Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየሴቶች ቀን የማያስታውሰው ሴተኛ አዳሪነት ከኢትዮጵያ ሕግ አንፃር

የሴቶች ቀን የማያስታውሰው ሴተኛ አዳሪነት ከኢትዮጵያ ሕግ አንፃር

ቀን:

ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀንን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕውቅና ችሮት በይፋ መከበር ከጀመረ አርባ ዓመታት አልፈውታል፡፡ ለዚህ በዓል መሠረት የሆነው እንቅስቃሴና ትግል ከተጀመረ ግን አንድ ክፍለ ዘመን በልጦታል፡፡ በተለይ ከእንቅስቃሴው ጋር በተገናኘ ሁልጊዜም  ከፍተኛ ትግል የፈጸሙ ብሎም በምርጫቸው ኢትዮጵያዊ የሆኑ፣ ሕይወታቸው ካለፈም በኋላ እዚሁ የተቀበሩ አንዲት ሴት አሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1914 የሴቶች መብትን ለማስከበር ሰላማዊ ሠለፍ ይመሩ ስለነበር ለእስራትም ተዳርገዋል፡፡ እኒህ ሴት ሲልቪያ ፓንክረስት ናቸው፡፡ እሳቸውና አጋሮቻቸው የታገሉለት ዘርፈ ብዙው የሴቶች ጥያቄ በዋናነት በሶሻሊስት አገሮች በየዓመቱ ሲከበር ቆይቶ ሲልቪያ ፓንክረስት ካለፉ በኋላ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በየዓመቱ ‹‹የሴቶች ቀን›› ተብሎ እየተከበረ ይገኛል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1996 ጀምሮ ደግሞ በየዓመቱ መሪ መልዕክት እየተመረጠለት ይከበራል፡፡ ለዚህ ዓመትም ወደ አማርኛ ሲጠጋጋ ‹‹ለለውጥ ደፋር ሁኑ!›› የሚል ጭብጥ ተመርጦለታል፡፡ እስከ ዛሬ ከነበሩት ጭብጦች ውስጥ በቀጥታ ሴተኛ አዳሪዎችን የሚመለከት ግን የለም፡፡ በዚህ ተግባር ተሰማርተው የሚገኙት በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንስት ቢኖሩም ቅሉ፣ እነሱን ብቻ የሚመለከት መልዕክት ተቀርጾና ተከብሮ አያውቅም፡፡ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሚዲያዎችም የተላለፉት የባለሥልጣናት ንግግር፣ የሴቶች ማኅበራትና ፌዴሬሽንም ቢሆኑ ስማቸውን እንኳን ሲጠቅሱ አልተሰሙም፡፡ ይህ ጽሑፍ የሚያተኩረውም እነሱን የሚመለከቱትን የሰብዓዊ መብት፣ የውልና የወንጀል ሕግጋት መቃኘት ላይ ነው፡፡ ከቅኝቱም በኋላ በዋናነት ስለእነሱ ሲባል፣ በመቀጠል ግን በአጠቃላይ ስለማኅበረሰቡ የአሁንም የወደፊትም ሁለንተናዊ ደኅንነትና ዕድገት ሲባል የፖሊሲና የተጨማሪ ሕግ አስፈላጊነትን ይጠቁማል፡፡

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሁሉም ዓይነት ገንዘብ ተከፍሎ የሚፈጸሙ የወሲብ ድርጊት አይዳሰሱም፡፡ በተለምዶ ‘ሴተኛ አዳሪነት’ (rostitution) ተብሎ የሚታወቀው እንጂ፡፡ የወንጀል ሕጉ የዝሙት አዳሪነት ብሎ ቢጠራውም፣ ሐረጉ ያልተለመደ ከመሆኑም በላይ ክብረነክ ስለሚመስል ይህ ጽሑፍ ግን የተለመደውን አጠራር ለመጠቀም መርጧል፡፡ ሴተኛ አዳሪነት ሲባልም አንዲት ሴት በተደጋጋሚ ቢሆንም ባይሆንም፣ ከአንድ ወንድ ጋር በክፍያ የሚፈጸመውን ወሲብ ይመለከታል፡፡

