Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየ‹‹አዲሱ ማርክሲዝም›› የመደብ ሥሪቶች

የ‹‹አዲሱ ማርክሲዝም›› የመደብ ሥሪቶች

ቀን:

ቅዳሜ የካቲት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ይህን ዜና አንብቤ ማመን አቅቶኛል፡፡ ዜናው ከሞላ ጎደል፣ ‹‹በተጠናቀቀው የፈረንጆች 2016 ዓመት ብቻ በአዲስ አበባ ከተማ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሀብት ያላቸው 20 አዳዲስ ሚሊየነር ባለፀጎች መፈጠራቸውን ናይት ፍራንክ… አስታውቋል፤›› የሚል ጭብጥ ያለው ወሬ አስነብቧል፡፡

ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ስለሚል፣ በጥቁር ገበያው ዋጋ መሠረት ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ገደማ መሆኑ ሀብት ያካበቱ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ በብር ካሰላነው ሚሊየነሮች ሳይሆኑ ቢሊየነሮች ተፈጥረዋል ለማለት ያስደፍራል፡፡ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በተራቡባት፣ የአንድ ኪሎ ቲማቲም ዋጋ እስከ 40 ብር በሚያሻቅብባት፣ የታክሲ ፈላጊ ሠልፈኛ ብዛት በኪሎ ሜትር በሚለካባት፣ የወጣቶች የሥራ አጥነት ምጣኔ የትየለሌ በሆነባት፣ ኢትዮጵያ ያውም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ብቻ እንዴት ይሆን ቢሊየነሮቹ ሊፈጠሩ የቻሉት፤ የሚችሉት? ይህ ለእኔ ኢኮኖሚያዊ እንቆቅልሽ ነው፡፡ በአዳም ስሚዝ መነፅር ወይስ በካርል ማርክስ መነፅር አለያ በየትኛቸው እንቃኘው ይሆን?

አሮጌው ማርክሲዝም

የጥንቱ ማርክሲዝም ካፒታሊስቶች ሀብታም የሚሆኑት ለሠራተኛው መደብ መክፈል የሚገባቸውን ደመወዝ በትርፍ መልክ እየበዘበዙ ገንዘብ በማካበት መሆኑን ይገልጻል፡፡ እንደ ማርክሲዝም አስተሳሰብ፣ በካፒታሊስት ሥርዓት ውስጥ ሠራተኞች የሚያገኙት ደመወዝ በምርት ተግባር ወቅት ለሥራ ከሚያፈሱት ኃይል ዋጋ በታች ነው፡፡ ይህ የሚሆነውም ሥርዓቱ ሥራ አጥነትን ስለሚቀፈቅፍ በአነስተኛ ደመወዝ ብዛት ያለው ሕዝብ ወይም ሠራዊት (ሪዘርቭ አርሚ) በግድ ስለሚፈጥር የሚለን ማርክሳዊ ርዕዮት ነው፡፡

በዚህም መሠረት፣ አሮጌው ማርክሲዝም ትርፍ ማለት ለሠራተኛው ያልተከፈለ ደመወዝ ወይም ተረፈ እሴት (ሰርፕለስ ቫሊዩ) ነው ይላል፡፡ የምርት አስተዋጽኦ ሒሳብ ሲደረግ፣ መሬት ኪራይ የሚሰጠው የምርት ኃይል ሲሆን፣ የካፒታል እልቀት (ዲፕሪሼዬሽን) እየተሰላ ይታሰብለታል፡፡ የካፒታሊስቱ የሥራ ኃይል ክፍል የሆነው ከፍተኛው የማኔጅመንት ደረጃም ከፍተኛ ደመወዝ ይሰላለታል፡፡ ሠራተኞች ግን በአንፃሩ እዚህ ግባ የማይባል ወይም ከዕለት ጉርስ የማይሻል ደመወዝ ይከፈላቸዋል፡፡ 

