Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሰባት ወራት የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ቅናሽ አስመዘገበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የ2.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሲጠበቅ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል

በበጀት ዓመቱ ሰባት ወራት የታየው የወጪ ንግድ አፈጻጸም እንደወትሮው ማሽቆልቆል አሳይቷል፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ይጠበቅ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ2.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ቢሆንም፣ አፈጻጸሙ ግን ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር ብዙም ፈቅ ሳይል ቀርቷል፡፡

ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በሰባት ወራት ውስጥ ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርናና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውጤቶችን ለዓለም ገበያ በማቅረብ በጠቅላላው 1.423 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህ ገቢ ግን በሰባት ወራት ውስጥ ይገኛል ተብሎ ከታቀደውም ሆነ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያ ዝቅተኛ ሆኖ መገኘቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባለፈው ዓመት ሰባት ወራት ውስጥ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 1.521 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡

‹‹በበጀት ዓመቱ ሰባት ወራት 2.488 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ በአፈጻጸም የተመዘገበው 1.423 (57.19 በመቶ) ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህ አፈጻጸም ባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወራት ከተገኘው 1.521 ቢሊዮን ዶላር ሲነፃፀር በ37.516 (6.46 በመቶ) ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል፤›› የሚለው የሚኒስቴሩ ሪፖርት፣ በተያዘው ዕቅድ አኳያ የ50 በመቶ በታች ቅናሽ ካስመዘገቡት የወጪ ንግድ ምርቶች ውስጥ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ዓሣ፣ ሰም፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች፣ ቅመማ ቅመምና የመሳሰሉት ሲጠቀሱ፣ ወርቅ፣ የቁም እንስሳት፣ የሥጋ ተረፈ ምርት ብረታ ብረትም ከግማሽ በላይ ቅናሽ ያሳዩ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

ዋና ዋና ከሚባሉት የወጪ ንግድ ሸቀጦች መካከል ቡና ቀዳሚው ነው፡፡ በቡና ወጪ ንግድ ዘርፍ ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 360.8 ሚሊዮን ዶላር ሆኗል፡፡ ይጠበቅ ከነበረው የገቢ መጠን አኳያ ማከናወን የተቻለው ከዕቅዱ 4.2 በመቶ ብቻ እንደሆነ ታይቷል፡፡ ምንም እንኳ ዓምና በተመሳሳይ ወቅት ከታየው ይልቅ ዘንድሮ የ14.67 ሚሊዮን ዶላር የገቢ ጭማሪ ቢመዘገብም፣ በመጠን ግን ለአራት ሺሕ ቶን የቀረበ ቅናሽ ተመዝግቧል፡፡

ዘንድሮ ለውጭ ገበያ የቀረበው የቡና መጠን 96.6 ሺሕ ቶን ነው፡፡ ዓምና በሰባት ወራት ውስጥ የቀረበው የቡና መጠን ግን ከ100 ሺሕ ቶን በላይ መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር ሪፖርት ያሳያል፡፡

‹‹በዚህ ወርና በአጠቃላይ በሰባት ወራት በመጠንና በገቢ የቀነሰበት ምክንያት በቡና አብቃይ ክልሎች በቂ የቡና ምርት እንዳለ ቢታወቅም፣ ይህንን ሁኔታ ገዢዎች በመረዳት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋጋ በታች እየሸጡ በመሆኑ በዋጋ ላይ መግባባት ባለመቻሉ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በቂ ኮንትራት አልተገባም፣ ገዢዎች ምክንያት እየፈጠሩ የሚላክላቸውን ናሙና ውድቅ በማድረግ L/C ከፍቶ ለመላክ በማዘግየታቸው ነው፤›› በማለት ቡና የታሰበውን ያህል ውጤታማ ያልሆነው የውጭ ገዢዎች የሚሰጡት ዋጋ ከአገር ውስጥ የምርት ገበያ ዋጋ አንሶ መገኘቱ ዋናው ምክንያት እንደሆነ ሚኒስቴሩ ይገልጻል፡፡

ይሁንና በወጪ ንግድ ዘርፍ እየታየ ላለው ደካማ ውጤት ከሚጠቀሱት መካከል በአገሪቱ የተከሰተው ሕዝባዊ ተቃውሞና ይህንንም ተከትሎ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያስከተለው የገበያ መናጋት እንደሆነ በቅርብ ጉዳዩን ከሚከታተሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአገሪቱ በመደበኛ መንገድ ለውጭ ገበያ መቅረብ የሚጠበቅባቸው ምርቶች በአብዛኛው በኮንትሮባንድ እየወጡ መሆናቸው ችግሩን እንዳባባሰው ሲገለጽ ይደመጣል፡፡ ከዚህ ባሻገር ሰሞኑን ንግድ ሚኒስቴር ከላኪዎች ጋር ባደረገው ዝግ ስብሰባ፣ አብዛኞቹ ከምርት ገበያው ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርት ማግኘት እንዳልቻሉ መግለጻቸው ተሰምቷል፡፡

ከኮንትሮባንድ ወደ ውጭ እየወጡ እንደሚገኙ ከተገለጹ ምርቶች መካከል ወርቅ ይገኝበታል፡፡ የወርቅ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ዝቅተኛ ሊሆን የቻለው የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ከመኖሩ ባሻገር ዘመናዊ አምራቾችም ቢሆኑ በዕቅዳቸው መሠረት አከታትለው መላክ ባለመቻላቸው ምክንያት ዝቅተኛ ውጤት ሊያስመዘግብ እንደቻለ ንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ከወርቅ ይጠበቅ ከነበረው ገቢ የ26 በመቶ ቅናሽ በማሳየት፣ የ111 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተመዝግቧል፡፡

የወጪ ንግዱ ዘርፍ እንዲህ ባለው ደረጃ እየተንሸራተተ መምጣቱ አገሪቱ የንግድ ሚዛን ጉድለት እያባባሰው መምጣቱን የዓለም የገንዘብ ድርጅት ሪፖርት አስታውቋል፡፡ ድርጅቱ ባለፈው ዓመት ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚጠቅሰው፣ አገሪቱ የከረንት አካውንት ጉድለት 7.4 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ሲሆን ይህም ከአገሪቱ ኢኮኖሚ (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) የ10 በመቶ ድርሻ ይዞ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል እ.ኤ.አ. ከ2006 እስከ 2016 ባሉት ዓመታት ውስጥ በአገሪቱ ገቢና ወጪ ንግድ መካከል የታየው የንግድ ሚዛን ጉድለት በአማካይ ሁለት ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ ዓምና የነበረው የንግድ ሚዛን ጉድለት ከ3.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደነበርም ተመልክቷል፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች