Sunday, April 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ድህነትና የአየር ብክለት ሲዛመዱ መዘዛቸው የከፋ ነው

በአሳምነው ጎርፉ

ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በየሩብ ዓመቱ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያሳትመው ‹‹ፋይናንስና ልማት›› የሚባል የምርምር መጽሔት አለው፡፡ ይኼ መጽሔት ከወራት በፊት ኒኮላስ ስተርን በተባለው ዓምደኛው “The Low Carbon Road” በሚል ርዕስ ጠንካራ ትንታኔ አቅርቧል፡፡ በዚህ የመጪው ዓለም በተለይም የሦስተኛው ዓለም ተግዳሮት ላይ ያተኮረ ጽሑፍ ድህነትና የአየር ብክለት የከፋ መዘዞች እንደሆኑ አስቀምጧል፡፡ መንግሥታትና ሕዝቦች በትኩረት ሊያስቡበት ስለሚገባው ጉዳይም በአፅንኦት ጠቁሟል፡፡

እንደ ኒኮላስ ትንታኔ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የዓለም አገሮች ለዓመታት በትኩረት የሠሩባቸው የምዕተ ዓመታት ግቦች ተግባራት ተጠናቀዋል፡፡ በኋላም የዘላቂ ልማት ግቦች እ.ኤ.አ. በመስከረም 2015 ፀድቀው በፍጥነት እንዲተገበሩ አቅጣጫ ወርዷል፡፡ በዚህም በተለይ ታዳጊ አገሮች ለመሠረተ ልማት መስፋፋት፣ ከብክለት ለፀዱ የኃይል አማራጮችና ማዕድናትን የማበልፀግ ሥራዎች፣ እንዲሁም ለኢንዱስትሪ መስፋፋትና ለከተሞች ማደግ መስጠት ያለባቸው ትኩረት ጎልቶ ተመልክቷል፡፡ ከዚህ አንፃር የእኛም አገር የጀማመረቻቸው ሥራዎች እንዳሉ የተሰወረ አይደለም፡፡

በእንግሊዛዊው ኢኮኖሚስት ትንታኔ መሠረት ዓለማችን በቀጣዮቹ 13 ዓመታት (እ.ኤ.አ እስከ 2030) ለመሠረተ ልማት ግንባታ ማስፋፊያና መልሶ ማደስ ብቻ 90 ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ያስፈልጋታል፡፡ ይኼ ብቻ ሳይሆን አሁን በዓለም ከተሞች የሚኖረው 3.5 ቢሊዮን ሕዝብ እ.ኤ.አ. በ2050 እስከ 6.5 ቢሊዮን እንደሚደርስ ተገምቷል፡፡ ይኼ አኃዝ ይበልጥ የሚጨምረው ደግሞ በታዳጊ አገሮች መሆኑ ታምኖበታል፡፡  

በዚህ ፈጣን የመሠረተ ልማት ግንባታና የከተሞች ዕድገት ታዲያ በጥንቃቄና በዕቅድ ካልተመራ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት ውድመትና የአየር ንብረት ብክለት እንዲከሰት በር እንዳይከፍት ተሠግቷል፡፡ የሚከናወኑ ልማቶች ፍትሐዊነትን ተላብሰው፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መንገድ መከናወን ካልቻሉም ጠቅላይ ባለሀብቶች (ሞኖፖሊስቶችን) በማብዛት ድህነት መስፋፋቱ አይቀርም፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ የአፍሪካ ኅብረትን የመሳሰሉ ተቋማት  በሦስትና በአራት አሥርት ዓመታት የተቀነበበ ግብ ማስቀመጣቸው ከዚሁ ነባራዊ ሥጋት በመነሳት ነው፡፡ ዓለም ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በፍጥነት እያሟጠጠች፣ በዚያው ልክ የሕዝብ ብዛቱ በከፍተኛ ፍጥነት እየገሰገሰ መሄዱ በአንዳች  ዓይነት ምጣኔ ሀብታዊ ሥሌት እየተጣጣመ እንዲሄድ ሁሉም ትረኩረትና ቀልቡን ሊነፍግ አይገባም፡፡   

