግ ባለፉት 25 ዓመታት በብቸኝነት አገሪቱን የመራው ፖሊሲና ስትራቴጂዎቹ በሕዝብ ተመራጭ በመሆናቸው እንደሆነ ሲከራከር መስማቱ አዲስ ነገር አይደለም፡፡
በመሠረቱ በ1987 ዓ.ም. ወደ ሥራ የገባው የኢፌዴሪ ሕገ መነግሥት ሰላማዊና ሕጋዊ ፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነትና በፍትሐዊነት በምርጫዎች እንዲሳተፉና እንዲንቀሳቀሱ መሠረታዊ ማዕቀፉን ያመቻቻል፡፡
አሁን ዋናው ጥያቄ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ በተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ውስጥ የተረጋገጡላቸው መብቶቻቸው በተግባር ይከበራሉ ወይ የሚለው ነው፡፡ ለበርካታ አስተያየት ሰጪዎች ከ1997 ዓ.ም. በኋላ የኢትዮጵያ አስተዳደር የለየለት ፈላጭ ቆራጭ ሆኗል፡፡ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ በተወሰነ መንገድ የሚለየው የገዢው ፓርቲና የመንግሥት ርዕዮተ ዓለምና የዕድገት ሞዴል ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥትም፣ ገዢው ፓርቲ ለረዥም ጊዜ የያዘውን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም አይሠሩም የሚለውን አቋሙን አጠናክሮ እንዲገፋበት ያበረታታው ይመስላል፡፡
ነገር ግን ይህ ሁሉ በ2008 እና 2009 ዓ.ም. በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በገዢው ፓርቲና በመንግሥት ላይ ተቃውሞዎችና አመፆች ከተካሄዱ በኋላ የተቀየረ ይመስላል፡፡ በግንቦት ወር 2007 ዓ.ም. በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ መቶ በመቶ በምርጫ ማሸነፉ በይፋ በተገለጸ በጥቂት ወራት ውስጥ በተጀመረው አውዳሚ አመፅ የተነሳ፣ ገዢው ፓርቲ የተለያዩ የማሻሻያ ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ ማስታወቁም አይዘነጋም፡፡ በተጨማሪ ገዢው ፓርቲ ከዚህ ቀደም ከሚታወቅባቸው አቋሞች ፍፁም በተለየ ሁኔታ በመደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆኑ መድረኮች የአገሪቱን ብዝኃነት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገንቢ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ መግለጽ ጀመረ፡፡ ከዚሁ ጋር በተገናኘም ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው የአንደኛ አላፊ የምርጫ ሥርዓት ላይ ማሻሻያ በማድረግ፣ የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ጋር በማዳቀል ተግባራዊ እንደሚሆን በይፋ አስታወቀ፡፡ ይህ የምርጫ ሥርዓትም በዘርፉ ባለሙያዎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የተሻለ ለማሳተፍ መፍትሔ መሆኑ ይነገርለታል፡፡
ከዚህ አንፃር በተቃውሞው ጎራ ያሉትን ፓርቲዎች ባሳተፈ ሁኔታ በገዢው ፓርቱና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ድርድር እንደሚኖር መጠበቅ ምክንያታዊ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ቃሉን በማክበር ለሁሉም አገር አቀፍ ፓርቲዎች የውይይትና የድርድር ጥያቄ ያቀረበው ከሁለት ወራት በፊት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ኢሕአዴግ ከ21 አገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋር አምስት ዙር ውይይቶችን አድርጓል፡፡ ስድስተኛውን ዙር ውይይትም መጋቢት 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ለማካሄድ ቀጠሮ ተይዟል፡፡ የእስካሁኖቹ ውይይቶች የውይይትና ድርድር ማድረጊያ ደንብ ላይ የተገደቡ ነበሩ፡፡
ውይይቶቹና ድርድሮቹ የሚካሄዱባቸውን ዝርዝር ሥነ ሥርዓቶች ለመወሰን በተደረገው ጥረትም 22ቱ አገር አቀፍ ፓርቲዎች በስምምነት ለመወሰን 12 ጉዳዮችን ለይተዋል፡፡ እነዚህም ጉዳዮች የድርድሩ ዓላማዎች፣ የድርድርና ክርክር ተሳታፊ ፓርቲዎች፣ የድርድርና የክርክር አባል ፓርቲዎችና የፓርቲ ተወካዮች ብዛት፣ ምልዓተ ጉባዔና ውሳኔ አሰጣጥ፣ የድርድር አጀንዳ ስለማቅረብና የማቅረቢያ ጊዜ ገደብ፣ እንዲሁም የድርድር አጀንዳ አወሳሰንና አጀማመር፣ የሚዲያ አጠቃቀም፣ የንግግርና የተናጋሪዎች አሰያየም፣ የድርድርና የክርክር አመራር፣ ታዛቢዎችና የሚኖራቸው ሚና፣ ሥነ ምግባርና ዲሲፕሊን፣ ውስጣዊ አደረጃጀት፣ አስተዳደርና የሎጂስቲክስ ድጋፍና የስብሰባ ቦታ ናቸው፡፡