ይህ ከሆነ በኋላስ ምርቱ ገበያ ላይ ወጥቶ ሲሸጥ ትርፍ ሊገኝ የሚችለው እንዴት ነው? ለሚለው ጥያቄም ምላሹ በአሮጌው ማርክሲዝም መሠረት፣ የምርቱ የገበያ ዋጋ የፈሰሰበት የሥራ ኃይል ዋጋ ድምር መሆን ይገባዋል፡፡ የሁሉም የምርት ኃይሎች (መሬት፣ ካፒታል፣ የሰው ኃይል እንዲሁም የፈጠራ ሥራ ወይም ኢንተርፕረነርሺፕ) የድርሻ ዋጋቸውን በሚያገኙ ጊዜ የትርፉ ምንጭ ምን ሊሆን ይችላል? ከተባለ ተገቢውን ዋጋ ያላገኘ የምርት ኃይል እንዳለ ያመላክተናል፡፡ ይህ የምርት ኃይል በአብዛኛው ሠራተኛው መደብ ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህ የሚያሳየው ትርፍ የብዝበዛ ውጤት እየሆነ መምጣቱን ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ንፋስ የማያስገባ ሊባል የሚችል አመክኖአዊ ንድፈ ሐሳብ የሚመነጨው ከአሮጌው ማርክሲዝም ነው፡፡

ስለዚህ እንዲህ ያለው ያልተመጣጠነ የትርፍ ክፍፍል መፍትሔው የመደብ ትግሉን ማጧጧፍና የካፒታሊስት ሥርዓቱን በመነቅነቅ ኮሚውኒስታዊ ሥርዓትን መመሥረት ነው፡፡ ኮሚውኒዝም ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደረስበት ሥርዓት አይደለም፡፡ እጅግ በመጠቀ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ታግዞ የሚመረት ምርት የሚትረፈረፍበት ሥርዓት ነው፡፡ ‹‹ለእያንዳንዱ እንደ ፍላጎቱ፤›› የሚሰጥበት ሥርዓተ ማኅበር ነው፡፡ አብዛኛው የምርት ተግባር በቴክኖሎጂ ታግዞ ስለሚካሄድ፣ ሠራተኛው መደብና አስተዋጽኦው ከሞላ ጎደል በሮቦቶች ይተካል፡፡ ነገር ግን ወደዚህ ውጤት የሚያደርሰን የትኛው ሥርዓት ነው? ካፒታሊዝም በጨቋኝነት ከተወገዘ ሌላ የሽግግር ሥርዓት መኖር አለበት፡፡

ታላቁ ካርል ማርክስ አብዛኛውን የምርምር ጊዜውን ያሳለፈው የካፒታሊዝም ሥርዓትን በማጥናት ነው፡፡ ዋናው የታተመ የጥናት ውጤት ሥራውም ‹‹ዳስ ካፒታል›› የተሰኘው መጽሐፉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ካሰፈራቸው ቁም ነገሮች ክብደት ሊሰጠው የሚገባው፣ ካፒታሊዝም ዕድገቱን ሲጨርስ ኮሚውኒስት ማኅበረሰብ ይገነባል ያለው ይመስለኛል፡፡ ግን ካፒታሊዝም ዕድገቱን የሚጨርሰው መቼ ነው? ለምሳሌ በመላው ዓለም ካፒታሊስቶች የምርት ተግባሮችን በሮቦቶች ከተኩና የሠራተኛውን መደብ ከሥራ እንቅስቃሴ ውጭ ካደረጉት፣ የሚያመርቱትን ምርት ለማን ይሸጡታል? የሚል ጥያቄ መነሳት ይኖርበታል፡፡

ካርል ማርክስ እንዳለው፣ በስልተ ምርቱና በምርት ግንኙነቶች መካከል ቅራኔ ይፈጠራል፡፡ ይህ ሲከሰት የሥርዓት ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ የሥርዓት ለውጡ ሲመጣም በምርት መትረፍረፍ ምክንያት ‹‹ለእያንዳንዱ እንደ ፍላጎቱ›› የሚሰጥበት ሊሆን ይችላል ማለት ነው፡፡ ይህ የታላቋ ማርክስ ድንቅ አርቆ የማስተዋል ችሎታንና የፍልስፍናውን ጥልቀት ያስቃኛል፡፡

