Wednesday, May 22, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ጥራት መጓደል ዜጎችን ከፍተኛ ጫና ውስጥ እየከተተ ነው!

ባለፉት 13 ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ 140 ሺሕ ያህል የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው በዕጣ ለነዋሪዎች ተላልፈዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በ10/90፣ በ20/80 እና በ40/60 ፕሮጀክቶች አማካይነት 130 ሺሕ ቤቶች እየተገነቡ ነው፡፡ ከከተማው ነዋሪዎች አንገብጋቢ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ጋር ሲነፃፀር ሒደቱ አዝጋሚ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ችግሩን ለማስተንፈስ የሚደረገው ጥረት ቀላል ግምት አይሰጠውም፡፡ እንደሚታወቀው በ2005 ዓ.ም. ዳግም ምዝገባ ሲከናወን አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች  ቤት ለማግኘት ተመዝግበዋል፡፡ አሁን ሌላ ዙር ምዝገባ ቢካሄድ ይህ ቁጥር ከእጥፍ በላይ ያድጋል፡፡ ይህ የጋለ ፍላጎት የሚያሳየው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከፍተኛ የሆነ የመኖሪያ ቤት እጥረት መኖሩን ነው፡፡ በዚህ ላይ ከነባር የመኖሪያ መንደሮች በልማት ምክንያት የሚፈናቀሉ ዜጎች ሲጨመሩበት የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ቁጥር በጣም ያሻቅባል፡፡ በአሁኑ አሠራር መቀጠል ስለማይቻል መንግሥት የተሻሉ አማራጮችን ማማተር አለበት፡፡ በሙያው የተካኑ ባለሙያዎችንና ተቋማትን በማሳተፍ የተሻለ አማራጭ መፈለግ ግድ ይላል፡፡ ከመኖሪያ ቤት ፅኑ ፍላጎት በተጨማሪ አሁን እየተገነቡ ያሉት ቤቶች ጥራት ጉዳይ በጣም አሳሳቢ በመሆኑ፣ መንግሥት በፍጥነት አማራጭ መፍትሔ መፈለግ ይኖርበታል፡፡

በ20/80 መርሐ ግብር በቱሉ ዲምቱ፣ በቦሌ አራብሳ፣ በኮዬ ፈጬ፣ በየካ አባዶ፣ በቂሊንጦና በመሳሰሉት የጋራ መኖሪያ ግንባታ ሳይቶች ወጥ የሆነ ግንባታ ባለመኖሩ አንዱ ብሎክ ከሌላው ብሎክ ጋር አይመሳሰልም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤቶቹን ግንባታ እንዲያቀላጥፉ ያቋቋማቸው ተቋማት በሚገባ እየተናበቡ ሥራቸውን ስለማይሠሩ፣ የሚመለምሉዋቸው ሥራ ተቋራጮችና አማካሪ ድርጅቶች በሕጉ መሠረት ኃላፊነታቸውን አልተወጡም፡፡ ሥራ ተቋራጩ በገባው ውል መሠረት ግንባታውን እያካሄደ መሆኑን አማካሪ ድርጅቱ ቁጥጥር ስለማያደርግ የቤቶቹ ግንባታ አፈጻጸምና ጥራት የተለያየ ነው፡፡ አንዱ ብሎክ በጥሩ ሁኔታ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ሌላው ደግሞ ለዓይን እስኪያሰቅቅ ድረስ ብልሽትሽቱ የወጣ ነው፡፡ በሚገባ ቁጥጥር ያልተደረገባቸው ቤቶች ግድግዳቸውና ወለላቸው የተሰነጣጠቀ፣ ቅርፃቸው የተጣመመ፣ የሳኒተሪ ዕቃዎቻቸው በአግባቡ ያልተገጣጠሙና የተሰባበሩ፣ የውኃና የኤሌክትሪክ መስመሮቻቸው በተገቢው ጥንቃቄ ያልተዘረጉ፣ ወዘተ ናቸው፡፡ እነዚህን ቤቶች በዕጣ የሚያገኙ በዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ለተጨማሪ ወጪ ተዳርገዋል፡፡ በኑሮአቸው ላይም ከፍተኛ የሆነ ጫና ተፈጥሯል፡፡