ነገር ግን የደንቡ ዝርዝር ይዘቶች ላይ ውይይት ከመጀመራቸው በፊት የደንቡ ርዕስ ላይ ከፍተኛ ክርክር አድርገዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ‘ድርድር’ እንዲባል ምርጫቸው ቢሆንም፣ ኢሕአዴግና ሌሎች ጥቂት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ከድርድር ባሻገር ውይይት ወይም ክርክር በቂ የሚሆንባቸው ጉዳዮች ሊኖሩ እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በርዕሱ ላይ ‘ክርክር’ እና ‘ውይይት’ እንዲካተቱ ጠይቀዋል፡፡
‹‹ትኩረታችን ድርድር ነው፤›› ሲሉ በአፅንኦት የተናገሩት በተቃዋሚነት ለረዥም ጊዜ በመቆየት አቻ የማይገኝላቸው የወቅቱ የመድረክ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ በአገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ ባይፈጠር ኖሮ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንኳን ለድርድር ለውይይትና ለክርክርም ቢሆን ዕድል አያገኙም ነበር፡፡ የኢሕአዴግ ተወካዮች አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴና አቶ አብዱላዚዝ መሐመድን ባላስደሰተ ሁኔታ ይህን ስሜት ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ተጋርተውታል፡፡
አቶ አስመላሽ፣ ‹‹ኢሕአዴግ የሚፈራ ድርጅት አይደለም፡፡ በተፅዕኖ አይደለም ወደ ድርድር እየገባ ያለው፡፡ የምንወያየውና የምንደራደረው የዚህን አገር ሕዝብ ይጠቅማል ብለን ስለምናምን ነው፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ሽፈራውም በተመሳሳይ፣ ‹‹አገሪቱ አጣብቂኝ ውስጥ አይደለችም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
ተሳታፊ ፓርቲዎች የሦስቱን ቃላት ጥቅምና ጉዳት ከተለያዩ አቅጣጫዎች በዝርዝር ካዩ በኋላ ሦስቱንም ቃላት ለማካተትና እንደየአስፈላጊነቱ ለመጠቀም ተስማምተዋል፡፡ ይሁንና አቶ አስመላሽ ኢሕአዴግ ከየትኛውም ፓርቲ ጋር በየትኛውም ጉዳይ ድርድር፣ ክርክር ወይም ውይይት ለማድረግ ዝግጁ ነው ማለት የፖሊሲ ወይም የሕግ ለውጥ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ይኖራል ማለት እንዳልሆነ አስጠንቅቀዋል፡፡ አቶ አስመላሽ፣ ‹‹ስንደራደር አጀንዳዎችን እንመዝናለን፡፡ ኢሕአዴግ የራሱ ርዕዮተ ዓለም አለው፡፡ ከራሱ ርዕዮተ ዓለምና ፖሊሲ በመነሳት የሚቀበለውን ይቀበላል፣ የማይቀበለውን ደግሞ አልቀበልም ይላል፤›› ብለዋል፡፡
በርዕሱ ላይ ከተደረገው ሞቅ ያለ ክርክር በበለጠ የድርድሩ ዓላማዎች ሰፋ ያለ ውይይትና ክርክር ጋብዞ ነበር፡፡ በዚህም ውይይት ፓርቲዎቹ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ስላለበት ደረጃ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተወያይተዋል፡፡ በውይይታቸው መጨረሻ በአገሪቱ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሥልጣን በምርጫ ሥርዓት ብቻ ለአሸናፊ የፖለቲካ ፓርቲ የሚተላለፍበትን ሥርዓት ይበልጥ ለማስፋት፣ በድርድር ወቅት የሚነሱ የተለያዩ ሐሳቦችን እንደ ግብዓት በመጠቀም መሠረታዊ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ሕጎችን ለማሻሻልና የአፈጻጸም ጉድለቶችን ለማስተካከል፣ የፓርቲዎችን የዴሞክራሲያዊ የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከርና ለአገሪቱ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ዕድገት የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ለማጎልበት፣ ሕዝቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን አማራጭ ሐሳብ፣ ያላቸውን ሐሳብ ተገንዝቦ በዕውቀትና በመረጃ ላይ ተመሥርቶ እንዲንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር፣ ለብሔራዊ መግባባት አስተዋጽኦ ለማድረግ፣ እንዲሁም የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት፣ ድርድሩን እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ተስማምተዋል፡፡