ካርል ማርክስ ከካፒታሊዝም ወደ ኮሚዩኒዝም በሚደረገው ግስጋሴ ወቅት ስላለው የሽግግር ወቅት ብዙ ሳይመራመርና ሳይጽፍ ተገታ፡፡ የብሩህ አዕምሮ ባለፀጋ የነበረው ማርክስ በሞት ከዚህ ዓለም ከተለየ 125 ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ ኋላ የመጡትና የሶሻሊዝምን ርዕዮት ምንነት ያቀነቀኑት እንደ ሌኒን ያሉ ተራማጅ የማርክስ ተከታዮች ነበሩ፡፡ ይሁንና ሶሻሊዝም ‹‹ካፒታሊዝም ዕድገቱን ሲጨርስ፤›› ከሚለው አመለካከት ጋር የሚጣረስ ነው፡፡ ሶሻሊዝም እንደ ሥርዓት ካፒታሊዝምን ለመተካት የሚጥር ርዕዮት ነው፡፡ ካፒታሊዝም በሶሻሊዝም የሚተካ ከሆነም የማርክስ፣ ‹‹ካፒታሊዝም ዕድገቱን ሲጨርስ ኮሚዩኒዝም ይተካዋል›› የሚለው አስተሳሰብ እንዴት ዕውን ሊሆን እንደሚችል ከጠየቅን፣ ሶሻሊዝም ካፒታሊዝም የቆመበትን መርህ ሙሉ በሙሉ የሚያፋልስና ውስጣዊ ተቃርኖ ያለበት ርዕዮት መሆኑን እንረዳለን፡፡

በካፒታሊዝም ሥርዓት መሠረት አንድ ሰው በግል ጥረቱ በፈጠረው እሴት የሚያገኘውን ገንዘብ የካፒታል ዕቃ (የማምረቻ መሣሪያ) ገዝቶ፣ ካፒታሊስት ድርጅት ሊያቋቁም ይችላል፡፡ በዚህም ድርጅት ሠራተኞች ቀጥሮ በነፃ ገበያው መሠረት ደመወዝ በመክፈል ሊያሠራ ይችላል፡፡ በሶሻሊዝም ሥርዓት ግን ይህ የተከለከለ ነው፡፡ ምክንያቱም ግለሰቦች የማምረቻ መሣሪያ ባለቤት እንዲሆኑ አይፈቀድም (ቢያንስ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ)፡፡ ካፒታሊዝም በግል ጥረትና እሴት ፈጠራ ላይ የተመሠረተ ርዕዮት ነው፡፡ ኅብረተሰብ የግለሰቦች ስብስብ እንደመሆኑ፣ ሶሻሊዝም የግለሰቡን ጥረትና የእሴት ፈጠራ የሚያዳክም ከሆነ፣ ግለሰቦች ብሎም ኅብረተሰቡ እንዴት ወደፊት ሊገሰግሱ ይችላሉ? ለዚህም ነው፣ ሶሻሊዝም ፀረ ዕድገት ነው የሚባለው፡፡