  ሴተኛ አዳሪነት ቀደምት ከሚባሉት ሙያዎች እንደ አንዱ ይቆጠራል፡፡ የሌለበት አገር አለ ማለትም አይቻልም፡፡ በኢትዮጵያም ቢያንስ በ17ኛው ክፍለ ዘመን ነገሥታቱ በሚሠፍሩበትና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር በከተመባቸው ኋላም ከተማ በሆኑት ቦታዎች ሴተኛ አዳሪዎች እንደነበሩ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ በአጠቃላይ የሴተኛ አዳሪነት ታሪክ  ደግሞ፣ በቅርቡ ሕይወታቸው ያለፈውና እንደ እናታቸው እዚሁ ኢትዮጵያ የተቀበሩት፣ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ጽፈውልናል፡፡ ስለዚሁ ጉዳይ ከተለያዩ የትምህርት ዘርፎች አንፃርም በየደረጃው የሚገኙ ተማሪዎች የመመረቂያቸው ማሟያ በማድረግ አጥንተውታል፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍም ይሁን አገር በቀል ድርጅቶች ድጋፍም እንዲሁ በርካታ ጥናቶች ተከናውነዋል፡፡

እነዚህን ጽሑፎች እንደው ከላይ ከላይ እንኳን በስሱ የተመለከተ ሰው ቢያንስ ሁለት ነጥቦችን ይታዘባል፡፡ የመጀመሪያው በኢትዮጵያ የነበረው ሴተኛ አዳሪነት እንደ ሌሎች አገሮች በተለይም እንደ አውሮፓውያን ብዙም የሚያዋርድ ተግባር ያልነበረ መሆኑን ነው፡፡ ሴቶቹም ቢሆኑ ይህንኑ ሙያቸውን በኩራት ይናገሩ ነበር፡፡ በ1923 ዓ.ም. በተከናወነው የጎንደር ከተማ ሕዝብ ቆጠራ ውጤት ካሰፈራቸው ውስጥ አንዱ የኗሪው ሙያ ስለነበር ሴተኛ አዳሪነትም እንደ ሙያ ተይዞ የሴቶቹ ብዛት ተዘግቧል፡፡ የሚያዋርድ ስላለመሆኑ የአውሮፓውያን ተጓዦችም ግርምታዊ ትዝብት ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ እየተቀየረ የመጣውና እንደሚያዋርድና አስነዋሪ እንደሆነ እየተቆጠረ የመጣው በቅርብ በተለይም ከደርግ ዘመን ጀምሮ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ ከሌሎች አገሮች በተለየ መልኩ የሴተኛ አዳሪዎች ቁጥር በትክክል እንኳን ባይሆን በሚጠጋጋ ደረጃም ቢሆን ሊታወቅ ያለመቻሉ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የተለያዩ ፖሊሲዎችን ለመንደፍ ሳንካ ይሆናል፡፡ ከተለያዩ ዕይታ አንፃርም ትንታኔ በማቅረብ ለፖሊሲ አውጭዎች ግብዓት እንዳይሆን እንቅፋት ይሆናል፡፡

ሴተኛ አዳሪነትና የሰብዓዊ መብት ሕግጋት

 • ሴተኛ አዳሪነት ድርጊትን በራሱ እንደ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚወስዱት አሉ፡፡ ለምን ብለው ለሚሞግቷቸው ደግሞ  ምላሻቸው የሚያጠነጥነው ተግባሩ የሴትን ልጅ ገላ እንደ ሸቀጥ በክፍያ ማግኘት ስለሆነ አዋራጅ፣ ክብረነክ፣ ጤናንና አካላዊ ደኅንነትን፣ እኩልነትን የሚቃረን፤ ሲብስም ከአካላዊም ሆነ አዕምሯዊ ጥቃትና ኢሰብዓዊ አያያዝ ነፃ የመሆን መብትን የሚጥስ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡

በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ሴቶቹ ላይ የሚደርሱት ጥቃቶች (አዕምሯዊም ይሁኑ አካላዊ) ለራስ የሚሰጥ ክብርና መተማመን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስላላቸው የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ሊኖረው የሚገባውን ክብር ስለሚጎዳ ሰብዓዊ መብትን ይጥሳል ይላሉ፡፡ በመሆኑም መጥፋት እንዳለበት አጥብቀው ይሟገታሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ጥበቃ መደረግ ያለበት ያለፍላጎታቸው ተገደው እንዳይገቡ፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱትን ጥበቃ እስከተደረገላቸው ድረስ ብሎም መገለልና ማዳላት እስካልተፈጸመባቸው ድረስ ሴተኛ አዳሪነት ወንጀል መሆን የለበትም፤ እንደውም ሕጋዊ መሆን አለበት የሚሉም አሉ፡፡