ትኩረታችን መሆን ያለበት የአገራችን ጉዳይ ላይ ነውና ወደዚያው እንመለስ፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ያለማቅማማት ከአሥር ዓመታት ለበለጠ ጊዜ ፈጣንና ተከታታይ ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በዓመት ከ100 ሚሊዮን ኩንታል በታች የግብርና ሰብል ምርት ወደ 300 ኩንታል ማደጉ ብቻ አይደለም፡፡ ወይም ከአሥር ዓመታት በፊት በአፍሪካ አንደኛ ደረጃ ላይ የሚያስቀመጥን የቁም እንስሳት ሀብት በአሥር ሚሊዮን መጨመሩ አይደለም፡፡ ይልቁንም አገሪቱ በፈጣን የመሠረተ ልማት፣ የማኅበረ ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ላይ አተኩራ በመሥራቷ ነው፡፡ ለአንዳንዶች እንደ መንገድ፣ ቴሌኮም፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ የመጠጥ ውኃ፣ የከተማ መኖሪያ ቤቶች፣ ወዘተ ላይ የተደረገው አመርቂ ርብርብ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡

የእነዚህ መንግሥት የሕዝብን አቅምና ሀብት ተጠቅሞ የዘረጋቸው የልማት ሥራዎች መጠናከር የአገር ውስጡንም ሆነ የውጭ ባለሀብቱን ወደ ልማት የማተኮር ፍላጎት አነሳስተዋል፡፡ መጠኑና ዓይነቱ ይለያይ እንጂ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት መስክ እንዲሁም በንግድ ማኅበራዊ ኢንቨስትመንት ያለው የተነቃቃ እንቅስቃሴ ለአብነት ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ መንግሥትም ቢሆን አለኝ ከሚለው ‹‹ልማታዊ›› ባህሪይ አኳያ የገበያ ክፍተትን በመሙላት የሚሰማራባቸው መስኮች፣ ለተገኘው ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አላበረከቱም ማለት ክህደት ነው፡፡

ያም ሆኖ ግን አሁንም የዓለም አቀፉ ተፅዕኖም ሆነ የራሱ የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ተደምሮ ድህነትና ኋላቀርነት የኢትዮጵያ ሥጋት መሆኑ አልቀረም፡፡ የአየር ንብረት መበከልና የኤልሊኖ ተፅዕኖም አሁንም የሚሊዮኖችን ሕይወት በመገዳደር ላይ ይገኛል፡፡ የድርቅና የችግርን ቀቢፀ ተስፋ ተመላላሽ ክስተት ደጋግመን ማየታችንም ሊጤን ይገባዋል፡፡

ድህነት አንዱ መሰናክል

Africa Renewal (May, 2016) ዕትም “How did partnerships work for Africa” (አገሮች በአፍሪካ ምን እየሠሩ ነው?) የሚል ጽሑፍ አስነብቦ ነበር፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለቤትነት የሚታተመው ይኼ መጽሔት አፍሪካ ከሰላሳና ከአርባ ዓመታት በፊት በነበረችበት ጥቅል ቁመና ላይ እንዳልሆነች ገልጾ፣ ያም ሆኖ ግን አሁንም በሰላም፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ በልማትና ዘላቂ ዕድገት ላይ ያለው አተያይ ወጣ ገብነት ያለበት፣ አፈጻጸሙም ዥንጉርጉር ገጽታ ያለው መሆኑን አትቷል፡፡

የኢትዮጵያን ሁኔታ ሲነሳም አገሪቱ በጤና፣ በትምህርት፣ በመሠረተ ልማትና በመሰል ጉዳዮች የምዕተ ዓመቱን ግብ ማሳካቷን ያወሳል፡፡ አሁንም ግን የድህነት አጀንዳ (በተለይም 100 ሚሊዮን እየደረሰ ካለው ሕዝብ አንፃር) ጫና መፍጠሩን ግን አልሸሸገም፡፡

በአገሪቱ 22 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ከዓለም አቀፍ መሥፈርት አኳያ በድህነት ውስጥ ያለ (ከሁለት ዶላር በታች የቀን ገቢ የሚያገኝ) ነው፡፡ 17 በመቶ የሚሆነው ወጣትና አምራች ኃይልም በሥራ አጥነት አሠላለፍ ውስጥ መገኘቱ በመንግሥት መረጃ መረጋገጥ ተችሏል፡፡ እርሱ ብቻ ሳይሆን ከስምንት እስከ አሥር ሚሊዮን የሚደርስ የአገሪቱ ቆላማ አካባቢ ሕዝብም የዕለት ዕርዳታ የሚፈልግ ሆኗል፡፡ ይኼ በተለይ ባለፈው ዓመት ከተከሰተው ድርቅ አንፃር መባባሱ ባይካድም፣ በኋላቀር አኗኗር ውስጥ መቆየቱ የራሱ ተፅዕኖ አልነበረውም ለማለት አይቻልም፡፡