አዲሱ ማርክሲዝም

አዲሱ ማርክሲዝም ካፒታሊዝም ዕድገቱን ሲጨርስ ወደ ኮሙዩኒዝም ሥርዓት ይሸጋገራል በሚለው መሠረታዊ ንድፈ ሐሳባዊ መርኅ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ንድፈ ሐሳባዊ መሠረቱ የተሳሳተ በመሆኑ፣ ሶሻሊዝምን እንደ ርዕዮትም ሆነ እንደ ሥርዓት አይቀበለውም፡፡ ሆኖም የካፒታሊዝም ታሪካዊ ዕድገት ብዙ ጉድለቶች ስላሉበት፣ ከንድፈ ሐሳባዊ መሠረቱ ያፈነገጠ ሆኗል፡፡ ከፊውዳሊዝም የወረሰው የመሬት ይዞታ ኢ-እኩልነቶችን በማስከተሉ፣ ከመነሻው የተከሰተው የካፒታልና የዕውቀት ልዩነት የነፃ ገበያና የነፃ ውድድር መርህን አፋልሷል፡፡ በመሆኑም፣ ካፒታሊዝም የሚያስፈልገው እንደ ሶሻሊዝም ዓይነት የሽግግር ሥርዓት ሳይሆን፣ ታሪካዊውን ኢፍትሐዊነትና ኢእኩልነት ለማካካስ የሚያስችል ጥገናዊ ለውጥ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በስዊድን፣ በኖርዌይ፣ በፊንላንድና በመሳሰሉት አገሮች ውስጥ ሲሞከር የቆየው የ‹‹ዌልፌር ስቴት›› በአብነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ዌልፌሪዝም ግን እሴት ሳይፈጥሩ ገንዘብ የሚገኝበት ሥርዓት መሆን የለበትም፡፡ ዌልፌሪዝም ከስያሜው ጀምሮ መቀየር ያለበት ሆኖ፣ ዓላማው ታሪካዊ እኩልነቶችን በመቀነስ፣ ሁሉም ዜጋ በነፃ ገበያው ውስጥ እኩል ተወዳዳሪ የሚሆንበትን ሥርዓት ማዳበር ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡

አዲሱ ማርክሲዝም መደበኛ ትርፍን እንደ ብዝበዛ ውጤት አይመለከትም፡፡ ይልቁኑ በንግድ ሒደት ከሸቀጦች አንፃራዊ ዕጥረት አኳያ የሚገኝ፣ ከማምረቻ ወጪ የበለጠው ጥቅም ነው የሚለውን ፅንሰ ሐሳብ ይቀበላል፡፡ የትርፍ ክፍፍሉ ላይ ግን ሠራተኛው (ከደመወዙ ባሻገር) የተወሰነ ድርሻ እንዲኖረው ይሟገታል (ካፒታሊስቶች) የማምረቻ ቴክኖሎጂን ለማሻሻል ከትርፉ ላይ ተለቅ ያለ ድርሻ ለምርምርና ልማት ማዋል እንዳልባቸው የታወቀ ቢሆንም)፡፡ አዲሱ ማርክሲዝም፣ ነፃ ገበያውና ነፃ ውድድሩ እየተጠናከሩ ስለሚሄዱ፣ የጥረትና የችሎታ ልዩነት ከሚፈቅደው በላይ የገቢና የሀብት ልዩነት እንደማይኖር ይጠቁማል፡፡ የሥራ አጥነት ምጣኔው አነስተኛ እንደሚሆን ያመለክታል፡፡ ይሁንና የእስካሁኑ የካፒታሊዝም ዕድገት ታሪክ ይህን አያመላክትም፡፡ በተለይ በአሜሪካ የገቢና የሀብት ልዩነቱ ከመጥበብ ይልቅ እየሰፋ ይገኛል፡፡ በአውሮፓ በተለይ እንደ ስፔንና ግሪክ ባሉት አገሮች ውስጥ የሥራ አጥነት ምጣኔው ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ፣ ማርክሳዊው የሥራ አጦች ሠራዊት ዕውን የሆነ ይመስላል፡፡ በዓለም ደረጃ የታየው የካፒታል ክምችት ግዙፍ ድንበር ዘለል ኮርፖሬሽኖች እንዲፈጠሩ በማድረግ እያደገ በሚሄደው የምርምርና ልማት ወጪ አማካይነት ሳይንስና ቴክኖሎጂ እየመጠቀ እንዲሄድ ያስቻለ ቢሆንም፣ በስልተ ምርቱና በምርት ክፍፍሉ መካከል ያለው ቅራኔ እየጎላ መጥቷል፡፡ ለዚህም ነው በአዲሱ ማርክሲዝም ከሚገኘው ትርፍ የሠራተኛው መደብ የበለጠ ተካፋይ መሆን አለበት ተብሎ የሚቀነቀነው፡፡

ስለ የእኛዎቹ ቢሊየነሮች

በአሜሪካ እነ ቢል ጌትስ፣ እነ ዋረን ቡፌት፣ እነ ማርክ ዙከርበርግ ቢሊየነሮች የሆኑት በምርትና በአገልግሎት የአሜሪካን ሕዝብ አንበሽብሸው ነው፡፡ የእኛዎቹ ቢሊየነሮች ምን ሠርተው፣ ምን አምርተው ነው ይህን ሁሉ ገንዘብ ያካበቱት?  የምርትና የአገልግሎት ዕጥረት ባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን ዕጥረት ማቃለል በመቻላቸው ቢሊየነር ሆነዋል ለማለት አንችልም፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በምግብ እጦት ምክንያት የረሀብ ሥጋት እየተስፋፋ መምጣቱ እየተነገረ ነው፡፡ የነፍስ ወከፍ ምርትና አገልግሎት መጠን ስለቀነሰ፣ የኑሮ ደረጃችን ከመሻሻል ይልቅ እየወረደ መጥቷል፡፡

በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ ባለሀብቶቹ ቢሊየነሮች ሊሆኑ የሚችሉባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሙስና (ስርቆትን ይጨምራል)፣ መደበኛ ያልሆነ ትርፍ (ልዕለ ትርፍ ወይም ሱፐር ፕሮፊት)፣ ከከፍተኛ ሽያጭ የሚገኝ መደበኛ ትርፍ፣ ስጦታና ሽልማት፣ ሎተሪ፣ መደበኛ ትርፍ፣ ወዘተ ዋናዎቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ቢሊየነሮች በምርትና አገልግሎት አቅርቦት ላይ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳላደረጉ ስለሚገመት፣ ከላይ ከተጠቀሱት ዘዴዎች እነሱን እንደሚመለከቱ የሚገመቱት ሙስናና መደበኛ ያልሆነ ትርፍ ናቸው፡፡ በሙስና ውስጥ ከሕጋዊ አሠራር ውጭ የተገኘ የባንክ ብድር፣ የከተማና የገጠር መሬት፣ ከፍተኛ መደለያ ገንዘብ (ጉቦ)፣ ከገበያው በታች የተሸጠ ንብረት፣ ከገበያው በላይ በሆነ ዋጋ ያለ ግልጽ ጨረታ የተሰጠ የሥራ ኮንትራት የመሳሰሉት የሚካተቱ ሲሆን፣ መደበኛ ያልሆነ ትርፍ በሞኖፖል ወይም በከፊል በሞኖፖል ከተያዘ ድርጅት የሚገኝ ልዕለ ትርፍን ይመለከታል፡፡

በሌላ በኩል፣ መንግሥት አውቆም ሆነ ሳያውቅ በተሳሳተ የገንዘብ ፖሊሲ ምክንያት የሚፈጠረው ከፍተኛ የዋጋ ንረት ከሕዝብ ሀብትና ንብረት ለመዝረፍ እንደ ዋና መሣሪያ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ ቪላ ቤት በሃምሳ ሺሕ ብር ይሸጥ በነበረበት ጊዜ መቶ ሰዎች ሊገዙት አቅም ከነበራቸውና፣ በመንግሥት የተሳሳተ የገንዘብ ፖሊሲ ሳቢያ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው የገንዘብ መጠን ከምርት ዕድገት ጋር ባልተጣጣመ መንገድ ጨምሮ ዋጋው አንድ ሚሊዮን ብር ቢገባ፣ በትእዛዝ ከፍተኛ የባንክ ብድር እንዲያገኝ የተፈቀደለት ሰው፣ በዋጋ ንረት መሣሪያነት ቪላ ቤቱን ከሕዝቡ ነጥቆ ይወስደዋል፡፡ የተሳሳተው ፖሊሲ ሳይሻሻል ከቀጠለም በሙስና በአንድ ሚሊዮን ብር የገዛውን ቪላ ቤት መልሶ በሦስት ሚሊዮን ሊሸጠው ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ሙሰኞች በዋጋ ንረት አማካይነት ሀብትና ንብረት ሊዘርፉ እንደሚችሉ መገንዘብ ይገባናል፡፡

ማጠቃለያና የመፍትሔ ሐሳብ

የኢሕአዴግ መንግሥት በመሠረተው የኢኮኖሚ መዋቅር ውስጥ በነፃ ገበያና በነፃ ውድድር ላይ ተመርኩዞ በሕጋዊ መንገድ ቢሊየነርም ሆነ ሚሊየነር የሚኮንበት ዘዴ በጣም ጠባብ ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከተው፣ በአሜሪካና በአውሮፓ በታሪካዊ ኢእኩልነቶች መሠረት በመነሻው ላይ ለሁሉም እኩል የሆነ መደላድል ያልነበረ ቢሆንም፣ ነፃ ገበያና ነፃ ውድድር ግን ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ግን እኩል መደላድልም፣ ነፃ ገበያም፣ ነፃ ውድድርም ገና አልዳበሩም፡፡ በሌላ አገላለጽ መደላድሉ የተስተካከለም ሆነ መደላድሉ ያልተስተካከለ ካፒታሊዝም የለም፡፡ በዚህ ምክንያት አዲሱ ማርክሲዝምም የለም፡፡ አሮጌው ማርክሲዝም እንደሌለም ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ሊኖር የሚችለው ሥርዓት የሙስናና የዘረፋ የግንኙነት መረብ (ኔትወርክ) ነው፡፡ መንግሥት ራሱ የዚህ የዘረፋ መረብ ዋናው አካል ሆነ እንጂ፣ እነዚህ  ቢሊየነር ተብዬዎች ራሳቸው ይፋ ባደረጉት የሀብት መረጃ መሠረት በፀረ ሙስና ኮሚሽን ቅድመ ምርመራ ተደርጎባቸው ለፍርድ መቅረብ ይገባቸው ነበር፡፡ ነገሩ ሁሉ ግን ‹‹ልጁ ቀማኛ አባቱ ዳኛ›› ሆነና የመፍትሔ ሐሳብ ከማቅረቡ ላይ አንደበታችን ተዘጋ፣ ብዕራችንም ነጠፈ፡፡

ለማንኛውም አንድ ሁለት የመፍትሔ ሐሳቦች ለመወርወር እንሞክር፡፡

1ኛ. በኢትዮጵያ አዲሱን ማርክሲዝም ከሩቅ አሸጋግሮ የሚማትር የፍትሐዊ ካፒሊዝም ሥርዓት (መደላድሉ የተስተካከለ) ለማዋቀር ጥረት ማድረግ፤

2ኛ. ሚሊየነሮችና ቢሊየነሮች የተባሉትም አስፈላጊውን ቅድመ ምርመራ በማድረግ አግባብ ያልሆነ ሀብት ያካበቱትን ለፍርድ ማቅረብና በሕጉ መሠረት እንዲቀጡ ማድረግ፤

3ኛ. በአዲሱ ማርክሲዝም ርዕዮት መሠረት፣ የመደብ ጠላቶች ካፒታሊስቶች ሳይሆኑ ሙሰኞች መሆናቸውን ተገንዝበን ሕዝባዊ ትግሉን በእነሱ ላይ ማካሄድ ተገቢ ነው፡፡ ሙስና ይውደም! ፍትሐዊ ካፒታሊዝም ይለምልም! ቸር ይግጠመን፡፡

(ተክለብርሃን ገብረሚካኤል፣ ከአዲስ አበባ)  

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...