በዚህ ስምምነት ገዢው ፓርቲ በሥራ ላይ ያሉ ሕጎችን በተለይም ከዜጎች የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ጋር የተገናኙ ሕጎችን በድጋሚ በማጤን ለመለወጥ ፈቃደኛነት ማሳየቱም ፍፁም የሆነ የአቋም ለውጥን የሚያሳይ ነው፡፡ ሆኖም እንደተጠበቀው መድረክ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የሐሳብ ልዩነት ማሳየቱ አልቀረም፡፡ ለአብነት ያህልም ከሚሻሻሉት ሕጎች መካከል ሕገ መንግሥቱ የሚካተት ስለመሆኑ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ የኢሕአዴግ ተወካዮች ሕጎችን ለማሻሻል ስምምነት እስከተደረገ ድረስ የሚሻሻለው የትኛው ሕግ ነው የሚለው የሚታወቀው በአጀንዳው ክርክር እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡
የመድረክ ሌላው የልዩነት ሐሳብ ድርድሩ ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ እንዲሆን ለማረጋገጥና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ዕውን ለማድረግ መዋል አለበት በማለት ያነሳው ሐሳብ ነው፡፡ ይህም ሐሳብ ከኢሕአዴግ ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡ አቶ አስመላሽ፣ ‹‹የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት በአገሪቱ የለም ወይም ተቀባይነት ያለው ምርጫ ተካሂዶ አያውቅም እያልን ነው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ጥያቄውን ይበልጥ ግልጽ ያደረጉት አቶ ሽፈራውም፣ ለሁለት የሥራ ዘመናት የፓርላማው አባል ለነበሩት ፕሮፌሰር በየነ፣ ‹‹እርስዎ ተወዳድረው ፓርላማ የገቡት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ዕውን ስለሆነ አይደለም እንዴ?›› የሚል ጥያቄ አቅርበውላቸዋል፡፡
በአነስተኛና ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ከመጠን ያለፈ መዘግየት መታየቱን በመጠቆም የመድረኩ መሪዎች ጉዳዮቹ በፍጥነት እንዲቋጩ ትብብር እንዲያደርጉ ጥቂት ፓርቲዎች መጠየቃቸውም አልቀረም፡፡ በዚህም የተነሳ የካቲት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደው ውይይት በበርካታ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ሊደረግ ችሏል፡፡ ይህም የተሳታፊ ፓርቲዎች ማንነት፣ የእያንዳንዱ ፓርቲ ተወካዮች ብዛት፣ ምልዓተ ጉባዔና ውሳኔ አሰጣጥ፣ እንዲሁም ማን አደራዳሪ ይሁን በሚሉት ጉዳዮች ላይ ስምምነት እንዲፈጠር በማድረጉ የሚገለጽ ነው፡፡
በተደጋጋሚ በፖለቲካ ተንታኞች እንደሚገለጸው ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ላሉበት የማይፈለግ ደረጃ ኢሕአዴግ ብቸኛው ተጠያቂ አካል አይደለም፡፡ በከፊል ራሳቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሕዝቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገሪቱ የፖለቲካ ሕይወት ብዙም ትርጉም ያለው ሚና እንዳይኖራቸው ለማድረግ ተጠያቂ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሚከሰሱባቸው ጉዳዮች መካከል እጅግ ደካማ መሆናቸው፣ ብሔርን መሠረት ያደረጉና የተከፋፈሉ መሆናቸው፣ ከሁሉም በላይ ለራሳቸው ክብር ይበልጥ ትኩረት በሚሰጡ ግለሰቦች የሚመሩ መሆናቸው፣ ጠንካራ የድጋፍ መሠረትና አማራጭ ፖሊሲ የሌላቸው መሆናቸው፣ እንዲሁም እርስ በርስ በጥርጣሬ የሚተያዩና የሚገዳደሩ መሆናቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በአምስት ዙር ውይይት ወቅት እነዚህ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ባህሪያት ከተወሰኑ ፓርቲዎች በግልጽ ተንፀባርቀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም መሰል መድረኮች እጅግ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብቅ የሚሉ መሆናቸውን በመጥቀስ መድረክ ውይይቱን በበጎ ጎኑ እንደሚያየው ገልጿል፡፡ ይሁንና የተሳታፊ ፓርቲዎች ማንነት ላይ ውይይት ሲካሄድ ባለፈው ጠቅላላ ምርጫ ባቀረበው የዕጩ ተወዳዳሪዎች ቁጥር የተነሳ ዋነኛ ተቃዋሚ በመሆኑ ከኢሕአዴግ ጋር ብቻ ለብቻ ለመደራደር ጥያቄ አቅርቧል፡፡ በዚህ የመድረክ ሐሳብ ላይ ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ማለት ይቻላል ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ ለሐሳቡ ተቃውሞዋቸውን የገለጹበት መንገድና ቋንቋም ደካማውን የመቻቻል ባህላቸውን ገሃድ አውጥቷል፡፡ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፣ ኢሕአዴግ ከየትኛውም ፓርቲ ጋር በጋራም ሆነ በተናጠል የሚያደርገው ድርድር ሌሎች ፓርቲዎችንም ተጠቃሚ እስካደረገ ድረስ ኢዴፓ ድርድሩን ግላዊ የማድረግ ፍላጎት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡ ሌሎች ፓርቲዎችም ተመሳሳይ አመለካከት ቢኖራቸው መልካም እንደሆነ አሳስበዋል፡፡ የኢዴፓ የጥናትና ምርምር ክፍል ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬም ከኢሕአዴግ ጋር በተወካይ አማካይነት መደራደር አስፈላጊ ከሆነ፣ ወይም ለፓርቲዎች ደረጃ ማውጣት አስፈላጊ ከሆነ ቅድሚያ መሥፈርት ወጥቶ ስምምነት ሊደረግበት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ከተሳታፊ ፓርቲዎች ማንነት ጋር በተገናኘ ሌላው አከራካሪ የሆነው ከሰማያዊ ፓርቲ አመራር ጋር የተያያዘው ያልተቋጨ ጉዳይ ነው፡፡ የፓርቲዎቹ ውይይት ሲጀመር ሰማያዊ ፓርቲ በአቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) ተወክሎ ነበር፡፡ ይሁንና በመሀል የውይይቱ ሰብሳቢ አቶ ይልቃል የውይይት አዳራሹን ለቀው እንዲወጡ አድርገዋል፡፡ ውሳኔው መሠረት ያደረገው ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተገኘን መረጃ እንደሆነም በወቅቱ ተገልጾ ነበር፡፡ መረጃው አቶ ይልቃልን በአመራርነት የሚቀናቀኑት አቶ የሺዋስ አሰፋን ተተኪ አድርጓል፡፡ ነገር ግን ምርጫ ቦርድ የሰማያዊ ፓርቲ ትክክለኛ መሪ ማን እንደሆነ ከወራት በፊት እንዲወስን ለቀረበለት ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም፡፡ አንዳንድ ፓርቲዎች ዋናው አጀንዳ ላይ ድርድር ከመጀመሩ በፊት ይህ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ጠይቀዋል፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ጊዜያዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩ ላይ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡ ኢሕአዴግ ጉዳዩ በአጀንዳነት ካልቀረበ ለውይይት ሊቀርብ እንደማይገባ ተቃውሞ አሰምቷል፡፡
በውይይቱ ተሳታፊ ፓርቲዎች አገር አቀፍ ቢሆኑም ኢሕአዴግ በፓርላማ መቀመጫ ያላቸው ክልላዊ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ ይሁንና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሐሳቡን ባለመቀበላቸው ውድቅ ሆኗል፡፡
ፓርቲዎቹ በቀሩት ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማድረግ እንዳይችሉ ሁለት ጉዳዮች ላይ ስምምነት አለመደረጉ ይዟቸዋል፡፡ ኢሕአዴግ ፓርቲዎቹ ጋር በተናጠልም ሆነ በጋራ ጠባብ ብለው ቢመርጡ ለመደራደር ፈቃደኝነቱን አሳይቷል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ ወይም በተናጠል መደራደር ምርጫቸው መሆኑን ለመወሰን ለመጋቢት 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ ይህን ሲወስኑም እያንዳንዱ ፓርቲ ስንት ተወካዮች ይኑሩት የሚለውን መወሰን ቀላል መሆኑ ላይ ተስማምተዋል፡፡ በመርህ ደረጃ ምልዓተ ጉባዔው 2/3ኛ እንዲሆን ስምምነት የተደረገ ሲሆን፣ አንድ ለአንድ ለሚደረገው ድርድር ደግሞ የሁለቱም ወገኖች መገኘት የሚፈለግ ይሆናል፡፡ ውሳኔ አሰጣጥን በተመለከተ በስምምነት እንዲሆን ተወስኗል፡፡
በመጨረሻም የአደራዳሪዎች ጉዳይ በይደር ተላልፏል፡፡ ነገር ግን ሁለት ምርጫዎች ቀርበዋል፡፡ አንዳንድ ፓርቲዎች ገለልተኛና ፕሮፌሽናል አደራዳሪ እንዲኖር ጠይቀዋል፡፡ በሌላ በኩል ፓርቲዎቹ በዙር ራሳቸው ያደራድሩ የሚል ሐሳብም ቀርቧል፡፡ ፓርቲዎቹ ይህንና የመሳሰሉ ሌሎች የደንቡ ክፍሎች ላይ መጋቢት 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ተስማምተው ዋናው ድርድር በቅርቡ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