የእብድ ውሻ በሽታ (ሬቢስ) ከአውስትራሊያ በስተቀር በቀሩት አህጉራት ተንሰራፍቷል፡፡ በሽታው ገዳይ በመሆኑ የተነሳ በዓለም ውስጥ በየዓመቱ 55 ሺሕ ሞት እንደሚመዘገብ ከኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በኢትዮጵያ የእብድ ውሻ በሽታ ከ1999 ዓ.ም. እስከ 2004 ዓ.ም. ድረስ 61.7 ከመቶ ያህሉ በውሾች ላይ፣ 34.6 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በከብቶች ላይ መከሰቱ ተመዝግቧል፡፡ በሽታው በተለይ በብሔራዊና በክልላዊ ፓርኮች በሚገኙ የዱር እንስሳት ላይም እየተዛመተ ነው፡፡
በሽታውን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ውሾቹን በዘመቻ መከተብና አስሮ ማስዋል ብቻ በቂ አለመሆኑን ያመለከተው ተቋሙ፣ ፈጽሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከተፈለገ ጉዳዩ በይበልጥ የሚመለከታቸውን የተለያዩ አካላትን ያሳተፉ የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወን ይገባል ብሏል፡፡
ከዚህ ግንዛቤ በመነሳት የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮና በንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የከተማ ግብርና ጽሕፈት ቤት በመዲናይቱ ውስጥ በእብድ ውሻ በሽታ ላይ ያተኮረ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ በጥምረት ለማከናወን የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ በቅርቡ አዘጋጅተዋል፡፡ ሰነዱ በበላይ አካላት በቅርቡ ታይቶ ከፀደቀ በኋላ ወደ ተግባር ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢንስቲትዩቱ የእንስሳት ነክ በሽታዎች ምርምር ቡድን አስተባባሪና ተባባሪ ተመራማሪ ዶ/ር አብርሃም ኃይሉ እንደገለጹት፣ ለሥራው ቅልጥፍና ሲባል ኢንስቲትዩቱ ከልዩ ልዩ ጤና ጣቢያዎች ለተውጣጡ 160 ጤና ባለሙያዎች፣ ከውሻ ንክሻ ጋር የተያያዘ ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀና ሳይንሳዊ መረጃን መሠረት ያደረገ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡
ከዚህም ሌላ የጽሕፈት ቤቱ ባለሙያዎች የሚገለገሉበትና ለእንስሳቱ መያዢያ የሚሆኑ መሣሪያዎችንና ልዩ ልዩ ዕቃዎችን አሜሪካ ከሚገኘው ሴንትራል ዲዚዝ ኮንትሮል (ሲዲሲ) ጋር በመተባበር ገዝቷል፡፡
ከአሜሪካ መንግሥትም ሆነ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በየክፍለ ከተማው በነፍስ ወከፍ አንዳንድ የእንስሳት ማቆያ እንዲገነባ ለማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተከናወነ መሆኑን ዶ/ር አብርሃም ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ግብርና ጽሕፈት ቤት የእንስሳት ሐኪም ዶ/ር ካሳሁን ታፈሰ ስለዚሁ ጉዳይ ተጠይቀው፣ ‹‹በሰነዱ መሠረት የየራሳችንን ድርሻ በጋራና በተናጠል ለማከናወን ዝግጁ ሆነን በመጠባበቅ ላይ ነን፤›› ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የኅብረተሰብ ጤና ምርምርና የአደጋዎች ቁጥጥር ዋና የሥራ ሒደት መሪው አቶ አብርሃም ተስፋዬ በአሥሩም ክፍለ ከተሞች የእብድ ውሻ በሽታ ላደረባቸው ሰዎች ተገቢው ሕክምና የሚሰጧቸው ጤና ጣቢያዎች ተለይተው እንደታወቁ ገልጸዋል፡፡
ቢሮው የራሱ የሆነ ማዕከላዊ ላብራቶሪ እንዳለውና ይህም ላብራቶሪ በዚህ በሽታ ዙሪያ የምርመራ ሥራ የሚያደርግበት መልክ ሊመቻች እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡
ከኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሌላ የእብድ ውሻ በሽታ ለያዛቸው ሰዎች እስከዛሬ ድረስ ሕክምና የሚሰጡት፣ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅና የቃሊቲ ጤና ጣቢያ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