Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየአፍዴራው ፍልውኃ

የአፍዴራው ፍልውኃ

ቀን:

በጨዋማው አፍዴራ ሐይቅ ዳርቻ የአካባቢው ተወላጆችና ጎብኚዎች ይዋኛሉ፡፡ በአፍዴራ ከተማ በሚኖሩ ወጣቶች ለጎብኚዎች ማረፊያ የተዘጋጀ ዳስ ውስጥ አረፍ ብለው ሐይቁን በቅርብ ርቀት እየተመለከቱ የሚዝናኑም አሉ፡፡ ብዙዎቹ ወደ አካባቢው ያመሩበት ምክንያት አፍዴራ ሐይቅ አጠገብ ያለውን ፍልውኃ ፍለጋ ነውና ከዋናውና ከዕረፍቱ አስከትለው ፍልውኃ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ፍልውኃው እንደ መዋኛ ገንዳ ያለ ሲሆን፣ ዙሪያውን በድንጋይ ተከቧል፡፡ ብዙም ጥልቀት ስለሌለው ሰዎች በቀላሉ ፍልውኃ ውስጥ መግባት ይችላሉ፡፡ ውኃው የጠራ ስለሆነ ከበታቹ ያለው አሸዋ በግልጽ ይታያል፡፡

የፍልውኃው ሙቀት እንዲሁም በውስጡ ያለው አሸዋም መድኃኒትነት እንዳላቸው ይታመናል፡፡ ፍልውኃውን በጎበኘንበት ወቅት በቦታው ያገኘናቸው ግለሰቦችም ይህንን ሰምተው ስለሄዱ ውኃ ውስጥ ከገቡ በኋላ ለደቂቃዎች አሸዋው ላይ ይረማመዳሉ፡፡ ፍልውኃው ውስጥና ዳር ላይ ያሉ በተፈጥሮ እንደ መቀመጫ ተስተካክለው የተጠረቡ ድንጋዮች ላይ ይቀመጣሉ፡፡ ፍልውኃ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ በጀርባቸውና በፊታቸው እየተኙ ጡንቻቸውን የሚያፍታቱም ተመልክተናል፡፡

ፍልውኃው ጡንቻን በማፍታታት ከሕመም ለማገገምና አዕምሮን ዘና ለማድረግም ፍቱን እንደሆነ ይነገራል፡፡ በአካባቢው የፍልውኃ ፍቱንነት እንደሚታመንበት ሁሉ በሌሎች የዓለም ክፍሎችም በየአገሩ ባለው ፍልውኃ መድኃኒትነት ይታመንበታል፡፡ መነሻው ጥንታዊው የሰው ልጅ ሥልጣኔ ቢሆንም በዘመናዊው ሳይንስም ቦታ ይሰጠዋል፡፡ በጥንታዊ ግብፅና ግሪክ ፍልውኃ ከፈዋሽነቱ በተጨማሪ የመዝናኛ አማራጭ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ ከእውናዊው የፍልውኃ ጥቅሞች ጎን ለጎን በሚቶሎጂ (ስነ ተረት) ፍልውኃ ከሰዋዊ ጉልበት የላቀ ኃይል እደሚያጎናጽፍ የሚገልፁ ጽሑፎች ይገኛሉ፡፡

- Advertisement -

ተፈጥሯዊው ፍልውኃ የተሸከማቸው ንጥረ ነገሮች የደም ዝውውርን ለማፋጠን፣ የጀርባ ሕመምን ለመቀነስ፣ ለቆዳ አለርጂ ፈውስና ለሌሎችም ሕመሞች መፍትሔ እንደሚሆን አንድ ጃፓናዊት ተመራማሪ የሠሩት ጥናት ያስነብባል፡፡ ለዘመናት በአገር በቀል መድኃኒትነቱ የታወቀው ፍልውኃ በዘመነኛው ዓለም ያለው ተቀባይነትም እየጨመረ መምጣቱን ተመራማሪዋ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ፍልውኃ ከሚገኝባቸው አካባቢዎች አንዱ አፋርን በጎበኘንበት ወቅት፣ በፍልውኃው ዙሪያ በርካታ ሰዎች ተመልክተናል፡፡ ፍልውኃውን ለጎብኚዎች መዳረሻ ከሆኑ ተፈጥሯዊ መስህቦች አንዱ የማድረግ እንቅስቃሴም አለ፡፡ በክልሉ የቱሪስት ጠቋሚ መጽሐፍ (ጋይድ ቡክ) ከተካተቱ አንዱም ይህ ፍልውኃ ነው፡፡

አዘውትሮ ወደ ፍልውኃው የሚሔደው መሐሪ ነጋሽ የአፍዴራ ከተማ ነዋሪ ነው፡፡ በተለይም ከጥቅምት እስከ የካቲት ባሉት ወራት አካባቢው ቀዝቀዝ ስለሚል ብዙዎች ወደ ፍልውኃ እንደሚሔዱ ይናገራል፡፡ ‹‹ፍልውኃው እንደ ፀበል ነው የሚታየው፡፡ ብዙዎች ሲታመሙ ማለትም ሰውነት ላይ እብጠት ሲኖር፣ ለወለምታና ብርድ ለመከላከልም ይመጣሉ፡፡ እንደ መዝናኛ የሚወስዱትም አሉ፤›› ይላል፡፡ ፍልውኃው አካባቢ ጨዋማ ያልሆኑ ምንጮች ያሉ ሲሆን፣ ውኃውን አቀዝቅዘው የሚጠጡት መኖራቸውንም ይናገራል፡፡

መሐሪ ቢያንስ በሳምንት ሁለት ቀን ፍልውኃ ውስጥ ይነከራል፡፡ ለደቂቃዎች ፍልውኃው ውስጥ መላ ሰውነቱን ነክሮም ይዋኛል፡፡ በሥራ የደከመ ሰውነቱንና ኅሊናውንም የሚያፍታታበት ቦታ መሆኑንም ይናገራል፡፡ ከጎበኘነው ፍልውኃ በቅርብ ርቀት ሌላ ፍልውኃ ያለ ሲሆን፣ ጠዋት ማታ የሚመላለሱ ሰዎች እንዳሉም ይገልጻል፡፡ በቀዝቃዛ ወራት ከአካባቢው ነዋሪዎች በተጨማሪ ጎብኚዎች ወደ ፍልውኃው ያቀናሉ፡፡

መሐሪ እንደሚለው፣ ወደ አካባቢው የሚያመሩ ጎብኚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ቢጨምርም፣ ፍልውኃው ካለው ጥቅም አንጻር የሚጠቀምበት ሰው ውስን ነው፡፡ ጎብኚዎችን በብዛት ለመሳብ አካባቢው በስፋት መተዋወቅ እንዳለበትና ወደ አካባቢው ለሚሔዱ ሰዎች ምቹ ማረፊያ መዘጋጀት እንዳለበት ያምናል፡፡ በአፍዴራ ሐይቅ ዳርቻ የተሠራው ዳስ በጥራትና በአገልግሎትም በቂ እንዳልሆነ ገልጾ፣ ለውጥ እንደሚያሻ ይናገራል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ካሳሁን አያሌው እንደሚናገረው፣ ሰዎች በአንድ አካባቢ ስላሉ የቱሪስት መስህቦች መረጃ ሲኖራቸው የመጎብኘት ተነሳሽነት ስለሚኖራቸው የማስተዋወቅ ሥራ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ መዳረሻዎችን በማስተዋወቅ የአገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎችን መሳብ እንደሚያስፈልግም ይገልጻል፡፡ የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ ያዩም ሐሳቡን ይጋራሉ፡፡ መዳረሻዎችን ከማስተዋወቅ ጎን ለጎን መሠረተ ልማት በማሟላት የጎብኚዎችን ቁጥር መጨመር እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡

ፍልውኃውን በጎበኘንበት ወቅት ከአገር ውስጥ ጎብኚዎች በበለጠ የውጪዎቹ ቁጥር እንደሚያመዝን አስተውለናል፡፡ ለአካባቢው ነዋሪዎች ግን ቀዳሚ መዳረሻቸው ከሆኑ መስህቦች መሀከል ፍልውኃው ይጠቀሳል፡፡ በተፈጥሯዊ መድኃኒትነቱ ፍልውኃው እንደምሳሌ ቢጠቀስም የአካባቢው ባህላዊ ሕክምና ፈርጀ ብዙ ነው፡፡ ተፈጥሮን በመጠቀም መድኃኒት የማዘጋጀት ጥበብ ከቤተሰብ ወደ ቤተሰብ የሚተላለፍ ሲሆን፣ አንድ ሰው ሕክምናውን ከአሥር ዓመቱ ጀምሮ መስጠት ይችላል፡፡ ባለሙያዎች በውርስ ከሚያገኟቸው የቅመማ ጥበቦች በተጨማሪ አዳዲስ በሽታዎች ሲከሰቱ መድኃኒት የመፍጠር ችሎታ እንዳላቸው በአፋር ብሔረሰብ ባህላዊ እሴቶች ላይ የተሠራ ጥናት ያመለክታል፡፡

የባህላዊ መድኃኒት ቀማሚዎች እርስ በእርስ ልምድ የሚለዋወጡበት ሥርዓትም ያለ ሲሆን፣ አንድ ባለሙያ ከሌላው ለመማር በግ፣ ፍየል፣ ላም ወይም ግመል ይከፍላል፡፡ ባለሙያዎቹ ስለ መድኃኒቱ አዘገጃጀትና አጠቃቀም ለማንም ሰው ሳይገልጹ በሚስጥር ይይዟቸዋል፡፡ በጥናቱ ‹‹የአፋር የባህል ሐኪሞች ለረዥም ዘመናት ያካበቱት ባህላዊ የሕክምና ዕውቀት አንጡራ ሀብታቸው፣ የገቢ ምንጫቸው፣ አንድ ሕመምተኛን በሚፈውሱበት ጊዜ የደስታና የዝና ምንጫቸው፣ ከኅብረተሰቡ ትብብርና ረዳት የሚያገኙበት፣ ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስር የሚፈጥርላቸው በመሆኑ ውርሱ ለቤተሰብ አባል ብቻ ነው፡፡ የመድኃኒት ዕውቀት የኅብረተሰቡ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ የሚመልስ የአገር በቀል ዕውቀት ነው፤›› በማለት ተገልጿል፡፡

የባህል ሕክምና ሰጪዎችና ተቀባዮቹ ከሕክምናው በፊትና በኋላም የሚከተሏቸው ሥርዓቶች አሉ፡፡ አንድ ሕመምተኛ የያዘውን በሽታ የሚለዩባቸው መንገዶችና ለየበሽታው ፈውስ የሚሰጡ ተፈጥሯዊ ግብዓቶችን የሚገለገሉባቸው ቅደም ተከተሎችም አሉ፡፡ የባህል ሐኪሞች ገንዘብ የሌላቸውን ሰዎች በነፃ የሚያክሙበት አግባብ ያለ ሲሆን፣ ባለሙያው በሽታውን መፈወስ ካልቻለ የወሰደውን ገንዘብ ይመልሳል፡፡

አንድ ማኅበረሰብ ለጥያቄዎቹ መልስ ለማግኘት በመጀመሪያ የሚያማትረው ወደ ተፈጥሯዊ ግብዓቶች መሆኑ እሙን ነው፡፡ ከግብዓቶቹ መሀከል ለጥያቄዎቹ መልስ የሰጡትን በመውሰድም ዕውቀቱን ከትውልድ ወደ ትውልድ ያሸጋግራል፡፡ የአፍዴራ ሐይቅ ፍልውኃም በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው፡፡ እንደ አካባቢው ተወላጆች ሁሉ ለሌሎችም ተደራሽ እንደሆነ ሲመቻች ተጠቃሚዎቹ ይበራከታሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...