በሴተኛ አዳሪነት ለመሠማራት ሊገፋፉ የሚችሉ በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ዋነው ኢኮኖሚያዊው ነው፡፡ በችግር ምክንያት ሙያውን የሚቀላቀሉት ወደ መቶ ፐርሰንት ይጠጋሉ፡፡ በሌሎች ምክንያቶች ሴተኛ አዳሪነትን የሚቀላቀሉት ኢምንት ናቸው፡፡

ከላይ የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ የሰብዓዊ መብቶች ዋናው መሠረታቸው የሰው ልጅ ክብር (ignity) ነው፡፡ ክብሩን ተነጥቆ ነገር ግን ሰብዓዊ መብቱ ተከብሮለታል ሊባል የሚችል ሰው ካለ ነገሩ ከቧልትነት የሚዘል አይደለም፡፡ ሰውን እንደ ሸቀጥ መውሰድ ካለም እንዲሁ ክብር ተጠብቋል ሊባል አይችልም፡፡

ሰብዓዊ መብትን ከሴተኛ አዳሪነት ጋር በማገናኘት ትንታኔ መስጠት የሚፈለግ ማንም ሰው ሊዘለው የማይችለው ሁሉን ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት መግለጫን ነው፡፡ ሰብዓዊ መብት ግቡ ወይም ዓላማው በዚህ ሰነድ ላይ ስለተቀመጠ ነው፡፡ ሰው በሰውነቱ ብቻ ያሉትን መብቶች ሲዘረዝር ሰብዓዊ ክብርን እንደ አንኳር መርሕ ወስዶታል፡፡ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ቢኖር ማንም ሰው ያለው ሰብዓዊ መብት ሴተኛ አዳሪዎችም አላቸው፡፡ ማንም ሰው ካለው በበለጠ ደግሞ ሴቶች ብቻ ያላቸውን ሰብዓዊ መብቶችም ጭምር አሏቸው፡፡ ቀጥሎ የሚነሱት ከእነዚህ  ላይ የተጨመሩትን ነው፡፡

ከላይ የተገለጸው ሰነድ በፀደቀ በዓመቱ ማለትም እ.ኤ.አ. በ1949 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰዎች ዝውውርን ለመቆጣጠርና ሌሎች በሴተኛ አዳሪነት ከመጠቀም የሚከለክለው ስምምነትም አገሮች ሴተኛ አዳሪነት ሰው በሰውነቱ ተከብሮና ታፍሮ የመኖር መብት ጋር ስለመጋጨቱ ዕውቅና ሰጥተውታል፡፡ ይህ ሰነድ በተለይ ሌሎች ሰዎች በሴተኛ አዳሪነት ጥቅም የማግኘታቸውን ነገር ይኮንናል፤ ይከለክላልም፡፡

በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ አድልኦን ለማስወገድ የተደረገው ስምምነትም ሌላው ተጠቃሽ ሰነድ ነው፡፡ አገሮች በማናቸውም መልኩ የሚፈጸሙ ሕገወጥ የሴቶች ዝውውርም ሆነ በሴተኛ አዳሪነት የሚፈጸሙ ብዝበዛዎችን የመቆጣጠር ግዴታ ጥሎባቸዋል፡፡ በሌላ አገላለጽ ሴተኛ አዳሪዎች ከብዝበዛ የመጠበቅ መብት አላቸው ማለት ነው፡፡

ከእነዚህ ሌላ ደግሞ፣ በተለምዶ በሲሲሊ ዋና ከተማ ስም፣ የፓሌርሞ ፕሮቶኮሎች በመባል ከሚታወቁት መካከል አንደኛው ሕገወጥ የሰዎች በተለይም የሴቶችና የሕፃናትን ዝውውርን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የወንጀሉን ፈጻሚዎች ለመቅጣት የወጣውን ፕሮቶኮል በዋናነት ሴተኛ አዳሪዎቹ ከአገራቸው ውጭ በሆኑ ጊዜ አገሮች ያለባቸውን ግዴታ ይዘረዝራል፡፡ ይህንን ፕሮቶኮል የኢትዮጵያ መንግሥት ከወጣ ከ12 ዓመታት በኋላ በ2004 ዓ.ም. አፅድቃዋለች፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ኮፊ አናን፣ እ.ኤ.አ. በ2003 በተለይም ለድርጅቱ ሠራተኞችና ሰላም አስከባሪዎች እንዲሁም በአጋርነት ስለሚሠሩ አካላት ‹‹የዜሮ ትዕግስት›› ፖሊሲ በማለት ያስተላለፉት ውሳኔ  ሌላው ተጠቃሽ ሰነድ ነው፡፡ እንደዚህ ሰነድ ማንኛውም የተባበሩት ድርጅት ሠራተኛ፣ ሰላም አስከባሪ ወይም በአጋርነት የሚሠራ ሰው በማናቸውም መልኩ የሴተኛ አዳሪነት ባሕርይ ያለው ድርጊት መፈጸም ክልክል ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ተግባር የሴትን መብት የሚጥስ ስለሆነ ድርጅቱ ጭራሹን የማይታገሰው እንደሆነ መመርያ አውጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትንም ስንመለከት ማንም ሰው በአንቀጽ 24 እና 25 ላይ የሚከተሉትን መብቶች እናገኛለን፡፡ ማንም ሰው ሰብዓዊ ክብሩ የመከበር፣ ስብዕናውን የማሳደግ መብት፣ በሰብዓዊነቱ ዕውቅና የማግኘት፣ በሕግ ፊት እኩል መሆንና እኩል ጥበቃ የማግኘት፣ በማኅበራዊ አመጣጥ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግበት ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት እንዳላቸው ተደንግጓል፡፡ በአንቀጽ 37 መሠረት ደግሞ ማንኛውም ፍትሕ የማግኘት መብት አለው፡፡

መንግሥትም እነዚህን መብቶች የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ በሌሎችም እንዳይጣሱ የማስከበር ብሎም ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ኃላፊነት አለበት፡፡ ከተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ወይም እኩል ዕድል በመነፈጋቸው ምክንያት ወደዚህ ተግባር ለመግባት እንዳይገፉ የመሥራት ግዴታ አለበት፡፡ እኩል መሆን አለመሆናቸውን ወደ ሴተኛ አዳሪነት የገቡበት ሁኔታም ጭምር ይወስነዋል፡፡ እኩል በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ከሆነ አድልኦ ተፈጽሞባቸው ነበር ማለት ነው፡፡  ሴተኛ አዳሪ በመሆናቸው ምክንያትም ከተለያዩ መንግሥታዊ አገልግሎቶች የመሳተፍ መብታቸው ሊነፈግ አይገባም፡፡ ለአብነት ጥቃት ደርሶባቸው ለፖሊስ ሪፖርት ሲያደርጉ፣ ፍርድ ቤት ሲሄዱ፣ በሌሎችም ተቋማት እኩል መገልገል አለባቸው፡፡ እንደማንኛውም ዜጋ መጠለያ (ለምሳሌ ኮንዶሚኒየም) እና ሌሎች አግልግሎቶችን የማግኘት መብት አላቸው፡፡

 • አዳሪነትና የውል ሕግ
 • አዳሪነት በክፍያ እንደሚፈጸም ከላይ ተገልጿል፡፡ እዚህ ላይ ውልን የሚመለከት አንድ ቁምነገር መነሳቱ አይቀርም፡፡ በወንዱና በሴቷ መካከል የሚደረገው ስምምነት በሕግ ዘንድ ተቀባይነት ወይም ዋጋ የሚሰጠው መሆኑ አሊያም ያለመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ በወንዶቹ ከሚደርስባቸው አካላዊና ሌላ ጥቃት በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ ክፍያ የመከልከል ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ በዚህን ጊዜ በሁለቱ መካከል የተደረገው ስምምነት ዋጋ ከሌለው መብታቸውን የሚያስከብሩበት ሁኔታ አይኖርም ማለት ነው፡፡
 • የፍትሐ ብሔር ሕግ መሠረት የሰው ልጅ አካል ከንግድ ውጭ ነው፤ አካልን በሚመለከት የሚፈጠሩ ስምምነቶች እንዲፈጸሙ ማስገደድ አይቻልም፡፡ እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ የሰውነትና የነፃነት መብቶች ከንግድና  ከማንኛውም መሰል ልውውጥ ውጭ መሆናቸውን ነው፡፡ ወዶና ፈቅዶ በራስ ላይ የሚደረጉ ገደቦች ቢሆኑም እንኳን ዋጋ አልባ ናቸው፡፡ በመሆኑም የሴተኛ አዳሪነት አድራጎትም የአካልና የነፃነት ጉዳይ ስለሆነ ከንግድ ነክ ነገር ውጭ ነው ማለት ነው፡፡
 • በተጨማሪ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ስለውል በደነገገበት ክፍሉ ላይ አንድ ውል የተደረገበት ጉዳዩ ለሞራል ተቃራኒ ከሆነ እንደማይጸና ይገልጻል፡፡ ዋጋ አልባ ነው፡፡ ነገር ግን ምንም ሁኔታዎች ለሞራል ተቃራኒ እንደሆኑ የመወሰን ሥልጣን ለዳኞች የተተወ ነው፡፡ ዳኛው ሴተኛ አዳሪነት ለሞራል ተቃራኒ እንደሆነ አድራጎት ከቆጠረው የሚጸና ውል የለም ማለት ነው፡፡
 • ሕጋዊ ውጤትን በተመለከተ ሁለት ነጥቦች ሊታወሱ ይገባል፡፡ አንዱ ከወንዱ በኩል የሚነሳው ነው፡፡ ክፍያ በመፈጸሙ የተነሳ ቀድመው የተስማሙበትን በሕግ ሴቷን በጭራሽ ልትገደድ የማትችል መሆኗ ነው፡፡ ሴቷ ግን ክፍያ እንዲፈጸምላት ወንዱን ብትጠይቅ ቢያንስ ሊፈጸም ስለሚችል ተጠያቂያዊ ነው፡፡ አንዳንድ አገሮች ‹‹በከፊል ተፈጻሚ ውሎች›› በማለት ይገልጿቸዋል፡፡ እንደዚህ ደንብ፣ ሴቷ እንደስምምነቷ ካልፈጸመች የወሰደችውን ገንዘብ ብቻ እንደትመልስ ሊወሰንባት ሲችል፣ ወንዱ ግን የተስማማውን ክፍያ የመፈጸም ግዴታ አለበት፡፡
 • አዳሪነትና የወንጀል ሕግ
 • አዳሪነት በራሱ ወንጀል የሆነባቸው አገሮች አሉ፡፡ የዓረብ አገሮችና ቀደም ሲል ሶሻሊስት የነበሩት የምሥራቅ አውሮፓዎች ምሳሌ ናቸው፡፡ ወንጀል ሆኗል ማለት ግን ጠፍቷል ማለት ስላለሆነ ሕገወጥነትን ማብዛት፣  ሴቶቹንም ለጥቃት ማጋለጥ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ጥቃቱ ደግሞ ከሕግ አስከባሪዎችም፣ ከሌሎች ወንዶችም ጭምር ነው፡፡ የሚፈጸምባቸውን ጥቃት ሪፖርት ሲያደርጉ ስለሚያዙ ከመደበቅ የተሻለ አማራጭ የላቸውም፡፡
 • በተለየ መልኩ ደግሞ በግል መሥራት የተከለከለባቸው፣ ነገር ግን ሌሎች ከሴተኛ አዳሪነት ገቢ የሚያገኙትንና የሚያቃጥሩትን ብቻ የሚቀጡ አገሮች አሉ፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ እንግሊዝን፣ አየርላንድን፣ ጣሊያን፣ ፖላንድን፣ ፊላንድን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ የመንገድ ላይ ሴተኛ አዳሪነትን ብቻ ነጥለው ወንጀል ያደረጉትም  አሉ፡፡
 • አዳሪነት በተጨማሪ ማገናኘትም ሆነ የሴተኛ አዳሪ ቤት ማዘጋጀት የተፈቀደባቸው አሉ፡፡ ኔዘርላንድ፣ ጀርመን፣ ግሪክ፣ ኒውዚላንድ ምሳሌ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ግን ብዝበዛና ዝውውር ይፈቀዳል ማለት አይደለም፡፡ ሴተኛ አዳሪዎችን የማገናኘትና ለሴተኛ አዳሪነት ቤት ማከራየትን በተመለከተ የተባበሩት ድርጅት የተወሰኑት ኮሚሽኖች አቋም ለምሳሌ የተባበሩት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ባን ኪ ሙንን ጨምሮ ሕጋዊ እንዲሆኑ ነው፡፡
 • ከቀረቡት ከሦስቱ አማራጮች ለየት የሚለው ‹‹የኖርዲክ አብነት›› የሚባለው አካሄድ ነው፡፡ ይኼ በመክፈል የሚፈጽሙትን ወይም ወንዶቹን መቅጣትና ክፍያ በመፈጸም ከሴተኛ አዳሪ ጋር ግንኙነት ማድረግን ወንጀል ያደረጉት ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ የወንጀል ሸክሙን ከሴቷ ወደ ወንዱ አዙረውታል፡፡ ነገሩ ‹‹ገዥ ከሌለ ሻጭ አይኖርም›› በሚል መርህ ላይ ተመሥርቶ ፈላጊን በመቅጣት አቅራቢን ማጥፋት እንደማለት ነው፡፡
 • ኢትዮጵያ ሕጎች ስንመጣ በመጀመሪያ የምንመለከተው ሴተኛ አዳሪዎቹ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ነው፡፡ ዋናውና ብዙዎቹን የሚያጋጥማቸው ለተላላፊ በሽታ መብዛትም በምክንያትነት የሚወሰደው አስገድዶ የመድፈር ወንጀል ነው፡፡ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 620 ላይ የተገለጹትን ስንመለከት ማንም ወንድ ኃይል በመጠቀም፣ በዛቻ፣ ህሊናን በማሳት ወይም መከላከል እንዳትችል በማድረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ከፈጸመ አስገድዶ ደፍሯል ይባላል፡፡ በመሆኑም፣ ገንዝብ ተክፍሏት ቢሆንም እንኳን በተለያዩ ምክንያቶች (በአካል ስትመለከት ሐሳብ በመቀየር ሊሆን ይችላል) የተስማማችውን ካፈረሰች በኋላ የሚፈጸመው ድርጊት ዞሮ ዞሮ አስገድዶ መድፈር ነው፡፡ ክፍያ መፈጸም ከተጠያቂነት አያድንም፡፡ ገንዘቡ እንዲመለስ ከመጠየቅ በስተቀር ማስገደድ ወንጀል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአንቀጽ 622 ላይ እንደተገለጸው ደግሞ የግብረ ሥጋ የመሰለን ማንኛውንም ለንጽሕና ክብር ተቃራኒ የሆነ ድርጊት እንዲፈጽም ማድረግ እስከ አሥር ዓመት ያስቀጣል፡፡
 • ከመድፈር በተጨማሪ የተላለፈ በሽታ ካለም በሽታ ማስተላለፍ ፈጻሚው ሊጠየቅ ይችላል፡፡ ሴተኛ አዳሪዎች በተደጋጋሚ የሚፈጸሙባቸው ጥቃቶችና ድብደባዎችም አሉ፡፡ 
 • አዳሪነት ዙሪያ የሚፈጸሙ የሚሳተፉ ሰዎችን የሚመለከቱ ወንጀሎችም አሉ፡፡ በዋናነት አንቀጽ 634 እና 635 ላይ የተገለጹት ናቸው፡፡ በእነዚህ አንቀጾች መሠረት፣ ማንም ሰው ጥቅም ለማግኘት ሲል ማለትም የገንዘብም ይሁን ወይም ሌላ የሚከተሉትን ድርጊቶች ከፈጸመ ጥፋተኛ ነው፡፡ የሌላውን ሰው የዝሙት ድርጊት የዘወትር መጠቀሚያው ካደረገ (ለምሳሌ በቡና ቤት ያሉ ሴቶችን የመውጫ /bar fine/ የሚቀበል ከሆነ)፣ ወይም ሌላን ሰው ለዝሙት ማቅረብ፣ ወይም ማቃጠር ወንጀል ነው፡፡
 • ሰው ቤቱን የሴተኛ አዳሪነት ድርጊት እንዲፈጸምበት ማድረግም ወይም ማከራየትም ያስቀጣል፡፡ እንደ ሕጉ ከሆነ በግል ቤት ቡና ቤት ከፍቶ ሴተኛ አዳሪዎችን በማሰባሰብ አገልግሎት ቢሰጥም ያስጠይቃል፡፡ አንድም ይሁን ከዚያ በላይ በሴተኛ አዳሪነት ሥራ ለሚያከናውኑ ሴቶች በማከራየት ገቢ ማገኘትም ወንጀል ነው፡፡ ሴቶቹ ጥፋተኛ አይደሉም፤ አከራዮቹ እንጂ! ይህ እንግዲህ ሕጉ ነው፡፡ ተግባሩ ግን ያው ማንም የሚያውቀው ነው፡፡
 • የሰዎች ዝውውርና ሴተኛ አዳሪነት በእጅጉ የተቆራኙ ናቸው፡፡ የሚዘዋወሩት ሴቶች ከሆኑና ማንም ሰው ለጥቅም ወይም የሌላን ሰው ፍትወተ ሥጋ ለማርካት በማሰብ ከፈጸመው በሴቷ ፈቃድም ቢሆን እንኳን በአንቀጽ 635 መሠረት ወንጀል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ለዝሙት አዳሪነት ማነሳሳት፣ ማባበል፣ ማቅረብ፣ ወይም በማናቸውም ዘዴ መገፋፋት፣ ለሌላ ሰው ለማቅረብ በዝሙት አዳሪ ቤት ማስቀመጥም ጭምር ጥፋት ነው፡፡
 • ገጹ ደግሞ የሴተኛ አዳሪዎቹን ራሳቸውን በደንብ መተላለፍ የሚያስጠይቁ አድራጎት አሉ፡፡ እነዚህ በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 846 እና 847 የተገለጹት ናቸው፡፡ ሴተኛ አዳሪነትን በይፋ ማስተዋወቅ (ለምሳሌ በሩ ክፍት በሆነ በቀይ ማብራት ላይ ራቁት ቢጤ ሆኖ ከርቀት በመታየት)፣ መንገድ ላይ በመቆም ማማለል፣ መጎተት፣ ማበሳጨት የመሳሰሉትንም ሊያካትት ይችላል፡፡ እንደ ሕጉ አገላለጽ ከሆነ በመንገድ፣ በአደባባይ፣ ለሕዝብ ክፍት በሆነ ቦታ ከመልካም ሥነ ምግባር ወይም ከመልካም ፀባይ ውጭ በሆነ አኳኋን ሌላን ሰው ምንም ያልፈለገን ለድሪያ መንካት ወይም ማበሳጨት፣ መገፋፋት፤ በዝሙት ወይም በኅብረተሰቡ በተወገዙ ድርጊቶች በመሠማራት አካባቢውንና ጎረቤቶችን ማወክ በደንብ መተላለፍ ያስቀጣል፡፡
 • ወንጀል የሆነው በርካታ ሆኖ ሳለ ሁሉም በሚባል ደረጃ በአደባባይ መከናወናቸው ነው፡፡ ምናልባት ያልተከለከለ ነገር ቢኖር በግል ቤት የሴተኛ አዳሪነትን በግል ማከናውንና ማንንም ሳያውኩ መንገድ ላይ በመቆም ብቻ ይመስላል፡፡ የመንገዱም ቢሆን በአደገኛ ቦዘኔነት ሊያስጠይቅ ይችላል፤ ምክንያቱም ሴተኛ አዳሪነት እንደ ሥራ በሕግ ዕውቅና ስላልተሰጠው፡፡
 • የማውጣትና ደንብ የማበጀት አስፈላጊነት
 • አገሮች ሴተኛ አዳሪነት የሚመለከቱ ፖሊሲዎች አሏቸው፡፡ ደንብም አበጅተውለታል፡፡ የፖሊሲዎቹ ትኩረትና ደንቦቹ የሸፈኗቸው ጉዳይ ላይ የተወሰኑ ልዩነቶች ቢኖራቸውም፡፡ ለፖሊሲ ማውጣት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ በዝርዝር ሳይሆን በማሳጠር ይቀርባሉ፡፡
 • ፖሊሲ ማውጣትና መተግበር ትኩረት እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡ ከመንግሥት በተጨማሪ የተለያዩ አካላትም በዕቅዶቻቸው ውስጥ እንዲያካትቷቸው ያግዛል፡፡ ለአብነት የሴቶች ፌደሬሽን፣ የሴቶችና ሕፃናት ሚኒስቴር ወዘተ፡፡ ከላይ ስለወንጀል እንዳየነው በተግባር ከሚያስጠይቀው የተተወው ስለሚበልጥ ሕጉን ሥራ ላይ እንዲውል ለማድረግ ግልጽ ፖሊሲ መኖሩ ይረዳል፡፡ ካልሆነም ያሉት ሕጎች ለማሻሻል ያስችላል፡፡ ሕግ ሲፈለግ የሚተገበር፣ ሳይፈለግ የሚተው ባጣቆየኝ ዓይነት መሆን ስለሌለበትም ጭምር ወይ መሻሻል ወይ ለመተግበር ያግዛል፡፡
 • በእንዲህ እንዳለ ሴተኛ አዳሪዎቹም ከፍትሕ ሥርዓቱም በወጉ እገዛ ስለማያገኙ፣ ሌሎች ተቋማትም ቢሆኑ በቀናነት ስለማይመለከቷቸው እንደዚህ ዓይነት ችግሮችን ለመቅረፍ፣ ሰብዓዊ ክብራቸው እንዲጠበቅ ለማድረግም ይረዳል፡፡ በተቻለ መጠንም ወደ ሌላ የሥራ መስክ መቀየር ለሚፈልጉ እገዛ ለማድረግ፣ ዕድሜ ልክ የሚሠራበት ሙያ ስላልሆነም የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት መንግሥታዊ ግዴታም ስለሆነ ነው፡፡
 • ሥርዓቱ (አስገድዶ መድፈር፣ ሌሎች ወሲባዊ ጥቃቶች፣ ውል መፍረስ፣ ለፖሊስ ሪፖርት ለማድረግ፣ ለምርመራ)፣ ለመደባቸው ምክንያት መድልኦ ወይም ሌሎቹን ውገና ሊኖር አይገባም፡፡ የመርማሪ ፖሊሶችን ማሠልጠን፣ መመርያ ማዘጋጀት፣ ሊታገሷቸው ስለሚገባቸው ነገሮች ማስታወቅ፣ የማስረጃ ዓይነቶችን ለይቶ ለፖሊስ ማሠልጠን ሊታሰብበት ይገባል፡፡ እንዲህ ሲሆን ማኅበራት ለመመሥረት፣ መብታቸውን ለማስከበር መደላድል እየሆነ ይመጣል፡፡
 • በተቃራኒው ደግሞ የየሌሎች አገሮች ልምድ እንደሚያሳየው ሴተኛ አዳሪነት የሚሠራባቸው ቦታዎችንም መለየት ተገቢ ነው፡፡ ከመኖሪያ ሰፈርም ሊለይ ይገባል፡፡ የቀይ መብራት (ለእዚህ ተብሎ የሚመደቡ ቦታዎች መጠሪያ ሆኗል) ሰፈሮችን በመለየት የተረጋጋና የሕፃናት መልካም አስተዳደግን ከግምት ማስገባት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ 
 • ሙያ የሚሠማሩ ሴቶች የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ ማስገደድም ሌላው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ፖሊሲ ያላቸው አገሮች፣ ያፈጠኑት በሳምንት ሁለት ጊዜ፣ ያዘገዩት ደግሞ በሦስት ወር አንድ  ምርመራ እንዲመረመሩና የምርመራ ውጤታቸውን የሚያሳይ ካርድ ሊይዙና ለደንበኛቸው ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ጣሊያናዊቷ ማዳም (ሴተኛ አዳሪ አቅራቢ ማለት ነው) ማምጣት ከጀመረች በኋላ ጣሊያኖቹ የሚያገኟቸው ሴተኛ አዳሪዎች በሳምንት ሁለት ጊዜ የጤና ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ እንዲህ ማድረጉ ኤችአይቪ/ኤድስን ለመቀነስና ተላላፊ በሽታን ለመከላከል ስለሚረዳና ጤናማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ሲባል ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ሴቷንም ሆነ ወንዱን ለመጠበቅም ይረዳል፡፡
 • ሥርዓቱም፣ በተለይ ወደ ሴተኛ አዳሪነት የሚገፋፉትንና አቃጣሪዎችን መርጦ መክሰስ፣  ሕፃናትን የሚመለምሉት ላይ ትኩረት መስጠት ይጠበቅበታል፡፡
 • የሥራ ዘርፍ በባሰ ሁኔታ ሴቶችን ለጥቃት የሚያጋልጥ ስለሆነ፣ ከሕጉ በተጨማሪ ራሳቸውን እንዴት ከጥቃት መከላከል እንዳለባቸውም የተለያዩ ስልቶችን ማስተማር ይገባል፡፡ ለወዲያው ወንዱን አቅም የሚያሳጡና ጉዳት የማያደርሱ ኬሚካሎችን ጭምር የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ እንዲሁም የሆቴልና መሰል ተቋማት ላይ ግጭት እንዴት መከላከልና መፈታት እንዳለባቸው ሲባል ፖሊሲ ማውጣትና ደንብ ማበጀት ተገቢ ነው፡፡ አልበለዚያ አዝማሪ፡-
 • አዲስ አበባ ችምችም ያለው መንደር፣
 • ሳይቃጠሩ እቅፍ አርጎ ማደር፡፡››
 • በዘፈነው የመንግሥት ባለሥልጣናትንም ሳይቀሩ እስክስታ እየመቱና ዳንኪራ እየረገጡ መኖሩ ውሎ አድሮ ለሴተኛ አዳሪዎቹም ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለሕዝቡም አይበጅም፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...