አንድ የጋራ መኖሪያ ቤት ለማግኘት ወረፋ የሚጠብቅ ዜጋ በየወሩ ከሚያገኘው ላይ መቆጠብ አለበት፡፡ ዕጣው ሲደርሰው ሃያ በመቶ ቅድሚያ ክፍያ የመክፈል ግዴታም አለበት፡፡ ከዚያም በቤቱ መጠን መሠረት በየወሩ ወገብ የሚያጎብጥ ክፍያ ይጠብቀዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሚከናወነው ከምግብ፣ ከልብስ፣ ከልጆች ትምህርት ቤትና ከሌሎች ተጨማሪ ወጪዎች ጋር እልህ አስጨራሽ ትግል እየተደረገ ነው፡፡ በዚህ ላይ በዕጣ የደረሰው ቤት በአግባቡ ባለመጠናቀቁ በትንሹ ከአንድ መቶ ሺሕ ብር በላይ ለማጠናቀቂያ የሚጠይቀው ሲሆን ደግሞ ጫናው ከሚሸከመው በላይ ይሆንበታል፡፡ ቤቶቹ ግን በተቻለ መጠን ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገባቸው ጥራታቸውን ጠብቀው ቢገነቡ ጫናውን መቀነስ ይቻላል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ መቀጠል ስለማይቻል ለግንባታ ጥራት መጨነቅ የግድ ነው፡፡ እየባከነ ያለው የአገር ሀብት ነው፡፡ በመኖሪያ ቤቶቹ ግንባታ ላይ የሚፈጸመው ሙስና በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ልዩ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡ ከግንባታና ከቁጥጥር በተጨማሪ በግንባታ ግብዓቶች አቅርቦት፣ በሳኒተሪ ዕቃዎችና በመሳሰሉት ላይ የሚፈጸመው ዝርፊያ ለጥራት መጓደል ዋነኛው መንስዔ መሆኑ ሊጠረጠር አይገባም፡፡ በብልሹ አሠራሮች ምክንያት ዜጎች ፈተና ውስጥ መግባት የለባቸውም፡፡

አዳዲሶቹ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተገነቡባቸው ሳይቶች ማኅበራዊ ተቋማት ማለትም ትምህርት ቤት፣ ክሊኒክ፣ ገበያና የመሳሰሉት መኖራቸው ቢገለጽም ነዋሪዎች አገልግሎቶቹን ማግኘት አይችሉም፡፡ በሪፖርት መኖራቸው የሚነገርላቸው እነዚህ ማኅበራዊ ተቋማት የሉም፡፡ መኖሪያ ቤቶቹ ከመጋቢ መንገዶች ጋር የተገናኙ ካለመሆናቸውም በላይ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ባለመመደቡ ቁልፍ ተረክበው ለሚገቡ ዜጎች ሌላው ፈተና ነው፡፡ ብዙዎቹ የኮብልስቶን ንጣፋቸው ጥራት የተጓደለ በመሆኑ ተሽከርካሪዎች ሲሄዱባቸው ይፈነቃቀላሉ፡፡ ብዙ ሚሊዮን ብሮች ወጥተውባቸው መገንባታቸው እንጂ የጥራታቸው ጉዳይ ችላ ተብሏል፡፡ የአገር ሀብት እየወደመ ነው፡፡ በአዳዲሶቹ ሳይቶች ቁልፍ ተረክበው የገቡና የሚገቡ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይልና ውኃ ስሌላቸው ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡ እጅግ በጣም አስመራሪ ከሆነ ኪራይ ተላቀው ወደ አዲሶቹ መኖሪያ ቤቶቻቸው መግባት ያለባቸው ዜጎችን የበለጠ ጫና ውስጥ የሚከቱ ችግሮች የመንግሥትን ፈጣን ዕርምጃ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ዕርምጃ አሁን ያሉትን የተዝረከረኩ አሠራሮች ከማስተካከል ባለፈ፣ ለዘለቄታው መፍትሔ መንገድ ጠራጊ መሆን አለባቸው፡፡

መንግሥት በጀት እየመደበና ዜጎችም እየቆጠቡ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚፈስባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክቶች፣ በጣም አዝጋሚ በሆነውና አቅም በሌለው የመንግሥት ቢሮክራሲ መከናወን አይችሉም፡፡ የአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች ወደፊትም በስፋት የሚቀጥሉ በመሆናቸውና በአገር አቀፍ ደረጃም ስለሚስፋፉ፣ የአገር ውስጥና የውጭ ልምድ ያላቸው ሥራ ተቋራጮችንና አማካሪ ድርጅቶችን የማሳተፍ ጉዳይ በጥልቀት ጥናት ሊደረግበት ይገባል፡፡ የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀትም ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ዜጎች በረጂም ጊዜ ሞርጌጅ ቤቶች እንዲገነቡላቸው ማድረግ፣ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ደግሞ በማኅበር ተደራጅተው እንዲገነቡ ማገዝ፣ የተሻለ አማራጭ ያላቸው ደግሞ በሪል ስቴት ወይም በሌላ መንገድ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ በጥናት ላይ የተመሠረተ ስትራቴጂ ማውጣት የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ መጠነ ሰፊ ግንባታዎች በመንግሥት አማካይነት ማካሄድ ሒደቱን ከማጓተቱም በላይ፣ በጥራት መጓደልና በብክነት ብዙ የአገር ሀብት ይጠፋል፡፡ ሌላው በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ያልተሠራን እንደተሠራ አድርጎ ሐሰተኛ ሪፖርት በማውጣት በአገር ላይ የሚፈጸመው ደባ ነው፡፡ የሌለን ነገር እንዳለ ማውራትና ማስወራት፣ መሬት ላይ የማይታይን ደግሞ በግድ ካላያችሁ ማለት የግልጽነትና የተጠያቂነት መጥፋት ማሳያ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ከአቅም በላይ እየሆነ ከመጣው የኑሮ ጫና በተጨማሪ፣ የመኖሪያ ቤት እጥረት ዜጎች ከሚቋቋሙት በላይ ፈተና ሆኗል፡፡ መንግሥት ላለፉት 13 ዓመታት በራሱ ባደረገው ጥረት በብዙ ሺሕ ለሚቆጠሩ ዜጎች አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ይህ ጥረት አድጎና ጎልብቶ ለዜጎች የበለጠ እርካታ እንዲፈጥር ደግሞ የተሻሉ አማራጮችን መቃኘት የግድ ይላል፡፡ የመንግሥት ሀብትና የዜጎች ጥሪት በአግባቡ ሥራ ላይ መዋል ሲገባው የሙሰኞችና የደንታ ቢሶች ሲሳይ መሆን የለበትም፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት አንዳችም ዓይነት ምዝገባ ባለመካሄዱ በአጋጣሚ ሌላ ዙር ምዝገባ ቢካሄድ የቤት ፈላጊዎች ቁጥር ከሚቋቋሙት በላይ ነው የሚሆነው፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየዓመቱ ከ100 ሺሕ በላይ ተመራቂዎች ይወጣሉ፡፡ ይኼ በራሱ የፍላጎትንና የአቅርቦትን ሰማይና ምድር መሆን ያሳያል፡፡ በነበረበት መቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን አመላካች ነው፡፡ መንግሥት በተለይ በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በፍጥነት ለመቅረፍ የፖሊሲና የስትራቴጂ ለውጥ ማድረግ አለበት፡፡ ለውጥን መጠራጠር ወይም አለመፈለግ ጫናውን የበለጠ ያበረታዋል፡፡ አሁን በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረሰ ያለው የጋራ መኖሪያ ቤቶች የግንባታ ጥራት መጓደል በዚህ ሁኔታ መቀጠል የሌለበት በዚህ ምክንያት ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...

ያልነቃ ህሊና!

ከሽሮሜዳ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ነቀፋ አንሶላው፣ ትችት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...