የኢትዮጵያ የፀረ ድህነት ትግል ጉዳይ ሲነሳ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ በአጭር ጊዜ ከድህነት መውጣቱ፣ በተለይ በጥቃቅንና አነስተኛ ኑሮውን መምራቱ ይጠቀሳል፡፡ በገጠርም ምርታማነት መጨመሩ፣ በባለሀብቱና በመንግሥት ፕሮጀክቶችም የሥራ ዕድል በብዛት መፈጠሩም ይወሳል፡፡ ያም ሆኖ ግን በአገሪቱ መሠረታዊ የመልካም አስተዳደርና ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ዝንባሌ መታየቱ የድህነት ቅነሳና ማስወገድ ሥራውን መጎተቱ የሚታወቅ ነው፡፡  

ኢትዮጵያ ውስጥ በፍጥነት የበለፀጉ ሚሊዮኖች በብዛት እንዴት ተፈጠሩ? ለዕለት ጉርስ ብቻ የሚሠሩ ወጣቶች ለምን አልተመጣጠኑም? ዜጎች በተለይ በከተሞች ለከፍተኛ የመኖሪያ ቤት ችግር ለምን ተጋለጡ? በዘላቂ ልማት (የከተሞች መስፋፋት፣ መሠረተ ልማት ዝርጋታና ኢንቨስትመንት) ሲባል ሚሊዮኖች ለምን ያለ በቂ ካሳ ይፈናቀላሉ? የአገሪቱ ወጣቶች ለስደትና አስከፊ ፍልሰት እየተጋለጡ ያለው ለምንድነው….? የሚሉ ጥያቄዎች ወቅታዊና አንገብጋቢ መሆናቸውን የሚገልጹ ሀቲቶችን በጥልቀት መመርመር ያስፈልጋል፡፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (CPJ)፣ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል . . የመሳሰሉት ተቋማት የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ባህል፣ የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ግንባታና ዘላቂ ልማት የሚሞግቱበት መንገድም ብርቱ ልቦናን የሚሻ ነው፡፡ ‹‹በአንድ አገር ውስጥ ዴሞክራሲ ከሌለ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና እኩል ተጠቃሚነት ብሎ ነገር የለም›› የሚሉ ትንታኔዎች ከፍ ከፍ ባሉበት ጊዜ በማንነት፣ በፆታ፣ በብሔር፣ በእምነት፣ በፖለቲከ አመለካከት፣ ወዘተ የአንድ አገር ዜጎች ጉራማይሌ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ይዘው ረዥም ርቀት መሄድ አይችሉም፡፡ ከዜሮ ድምር ፖለቲካ ለመውጣትም ፈተና መደራረቡ አይቀሬ መሆኑን የሚገልጹ ተንታኞች እየበረከቱ ነው፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዝኃነት ያለባቸው አገሮች ፖለቲካዊ ሁለንተናዊነት አለመረጋገጥና የግልጽነትና የተጠያቂነት ባህል አለመገንባት፣ በየትኛውም መስክ የሚገነባን ኢኮኖሚና ፀረ ድህነት ትግል ማወኩ አይቀሬ ነው፡፡ በተለይ ከቅርብ ወራት ወዲህ እንደ አገር የታዩ የሕዝብና መንግሥት አለመግባባቶች፣ ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ይልቅ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታየት ዘላቂ ልማትን መፈተኑ አይቀርም፡፡ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳይኖርና ፀረ ድህነት ትግል እንዲዳከምም ያደርጋል፡፡ ይኼ ከላይ በተጠቀሱ ትንታኔዎችም ሆነ በዘርፉ ልሂቃን የተመሰከረ ጉዳይ ነውና በወጉ ሊጤን ይገባል፡፡

የአየር ብክለት ሌላኛው ተግዳሮት

ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙዎቹ የአኅጉሩ አፍሪካ አገሮች በግብርና ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ያላቸው ናቸው፡፡ በራሳቸው ብቻ ሳይሆን ሌላው ዓለም በአየር ንብረት ብክለት ላይ በደነቀረው ሳንካ ምክንያት ዋጋ እየከፈሉ ያሉትም ለዚሁ ነው፡፡ እዚህ ላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ ፎረሞች አደራዳሪነት እ.ኤ.አ. በ2012፣ 13፣ 14ና 15 ድረስ በየዓመቱ እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር የበለፀጉ አገሮች ለደሃ አገሮች ለመስጠት (ለመደጎም) የአየር ብክለት ድጎማ ስምምነት ሲደረግ የነበረው፡፡ ያም ሆኖ በኢንዱስትሪ የተበከለ ጋዝ ልቀትና በውቅያኖስም ሆነ በንፁህ አየር መታወክ የሚወቀሰው ዓለም እዚህ ግባ የሚባል ካሳ ሲሰጥ አልታየም፡፡ ምናልባት እንደ ቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ያሉት የደሃው ዓለም መሪዎችም የጀመሩት ህልምም እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ማምጣቱ አልታየም፡፡ በእርግጥ አገሮች ሕዝቦቻቸው በራሳቸው ጥረት ያስመዘገቡዋቸው መልካም ውጥኖች (በተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ በመልሶ ልማትና አካባቢ ጥበቃ እንዲሁም በታዳሽ ኃይል ልማት መጠናከር) እንደ በጎ ጅምር ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡

ዓለም አቀፍ የአየር ብክለት ግን የአካባቢ ሁኔታን በማዛባት ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም፡፡ እነሆ በአፍሪካ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለድርቅ ያጋለጠው መንስዔው ይኼው ነው፡፡ በአንዳንድ የምሥራቅና ምዕራብ አገሮች የከፋ ድርቅ፣ የተባባሰ ሰደድ እሳት፣ አሊያም የጎርፍ አደጋ ለመከሰቱ መንስዔውም ይኼውና ይኼው ብቻ ነው፡፡

ከሕዋ ሥነ ምህዳርና ከአካባቢ መበከል ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ታዳጊ አገሮች በውስጣቸው ያለው የኑሮ ተስማሚነት ደረጃም መጤን ያለበት ነው፡፡ የተሻለ መኖሪያ ቤት፣ ተመጣጣኝ ምግብ፣ የተሟላ አልባሳት ያላገኘ ሕዝብ የታመቀባቸው አገሮች በነፍስ ወከፍ ገቢ ሥሌት ብቻ አደጉ ማለት አዳጋች መሆኑን ኒኮላስ ስተርን በዝርዝር ጽፎታል፡፡

በዚህ ረገድ አገራችን ከተሞችና የኢንዱስትሪ ቀጣናዎችም የተደቀነባቸው ፈተና ቀላል አይደለም፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ ከተሞቻችን በደረቅ ቆሻሻ ክምር የተሞሉና የፈሳሽ አወጋገዳቸው በቴክኖሎጂ ያልታገዘ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ከኢንዱስትሪና ከአነስተኛ ማምረቻዎች የሚወጣ ብክለት የከርስና የገጸ ምድር ውኃን እስከ ማጥፋት የሚያደርስበት ጊዜ ትንሽ አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ እጅግ ሰፋፊ የሚባሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች፣ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች፣ በሚሊዮን ሔክታር የሚገመት የተፋሰስና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ፣ የታዳሽ ኃይል አጠቃቀም (ለምሳሌ በኤሌክትሪክ የሚሠራ ባቡር . . .)  መጠናከራቸው በጎ ጅምር ሊባል ይችላል፡፡ በዚያው ልክ ግን አሁንም በገጠርና በአርብቶ አደሩ አካባቢ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የእንስሳት ሀብት (ጥራቱ ዝቅተኛ ነው) ብክለትን የሚያመጣ ነው፡፡ በተለይ ልቅ ግጦሽን ሙሉ በሙሉ ማስቆም ባለመቻሉ የጉዳት መጠኑ እንደ ኢንዱስትሪ ብክለት አይሁን እንጂ፣ ለድርቅ ሥጋት አንድ መንስዔ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

በኢትዮጵያ ሁኔታ በቆላማ አካባቢዎች ላለው የድርቅ ሥጋት እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ሌላው ችግር አሁንም ከዝናብ ጠባቂነት ያልተላቀቀ ኢኮኖሚ የመኖሩ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ኋላ ቀርና የድህነት መገለጫ የሆኑ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ለመላቀቅ ብርቱ ሥራ ማስፈለጉ ብቻ አይደለም መዘንጋት የሌለበት፡፡ ይልቁንም በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ ፍትሐዊ የልማት ትግበራና ፍትሐዊ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ መኖሩ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በኒኮላስ ስተርን ትንታኔም የሦስተኛው ዓለም አገሮች የድህነትና የአየር ብክለት ተፅዕኖ አስጨናቂ ፈተና ትንተናም የሚቆመው በዚሁ ሐሳብ ላይ አተኩሮ መሆኑ ሲታይ የዚህ ጽሑፍ ድምዳሜን ትክክለኛነት ያሳያል፡፡ አገራችንን ጨምሮ ታዳጊ አገሮች ድህነትን ለማስወገድ በተለይም በፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና የአየር ብክለት ተፅዕኖ መቋቋም ካልቻሉ ከመፍገምግም መውጣት አይቻልም፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

    

 

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles