ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) በየመንና በጂቡቲ በችግር ላይ የነበሩ 146 ኢትዮጵያውያን ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን አስታወቀ፡፡ ከተመለሱት ስደተኞች መካከል ሕፃናትም ጭምር የነበሩ ሲሆን፣ ተመላሾቹ የትራንስፖርት፣ መጠለያና ልብስ ያሉ ድጋፎች ተደርጎላቸው በመጨረሻ ወደየቀያቸው እንዲሄዱ መደረጉም ተጠቁሟል፡፡
ከተመላሾቹ መካከልም ከወላጆቻቸው የተለያዩ ሕፃናት ቤተሰቦችን የማፈላለግ ሥራም ከአዲስ አበባ የሴቶችና የሕፃናት ቢሮ እንዲሁም የተመድ ሕፃናት አድን ድርጅት ከሆነው ዩኒሴፍ ጋር በመተባበር እያከናወነ መሆኑን፣ ወላጆች እስኪገኙ ድረስ ግን ሕፃናቱ በአይኦኤም የሕፃናት ማቆያ እንዲሆኑ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮ ኤርትራ ድንበርን አቋርጠው የገቡ 4500 ኤርትራውያን አስፈላጊው አፋጣኝ ዕርዳታ ተደርጎላቸው፣ ከሽሬ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው የእንዳባጉና የስደተኞች መቀበያ ጣቢያ መሸኘታቸውን ድርጅቱ መጋቢት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡ ስደተኞቹ በጣቢያው በስደተኞችና ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ በሆነው ዩኤንኤችሲአር የሚመዘገቡ ሲሆን፣ እንዳባጉና የስደተኞች ምዝገባ ጣቢያ በአሁኑ ወቅት በሦስት እጥፍ ከአቅሙ በላይ ስደተኞችን እያስተናገደ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የዩኤንኤችሲአር መረጃ እንደሚያመለክተው ወደ ጣቢያው ከገቡት አዲስ ስደተኞች 30 በመቶ የሚሆኑት ብቸኛ ሕፃናት (ወላጆቻቸው አብረዋቸው የሌሉ) ናቸው፡፡