አቶ ኑረዲን መሐመድ፣ በንግድ ሚኒስቴር የአክሲዮንና የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ጉዳዮች ድጋፍና ክትትል ዳይሬክተር
በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት በአክሲዮን ኩባንያዎች ደረጃ የሚቋቋሙ ኩባንያዎች ቁጥር በርካታ ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ እንደ አነሳሳቸው መዝለቅ አልቻሉም፡፡ በጅምር በቀሩት የአክሲዮን ኩባንያዎች ውስጥ ተፈጠረ የሚባለው ችግር ከየአቅጣጫው መሰማት ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃም ከ430 በላይ የአክሲዮን ኩባንያዎች ቢኖሩም ሥራ ላይ ያሉት ከ200 የሚበልጡ አይደሉም፡፡ ብዙዎቹም ባሰቡት ያህል አልተራመዱም፡፡ በመኖርና ባለመኖር መካከል ያሉም ጥቂት አይደሉም፡፡ ዛሬም በአክሲዮን ኩባንያዎች ውስጥ አሉ የሚባሉ ችግሮች በእንጥልጥል ላይ ናቸው፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጉዳዩ የሚመለከተው የንግድ ሚኒስቴር በሥሩ እነዚህን ተቋማት የሚመለከት አንድ ራሱን የቻለ ዳይሬክቶሬት ለማቋቋም የተገደደው፣ በአክሲዮን ኩባንያዎች ውስጥ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች በመበራከታቸው እንደሆነ ይታመናል፡፡ ሚኒስቴሩ አሉ የተባሉትን ችግሮች ለመፍታት፤ እንደ መፍትሔ አድርጎ ካሰባቸው ጉዳዮች መካከል፣ ወደፊት የሚቋቋሙትም ሆነ ነባሮቹ የአክሲዮን ኩባንያዎች ሊገዙበት የሚገባ አንድ ሕግ ያስፈልጋል የሚል ነው፡፡ በዚህ መሠረት አዲስ ረቂቅ አዋጅ በማሰናዳት ለውይይት ሊያቀርብ መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህ አዋጅና በአሁኑ ወቅት በንግድ ምክር ቤቶች አካባቢ እየታዩ ያሉ የተለያዩ ችግሮችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ዳዊት ታዬ የንግድ ሚኒስቴር የአክሲዮን፣ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጉዳዮች ድጋፍና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ኑረዲን መሐመድን አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር:- ንግድ ሚኒስቴር የአክሲዮን ኩባንያዎች እንደሚገዙበት ያመነበትን አዲስ አዋጅ ለማውጣት ስታዘጋጁ ቆይታችኋል፡፡ ረቂቁንም አሰናድታችኋል፡፡ ይህ አዋጅ አጠቃላይ ይዘቱ ምንድነው?
አቶ ኑረዲን፡- የአክሲዮን ማኅበራት አሠራር አዋጅ የተቀረፀበት የተለያዩ ምክንያቶች አሉት፡፡ ዋነኛ ምክንያቱ ከ50 ዓመታት በላይ ባገለገለው የንግድ ሕግና በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ውስጥ ያልተካተቱ ክፍተቶችን እንዲሞላ ነው፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት የአክሲዮን ማኅበራት ምሥረታ ታሪክ፣ በይበልጥ ደግሞ ካለፉት አሥር ዓመታት ወዲህ እያደገ ከመጣው የአክሲዮን ማኅበራት አመሠራረት ጋር ተያይዞ ቁጥጥር ማድረግ በማስፈለጉ ነው፡፡ ሕጋዊ መሠረት ማስያዝ ስለሚገባ የተወሰደ ዕርምጃ ነው፡፡ በባለአክሲዮኖችና በቦርድ ዳይሬክተሮች፣ በማኔጅመንት አባላትና በሦስተኛ ወገን መካከል ያሉ ጉዳዮችን ሕጋዊ በሆነ አግባብ ለመፍታት የሚያስችል መሠረት እንዲኖረው በማስፈለጉ ይህ አዋጅ እንዲሰናዳ እያደረግን ነው፡፡ እስከ ዛሬ ከነበሩ ልማዶች ያየነው የቦርዱና የማኔጅመንቱ ግንኙነት ግልጽ አይደለም፡፡ በአክሲዮን ኩባንያዎች እንቅስቃሴ ውስጥ አነስተኛ መጠን ያላቸው ባለአክሲዮኖች ሚና ጎልቶ የወጣ አይደለም፡፡ ትልልቅ የአክሲዮን ድርሻ ያላቸው ወይም በድምፅ የሚያሸንፉ ከፍተኛ ባለአክሲዮኖች ብዙ ጊዜ በቦርድ ምርጫዎች ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ የቦርድ አመራሮችን፣ የኦዲት ሪፖርቶችን በጠቅላላው የአክሲዮን ኩባንያዎችን አካሄድ ጭምር የሚወስኑት እነዚሁ ትልልቅ ባለድርሻዎች ናቸው፡፡ ይህም አነስተኛ የአክሲዮን ድርሻ የያዙ ባለአክሲዮኖችን መብት በማስጠበቅ ረገድ ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን ለመድፈን የሚያስችል የአክሲዮን ማኅበራት አዋጅ አስፈላጊ ሆኗል፡፡
ሌላው ከአክሲዮን ኩባንያዎች አሠራር ጋር ተያይዞ እንደ ችግር የታየው የቦርድ አመራሮች ምርጫ ነው፡፡ ቦርድ እንዴት ሊመረጥ እንደሚችል ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ ቦርድ እንዴት ይመራል? የቦርድ አመራርና አመራረጥ ምን መሆን እንዳለበት ሕጋዊ የሆነ የመቆጣጠሪያና የማስፈጸሚያ ሕግ የለም፡፡ እስካሁን ሲሠራበት የነበረው በድፍኑ ቦርድ ይመረጣል ይላል፡፡ ቦርድ ለስንት ዓመት እንደሚያገለግልም አስቀምጧል፡፡ ነገር ግን በተደጋጋሚ በቦርድ አመራርነት መቀመጥ የሚያመጣውን ችግር አያሳይም፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ምርጫ ሳይደረግ የቦርድ አባላት ረዥም ጊዜ ቢቆዩ ምን ዕርምጃ ይወሰዳል? ብለህ ብትጠይቅ አጥጋቢ መልስ አታገኝም፡፡ ወይም አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ለማጥራት አዲሱ አዋጅ ምላሽ ይሰጣል፡፡
ሪፖርተር:- ከንግድ ሕጉ ውጪ በአክሲዮን ኩባንያዎች አመራር ላይ የታየው ክፍተት ይህ ብቻ ነው?
አቶ ኑረዲን፡- ሌሎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ቦርድ አክሲዮን ማኅበሩን ማስተዳደር ባልቻለበት ወቅት ምን ማድረግ ይችላል? ሲባል አሁን ባለአክሲዮኖች ፍርድ ቤት ሄደው ነው ችግሮቹ እንዲፈቱ እየተደረገ ያለው፡፡ ከዚህ በመለስ ችግሮች ሊፈታበት የሚቻልበት አግባብ የለም ወይ? እስካሁን ባለው ሕግ አደራጅና መሥራች አንድ ስለመሆናቸው ብቻ ነው የተቀመጠው፡፡ አደራጅ ምን ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል? አደራጁ ምን ያህል ተዓማኒ ነው? አደራጁ ምን ዓይነት ግለ ታሪክ አለው? የሚለው ንግድ ሕጉ ውስጥ አልተቀመጠም፡፡ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ ግን አደራጆች፣ የቦርድ አባላት፣ የማኔጅመንት አባላት የግል ታሪክ ሊታይ እንደሚገባ የሚደነግጉ አንቀጾች ይኖሩታል፡፡ አመራሮቹ በየስድስት ወራት የኩባንያዎቻቸውን እንቅስቃሴ የሚያሳይ ሪፖርት እንዲያቀርቡ ሁሉ የሚያስችል አዋጅ ነው፡፡
ሪፖርተር:- በተለያዩ ደረጃዎች የሚቀመጡ የአክሲዮን ኩባንያዎች አመራሮች የግል ታሪክ ይታያል የሚለው ግልጽ ቢሆን?
አቶ ኑረዲን፡- በቦርድ አባልነት ወይም በአደራጅነት የሚሠራ ሰው ከዚህ በፊት ወንጀል የሠራ (ብላክ ሊስት) ውስጥ የገባ ከሆነ የአክሲዮን ማኅበራት አደራጅ መሆን እንደማይችል ለማድረግ ነው፡፡ ወንጀል ያለባቸው ሰዎች በማደራጀትም ሆነ በአመራርነት እንዳይሳተፉ ለተቆጣጣሪው የመከልከል ሥልጣን መስጠት የሚያስችልና እንዲህ ያሉ ክፍተቶች የሚደፍን አሠራር በአዋጁ ውስጥ አስቀምጠናል፡፡ ኩባንያዎች ችግር ሲገጥማቸው ሞግዚት እንዴት ሊሰየምላቸው ይችላል? ሞግዚቱስ ምን ዓይነት ሥራ ሠርቶ ሊመጣ ይችላል? የሚለውን ደግሞ ከንግድ ሕጉ በተጨማሪ በዚህ አዋጅ ውስጥ ተብራርቶ እንዲካተት ተሞክሯል፡፡
ሪፖርተር:- ከአክሲዮን ኩባንያዎች ጋር በተያያዘ ብዙ ጊዜ የሚሰሙ እሮሮዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ እሮሮዎች ለዚህ አዋጅ መነሻ ናቸው ማለት ይቻላል?
አቶ ኑረዲን፡- አንዱ እሱ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የአክሲዮን ማኅበራት ተጀምረው ሥራቸውን መጨረስ አለመቻላቸው ነው፡፡ ብዙዎቹ የአክሲዮን ኩባንያዎች ለዓመታት ተንጠልጥለው መቅረታቸውም ለአዋጁ መውጣት እንደ ምክንያት ሊወሰድ ይችላል፡፡ ችግራቸው ምንድነው? ብለን የዳሰሳ ጥናት አድርገናል፡፡ ከዚህ በመነሳት በመንግሥት ወይም በሪጉላቶሪ አካላት መፈታት የሚችሉ ነገሮችን ለማካተት ተሞክሯል፡፡ በባለአክሲዮኖች መካከል ያለመግባባት ቢፈጠር በራሳቸው መንገድ መፍታት የሚያስችላቸው ዕድል በአዋጁ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ በዚህም መነሻነት ከመደበኛና ከድንገተኛ ጉባዔ ውጪ ኩባንያው ችግር ላይ ነው በሚባልበት ወቅት አስቸኳይ ጉባዔ መጥራት የሚቻልበትን መንገድ ያሳያል፡፡ ጣልቃ ሊገባ የሚቻልበት አግባብ ምን ሊሆን እንደሚችል በማስቀመጥም ክፍተቶችን ለመድፈን ነው እየሞከርን ያለነው፡፡ እነዚህ የአክሲዮን ማኅበራቱ ከታየባቸው ችግሮች በመነሳት በአዋጁ የተካተቱ ናቸው፡፡ የዓለም ልምድ ምንድነው? ብለን በማየትም የተዘጋጀ ረቂቅ ነው፡፡ በፋይናንስ ዘርፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በራሱ አዋጅና በመመርያዎች እየሠራባቸው ያሉትን ልምዶችም ተጠቅመናል፡፡ በዚህ የአክሲዮን ኩባንያዎች አዋጅ የሚገዙት ንግድ፣ ቱሪዝም፣ ትራንስፖርት፣ ኢንዱስትሪ፣ ማኑፋክቸሪንግና የመሳሰሉትን የሚመለከት በመሆኑ የዘርፎቹን ችግሮች ያካተተ ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ባንኩ ጠንካራ ባይሆንም የአክሲዮን ማኅበራቱ ወደ መስመር እንዲገቡ ያደርጋል፡፡
ሪፖርተር:- ከዚህ ቀደም ሲባል እንደሰማነው የአክሲዮን ማኅበራት ይገዙበታል የተባለው አዋጅ፣ አሁን የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት የሚገለገሉበትና ብሔራዊ ባንክ የሚጠቀምበትን የመቆጣጠሪያ ሕግ እንዲመስል መፈለጉን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የአክሲዮን ማኅበራቱ አዋጅ ከብሔራዊ ባንክ አዋጅና መመርያዎች ጋር ይመሳሰላል የሚባለው እንዴት ነው? አመሳስሎ መቅረፅ ያስፈለገበት ምክንያት ምንድነው?
አቶ ኑረዲን፡- የቦርድ አመራሮችን ሚና የተመለከተው፣ ሞግዚት ማቋቋም፣ ሬጉላቶሪ (ተቆጣጣሪ) ጣልቃ የሚገባበት አግባብ፣ የአነስተኛ ባለአክሲዮኖች መብትና የመሳሰሉትን ጉዳዮች የሚመለከቱት የዚህ ረቂቅ አዋጅ ክፍሎች ከፋይናንስ ተቋማት መቆጣሪያ ሕግጋት ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡ ሌሎችም ተመሳሳይ ጉዳዮች አሉ፡፡
ሪፖርተር:- ለምሳሌ የፋይናንስ ተቋማት በሚመሩበት ሕግ ውስጥ የመቋቋሚያ ካፒታል መጠን ያስቀምጣል፡፡ አንድ ባለአክሲዮን ሊይዝ የሚችለው የአክሲዮን መጠን ወይም የባለቤትነት ድርሻው ከዚህን ያህል መብለጥ የለበትም ይላል፡፡ በአዲሱ የአክሲዮን ኩባንያ አዋጅስ?
አቶ ኑረዲን፡- በባንክ ሕግ ካፒታልና የአክሲዮን መጠን ጣሪያ ተቀምጧል፡፡ በዚህ ሕግ ላይ ግን የአክሲዮን ኩባንያዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የሚሰማሩ በመሆናቸው፣ የባለአክሲዮችን የባለቤትነት ድርሻ ጣራ ማስቀመጡ ለጊዜው አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ግን በሒደት እንዲመጣ መንገድ ይመቻቻል፡፡ ምክንያቱም አነስተኛ አክሲዮን ያለው መብት እንዳለው ካስቀመጥን፣ ከፍተኛው እስከምን ድረስ ነው የሚለውን ነገር በሒደት እያስተካከልን የምንመጣበትን ያሳያል ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር:- በርካታ የአክሲዮን ኩባንያዎች ብዙ ችግሮች አሉባቸው ተብሎ ሲነገር ነበር፡፡ በተጨባጭ የታዩ ችግሮችም አሉ፡፡ ገንዘባችን ተበላ፣ ይቋቋማል የተባለው ኩባንያ ሳይቋቋም ቀረ የሚሉና የመሳሰሉ እሮሮዎች ሲሰሙ ነበር፡፡ እናንተ ደግሞ ወደዚህ የሕግ ረቂቅ ከመግባታችሁ በፊት ብዙ አቤቱታዎች ቀርበውላችሁ ነበር፡፡ በአጠቃላይ የአክሲዮን ኩባንያዎችን በተመለከተ ባደረጋችሁት ቅኝት ምን አገኛችሁ? ምንስ አያችሁ?
አቶ ኑረዲን፡- ብዙ ነገሮች ታይተዋል፡፡ በተለይ ገዝፎ ያየነው ነገር በቦርድና በማኔጅመንት፣ በቦርድና አነስተኛ አክሲዮን ባላቸው ባለአክሲዮኖች፣ በከፍተኛና በአነስተኛ ባለአክሲዮኖች መካከል፣ እንዲሁም በቦርድና ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ ባላቸው ባለአክሲዮኖች መካከል ያሉ ፍትጊያዎች ናቸው፡፡ ይህም የአክሲዮን ኩባንያዎች ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል ማለት ይቻላል፡፡ የአክሲዮን ኩባንያዎች የሚቋቋሙበት ዓላማ፣ ታሳቢ የሚያደርጉ የሚያመጧቸው ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናታቸው የተሟላ አለመሆንም ችግር ነበር፡፡ በዚህ አዋጅ ወይም ደንብ የምንመልሰው አይደለም፡፡ የአዋጭነት ጥናት ጠንካራ እንዲሆን ምንድነው ማድረግ ያለብን? አደራጆች ብቃት ያላቸውና ክህሎት ያላቸው ማድረግ ብቻ ነው፡፡ በእኛ በኩል መቆጣጠር የምንችለውም ይህንን ነው፡፡ ስለዚህ የአደራጆችን ግለ ታሪክና የማደራጀት አቅም በዚህ አዋጅ ለማየት ተሞክሯል፡፡ ነገር ግን የፕሮጀክቱን አዋጭነት ጥናት ሬጉላቶሪው የሚቆጣጠረው ከሆነ ፕሮጀክቶቹ ሳይሳኩ ሲቀሩ ሊጠየቅ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ወደ አዋጭነት ጥናቱ አልገባንም፡፡ አዋጭነት ጥናቱ የሚያቀርቡ አካላት የሚያቀርቡት የሚፈለገውን ነገር ማድረግ የሚያስችል ነው ወይ? የሚለውን ግን የማየት ነገር በአዋጁ ውስጥ አካተናል፡፡
ሪፖርተር:- የአክሲዮን ኩባንያዎች ሲቋቋሙ ወይም በመደራጀት ላይ ሳሉ አክሲዮኖችን ለመሸጥ የሚቀርቡ ፕሮጀክቶችና ያተርፋሉ ተብሎ የሚቀርበው አኃዛዊ መረጃ አማላይ ናቸው ይባላል፡፡ አክሲዮን ገዥውም ይህንን ዓይቶ ይገዛል፡፡ ይህ የአክሲዮን ኩባንያዎች ከሚታይባቸው ችግር እንደ አንድ ምክንያት ሆኖ ይቀርባል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቆጣጠር አሁን የገለጹልን ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል?
አቶ ኑረዲን፡- በቂ ይሆናል ብለን አልዘጋንም፡፡ እንደ መነሻ ግን ወደ ሬጉላቶሪ መስመሩ ወይም ወደሚያዋጣው መስመር እንዲገቡ የሚያስችል በር ነው ብለን የወስድነው፡፡ የአዋጭነት ጥናት ውጤታማ ሊሆንም ላይሆንም የሚችልበት አግባብ ሊኖር እንደሚችል እናምናለን፡፡ ሌላው ቀርቶ በመንግሥት የሚያዙ ትልልቅ ፕሮጀክቶች በታቀደው መሠረት እስካልሄዱ ድረስ አያዋጡም ብለን ልንወስድ እንችላለን፡፡ በጣም በከፍተኛ ደረጃ የታሰቡ ዕቅዶች ላይሳኩ ይችላሉ፡፡ ያ ሳይሆን ሲቀር ባለአክሲዮኖች መብታቸውን እንዴት ያስከብራሉ? የሚለውን ለማየት ነው የፈለግነው፡፡ በሚፈለገው መንገድ ያልተጓዘን ማኅበር አደራጆቹ ወደ ሌላ ዓላማ እንዴት ሊያስለውጡት ይችላሉ? ሚናቸውስ ምን ይሆናል? መንግሥትስ ምን ሊደግፋቸው ይችላል? እንዴት ሊቆጣጠራቸው ሊያደርጋቸው ይችላል? የሚለውን ይዟል፡፡
ሪፖርተር:- በአሁኑ ወቅት በቢራ፣ በሪል ስቴት፣ በትራንስፖርት፣ በኮንስትራክሽን፣ በሲሚንቶ፣ በእርሻና በመሳሰሉት የኢንቨስትመንት መስኮች ኢንቨስት ለማድረግ የተደራጁ ወይም የተቋቋሙ አክሲዮን ማኅበራት አሉ፡፡ አዋጁ ሲወጣ ነባሮቹ አክሲዮን ማኅበራት እንደ አዲስ አሟሉ የሚባሉት ነገር ይኖራል? በአዋጁ ውስጥስ ይህንን የተመለከተ ነገር ተቀምጧል? አዲሶቹስ ሲመጡ ምንድነው ማድረግ የሚጠበቅባቸው?
አቶ ኑረዲን፡- ይኼ አዋጅ ነባሮቹ በዚህ ሥርዓት ውስጥ እንዴት ይገባሉ? የሚለውን ነገር በሒደት የሚያስተካክለው ነው፡፡ ከዚህ አዋጅ በተቃራኒ የሚሠሩ ነገሮች ይቆማሉ፡፡ አዲስ የሚቋቋሙ የአክሲዮን ማኅበራት ይኼንን ተከትለው እንዲሄዱ ይደረጋል፡፡ ነባሮቹ ደግሞ መደበኛና ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔያቸውን፣ የቦርድ ምርጫቸውንና የፕሮጀክት ክትትል ሥራቸውን እንዴት መሥራት እንዳለባቸው ይኼ አዋጅ ይደግፋቸዋል፡፡ ምክንያቱም በአዋጁ መሠረት ተቆጣጣሪው መሥሪያ ቤት የአክሲዮን ኩባንያዎቹን ዓመታዊ የኦዲት ሪፖርታቸውን ያያል፡፡ ጠቅላላ ጉባዔያቸውንም ይታዘባል፡፡ ኢንስፔክተር መመደብም ይቻላል፡፡ ይህ ለሁሉም የሚሠራ ነው፡፡ አሁን ላሉት ለአክሲዮን ማኅበራት በማንኛውም ጊዜ ኢንስፔክተር በመመደብ ይፈተሻል፡፡ ያሉበትን ደረጃ እያየ የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፡፡ የሚቋቋሙትን ደግሞ ኢንስፔክት እያደረገ በበሩ በኩል በትክክል እየገቡ መሆኑን በመከታተል እንዲሠሩ ያደርጋል፡፡ ከዚህ ሌላ አሁን ከሕግ ባለሙያዎች፣ ከመንግሥት አካላትና ከባለአክሲዮኖች ጋር ሰሞኑን በምናደርገው ውይይት ደግሞ እኛ ያላየናቸውና መካተት ያለባቸው ሌሎች ግብዓቶች ካሉ በረቂቅ አዋጁ እንዲካተቱ ይደረጋል፡፡ አሁን እኛ ያደረግነው ያየናቸውን ክፍተቶችና የዓለም አሠራርን በመቃኘት ያዘጋጀነው ነው፡፡ ዋነኞቹ ባለጉዳዮች የሆኑት የአክሲዮን ማኅበራትን ጨምሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በሚደረጉ ውይይቶች አዋጁ እንዲዳብር ይደረጋል፡፡ ሕግ አርቃቂ ባለሙያዎች የሚሰጡትን ግብዓት ሁሉ በመጠቀም ጠንከር ያለ ሕግ በማውጣት፣ የአክሲዮን ኩባንያዎችን ወደ ተሻለ አቅጣጫ የሚመራ አዋጅ ይወጣል ብለን እንጠብቃለን፡፡
ሪፖርተር:- ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ከተደረገበት በኋላ ረቂቁ እንዲዳብር ይደረጋል ተብሏል፡፡ አዋጁ ግን ጣጣውን ጨርሶ መቼ ፀድቆ ሥራ ላይ ይውላል?
አቶ ኑረዲን፡- አዋጁ ተግባራዊ መሆን አለበት ብለን ያስቀመጥነው ጊዜ አለ፡፡ ፓርላማ ፕሮግራም አስይዘንበታል፡፡ ውይይቱ ከተጠናቀቀ በኋላ አዋጁ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ እንዲፀድቅ እናደርጋለን ብለን አስበናል፡፡ እዚህ ላይ የምንፈራቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ በምንፈልገው ልክ ግብዓት ማግኘትና በፓርላማ ወረፋ ማግኘት መቻላችን፣ ባለድርሻ አካላት የምንጠብቀውን ያህል እርካታ ማግኘታቸው ወሳኝ ነገሮች ናቸው፡፡
ሪፖርተር:- ቀደም ብለው እንደገለጹልኝ ይህንን ዓይነት አዋጅ ለማውጣት አንዱ ምክንያት ጥቂት የማይባሉ የአክሲዮን ኩባንያዎች ውስጥ የተፈጠረ ችግር ነው፡፡ የፈረሱ አሉ፡፡ ገንዘባቸው የባከነባቸው እንዳሉም ተነግሯል፡፡ ለመፍረስ በማንገራገር ላይ የነበሩ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮች ያሉባቸውና እናንተ ይዛችኋቸው የነበሩ ጉዳዮች ምን ደረጃ ላይ ናቸው?
አቶ ኑረዲን፡- በንግድ ሚኒስቴር ሥር የአክሲዮንና የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ጉዳዮች ድጋፍና ክትትል ዳይሬክቶሬት በተቋቋመ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ60 በላይ የአክሲዮን ኩባንያዎችን መርምሯል፡፡ ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ታዝቧል፡፡ ቁጥጥር አድርጓል፡፡ ተቋቁመው ወይም ተመሥርተው ወደ ሥራ ያልገቡ የአክሲዮን ኩባንያዎችን እየጠራንና ወዳሉበት ቦታ እየሄድን ጭምር ለማየት ሞክረናል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ጭምር ነው ይህ አዋጅ የሚጠቅመን፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ያሉባቸውን ችግሮች ዓይቶ ድጋፍና ክትትልም ያደርጋል፡፡ አንዳንድ የአክሲዮን ኩባንያዎችን ጉዳይ ይዘን እስከ ሴክተር መሥሪያ ቤት ድረስ በመሄድ የሚታገዙበትን መንገድ ለመፈለግ ሞክረናል፡፡ ለምሳሌ ገቢዎችና ጉምሩክ፣ ብሔራዊ ባንክ፣ መሬት አስተዳደርና ሌሎች ችግሮች አሉባቸው ወደተባሉ አካላት ድረስ በመሄድ ድጋፍ እንዲያገኙና ወደ ሥራ የሚገቡበትን መንገድ እየተሞከረ ነው፡፡ የዚህ አዋጅ መውጣት ደግሞ ተቋሙን ያጠናክረውና ሕገወጦችን እንዴት መቆጣጠር እንደሚኖርበት፣ እንዲሁም መስመር ውስጥ የሌሉትን እንዴት ማስተካከል እንደሚቻል፣ ከመስመር የወጡትን ደግሞ በመቆጣጠር እስከ ዕግድ የሚደርሱ የተለያዩ ዕርምጃዎችን መውሰድ ይቻላል፡፡ መሰረዝንም ያካተተ ዕርምጃ ይወሰዳል፡፡ ከሕጉ ውጪ የሆኑ የቦርድና የማኔጅመንት አባላት ካሉም ለማገድ ዕርምጃ ይወሰዳል፡፡ ሞግዚት የማቋቋምና ተቆጣጣሪ የመመደብ ሥራውም እየተጠናከረ ይሄዳል፡፡
ሪፖርተር:- አዋጁ ከብሔራዊ ባንክ ሕግ ጋር ተመሳሳይ ነው ተብሏል፡፡ የአክሲዮን ኩባንያዎችን ቦርድና ማኔጅመንት ለመቆጣጠር የሚሠራ ከሆነ ደግሞ፣ የአክሲዮን ማኅበራትን እንዲመሩ የሚመረጡ ቦርዶችንና ኃላፊዎችን ሹመት የማፅደቅና የመሻር ሥልጣኑ የተቆጣጠረው መሥሪያ ቤት ይሆናል ማለት ነው? ተቆጣጣሪውስ ንግድ ሚኒስቴር ነው?
አቶ ኑረዲን፡- አዎ፡፡ ቢያንስ ቦርዱን የማፅደቅ ሥልጣን በአዋጁ ይሰጠዋል ብለን እናስባለን፡፡ በአዋጁ ውስጥም ተቆጣጣሪው አካል የእነዚህን ተመራጮች ሹመት የማፅደቅ ሥልጣን እንዲኖረው ይደረጋል፡፡ ይህንንም ተመራጩ ለሥራው ብቁ ነው ወይ? ግለ ታሪኩ መልካም ነው ወይ? የአክሲዮን ኩባንያውን ዓላማ ያሳካል? የሚለውን ዓይቶ ማፅደቅ ነው፡፡
ሪፖርተር:- የአክሲዮን ኩባንያን ስኬት እንዳያገኝ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ፣ ኩባንያውን ለማቋቋም ከሚነሱ አደራጆች አቅምና ሰብዕና ጋር ይያያዛል፡፡ ስለዚህ የአክሲዮን ኩባንያ አደራጆች በዚህ አዋጅ አሟሉ የሚባሉት ነገር ይኖራል?
አቶ ኑረዲን፡- አደራጆች ሐሳብ አመንጪዎች ናቸው፡፡ ይህንን ሐሳብ ይዘው ሲመጡ የንግድ ስሜን ከመስጠት ጀምሮ ክትትል እናደርጋለን፡፡ እዚህ ላይ ግን የአዋጭነት ጥናትን ማየት ግን የራሱ የሆነ ችግር አለው፡፡ ታሳቢውን ማየት አለብን፡፡ ምን ያህል አዋጭ ነው? የሚለውን ነገር ማየት አለብን፡፡ የአዋጭነት ጥናቱን ማየት ከጀመርን ግን የሚያነካካን ነገር አለ፡፡ ጥናቶች መሰራረቅና ጥናቶቹ ላይ አቅም በሌለው ሰው ያልሆነ ውሳኔ መወሰን ሊገጥም ስለሚችል ወደዚህ እንዳንገባ ጥንቃቄ እያደረግን ነው፡፡ ነገር ግን አደራጆች ያመጡትን ዕቅድ የማስፈጸም አቅም አላቸው ወይ? የኋላ ታሪካቸው ይህንን ያሳያል ወይ? በኋላ ታሪካቸው የፈጸሙት ነገር አለ ወይ? በገንዘብስ ምን ያህል አቅም አላቸው? ሥራውን በአግባቡ ለመሥራት ያላቸው ተነሳሽነት ምንድነው? የሚለውን ሁሉ ለማየት እንሞክራለን፡፡ ይህንን ካየን በኋላ በስድስት ወራትና በዓመት አደራጆች እየመጡ ሪፖርት እዲያደርጉና የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወስዱ የሚደረግበት አሠራር ይኖራል፡፡ በተፈለገው አቅጣጫ ካልተካሄደ ደግሞ ባለአከሲዮኖች ገንዘባቸው እንዴት ሊመለስላቸው ይችላል? የሚለውንም ይመልሳል፡፡ አሁን እኮ ካልተሳኩ የአክሲዮን ኩባንያዎች ገንዘባቸውን ለማግኘት ፍርድ ቤት እየሄዱ ነው፡፡ አሥር ዓመት ገንዘብ አዋጥተው ገንዘቡ የት እንደገባ እንኳን የማያውቁ አሉ፡፡ በዝግ አካውንት ተቀምጦ ቁጭ ያለ ገንዘብም አለ፡፡ ስለዚህ አዋጁ እንዲህ ያለው ገንዘብ እንዴት ሊለቀቅላቸው እንደሚችል መልስ ይኖረዋል፡፡
ሪፖርተር:- ንግድ ሚኒስቴር በተለይም እርስዎ የሚመሩት ዳይሬክቶሬት ከሚመለከታቸው ጉዳዮች አንዱ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ናቸው፡፡ እነዚህን ንግድ ምክር ቤቶች የተመለከቱ በርካታ ችግሮች እንዳሉ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በቅርቡም የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ ያልቻለበት ደረጃ መድረሱ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንፃር እነዚህ ንግድ ምክር ቤቶች ከውዝግብ ወጥተው ትክክለኛውን መስመር እንዲይዙ ንግድ ሚኒስቴር ምን ለማድረግ አስቧል?
አቶ ኑረዲን፡- ንግድ ሚኒስቴር አሳታፊ ምርጫዎች በየክልሉ ተከናውነው አገር አቀፉን የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱን እንዲያቋቁሙ የማድረግ ሥራ ይሠራል፡፡ ከዚህ በፊት እንደነበረው የእነዚህ ምክር ቤቶች ጉዳይ አንዴ ያዝ ሌላ ጊዜ ተወት እየተደረገ ቢቆይም አሁን ግን ይህ አይኖርም፡፡ እየተጀመሩ የሚቋረጡበት አሠራር አይኖርም፡፡ አሁን መንግሥት በቁርጠኝነት በመግባት ምርጫዎች በ341/95 አዋጅና በየተቋማቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት እንዲከናወን ማድረግና የመከታተል ሥራ ይሠራል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን አዋጁን የማሻሻል ዕርምጃ በመውሰድ፣ ወደፊት ምክር ቤቶቹ ውጤታማና ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን የመፈለግ ሥራ ነው የሚሠራው፡፡
ሪፖርተር:- ጥቂት የማይባሉ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች አሁን የያዙት አቋም ጥሩ አይደለም እየተባለ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ የግለሰቦች ቤት እየሆኑ ነው፣ ተልኳቸውንም እየሳቱ ነው የሚባለው አስተያየት መሰጠት ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ይህንን ማስተካከል ያለበት ንግድ ሚኒስቴር ሆኖ ሳለ ሥራውን በሚገባ ባለመከናወኑ ችግሩ ተባብሷል የሚባል ትችት አለ፡፡ አሁን ተከሰተ የሚባለውን ችግር ለመፍታት ዘግይቶም ቢሆን ንግድ ሚኒስቴር ዕርምጃ መውሰድ ሲጀምር ደግሞ አያገባውም የሚሉ ሙግቶች እየተነሱ ነው፡፡ በእርግጥ ያለውን ችግር ለመፍታት ንግድ ሚኒስቴር ሥልጣን የለውም?
አቶ ኑረዲን፡- ንግድ ሚኒስቴር ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው በመሆኑ 341/95 አዋጅን ብቻ ማየት ይበቃል፡፡ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች እንዲቋቋሙ ሰርተፊኬት የመስጠት ሥልጣን ያለው አካል ሰርተፊኬቱንም የመሰረዝ ሥልጣን አለው፡፡ ዕውቅና የሚሰጣቸው የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መሆናቸውን እያረጋገጠ ነው፡፡ አሁን የተጀመረው እሰጥ አገባ የመጣው ዕውን ነጋዴዎች ናቸው? ዕውን የዘርፍ ማኅበራት ናቸው? በራሳቸው መተዳደሪያ ደንብ ይሠራሉ ወይ? የሚለው ሲነሳ እኮ ነው፡፡ እነዚህን ነገሮች ለማጥራት ተጀምረው ተንጠልጥለው የቀሩ ነገሮች ስለነበሩ፣ ጉዳያቸውን በራሳቸው መንገድ ይፍቱ እየተባለም ስለነበር የተፈጠረ ነው፡፡ ተሸፋፍኖ ቆይቶም ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ግን መንግሥት በቁርጠኝነት ነው የገባበት፡፡ አሁን ከምርጫው ጀምሮ አዋጅ እስከማሻሻል የሚደርስ ጠንካራ ዕርምጃ ነው የሚወስደው፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን ከተፈጠረው ችግር ጋር ተያይዞ ባደረጋችሁት ፍተሻ ንግድ ምክር ቤቶችን እንዴት አገኛችኋቸው? አሁን ባላቸው አቅም በእርግጥ የንግድ ማኅበረሰቡን የሚወክሉ ናቸው ማለት ይቻላል?
አቶ ኑረዲን፡- እስካሁን ባለን እንቅስቃሴ አንዳንዶቹ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ጠንካሮችና ለንግድ ኅብረተሰቡ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ዓይተናል፡፡ ከዚያም አልፎ በፕሮሞሽን ሥራዎች፣ ነጋዴዎችን በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች ላይ በማሳተፍ፣ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶችን ወደ አገር ውስጥ በማምጣቱ ሥራ ላይ ውጤት እንዳላቸው ዓይተናል፡፡ ከዚህ አልፎ የነጋዴውን መብትና ጥቅም የማስከበር ላይ ሄደዋል ወይ ስንል ግን አንዳንዶች ከጉዞና ቪዛ ከማግኘት ውጪ፣ አንዳንዶች ደግሞ በዘርፉ ውጭ ላይ ከመጨፈር የተሻለ ያየንባቸው ነገር የለም፡፡ በሒደት ግን ይህንን ማስተካከል የሚችሉት አባላት ናቸው፡፡ አባላት ላይ መሠራት አለበት፡፡ አባላት እንዲበዙ በጣም ጥረት አድርገናል፡፡ በአማራና በትግራይ ክልሎች ካሉ ነጋዴዎች ከ65 በመቶ በላይ የሚሆኑትን ወደ ምክር ቤቶቹ እንዲገቡ አድርገናል፡፡ ይህንን በሌሎችም ክልሎች እያሳካን ስንመጣ ነጋዴው ያቋቋመው ማኅበር መሆኑን አውቆ ለመብቱ እንዲታገልለት ማድረግ ይጀምራል፡፡